Wednesday, 19 March 2014

በኩዌይት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው

መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ውጥረቱ የተጀመረው አንዲት ኢትዮጵያዊት አንድ የአገሪቱን ባለስልጣን ልጅ መግደሉዋን ተከትሎ ነው። ኢትዮጵያዊቷ ግድያውን የፈጸመችበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ባይቻልም፣ ገዳዩዋን በቅርብ እናውቃለን ከሚሉ ወገኖች የተገኘው መረጃ በቂም በቀል ተብሎ የተደረገ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ይገልጻሉ። ከሶስት አመት በፊት ወደ ኩዌት የገባችው ወጣት በመጀመሪያው ወር በአሰሪዋ ልጅ መደፈሩዋን ለመበቀል በሚል የባለስልጣኑን ልጅ ለመግደል እንደተነሳሳች መግለጿን ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ።
የኩዌት መንግስት ስለ ግድያው መንስኤ እስካሁን በኦፌሴል ያሳወቀው ነገር የለም። ይሁን እንጅ የኩዌት የፓርላማ አባላትና አንዳንድ ባለስልጣናት ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው እንዲወጡ እየወተወቱ ነው።
የሟች አክስት የሆነች አንዲት ማንነቱዋ ያልተገለጸ አሰሪ ከአራት ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች መካከል እጣ በማውጣት አንደኛዋን ኢትዮጵያዊት በማረድ የአክስቷን ልጅ ሞት መበቀሉዋን ኢትዮጵያውያን በፎቶ ግራፍ አስደግፈው ለኢሳት የላኩት መረጃ ያሳያል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ከቤት ለመውጣት እንዳልቻሉ፣ ከቤት ቢወጡ ተይዘው እንደሚታሰሩ ወይም የበቀል ሰለባ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በፍጥነት ደርሶ አሁን የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያረግብም ኢትዮጵያውያን ተማጽነዋል። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁኔታውን በንቃት እንዲከታተሉት ጥሪ አቅርበዋል። ኢሳት የኩዌት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሰካም።

ውዳሴ መስከረም ወጽዮን

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
woman flag


በብዙ አገሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ የሴቶችና የወንዶች ቁጥር ብዙም አይለያይም፤ እኩል ለእኩል ይሆናሉ፤ ነገር ግን ይህ የቁጥር እኩልነት በኑሮአችን ላይ አይታይም፤ በ1983 የወያኔ ሠራዊት በየመንገዱ ይታይ በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን ወደሂልተን ሆቴል ስገባ አንዲት ልጅ ከቁመትዋ የሚረዝምና ከክብደትዋ የበለጠ ጠመንጃ ይዛ አየሁና ዕድሜዋን ብጠይቃት አሥራ አራት አንደሆነ ነገረችኝ፤ ይቺ ልጅ በዚህ ዕድሜዋ ስንት መከራ እንዳየች እግዚአብሔር ይወቀው፤ በዚያን ጊዜ እንደስዋ ያሉ ብዙ ሴቶች ወያኔዎች አይቻለሁ።
የመጀመሪያው ወያኔ/ኢሕአዴግ ያዘጋጀው ጉባኤ በተካሄደበት ጊዜ በጉባኤው ውስጥ አንዲት ሴት ብቻ ነበረች፤ እስዋም ከሠራተኞች ማኅበር የተወከለች ነበረች፤ እነዚያ ጠመንጃ እየተሸከሙ በእግራቸው አዲስ አበባ የገቡትና በየመንገዱና በየመሥሪያ ቤቱ በር ላይ ሲጠብቁ የነበሩ የወያኔ ሴቶች በጉባኤው ላይ በአንድም ሴት አልተወከሉም ነበር፤ ነገሩ በጣም ከንክኖኝ ለመለስ ዜናዊ ነገርሁት፤ ይህንን ጉድለት በማንሣቴ ደስ ባይለውም ስሕተት መሆኑን ተቀብሎ ወደፊት እንደሚታረም ነገረኝ፤ ከዚያም በኋላ ቢሆን ከነጻነት አስፋው ሌላ (የእስዋን አርበኛነት ባላውቅም) በመድረኩ ላይ የምትታይ ሴት አልነበረችም፤ ምናልባት እነዚያ ከጫካ የመጡት እንደ ነጻነት በአውሮፓና በአሜሪካ አልሠለጠኑም ይሆናል፤ እንዲያውም ትንንሾቹን ወያኔዎች ወደትምህርት ቤት ቶሎ ማስገባት ያስፈልጋል ብዬ በመናገሬ ነጻነት አስፋው አንተ ብሎ ለነሱ አሳቢ ብላ ቁጣዋን አውርዳብኛለች፤ ምናልባትም ተማሪዬ በነበረች ጊዜ የደረሰባትን ‹‹ግፍ›› ልትመልስ ይሆናል፤ ዋናው ነጥቤ ግን በወያኔ ዘመን ብዙው ሰው ሲያልፍለት እነዚያ ጠመንጃ ተሸክመው ያየኋቸው እንኳን ሊያልፍላቸው ለዓይንም የጠፉ ይመስላል፤ አሁን በቅርቡ አንዳንድ መደበኛ የትራፊክ ፖሊሶች ሆነው አይቻለሁ፤ በተቀረ ከላይ ተንሳፍፈው የምናያቸው የእንትና ሚስት ወይም የእንትና እኅት ናቸው ይባላል።
ነጻነት አስፋው
ነጻነት አስፋው
እንዴት እንዲህ ሆነ? ይህ እንግዲህ ከአገዛዙ በኩል የጎደለ ነገር መኖሩን ያሳያል፤  ሴቶቹ የተፈለገባቸውን ግዴታ ከወንዶቹ እኩል ከአከናወኑ በኋላ ከመድረኩ የወጡ ይመስላል፤ አገልግሎታቸውን ጨርሰው የወጡም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወንዶችም ወጥተዋል፤ ግን ይህ ብቻ አይመስለኝም፤ እንዴት እንደገቡ ስለማናውቅ እንዴት እንደወጡ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፤ ስለዚህ ወደሌላ አቅጣጫ ብናተኩር ኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ) ሲቋቋም ከመሥራቾቹ ቢያንስ ግማሹ ሴት እንዲሆን ያላደረግሁት ጥረት አልነበረም፤ ቢሮአቸው ወይም ቤታቸው ድረስ እየሄድሁ የለመንኋቸው ነበሩ፤ በመጨረሻም የኢሰመጉ አባሎች ውስጥ ሴቶች አሥር ከመቶም አልደረሱም፤ በኋላ ለኢሰመጉ አቤቱታውንና ኡኡታውን የሚያቀልጡት አብዛኛዎቹ ሴቶች ነበሩ፤ ቆይቶም ለቅንጅት እንቅስቃሴ ብዙዎቻችን በተቻለን መጠን የሴቶችን ቁጥር ለማበርከት ከፍተኛ ጥረት አድርገን ነበር፤ ውጤቱ ግን የማያረካ ነበር፤ ዛሬም ቢሆን በየፓርቲዎቹ የሚታዩት አብዛኛዎቹ ወንዶች ናቸው፤ ሴቶች ከአሥር በመቶ እንዳያልፉ የወሰኑ ይመስላል፤ ግን የትና እንዴት ተሰብስበው ወሰኑት!
በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ የሚጽፉም ቢሆን በእኔ ግምት ከአሥር በመቶ አያልፉም፤ በቃሊቲ እስር ቤት ከርእዮት ሌላ ሴት ጋዜጠኛ ያለ አይመስለኝም፤ እዚያም ቢሆን ያው ከአሥር አንድ ግድም ሊሆን ነው፤ እየፈሩና እያፈሩ ነው እንዳንል ይህንን የሚያስተባብሉ ሌሎች ምክንያቶች አሉ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች በማዝናኛው መስክ ያላቸው ድርሻ በጣም የላቀ ነው፤ በዘፈንም በጭፈራም ቢሆን ከወንዶቹ ጋር የማይተናነስ ቁጥር ያላቸው ይመስለኛል፤ በስፖርትም በወንዶችና በሴቶች መሀከል ያለውን ርቀት በጣም እያጠበቡት ነው፤ ሌላም ድርጅት ሴቶች በብዛት የሚገኙበት አለ፤ እድር፤ ታድያ ለሌሎቹ ማኅበራት ሲሆን፣ ለፖሊቲካና ሀሳብን ለመግለጹ ሲሆን ወደኋላ የሚይዛቸው ወይም እንዳይገቡበት ወደውጭ የሚገፋቸው ምን ዓይነት ኃይል ነው? ሌላ ትዝ ያለኝና የሚያስደስተኝ በሥጋ ቤት በላተኛነትም ሴቶቻችን የሚያሳዩት የነጻነትና የእኩልነት መንፈስ ነው፤ ይህንን የኢትዮጵያ ሴቶች በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አነስተኛ ተሳትፎ እንደትንሽ ነገር ሳንመለከተው ጥልቅና ትክክለኛ ጥናት ሊደረግበት የሚገባ ይመስለኛል፤ ይህንን ረጅም መንደርደርያ (እኔ አስተማሪ ሆኜ ይህንን ያህል መንደርደሪያ የሚጽፍ ተማሪ ፍሬ ነገሩ ጥሩ ቢሆንም ከD በላይ አያገኝም ነበር!) መንደርደሪያው ያነጣጠረው ዕድልና ጊዜው ያለው ሰው ይህንን ጉዳይ እንዲያጠና/አንደታጠና ለመቀስቀስ ነው፤ የጽሑፌ ዓላማ ውዳሴ መስከረም ወጽዮን ነው።Olympics Day 7 - Athletics
እንዳመጣጣቸው ቅደም-ተከተል ወይዘሮ መስከረምና ወይዘሮ ጽዮን ለፋክት መጽሔት ብርቅ ጽሑፍ አቅራቢዎች ናቸው፤ ብድግ ብዬ እጅ እየነሣሁ እንኳን ደህና መጣችሁ! ያበርታችሁ! እላለሁ፤ በሀሳብ ማሰራጫው ዓለም ለወጉም ቢሆን ከወይዘሮ መዓዛ ሌላ የለም፤ በማናቸውም የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለየብቻቸውም ሆነ በቡድን የሚሠሩ ሰዎች የኢትዮጵያን ወንዶች ይወክላሉ አልልም፤ በተጨማሪም ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሆኑትን ሴቶች አይወከሉም፤ ሁሉንምና ማናቸውንም የኢትዮጵያ ጉዳይ ወንዶች ብቻ ያውም ማንንም በትክክል የማይወክሉ ወንዶች (ወንዶች የምለው ሰዎች እንዳልል ነው፤)  ገርድፈው እያቀረቡት ሲወሰን አንድ አገርና ሕዝብ የሚሄድበትን አቅጣጫ ለመገመት አያስቸግርም፤ በምንም ተአምር ወደላይ ሊሆን አይችልም።
በበኩሌ ወይዘሮ መስከረምንና ወይዘሮ ጽዮንን የማደንቃቸው በአእምሮአቸው ለምነትና ንቃት ብቻ ሳይሆን በመንፈሳቸውም ጥንካሬ ነው፤ የቁልቁለቱ ኃይል በሚያስደነግጥ ሁኔታ እያደገ በመጣበት ዘመን ድምጽን ማሰማትና ለየት ያለ ሀሳብን ይዞ ወደአደባባይ መውጣት አስቸጋሪም አደገኛም በሆነበት ጊዜ የወይዘሮ መስከረምና የወይዘሮ ጽዮን ብቅ ማለት የወደፊቱን አመልካች የሆነ ልዩ ብርሃን ስለሚመስለኝ ደስ ይለኛል፤ የኤፍሬም ሥዩም የቅኔ ችሎታ ቢኖረኝ ለነዚህ ለፋክት አዳዲስ ብርሃናት መወድስ እቀኝላቸው ነበር፤ ወይም አላሙዲንን ብሆን ጠቀም አድርጌ እሸልማቸው ነበር፤ አግረ-መንገዴን አላሙዲን ስለሽልማት ማሰብ እንዲጀምር ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
የህንድን፣ የቻይናን፣ የታይላንድን፣ የመሀከለኛው ምሥራቅን ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ ስመለከት እቀናለሁ፤ የእኛዎቹን ምን ነካቸው እያልሁም ራሴን እጠይቃለሁ፤ በአፍሪካም ሴቶች ፕሬዚደንቶች ሲሆኑም እቀናለሁ፤ ለዚህ ነው መስከረምንና ጽዮንን ብርቅ ናቸውና ብርቅ አድርጌ የማያቸው።
የሴቶችን ተሳትፎ እኔ በቀላሉ አላየውም፤ ትግሉን በስሜት ስለሚገጥሙ የሚያይ ሁሉ ለመሳተፍ ያምረዋል፤ አባቶቻችን ትልቁን ቁም-ነገር አበላሽተው ሴት የላከው ሞት አይፈራም ያሉት በዚህ ምክንያት ነው፤ ፈረንጆች መለስ አድርገው በእያንዳንዱ ትልቅ ሰው በስተጀርባ አንዲት ሴት አለች ይላሉ፤ እንደየቴዎድሮስ ምንትዋብ፣ የምኒልክ ጣይቱ ማለት ነው፤ የምፈራው በዚህም በኩል ሳኡዲ አረብያና የመን እንዳይቀድሙን ነው፤ ሴቻችን ካልተነሣሱ ቆመን መቅረታችን ነው።

Thursday, 13 March 2014

ግብጽ ጦሯን በደቡብ ሱዳን ልታሰፍር ነው:

ለሰላም ማስከበር ይሁን በቅርብ ርቀት ኢትዮጵያን ለመውጋት ውሉ አለየለትም::

 

 የግብጽ እና የደቡብ ሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገናኝተው ግብጽ በአየር እና በምድር የታጠቀ ጦሯን በደቡብ ሱዳን እንድታሰፍር መስማማታቸው የተሰማ ሲሆን ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያን የሚያሳስባት ሲሆን ኢትዮጵያን እና የህዝቧን ሉዋላዊነት እና ደህንነት ደቡብ ሱዳን አደጋ ላይ ለመጣል ያሴረችው ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል::

በማርች 2014 መጨረሻ ድረስ ግብጽ በጦር ልምምድ ስም የኢትዮጵያን የግድብ ስራዎች ሂደት ለመቃኘት እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ታስቦ ሊሆን ይችላል ሲሉ ፍራቻቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች ግብጽ ኢትዮጵያን ለመውረር ውይንም ለማስፈራራት ያደረገችው አዲስ እቅድ መሆኑን ሲገልጹ ደቡብ ሱዳን የኢሕኣዴግ መንግስት የሳልቫ ኬርን ተቃዋሚዎች ይረዳል በሚል ስለምታስብ ግብጽን ኢትዮጵያን ለማስደንገጥ ልትጠቀምባት ሊሆን ይችላል ሲሉ ገምተዋል::

እስካሁን በዚህ ጉዳይ አስተያየት ያልሰጠው የኢሕአዴግ መራሹ መንግስት ምን አይነት እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው:: የኢሕኣዴግ መንግስት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ የውጪ መንግስታት የሚያራምዱትን ፖሊሲ በቸልተኝነት የሚመለከት ሲሆን አሁን ግብጽ በደቡብ ሱዳን ልታደርግ ያቀደችውን የጦር ሰፈራ ግን እንዴት ሊመለከተው ይችል ይሆናል የሚሉ ወገኖች በርክተዋል::ምንሊክ ሳልሳዊ

የግብጽ መንግስት በሶስት ቡድን ከፍሎ የሚያሰፍራቸው የጦር ሰራዊቱ አብዛኛውን በምስራቅ የደቡብ ሱዳን አማካጭ የስትራቴጂ አከባቢዎች ለ አማራው ክልል ይቀርባልኡ ተብለው በሚገመቱ ቦታዎች ሲሆን በዚህ በሚሰፍረው ጦር ውስጥ ከጦር አይሮፕላኖሽ ጀምሮ ሚሳኤሎች እና ታንኮች በተጨማሪም ወታደራዊ ኮማንዶዎች እንዲሁም ከፍተኛ ወታደራዊ ደህንነቶንች እና እግረኛ ወታደሮች ይጠቃለላሉ::ምንሊክ ሳልሳዊ

በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን የኢሕኣዴግ መራሹ መንግስት የተናገረው ነገር የለም::

ምንሊክ ሳልሳዊ

“ኢህአዴጋዊ ምርጫ” በሰሜን ኮሪያ

ኪም ጆንግ ኧን 100% ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል!

kim un


ድምጽ የመስጫው ጊዜ ተጠናቅቆ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ መቁጠር በጀመሩ ጊዜ ኪም ጆንግ ኧን የማሸነፋቸው ጉዳይ አሳስቧቸው በስጋት ውስጥ ነበሩ፡፡ ቆጠራው ተጠናቀቀ፤ ውጤቱ ይፋ ሆነ፤ አሸናፊው ታወጀ፤ ኪም ጆንግ ኧን ሥልጣን ከያዙ የመጀመሪያውን ምርጫ በ100% አሸነፉ፤ ከጭንቀታቸው አረፉ፤ ሕዝቡም በደስታ ፈነጠዘ፣ የክት ልብሱን ለበሰ፤ በአደባባይ ወጥቶም ዳንኪራ ረገጠ፡፡
korea2እሁድ በተደረገው ምርጫ የተሰጠውን እያንዳንዱን ድምጽ ኪም ጆንግ ያለተቀናቃኝ የራሳቸው አድርገዋል፡፡ በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው ምርጫ የተሳተፈው ሕዝብ የምክርቤት አባላትንም መርጦዋል፡፡ በደንቡ መሠረት ምርጫው የሚካሄደው ለምክርቤት ምርጫ ሲሆን የተመራጮች ዝርዝር ውጤት ከመታወቁ በፊት የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት ኪም ጆንግ ኧን ያለተቀናቃኝ በተወዳደሩበት ወረዳ አንድም ተቃዋሚ ድምጽ ሳይሰጥባቸው የሁሉንም መራጭ ይሁንታ በማግኘት መመረጣቸውን ዘግቧል፡፡ ያለፈው ምክርቤት 687 መቀመጫ የነበሩት ሲሆን የአሁኑ ምን ያህል እንደሚኖረው እስካሁን አልታወቀም፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጠቃቸውና የኒዎሊበራል አቋም የሚያራምዱ ጽንፈኛ ኃይሎች ታላቅ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተከፈለበትን ምርጫ በማጣጣል ልማታዊውን መሪ መመረጥ ለመቃወም ቢሞክሩም “ምርጫው የኮሪያ ሕዝብ በታላቁ መሪ ኪም ጆንግ ኧን ላይ ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳየበትና በእርሳቸው ራዕይ ለመመራት መወሰኑን በአንድ ድምጽ የገለጸበት ነው” በማለት የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት አጣጥሎታል፡፡
ምርጫ በተደረገበት እያንዳንዱ ወረዳ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ የቀረበ ሲሆን መራጮች ድምጽ ሲሰጡ የሚመርጡት በተወዳዳሪው ስም አቅጣጫ “እመርጣለሁ” ወይም “አልመርጥም” የሚል ብቻ እንደነበር ተገልጾዋል፡፡ በህመምና በተለያዩ ምክንያቶች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው መምረጥ ለማይችሉ ተንቀሳቃሽ የምርጫ ሳጥን ተዘጋጅቶ ያሉበት ቦታ የምርጫ ኮሮጆ በመውሰድ ድምጻቸውን እንዲሰጡ መንግሥት ያመቻቸላቸው መሆኑን የሰሜን ኮሪያ መንግሥታዊ ዜና አገልግሎት ጨምሮ ዘግቧል፡፡korea4
የሰሜን ኮሪያው ተሞክሮ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የማድረግ ልምድ ላላቸው አገራት ተምሳሌት ከመሆኑ አኳያ በርካታ ልምምድ ሊወሰዱበት የሚችሉ እንደሆነ ምርጫውን የታዘቡ ገለልተኛ ያልሆኑ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በአንድ የምርጫ ቀበሌ አንድ ተመራጭ ብቻ “በማወዳደር” አላስፈላጊ የሆኑና የማያሸንፉ ተወዳዳሪዎችን በማስወገድና ወጪን በመቀነስ ልማታዊ ምርጫን ማበረታታት ከአሁኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ እነዚሁ ክፍሎች ተናግረዋል፡፡
በምርጫው ወቅት አብዮታዊና አውራ ፓርቲያዊ ቀስቃሽ ዜማዎች የተሰሙ ሲሆን ሰሜን ኮሪያን ለ46ዓመት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጠ/ሚ/ርነት እና በፕሬዚዳንትነት አገልግለው የተሰውትን የቀድሞውን ባለራዕይ መሪ፣ የኮሪያ ላብአደር ፓርቲ ሊቀመንበር፣ የጦር ኃሎች አዛዥ፣ ማርሻል እና የሪፑብሊኩ ዘላለማዊ መሪ ኪም ኢል ሱንግን የሚያወሱ “በሌጋሲ” የተሞሉ ዜማዎችም ቀርበዋል፡፡
http://www.goolgule.com/eprdf-style-election-in-north-korea/

Saturday, 8 March 2014

አንድነት ሁለተኛውን ዙር “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት”ንቅናቄ ጀመረ

የመሬት ፖሊስን ለማስለወጥ እታገላለሁ ብሏል  
አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የመሬት ጥያቄን አጀንዳው በማድረግ ለሶስት ወራት የሚዘልቅ ሁለተኛ ዙር “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ንቅናቄ መጀመሩን ጠቁሞ መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆኑን በመቃወም እንደሚንቀሳቀስ ገልጿል፡፡
ፓርቲው በትናንትናው እለት በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋሉን በመቃወም የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ ጫና ለመፍጠር፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተመረጡ 14 የክልል ከተሞች ህዝባዊ ስብሠባ የሚያካሂድ ሲሆን ስብሠባዎቹ እንደቀድሞው በመንግስት የሚደናቀፉ ከሆነ ወደ ሠላማዊ ሠልፍነት እንደሚለወጡ አስታውቋል፡፡ በመሬት ጥያቄ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የፓርቲው የ3 ወር ንቅናቄ፣ በመጪው ሳምንት መጋቢት 7 አዲስ አበባ ላይ በሚካሄድ ህዝባዊ ስብሠባ ተጀምሮ፣ በሣምንቱ በደሴ እና በድጋሚ በአዲስ አበባ የሚደረግ ሲሆን በየ15 ቀን ልዩነት በሃዋሣ፣ አዳማ፣ ለገጣፎ፣ መቀሌ፣ ደብረታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ድሬዳዋ፣ ጂንካ፣ ቁጫ፣ አሶሣ፣ ነቀምት እና ጋምቤላ ከተካሄደ በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሚደረግ ማጠቃለያ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚቋጭ የፓርቲው አመራሮች ገልፀዋል፡፡ እነዚህ የክልል ከተሞች የተመረጡት ለገበሬው ቅርብ ስለሆኑ ነው ብሏል - ፓርቲው፡፡
አንድነት ባለፈው ዓመት ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2005 ዓ.ም ባካሄደው የመጀመሪያ ዙር “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ንቅናቄ የፀረ ሽብር አዋጁን፣ የፕሬስ ህጉን፣ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንና የዜጐች ከቀዬአቸው መፈናቀልን አጀንዳው አድርጐ በአዲስ አበባና 11 የክልል ከተሞች ባካሄዳቸው ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ወከባ ቢደርስበትም ንቅናቄው ስኬታማ እንደነበር መግለፁ  ይታወሳል።  

http://addisadmassnews.com/

ህዝብን በመጨቆን ሀገርን መምራት አይቻልም!

በአሸናፊ ንጋቱ

የፖለቲካ ስርአትና የአንድ ሀገር እድገት ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አላቸዉ። አንድ አገር ትክክለኛ ባልሆነ የፖለቲካ አገዛዝ ይበለፅጋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ሃገራችን ኢትዮጵያም የወያኔ መንግስት ባነገሰው የተዛባ አገዛዝ ሳቢያ ህዝባችን ለከፋ ችግር መዳረጉ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው። ታዲያ በዚህ ወያኔያዊ የተዛባ አገዛዝ እንዴት ከችግር ልንወጣ እንችላለን? አገራችን ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት ብትሆንም በአየር ንብረትም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት ጥሩ ከሚባሉት ሀገሮች አንዷ ብትሆንም እንደ እድል ሆኖ መሪዎች ግን አልተሳኩላትም። ለምን ኢትዮጵያ የረሃብ አገር ተባለች ለምን ዜጎቿ ተደስተው በነጻነት መኖርን እንደተመኙ ህልማችዉ ከንቱ ሆነ? ብዙዎች የሞቱላት አገር  አንገታቸዉ ለሰይፍ ደረታቸዉ ለጥይት የሰጡላት አገር ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ታታሪነት አለም ያደነቃት ለምን ተዋርዳ ተገኘች!?
እውቀትን፣ ስልጣኔን፣ ጥበብን ለአለም ያበረከተች ሃገር ዛሬ ላይ በቤተ መንግስቱም ይሁን በቤተ ክህነቱ የተማሩ ሰዎችን ናፊቂ ሆናለች፡፡ ምክንያቱም ምሁራኑ በሃገራቸው ሊኖሩ የሚያስችላቸው እድል ስላልተመቻቸላቸው ሁሉም ጉዟቸው ወደ ውጭው አለም ስደት በመሆኑ ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች በረሃብ አለንጋ የሚገረፍባት ሲኦልም ከሆነች ዘመናትን አስቆጥራለች፡፡ እንዲሁም መለያየትን ወይም ዘረኝነት በግልፅ የምትሰብክ የዘረኞችና የጎሰኞች መሰማሪያ ሜዳ ሆና ክፉ አድራጊዎች እንደፈለጉ እየዘፈኑባት ትገኛለች፡፡ በቃል ከሚወራ ዲሞክራሲ፣ እድገት፣ ብልፅግና በስተቀር በተግባር የሚታይ አንዳችም መልካም ነገር የማናይባት አሳፊሪ ሃገር ሆናለች፡፡ በደልና ጭቆና በዝቷል ድህነትና ጉስቁልና ከመቼዉም በባሰ ተንሰራፍቷል እስርና ሰቆቃ ተራ ነገሮች ሆነዋል። በአሸባሪዎች ስም እራሳቸዉ ቦንቦች አጥምደው ህዝቦች እየፈጁ ሰላማዊ ዜጎች በአሸባሪነት እየተፈረጁ ለስቃይ እየተዳረጉ ነዉ። ዛሬ በሃገራችን አርሶም ሆነ ነግዶ መኖር አይቻልም። መኖር የሚቻለዉ ኢሕአዴግ ልማት ነዉ የሚለዉን መዝሙር በመዘመር ብቻ ነዉ።
የሁሉም ነገር መሰረት እንደሆነ የሚታመንበት ትምህርትን ብንመለከት እንኳ ትምህርት በኢትዮጵያ ሞቷል ለማለት በሚያስደፍርበት ጀረጃ ደርሷል። ከተለያዩ ሀገሮች ያለምንም ጥናት በኩረጃ የሚያመጧቸዉ የትምህርት ፖሊሲዊች ምንም እንኳን ብዙ ወጭ ቢወጣባቸዉም የሚሰራባቸዉ ለአንድ የትምህርት መንፈቀ አመት ብቻ ነዉ። በኢትዮጵያ ወያኔ ልማት ነዉ በሚል አባዜ የተለከፈ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ልማታዊ መንግስት፣ ልማታዊ፣ ዘፋኝ፣ ልማታዊ አስተማሪ፣ ልማታዊ የእምነት ዘርፍ፤ ወዘተ… በማለት ከወያኔ ጎን ካልተሰለፉ ኢ-ልማታዊ/ ሽብርተኛ የሚል ስም ይሰጣቸዋል ይህንንም ተመርኩዞ ለእንግልትና ለእስራት ይዳረጋሉ። ‘‘ዶሮ ጭንቅላቷ ላይ ስጋ ተሸክማ ወይ አትበላዉ ወይ አታስበላዉ‘‘ እንደተባለዉ ማንንታቸዉና እዉቀታቸዉን ትተዉ የወያኔ መዝሙር ብቻ በመዘመር የሚኖሩ ጥቂት ሰዎች በኢትዮጵያ ዉስጥ የማይጠበቅ ኑሮን ሲኖሩ ይታያሉ። የሚላስ የሚቀመስ በጠፋበት በአሁኗ ኢትዮጵያ ዘይትና ሽንኩርት ለመግዛት እንኳ አንድ ግለሰብ የወር ደሞዙ በቂ አልሆን ባለበት ግዜ እንዴት ጥቂት ባላባቶች ፎቆችና ቪላዎች ይገነባሉ? የህዝብ ንብረት ካአልተዘረፈ በቀር እነሱ ከየት አመጡት? ወይስ ኢትዮጵያ ሲባል እነሱን አይጨምርም?  ከአዉሮፓ መንግስታት የሰዉ ፍጥረት በረሃብና በህክምና እጥረት ህይዎቱን ለማዳን ተብሎ የሚላከው ገንዘብ እነሱ ዉስኪ ሲራጩበት ሊሞዚንና አሉ የተባሉ ምርጥ በአለም ከታወቁ ካምፓኒዎች የተሰሩ መኪናዎች ሲገዙበት ለህዝቡ ድህነት  ባህላችን መሆኑን ዘላለም በመተረክ ይኖራሉ። በስብሰባ ፍቅር ብቻ የተለከፉ ባለስልጣናቶቻችን ስብሰባዉን እንደጨረሱ አበል በሚል ስም ገንዘብ ይከፋፈላሉ። ይህንን እንስሳዊ የሆነ አስተሳሰብ አልደግፍ ያሉት ደግሞ ፀረ ልማትና አሸባሪ በሚል ስም ለእንግልት ይዳረጋሉ። አሸባሪነት ለምን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆነ? አሁን የታሰሩት ዉብ የኢትዮጵያ ልጆች አሸባሪዎች እንደሆኑ የሁል ግዜ ለጆሮ የሰለቸ ንዝንዝ ነዉ፤ ስለዚህ አሸባሪነት ለአምባገነናዊ መንግስት አለመዘመር ከሆነ ወደድክም ጠላህም መኖርም ሆነ መስራት የሚቻለዉ ይህንኑ ስትዘምር ብቻ ነዉ። ለዚችው በሺህ የሚቆጠሩ የነፃነት ታጋዮች የታሰሩባት; ረሃብ፣ ጦርነት፣ሞትና ግድያ መለያየት የሰፈነባት፤ ዜጎችዋ በሰላም ወጥተው በሰላም ለመግባት ለሚሸማቀቁባት ሃገር ለታሪኳ ሁለ መበላሸት ተጠያቂው ወይም ተወቃሹ ገዳዩ የወያኔ አገዛዝ ነው፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ የድንቁርና ፣ የመለያየት፣ የጦርነት፣ ያለማወቅ፣ የግድያ ጭለማ እንዴት ይወገድ ወደሚለው መፍትሄ ሃሳብ ስንመጣ፤ በኢትዮጵያ ያለው የክፉ ነገሮች ሁሉ ጨለማ የሚወገደው በወለደቻቸው እና ባሳደገቻቸው ኢትዮጵያውያን ሃገር ወዳድ ልጆቿ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም ናፍቋት የሰላም ያለህ እያለች ነው፡፡ ውድ ልጆቿም አረመኔው የወያኔ መንግስት በየጊዜው እየቀሰፈባት እረፍትን ትሻለች፡፡ በመሆኑም ይህን አምባገነናዊ  የወያኔ ስርዐት በማስወገድ  ; በሃገራችን የእውቀትና የሰላም ብርሃን እንዲፈነጥቅ ; ዜጎቿም በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ;  መብቶቻቸውም ሊጠበቁ የሚችሉበትን እንዲሁም የምንፈልገውን ነፃነት፣ እድገት፣ፍትህ፣ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ለማምጣት የራሣችንን ቁርጠኝነት ማሣየት ይጠበቅብናል!!!
ድል ለጭቁኑ ህዝብ!!!
በ andethiopia16@gmail.com አስተያየትዎን ይላኩልኝ።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11340/

ፓትርያርኩ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በዩኒቨርስቲ ምሩቃን አትመራም›› ማለታቸው ቅሬታ ፈጠረ

  • ስለ ማኅበራት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት ተጠየቀ
  • ‹‹ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከል ይገባል›› መንግሥት
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፴፰፤ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
His hHoliness00የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ቤተ ክርስቲያንን እንምራ እያሉ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና ሥርዓት አላት፤ እንዲህ ማለት አይችሉም›› በማለት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት በንግግራቸው ቅር የተሰኙ የመንፈሳውያን ማኅበራት አገልጋዮች ጠየቁ፡፡
አገልጋዮቹ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ አቡነ ማትያስ ይህን አስተያየት የሰነዘሩት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋራ በመተባበር የካቲት ፳፩ እና ፳፪ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል የምክክር ጉባኤ በተካሔደበት ወቅት ነው፡፡
በምክክር ጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹በባዮሎጂና ኬምስትሪ እንቀድስ እያሉ ነው፤›› ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ‹‹ምን እያልኹ እንደኾን ይገባችኋል›› በማለት ስለማን እንደ ኾነ የማሳየት ያህል የጠቆሙበት አስተያየት ያልተለመደና ጥቂት የማይባሉ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ያሳዘነ እንደነበር የጉባኤው ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በምክክር ጉባኤው ላይ ለውይይት በቀረቡ ጽሑፎች፣ በአዲስ አበባ እስከ ሰማንያ ሺሕ የሚገመቱ መንፈሳውያን ማኅበራት በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እንደሚንቀሳቀሱ የተጠቀሰ ሲኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራቱ በሕግና በሥርዐት የሚመሩበት ደንብ አውጥታ እስካልተቆጣጠረቻቸው ድረስ እየተከሠቱና ሊከሠቱ የሚችሉ ችግሮች በቀላሉ እንደማይታዩ ተመልክቷል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፣ በማኅበር ሽፋን ለግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው የሚሯሯጡ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ሕጸጽ የሚታይባቸው ማኅበራት የመኖራቸውን ያህል ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ምእመናንን በማትጋት ለበለጠ ሀብተ ጸጋ የሚያበቁ ጠንካራ ማኅበራትም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ በምክክር ስም በሚዘጋጁ መድረኮችና በቤተ ክህነቱ ጉባኤያት እየታየ ያለው ‹‹ማኅበራት አላሠራ አሉን›› በሚልበጅምላ የመፈረጅና የመኰነን ዝንባሌ፣ አብዛኞቹ ማኅበራት ለሀገር በአጠቃላይና ለቤተ ክርስቲያን በተለይ እያበረከቱ ያለውንና በቤተ ክህነቱ ቀጥተኛ አቅም ሊሸፈን የማይችለውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በሚዛን ያላስቀመጠ ነው ብለዋል – የማኅበራት አገልጋዮቹ፡፡
‹‹በአሁኑ ጊዜ ማኅበራት የአባሎቻቸውን አስተዋፅኦና የበጎ አድራጊ ምእመናንን የገንዘብ፣ የዕውቀትና ሞያዊ አቅም በማስተባበር የገጠር አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ት/ቤቶች በተቀናጀ መንገድ እንዲረዱ ያደርጋሉ፤ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ዕድገት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ጥናቶችን ያካሒዳሉ፤ በጠረፍ የሀገሪቱ ክፍል በሚያከናውኑት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ምእመኑ በቋንቋው የሚገለገልበትን ኹኔታ ያመቻቻሉ፤ የቅዱሳት መካናት ተሳላሚዎችን የክብረ በዓላት ጉዞዎች በማስተባበር ሕዝቡ ቅርሱንና ባህሉን ዐውቆ እንዲጠብቀውና እንዲከባከበው ከማስቻላቸው ባሻገር ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መስፋፋትና መጠናከርም ያላቸው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤›› ሲሉ በበጎ ፈቃድ የሚሰበሰቡ ማኅበራትን አገልግሎትና ድርሻ አብራርተዋል፡፡
ማኅበራቱ አብዛኞቹን ተግባራት የሚያከናውኑት በየደረጃው ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሓላፊዎችና አባቶች ፈቃድ እያገኙና መመሪያ እየተቀበሉ መኾኑን የሚገልጹት አገልጋዮቹ፣ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. የማኅበራትን ቁጥር ስለ መቆጣጠር ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ በነበረ ጥናት መነሻነት ምልዓተ ጉባኤው ራሱን የቻለና ማኅበራቱን የሚያሠራ ሕግ እንዲዘጋጅ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበትደንብ አዘጋጅ ኮሚቴ ሠይሞ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የማኅበራት አደረጃጀትና የፋይናንስ ቁጥጥር መርሖን ጠብቆ እንደሚወጣሲጠበቅ የቆየው ደንብ ከሚገባው በላይ መዘግየቱ ችግሩ ከቤተ ክህነቱ እንጂ ከማኅበራቱ አገልግሎትና ብዛት አለመኾኑን እንደሚያመለክት ይከራከራሉ፡፡
ፓትርያርኩ አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማስተዳደር በዕለተ ሢመታቸው ቃለ መሐላ መፈጸማቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በምክክር ጉባኤው ላይ በተጠቀሰው አኳኋን የመናገራቸው ግፊት የተለያየ መነሻ ሊኖረው እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የመጀመሪያው መንሥኤ፣ የሙስናንና ብልሹ አሠራርን ችግር ለመቅረፍና ለማድረቅ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተሠራው የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ተቃዋሚዎች ‹የጥናቱ ባለቤት ነው› በማለት በሚከሡት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር አማካይነት እንዲፈጠር የሚሹት ጫና ነው፡፡
ኹለተኛው መንሥኤ ደግሞ በመንግሥት በኩል፣ ‹‹በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚታየው ህልውናቸውና ዓላማቸው ሃይማኖታዊና በሃይማኖቱ የበላይ ጠባቂዎች ይኹንታ በተቋቋሙ የወጣት ማኅበራት አደረጃጀቶች ውስጥ በመሸጉ አካላት ነው፤ ስለዚህም ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከሉ ይገባል፤›› የሚለው [በአንድ ማኅበር ላይ እንዳነጣጠረ ግልጽ እየኾነ የመጣው] የአክራሪነት ውንጀላና ክሥ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያሳደረው ማኅበራቱን በምዝገባና ክትትል የመቆጣጠር ጫና ነው፡፡
የአክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ምንነት መፍትሔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች በሚያብራሩት የመንግሥት ሰነዶች፣ የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ከሚባሉት ኹኔታዎች ውስጥ÷ ‹‹የሃይማኖት ተቋማቱ የሰው ኃይል አስተዳደርና የፋይናንስ ሥርዐት ለተከታዩ ሕዝብ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው መኾኑና ከዚኹ ጋራ ተያይዞ በሙስናና በአስተዳደር በደል ሳቢያ የሚፈጠር ግጭት፣ የሰው ኃይል አስተዳደር በዘመድ አዝማድና በጉቦ እየኾነ የሥራ ብቃት በሌላቸው ሰዎች የሚሠራበት፣ የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ የሚተችበትና አስተያየት የሚሰጥበት ሥርዐት አለመዳበሩ፣ ምእመናን የአክራሪነት ሰርጎ ገብ አስተሳሰቦችን የሚቋቋሙበት በሃይማኖት ዕውቀት የማስታጠቅ ክፍተት›› ይገኙበታል፡፡
በመንግሥት ትንታኔ መሠረት አክራሪነትን የመዋጊያው ቁልፍ መሣሪያ÷ የሀገር ልማትንና ዕድገትን ማፋጠን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን፣ የወጣቶችና ሴቶች ሥራ አጥነትን መቅረፍ፣ ሕዝቡን በሃይማኖታዊ ዕውቀቱ ማስታጠቅ ነው፡፡
የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጓቸዋል የተባሉት የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሠራር ችግሮች÷ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም ባልተሳተፈበትና በተቃዋሚዎች አላግባብ በሚከሠሥበት የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ትግበራን በማፋጠን እንዲኹም ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ በርካታ ማኅበራት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የገዳማትና የአብነት ት/ቤት ማኅበረሰቦችን በልማትና ተራድኦ ከመደገፍ ጀምሮ በሚያከናውኑት የሐዋርያዊ ተልእኮ ንቃት ሊወገድ እንደሚችል ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያምናሉ፡፡
ከዚኽም አንጻር ፓትርያርኩ ንግግራቸውን[ከንግግራቸው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከአዳራሹ ወጣ ብለው በተቀበሉት የስልክ ውይይት እንደተቀበሉት የተጠቆመውን] መልሰው በማጤን ማኅበራት አገልግሎታቸውን በተገቢው የአደረጃጀትና የፋይናንስ ቁጥጥር መርሖመሠረት አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችላቸው ኹኔታ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል፡፡
http://haratewahido.wordpress.com/