Wednesday, 14 January 2015

“ሕዝብን ለማውደም ውጤታማው መንገድ ታሪካቸውን የሚረዱበትን መንገድ ማስካድና ጨርሶውኑ መደምሰስ ነው” ጣይቱ ወደመ ቀጣይ ተረኛ . . .?

“ሕዝብን ለማውደም ውጤታማው መንገድ ሰዎች ታሪካቸውን የሚረዱበትን መንገድ ማስካድና ጨርሶውኑ በመደምሰስ ነው” የሚለው የእንስሶች እርሻ ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ብሒል ሰሞኑን ከፍተኛ መነጋሪያ ሆኗል፡፡ ለዚሁም መነሻው በየተራ እንዲወድሙ ከተደረጉት የሕዝብ የማንነት መገለጫዎች መካከል አንደኛ ቅርስ የሆነው የጣይቱ ሆቴል መውደምን ተከትሎ ነው፡፡
የእንስሶች እርሻ መጽሐፍ ህወሃት በተሰነጠቀበት ወቅት የእነ መለስ መገለጫ ነው ተብሎ በስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲነበብ የነበረ መጽሐፍ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የውኅዳኑ ደጋፊ ሪፖርተርም በየሳምንቱ እየተረጎመ ያቀርበው እንደነበር ጋዜጣው ምስክር ነው፡፡
ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ በጻፈው “አጤ ምኒልክ” መፅሐፍ ገጽ 328-330 የሆቴሉ ታሪክ እንዲህ ይነበባል፡፡
በአዲስ አበባ የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ተሠርታ በምትመረቅበት ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ ያሉ መኳንንት ለምረቃው ተጠርተው ነበር፡፡ ለተጠራው እንግዳ ማሳረፊያ እንጦጦ አይበቃ ስለነበር እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ተራራ ሥር ያለው ሕዝብ ሁሉ ለሚጠራው እንግዳ መጠለያ ቤት እንዲሰጥ ለመኑ፡፡ እንግዳ የሚያሳድር ሁሉ ሽሮ፣ በርበሬና ቅቤ፣ ዱቄትና ሥጋ ከቤተ መንግሥቱ እየወሰደ እንግዶቹን እንዲያስተናግድ አዘዙ፡፡ በዚህ ዓይነት የእንጦጦ ቤተ ክርስቲያን ምረቃ ተፈጸመ፡፡ ከዚህም በኋላ ለሚመጣው እንግዳ ማረፊያና መመገቢያ ችግር እየሆነ መጣ፡፡
ምኒልክ “እህእ” እያሉ ወሬ ያጠያይቁ ጀመር፡፡ “በፈረንጅ አገር ሆቴል የሚባል ቤት ስላለ ማንኛውም እንግዳ ገንዘቡን እየከፈለ ያርፍበታል፤ ምግቡንም ይበላበታል” አሏቸው፡፡ በዚህ መሠረት ሥራው እንዲጀመርአዝዘው ሕንጻው ተሠርቶ ሆቴል ቤቱ በ1898 ዓም በነሐሴ ወር ሥራው ጀመረ፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ስለ ሆቴል ቤቱ ሲያብራሩ “ስሙም ሆቴል ተባለ” ይላሉ፡፡ ኃላፊነቱም፣ ሥራውንም እቴጌ ጣይቱ ተክበው ይመሩና ያስተዳድሩ ጀመር፡፡ በ1900 ዓም ጥቅምት 25 ቀን ምኒልክ በአዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶችንና የውጭ አገር ሰዎችን ጋብዘው ሆቴሉን አስመረቁ፡፡ የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅም ሙሴ ፍሬደሪክ ሐል ነበር:: በኋላ ግን አቶ ዘለቃ አጋርደው ተሾሙ፡፡
እንደ አገር አባባል ጣይቱ እጅ የሚያስቆረጥም ወጥ እያሠሩ ገበያ ቢጠብቁ ጠፋ:: እንኳን ምግብ መብላት ከግሪኮች ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ መጠጣት ነውር ነበረና ጣይቱ ጠዋት የሚያሠሩት ወጥ ለሠራተኞቹ የማታ ራት ይሆን ጀመር፡፡ የሚስታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኩዋንንቶች “ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለችና ኑ እንሂድና ልጋብዛችሁ” ብለው ወሰዱዋቸው፡፡ መኳንንት በላ ጠጣና ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ፡፡
በማግሥቱ እንደተለመደው ገበያ ቢጠበቅ ጠፋ ቀጥሎም ጠፋ፤ ቀጥሎም ጠፋ፡፡ እንደገና ምኒልክ ሆቴል ገብቶ መብላት ነውር ያለ መሆኑን ለመኳንንቱ ገልፀው እንደገና ምሣ ጋበዙ፡፡ በሌላው ቀን አሁንም ገበያ አልተገኘም፡፡ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድርሽ የሚል ሰው ጠፋ፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ አጤ ምኒልክ ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በዙሪያቸው ላሉ መኳንንት “ሰማችሁ ወዳጆቼ” አሉ:: “በፈረንጅ አገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደሆነ ያ የተጋበዘ ሰው በሌላ ቀን ደግሞ ብድሩን ይከፍላል ብድሩን ካልከፈለ ግን እንደ ነውር ይቆጠርበታል፡፡” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መኳንንቱ “እርስዎን ፈርተንና አፍረን ነው እንጂ የሚሆንልን ከሆነ የምኒልክን ብድር ለመመለስ እኔ አለሁ” እያለ ተራ በተራ ከሆቴል ቤት ምኒልክንና ጣይቱን ይጋብዝ ጀመረ፡፡ ገበያ እየደራ ሄደ፡፡ ምሳችንን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ የሚለው ስለበዛም ስሙ እቴጌ ሆቴል ተባለ፡፡
ዛሬ በታላላቅና በሌሎችም ሆቴል ቤቶች ጋሻና ጦር እየተሰቀለ እናያለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አደራረግ የተጀመረው በምኒልክ ነው፡፡
[እምዬ ምኒልክ መጋቢት 3፤ 1900ዓም ለደጃዝማች ሥዩም የላኩት መልዕክት እንዲህ ይነበባል]
ይድረስ ለደጃዝማች ሥዩም፤
“. . . የላክኸው የዝሆን ጥርስ አልጋና ተምቤን የተሠራ ጋሻ ደረሰልኝ፡፡ ጋሻ ግን ለግራኝ ተብሎ ተሠርቶ እንደሆነ ነው እንጂ ሌላ ሰው ይይዘዋል ተብሎ አልተሠራም፡፡ ነገር ግን ለሆቴል ቤት ለላንቲካ እንዲሆን አደረግሁት. . . ”
**********************************
?
አይመስለኝም ነበር እሳት ወኔ ኖሮት
ጣይን የሚገላት
ወልዮልሽ አራዳ … …. ወዮልሽ ሃገሬ
ማን ሊያሞቅሽ ነዉ
አድማስ ተደርምሶ ጣይሽ ጠልቃ ዛሬ?
(Binu Ye Tsehay ፌሰቡክ)

“ሕዝብን ለማውደም ውጤታማው መንገድ ሰዎች ታሪካቸውን የሚረዱበትን መንገድ ማስካድና ጨርሶውኑ በመደምሰስ ነው” ጆርጅ ኦርዌል፡፡

taitu hoteltayitu hotelItegue-Taitu-Hoteltaitu hTaituHotelTaitu-hotelTaitu_hTaytu-Hotel

በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣ ዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ መሀል የተደረገውን ውህደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣

በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣ ዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ መሀል የተደረገውን ውህደት በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በዛሬው ዕለት፣ ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ ለዴሞክራሲና የነጻነት፣ ንቅናቄ፣ ድርጅቶች፣ ተዋህደን “አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ”፣ በሚባል ሥም መጠራት መጀመራችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስናበስር፣ እጅግ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ባለፉት በርካታ አስርተ አመታት፣ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነጻነት፣ መብትና አንድነት፣ ከፍተኛ ትግል ሲያካሂድ ቆይቷል። በአደረገውም ትግል እጅግ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍሏል። ለከፈለው ከፍተኛ ዋጋ የሚመጥን ግን ምንም ዓይነት ውጤት አላገኘም። እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የመብት ረገጣው፣ አድሎው፣ ማስፈራራቱና ማዋከቡ ተጠናክረው መቀጠል ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልትቀጥል የማያስችል ከፍተኛ የመበታተን አደጋ አንጃቦባት ትገኛለች ።
በሀገራችን ላይ ላንጃበበው ከፍተኛ የመበታተን አደጋ ምክንያት የሆነው በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ የአምባገነን ቡድን ነው። ይህ ዘረኛ አምባገነን ቡድን በሀገራችን ታሪክ በሥልጣን ላይ ከመጡ የገዥ ሃይሎች ጋር ሲወዳደር ሀገርን ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ፣ ሕዝቧን በማወረድ፣ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ዕኩይ ሃይል መሆኑን በበርካታ ተግባራቶቹ ያለ ምንም ጥርጣሬ አረጋግጧል።
በሌላ በኩል ለቀድሞቹም ሆነ ለዛሬው ዘረኛው የወያኔ አምባገነን ገዥ በሕዝብና በሀገር ላይ በደል እየፈጸመ በሥልጣን መቆየት የቻለበት ምክንያት፣ በተቃዋሚነት የሕዝቡን ትግል ለመምራት የተንቀሳቀስን ድርጅቶች፣ የተቋቋምንበት ዓላማ መለያዬት ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ዓይነት ዓላማ ያለንም ብንሆን፣ ከድርጅቶቻችን ጠባብ ፍላጎቶችና ስሜቶች ባለፈ፣ የሀገርና የሕዝብን ጉዳይ በማስቀደም በጋራ መሰባሰብና መታገል ስላቃተን ነው። በዚህም ድርጊታችን የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የወገናችንንም የመከራ ዘመን እያራዘምን እንገኛለን ።
ይህ ሁኔታ በተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶች መሀል ከፍተኛ ጥርጣሬና ፍርሀት ከመፍጠሩ የተነሳ በምንም ዓይነት ሁኔታ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች በጋራ በሀገርና በሕዝብ ደረጃ ትርጉም ያለው ስራ መስራት አይችሉም፣ የሚለው አመለካከት የበላይነት እንዲያገኝ አድርጎታል።
በዛሬው ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ ውህደት የመጣነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7፣ ለፍትህ፣፡ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ መዋሃድ መወሰናችንን ፣ ስንገልጽ በተናጠል ከሚደረጉ በጋራ የሚደረጉ የትግል ጥረቶች ውጤታማ ይሆናሉ በሚል ብቻ ሳይሆን፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ በሀገርና በሕዝብ ደረጃ ትርጉም ያለው ሥራ በጋራ መስራት አይቻሉም የሚለውን፣ አስከፊ ተመክሮና አመለካካት ለመስበርም ነው።
በእኛ እምነት ከትናናሽ ድርጅቶች ዙሪያ ከሚሽከረከሩ ሀሳቦችና ስሜቶች ለመውጣትና ሀገራዊና ሕዝባዊ የሆነው ጉዳይ ለማስቀደም የወሰነ ማንኛውም ድርጅት፣ አርበኞችና ግንቦት7፣ የደረሱበት የውህደት ውሳኔ ወይም በሌሎች በጋራ ሊያሰሩ በሚችሉ ስምምነቶች አብሮ ለመስራት መወሰን የማይችልበት ምንም ምክንያት አይታየንም። በወያኔ አድሎ ስርዓት የተንገፈገፈና ትግሉን ለመቀላቀል የቆረጠ ማንኛውም ዜጋ፣ የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ትግሉን መቀላቀል ይችላል፣ የኢትዮያ ሕዝብ በአንድነት የተነሳ ቀን ደግሞ፣ የወያኔ ግብዓተ መሬት ይፈጸማል፣ ብለን ከልብ እናምናለን።
ይህም በመሆኑ፣
ለተቃዋሚ ድርጅቶች፣
ዛሬ በአርበኞችና በግንቦት 7፣ የተጀመረው ጉዞ ውጤታማ በመሆን ሀገራዊና ታሪካዊ ትርጉም እንዲኖረው፣ ሌሎችም በተግባር የምትንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ወያኔን የማስወገድንና ብሎም ሀገር የማረጋጋቱን ሀላፊነት በጋራ እንድንወጣ የሚያስችል መቀራረብ እንድናደርግ ፣ በውህደት በመሰረትነው፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ለወታደራዊና የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣
የወያኔ ዘረኛና አምባገነን ቡድን ዕድሜን ለማሳጠርና ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ሀገር እንድትኖር ፣ በየቦታው የሚደረገውን ትግል፣ የሰሞኑን ቆራጥ የዓየር ሃይል መኮንንኖች ያሳዩትን ዓርያነት በመከተልና በተገኘው አጋጣሚና ሁኔታ በመጠቀም፣ እንድትቀላቀሉ በውህደቱ ድርጅት፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣
በረጅም ታሪክህ አይተሄው ለማታውቀው፣ ውርደት፣ ክፋት፣ የመከፋፈልና የመጋጨት አደጋ፣ የመብት እረገጣና አፈና፣ ሀገርና ሕዝብን የማራከስና የመሸጥ፣ ዕኩይ ተግባር፣ የተጠናወተው ወያኔ እና የግብር አበሮቹን፣ ጠራርጎ ለማስወገድ በተጀመረው የጋራ ትግል ውስጥ በቀጥታ እንድትሳተፍም ሆነ በምትችለው ሁሉ እርዳታ እንድታደርግ፣ በዛሬው ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም የአርበኞችና የግንቦት 7 ውህደት በወለደው፣ በአርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ ሥም፣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ፣
ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም

Friday, 12 December 2014

ከዓለም የተሰባሰቡ ሴቶች የእናት ሃገር ጥሪ ጠርቶዎታል!!!ሁሉም ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጀች እንድትታደሙ ተጋብዘዋል!!!


Friday, 28 November 2014

እስረኞችን ለመጠየቅ ቃሊቲ የሄዱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ተለቀቁ

በአንድነት ፓርቲ በቃሊቲ እና ቂሊንጦ የሚገኙ የህሊና እስረኞችን ለመየጠቅ ወደስፍራው ያመሩ ወደ 30 የሚገመቱ ሰዎች ቀትር ላይ በቃሊቲ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ መለቀቃቸው ታወቀ፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አስራት አብርሃ ከ30 ደቂቃዎች በፊት በስልክ እንደነገሩኝ ከሆነ ‹‹እነእስክንድርንና አንዷለምን መጠየቅ አትችሉም፡፡ ተባልን ከዚያም ‹‹ለምን?›› ብለን ስንጠይቅ በዋናው በር በኩል ኃላፊውን አነጋግሩ የሚል መልስ ተሠጠን፡፡ እኛም ይህንን አምነን ሄድን፡፡ ስንደርስ በቁጥጥር ሥር ውላችኋል ብለውን ወደ 30 የምንገመት ሰዎችን መታወቂያችንን ከመዘገቡ በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ ለጊዜው እንገኛለን›› ብለውኝ ነበር፡፡ አሁን ባገኘሁት መረጃ መሰረት ደግሞ በኮንቴይነር ውስጥ ታግተው የነበሩት እስረኛ ጠያቂዎች ከበድ ያለ ፍተሻ ተደርጎላቸው ከቃሊቲ ግቢ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

“ምስጢር ካወጣህ ቤተሰቦችህን እንፈጃቸዋለን” “ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል”


“የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል”
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ በዝዋይ እስር ቤት ለወራት ስቃይ የተፈፀመበት
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ይባላል፤ አርሲ አርባ ጉጉ ተወልዶ አዳማ/ናዝሬት አድጎ፣ በ1998 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ ተመርቋል፡፡ በ2000 ዓ.ም በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር በሲኒየር ካልቸራል ኤክስፐርትነት የስራ መደብ እስከ ሚያዝያ 2003 ሰርቷል፡፡ ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በግልፅ ባልተረዳው ምክንያት የመንግስት ደህንነት ሀይሎች ተያዞ ለ23 ወር በዝዋይ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈፀመበት መቆየቱን ይናገራል፡፡ መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም ከእስራት ሲለቀቅም አንድ ጊዜም እንኳን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ ለፍኖተ ነፃነት አስረድቷል፡፡ ከወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ጋር ያደረግነውን ቆይታ ተከታተሉን፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- ማን ነበር ያሰረህ?
ወጣት ተስፋዬ:- ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በማለዳ ቤቴ ተንኳኳ፤ ተነስቼ ከፈትኩኝ፡፡ የማላውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ “ና ውጣ፤ ልብስህን ለብሰህ ውጣ” አሉኝ፡፡ እኔ እናቴ ሞታ ሊያረዱኝ የመጡ መስሎኝ “ምነው ቤተሰብ ደህና አደለም? የተፈጠረ ችግር አለ?” አልኳቸው “ዝም ብለህ ናውጣ” አሉኝ፡፡ ልብሴን ለበስኩኝና ወጣሁ፤ አንቀው መኪና ውስጥ ከተው ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝና 3 ወር አሰሩኝ ከዛም አንድ አመት ከ8 ወር ዝዋይ ማረሚያ ቤት፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- መታሰርህን ለቤተሰብ ተናግረሀል?
ወጣት ተስፋዬ:- ለማንም ሰው እንድናገር አልፈቀዱልኝም፤ መስሪያ ቤቴ አልጠየቀኝም፣ ደሃዋ እናቴ ያለችው ናዝሬት ነው እሷም የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ አባቴ አቶ ተካልኝ አስተማሪ ነበር አርባ ጉጉ ላይ ነው በ1985 ዓ.ም በነበረው ግጭት ነው የተገደለው፡፡ ማንም ሳይጠይቀኝ፣ፍ/ቤት ሳልቀርብ 23 ወር ታሰርኩ ልብስ ምግብም የሚያመጣልኝ ሰው አልነበረም፡፡ እናቴም መታሰሬን እንኳ አታውቅም መስሪያ ቤቴም ስኮላርሽፕ አግኝቷል፤ ወደ ውጪ ሃገር ሊማር ሊሄድ ነው የሚባል ነገር ስለነበረ አልጠየቁኝም፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- የት ነበር ስኮላርሺፕ ያገኘኸው?
ወጣት ተስፋዬ:- የዛሬ 2 ዓመት አካባቢ የራስመስ ሙንደስን ስኮላርሽፕ አግኝቼ ነበር፡፡ ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያና ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶክዮ ባሉ ምሁራን ሪኮመንድ ተደርጌ በጣሊያኑ ፌራሪ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ እንደተፈታሁ ሄጄ ስጠይቃቸው ብዙዎቹ ጓደኞቼ በጣም ደነገጡ፡፡ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ቅማል ተወርሬ … ባካችሁ ተውኝ … ምንም የሌለ ነገር የለም በጣም ተጎድቻለሁ፡፡ ከማረሚያ ቤት እንደወጣሁ እናቴ ጋ ስሄድ በጣም ደነገጠች፣ በሕይወት ያለሁ አልመሰላትም 23 ወር ሙሉ ከቤተሰብ ስለተለየሁ ግራተጋባች፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- በእስር ወቅት የደረሰብህ ድብደባና ማሰቃየት ነበር?
ወጣት ተስፋዬ:- ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ በኤሌክትሪክ ጀርባዬ ላይ አቃጥለውኛል፣ በብልቴ ላይና በኩላሊቴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱብኝ ሽንት ችዬ አልሸናም፣ ሽንቴን መቆጣጠርም አልችልም፡፡ ኩላሊቴንም በጣም ያመኛል፡፡ ውሃ ውስጥ እየነከሩ በጣም ደብድበውኛል፡፡ አሁን ስናገር ያመኛል ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- እንደው ስታስበው ለእስር ያበቃህ ወይም ከመንግስት ጋር ያጋጨህ አጋጣሚ ነበር?
ወጣት ተስፋዬ:- መስሪያ ቤቴ ውስጥ የኢህአዴግ አባላት ነበሩ፤ በጣም ይከታተሉኛል፡፡ በቢ.ፒ.አር ላይ ስብሰባ በተደጋጋሚ ይጠራ ነበር፡፡ እኔም ሠራተኛ ላይ ተፅእኖ የሚያደርሱ ነገሮች ሲመጡ እኔ አልቀበልም በግልፅ እናገር ነበር፤ ሠራተኛውም እኔን ይደግፋል፡፡ ከመታሰሬ ጥቂት ጊዜ በፊት ገነት ሆቴል ስብሰባ ነበረን፡፡ በዛ ስብሰባ ላይ በጣም ተከራከርኩ፤ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አቶ ፀጋዬ ማሞ የሚባሉ አሰልጣኝ፣ ከውጭ ጉዳይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና ከንግድና ኢንዱስትሪም የመጡ ነበሩ ስማቸውን የማላስታውሳቸው ባለስልጣን ነበሩ፤ እዛ ላይ ሀሳብ አንስቼ ተከራክሬ ነበር፡፡ “የሠራተኛን ሀሳብ ዳይቨርት ያደርጋል” ይሉኝ ነበር፡፡ መቼም ግን ሀሳቤን በመናገሬ ይህን የመሰለ ስቃይ ይደርስብኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ “አሸባሪ፣ ግንቦት ሰባት” እያሉ እኔ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ያለምንም ፍርድ በርሜል ውስጥ ውሃ ጨምረው እያስተኙ አሰቃዩኝ፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- እንደዚህ ያሰቃዩህ ምን አይነት ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ ነው?
ወጣት ተስፋዬ:- እኔን ጥፋተኛ የሚያስደርግ ምንም መረጃ አላገኙም፣ እኔን አስረው ወደ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ ይደውሉ እንደነበር ይነግሩኝ ነበር፡፡ የኢሜይል አድሬሴንም ተቀብለው በርብረዋል ግን ምንም አላገኙም፡፡ እኔ ከማንም ጋር ሊንክ የለኝም ኢሜሌ ላይ የስኮላርሺፕ መልዕክት ካልሆነ በስተቀር ምንም የለውም፡፡ በመስሪያ ቤቴ ሪሰርቸር ነበርኩ፣ በሶሲዮሎጂ ነው የተመረኩት፡፡ ሉሲ የተገኘችበት ሣይት ላይ አፋር፣ ጋምቤላ ብዙ ሳይቶች ሰርቻለሁ፡፡ ከአለቆቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት ሰላማዊ ነው እነሱ ናቸው ስኮላርሽፕ ሪኮመንድ ያደረጉኝ፡፡ አንደኛው ፕሮፌሰር 25 ዓመት ሙሉ እዚህ አገር ሰርቷል፣ አርዲን ያገኘው እሱ ነው፡፡ ሄነሪ ጊልበርት ይባላል፤ እሱም ሪኮመንድ አድርጎኛል፡፡ እኔ በጣም የሚቆጨኝ ደሃዋ እናቴ አረቄና ጠላ ሸጣ ነው ያስተማረችኝ ምን ብዬ ልንገራት እንደዚህ አትጠብቀኝም ከበደኝ፣ አሁን እሷ የምትሰጠኝ ምግብ ራሱ ደምደም አለኝ… (ረጅም ለቅሶ)፡፡ ልጄ በደህናው አይደለም የጠፋው ሞቷል ወይም መኪና ገጭቶታል ብላ ነበር የምታስበው፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- የከመታሰርህ በፊት ፖለቲካ ተሳትፎ ነበረህ?
ወጣት ተስፋዬ:- 1997 ዓ.ም የቅንጅት ደጋፊ ነበርኩ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ በ97 የነበረው ሁኔታ ስንት ሰው አለቀ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር ታውቃላችሁ ምንም የምናደርገው ነገር አልነበረም ፡፡ በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን መያዝ እንደማይቻል ተረዳሁኝ፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አልሆንኩም፡፡ ከዚህ በኋላ ከምንም ነገር የተገለልኩ ሆኛለሁ፡፡ አንድ ብርጭቆ ሳትሰብር አሸባሪ ስትባል አስብ እንግዲህ አንድ ብርጭቆ እንኳን ሰብሬ አላውቅም ባለኝ እውቀት እንደውም ለእውቀት ነው የምጓጓው እውቀቴን አሳድጌ አገሬን ለመለወጥ ነው የማስበው እኔን ምንም የሚመለከተኝ ነገር የለም አሸባሪም ግንቦት ሰባትም አይደለሁም፡፡ስትደበደብ፣ ስትሰቃይ ያላደረከውን አድርጌያለሁ ትላለህ፤ በርሜል ውሃ ሞልተው ይከቱሃል ያሰቃዩሃል፡፡ አያሳዝንም ይሄ? እንዴት አድርጎ እዚህ አገር ይኖራል? 23 ወር ሙሉ አስረው ማሰቃየታቸው ሳያንስ የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል፡፡ እኔ ግን ከዚህ በላይ ሞት የለም ብዬ ነው የነገርኳችሁ፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- አሁን የት ነው የምትኖረው?
ወጣት ተስፋዬ:- መኖሪያ የለኝም … (ረጅም ለቅሶ)
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝን ለመርዳት የምትፈልጉ አንባብያን ከፍኖተ ነፃነት መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ (ምንጭ ፍኖተ ነጻነት)

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ የወጣቶች ክፍል አዘጋጅነት ታላቅ ሰላማዊሰልፍ በኖርዌይ ኦስሎ ተካሄደ!!!

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ የወጣቶች ክፍል አዘጋጅነት በዛሬው እለት ሀሙስ (November 27,2014)  በኖርዌ ኦስሎ በእንግሊዝ ኢንባሲ ፊት በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሩቅም ከቅርብም በአንድነት በመሰባሰብ ከቀኑ 13፡30 እስከ 15፡00 ስዓት ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
DSC_0233DSC_0220DSC_0268DSC_0230
የሰልፉ ዋና አላማ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሃፊና የሰባዊ መብት ተቆርቋሪ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ  በአንምባ ገነኑ የወያኔ ቡድን በህገ ወጥ መንገድ ታፍነውና ፍትህ ተነፍገው በእስር ቤት መታሰራቸውን ለመቃወም ሲሆን በሰልፉ ስፍራ የተገኙ ሰዎች ሁሉ አቶ አንዳርጋቸው ለዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት መከበር ከወጣትነት ጀምሮ የታገለ ታላቅ የሰላም ምሳሌ፣ የፍትህ ተምሳሌት፣ የነጻነት በር ከፋች እንዲሁም አገራዊ ስሜት የተላበሰ አርበኛ እንጂ እስር፣ ድብደባና መሰቃየት የሚገባው ሰው አልነበረም በማለት ለእንግሊዝ መንግስት በኢንባሲው አማካኝነት ዜጋዋን ከአረመኔና ጨካኝ መዳፍ እንድትታደግና ፍትህ እንዲያገኝ  በከፍተኛ ድምጽ አሳስበዋል።
ወጣቶች እጃቸውን በሰንሰለት በማሰር እኛም እንደ አርበኛው አንዳርጋቸው ጽጌና በእስር ቤት የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውን የቁም እስረኞች ነን የሚል ጥልቅ መልእክት አስተላልፈዋል። ብዙ መስራትና መጻፍ የሚችሉ እጆች፣ መናገር የሚችል አንደበት፣ የእውቀት ባለቤት የሆነ አእምሮ ታስረዋልና እኛም ወጣቶች እስረኞች ነን በሚል ውስጣዊ ስሜት ለስዓታት የኖርዌ ብርድና ቁር ሳይበግራቸው እጃቸውን በሰንሰለት በማሰር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።
DSC_0185DSC_0193DSC_0208DSC_0323

እንዲሁም ሰልፈኞቹ  የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ በታላቅ ድምጽና ስሜት ለኢንባሲው  አሰምተዋል።  ከአሰሟቸው  መፈክሮች መካከል ለአብነት “ UK, were is your citizen, Free Andrgachew Tsige, Andargachew is our icon of democracy, where is your action , stop discrimination among citizens, Yes, we are all Andrgachew Tsige, Brtain dont support terrirost regim in Ethiopia” የሚሉት ይገኙበታል::
ሰልፎኞችም የኢንግሊዝ  መንግሥት የነጻነት ታጋዩን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ከወያኔ እጅ እስካላወጡ  ድረስ ተቃውሞው በቀጣይ እስከ መጨረሻው ድረስ ከዚህ በበለጠ ቁጣና እልህ በተሞላበት ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ተናግረዋል።  በተመሳሳይም ለአንዳርጋቸው ያላችውን ፍቅርና ክብር በአደባባይ አስመሰክረዋል።
በመጨረሻም በድርጅቱ የተዘጋጀውን  ደብዳቤ በድርጅቱ ሊቀመንበር በአቶ ዮሃንስ ዓለሙ  አማካኝነት ለእንግሊዝ ኢምባሲ ተወካይ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻና ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ለማሳሰብ ቢፈለጉም ተወካይ ሊመጣ ባለመቻሉ ደብዳቤው በበር ጠባቂው አማካኝነት እንዲደርሳቸው ተደርጓል። በተጨማሪም ደብዳቤውን በኢሜይል በድጋሚ እንደሚላክ ለሰልፈኞች አሳውቀዋል። ወደፊት በሚደረገው ተቃዉሞ ላይ ተወካይ መጥቶ እስካልተቀበለንና አቶ አንዳርጋቸው የደረሱበትን እስካላወቅን ድረስ ከኢንባሲው በር የማንቀሳቀስ መሆኑን ሁሉም በከፍተኛ ድምጽ አሰምተው ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ ከቀኑ 15፡00 ተጠናቋል።

ዛሬም ነገም ሁላችንም አንዳርጋቸው ፅጌ ነን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ