EWNET LEWEGENE (እውነት ለወገኔ)
Tuesday, 30 August 2016
የአዲስ አበባ
ህዝብ ለምን
በአደባባይ ተቃውሞውን
ማሰማት አልቻለም?
(በኤልሳቤጥ
ግርም ፣ ኖርዌይ)
ህዝባዊ ተቃውሞው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ በሁሉም አካባቢዎች ማለት ይቻላል የወያኔን አንባ ገነናዊ አገዛዝ ተገዳድሮታል።
በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመፅ ወደ አማራ ክልል
በመስፋፋቱ ህወሓትን መድረሻ አሳጥቶታል። የህወሓት ባለስልጣናትንና በሥሩ ካሉት ካድሬዎቻቸው ሳይቀር ከመቸውም በላይ እንቅልፍ ነስቷቸዋል።
ስልጣናቸው አደጋ ውስጥ እንዳለ በሚገባ ተረድተዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በዘረፋ የሰበሰቡትን ንብረት እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን
ማሸሽ ጀምረዋል። እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆቻቸውን እንኳን ቀደም ብለው ወደ ኢሲያና አውሮፓ ልከው በትምህርት ስም የወደፊት
ኑሯቸውን እንዲያደላድሉ ማድረጋቸው ሳይጠቅማቸው የቀረ አይመስለኝም።
የወያኔ ሃርነት ትግራይ ነጻ አውጪ ቡድን ህዝባዊ ተቃውሞው መቆጣጠር ከሚችሉት አቅም በላይ ተጧጡፏል፤ ሽንፈትንና ውርደትን
አከናንቧቸዋል። ለስልጣኔ መከታ ይሆናል ብሎ ለዘመናት ያቋቋመው የአግዓዚ ጦር ህዝባዊ ተቃውሞውን ማክሸፍ አለመቻሉ እጅግ ፍራታቸውን እንዲጨምር አድርጎታል። ለ25 ዓመታት ሥልጣናቸው እንዲቀጥል ያደረገው
የከፋፍለህ ግዛው ስልትም ዛሬ ላይ ውጤታማ ሊያደርጋቸው አልቻለም። ህዝብ ከወያኔ ሌላ ጠላት የለንም፤ በየትም አካባቢ በግፍ በአደባባይ የሚፈሰው ደም የእኛም ደም ነው ብሎ ድምጹን ከፍ አድርጎ ማሰማት ጀመረ። ይህ ለወያኔ ትልቅ መርዶ ነው። ሚኒስቴር ተብዬው አቶ ጌታቸው
ረዳ “ ሁለት አካላት እሳት እና ጭድ የሆኑ እንዴት አንድ ሊሆኑ ቻሉ” ብለው የተናገሩት የኦሮሞና የአማራ ተጋድሎ ቅንጅት ከፈጠረ
የስርዓቱ ማብቂያ ሰዓቱ መድረሱን በግልጽ እየነገሩን ነው። የ1997 ዓም የአንድነት የህዝብ መአበል ሊረሱት ፈጽሞ አይችሉምና ሃገራዊ
የህዝብ ድምጽን ሲሰሙ ያቅለሸልሻቸዋል።
በተለይ ከ1997 ብሄራዊ ምርጫ በኋላ ኢትዮጵያ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን በወያኔም ሆነ በተቃዋሚው በኩል ሲነገር መስማት
አዲስ ነገር አይደለም። ሁለቱም በተረዱትና በእራሳቸው እውነታዊ ዓለም ተነስተው የሀገራችንን በለውጥ ጎዳና መጓዝ በግልጽ መናገራቸው
ምንም ስህተት የለባቸውም። ምክንያቱም ከወያኔም እውነት ስለማንጠብቅ ከህዝብ ደግሞ ውሸት ስለማይጠበቅ ሁለቱም ትክክል ናቸው። ለምን
ቢባል በወያኔ አነጋገር ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ናት ሲሉ ለስልጣናቸው መራዘም ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልገነቡት አጥር ስለሌ
ኢትዮጵያን በመከፋፈልና ህዝቧን ለከፋ ስቃይና መከራ በመዳረጋቸው ይህም የለውጥ አካል ነው፤ እንዲሁም ሰባዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተፈጥሮአዊ
መብቶች ሙሉ በሙሉ ከህዝብ በወያኔ በመገፈፋቸው ሌላው ትልቁ ለውጥ ነው። አካባቢን መሰረት አድርጎ ህዝብን በመያዝና አንድ ለ5 በቡድን ጠርንፎ የወያኔ ደጋፊ ለማድረግ የተሞከረው
ሙከራም ቀላል የሃገሪቱ ለውጥ አይደለም።
ርዕስ ወደ አደረኩት የአዲስ አበባን ህዝብ የተቃውሞ ሁኔታ ስንመለከት አንዱና ትልቁ ጉዳይ ከ1997 ምርጫ በኋላ የተደረጉ
ድርጊቶችን በአጽንኦት መመልከቱ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። በመጀመርያ በእውነት የአዲስ አበባ ህዝብ ተቃውሞ እያሰማ
ነው ወይስ አይደለም የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ይመስለኛል። እኔ እንደምገነዘበው ከሆነ የአዲስ አበባ ህዝብ የወያኔን ጥላቻ በተለያየ
ጊዜና መንገድ በደንብ አሳይቷል ብዬ አስባለሁ፤ የሰላም እንቅልፍ የተኛበትን ወቅት ፈጽሞ አላስታውስም። ወያኔ ለሃገር እንደማይበጅና
የማስተዳደር ብቃትም ሆነ አቅም እንደሌለው በ1997 በሚገባ ለዓለም አሳይቷል። ዛሬ ላይ በህብረት ወጥቶ ማሰማት ያልቻለበት የተለያዩ
ምክንያቶች ቢኖሩትም ከወያኔ ጋር ግን አብሮ መቀጠል እንደማይፈልግ የተለየ ማስረጃ አያሻንም።
የአዲስ አበባ ህዝብ በወያኔ አንባ-ዘር ገነን አገዛዝ ልጆቹን በእስር፣ በስደትና በሞት የተነጠቀበትን አሰቃቂና ዘግናኝ የቀን ከቀን ድርጊት ረስቶ ከወያኔ ጋር ህብረት ይኖረዋል ብሎ የሚያስብ ሰው ይኖራል ብዬ በፍጹም አላስብም። በንግድ እንቅስቃሴውም ሆነ
በህንፃ ግንባታው ወያኔዎች/ህወሓታዊያን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩበትን የማንአለብኝነት እኩይ ተግባር እንደ አዲስ አበባ ህዝብ ያየ
ህብረተሰብም የለም። ለዚህ ደግሞ በሁሉም ክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎችና
ቀበሌ ነዋሪዎች ህያው ምስክሮች ናቸው። ምስኪኑ ህብረተሰብ በጠራራ ፀሃይ ካለተመጣጣኝ ካሳና ክፍያ ከቤት ወጥቶ ሲወረወር በከተማ ልማት ስም አንዱ የህወሓት አሽከር ፎቅ ሲገነባ እንደ ማየት፣
ምስኪኑ ኗሪ የጀመረውን ግንባታና ንግድ አስቁሞ አንዱ የጠገበ የህወሓት አባል ትግሬ ነጥቆ የራሱን ድርጅት ሲያቋቁም እንደማየት ሌላ ምን የሚዘገንን ነገር አለ።
የአዲስ አበባ ህዝብ በቤት እጦትና በኑሮ ውድነት ከመቸውም በላይ የሚሰቃይ በህወሓት ዘመነ ግዛት ነው። በአፍሪካ መዲና በሆነችው ዋና ከተማ እየኖረ መብራትና ውሃ በፈረቃ የሚጠቀም ምስኪን
ህዝብ ቢኖር የአዲስ አበባ ህዝብ ነው። በሙስናው፣ በመልካም አስተዳደር እጦት በአጠቃላይ ጭቆናው፣ እንግልቱ፣ መከራውና ስቃዩ በአዲስ
አበባ ህዝብ ይብሳል። ህወሓት ወያኔ በማነኛውም መልኩ ክንዱን አጠንክሮ ለመግዛት የሚሞክረው የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ ከወጣ
ለስልጣኔ(“ጣ” ላልቶ ይነበብ) አደጋ ነው ብሎ በማሰብ እንደሆነ ጥርጥር የለዉም። እውነት ነው የአዲስ አበባ ህዝብ በአንድነት
ከወጣ ወያኔን ከተቀመጠበት ቤተ መንግሥት አስወጥቶ ደደቢት በርሃ የማስገባት አቅም አለው።
በተለያዩ አካባቢዎች ህዝባዊ አመጹ ሲቀጣጠል የአዲስ አበባ ህዝብ ለምን ዝምታን መረጠ????
በዚህ ዙርያ በርካታ ምንክንያቶች ቢኖሩም የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ በመሆኑ በእኔ እይታ ምክንያት ናቸው ያልኳቸውን
ነጥቦች እንደሚከተለው ላስቀምጥ፤ ቀሪውን እናንተ እንደምትጨምሩበት እርግጠኛ ነኝ።
·
ህዝቡ ህብረብሄር ስለሆነ
ህዝቡ በወያኔ ስርዓት መቀጠል እንደማይፈልግ የአደባባይ ምስጢር ነው። ጥያቄው በምን
እና እንዴት ባለ መልኩ ስርዓቱን ዳግም ላይመለስ ማስወገድ ይቻላል የሚለው ነው ህዝቡ ቆም ብሎ እንዲያስብ ያደረገው። አዲስ አበባ
ከተለያዩ ቦታ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ እውቀትና ፍላጎት የተወጣጣ ህብረተሰብ የሚኖርባት ከተማ እንደመሆኗ መጠን ህዝቡ አንድን ነገር
ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ፣ ለመተቸትም ሆነ ለማሞገስ፣ ለመትከልም ሆነ ለመንቀል የሚያስብበት፣ የሚነጋገርበትና የሚወስንበት ጊዜ
ያስፈልገዋል። ህብረብሄር መሆኑ ትልቅ ውበት ቢኖረውም በቀላሉ ደግሞ
በአንድ አጀንዳ እንደ አንድ አካባቢ ህዝብ መወሰንና ማጽደቅ ይቸገራል። ወያኔን ለመጣል ወይም ለማስወገድ ቢስማማም በምን
መልኩ እናስወግደው በጦር ወይስ በጎራዴ፣ በሰላም ወይስ በሃይል፣ በምክር ወይስ በተግሳፅ በማለት ብዙ ሊከራከር ይችላል፤ ለምን
ህዝቡ ህብረብሄር ስለሆነ አስተሳሰቡም በዚያው ልክ የየቅል ነውና። ስለዚህም በኦሮሚያ የተነሳውን ህዝባዊ አመፅ በልቡ ይዞ እያዘነ
ነገር ግን በአደባባይ መቃወም እና ዛሬም በአማራ ክልል የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት በተግባር መቀላቀል ያልቻለበት ምክንያት
አስተሳሰቡና አመለካከቱ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ልዩነት ስላለው ነው። የአዲስ አበባን ህዝብ በነቂስ ለማስነሳት ህብረብሄራዊ/ሃገራዊ
አጀንዳ ያስፈልገዋል። እንደ ግለሰብ ሁሉም ሰው ወያኔ ለአንድ ቀንም እድሜ እንዲኖረው አይፈልግም ነገር ግን በህብረት ወጥቶ በቃን ለማለት ከአንዳንድ አካባቢ ከሚነሱ አጀንዳዎች በላይ ኢትዮጵያዊነት
የተላበሰ አጀንዳ፣ ሃገራዊ ጉዳይ የሚዳስሱ ጥያቄዎች እና አንድነትን የሚሰብኩ ጉዳዮች እንዲነሱ ይፈልጋል፤ ለምን አዲስ አበባ የብሄር
ብሄረሰቦች መቀመጫ ናትና።
·
ከወያኔ ለውጥ በኋላ ፍጹም ዲሞክራሲያዊ
መንግስት ስለሚፈልግ
እርግጥ ነው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከዚህ አረመኔያዊ አገዛዝ ውድቀት በኋላ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ሊያሰፍንና ሊያረጋግጥ
የሚችል ዲሞክራሲያዊ መንግሥት/ስርዓት ይፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንባ ገነናዊ ስርዓት ምን ያክል ለሃገር እንደማይጠቅም ከ
4 አስርት አመታት በላይ አይቶታል። የሚመጣው ስርዓት ፍጹም ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ፣ ክብሯንና ሰንደቅ ዓላማዋን ሊያስከብር የሚችል፣
ዳር ድንበሯን፣ ዜጎቿን፣ ንብረትና ታሪኳን ሊጠብቅ ሊያስጠብቅ የሚችል አካል መሆኑን ከለውጥ በፊት እርግጠኛ መሆንን ይፈልጋል።
ከሁሉም በፊት የህዝብን መብት ሊያከብር የሚችል፣ የህዝብን ጥቅም ሊያስቀድም የሚችል፣ እወነተኛ ፍትህንና ነጻነትን ሊያጎናጽፍ የሚችል ስርዓት ይናፍቃል። የማይከዳው፣ ቃሉን የሚጠብቅ፣ በህግና በስራት
የሚመራ ፓርቲ ይሻል። እንደ 1997ቱ የቅንጅት መሪዎች ሳይጀመር ክፍፍልን መስማትም ማየትም አይፈልግም። ዛሬም እንደምናያቸው ከወያኔ
የማይሻሉ አንዳንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ስልጣንን ሙጭጭ ብለው አንለቅም የሚሉ ግለሰቦችን ወደ ሥልጣን ማንገስ የአዲስ
አበባ ህዝብ በፍጹም አይፈልግም። እነዚህና መሰል ነገሮች ባይዙት ኑሮ የአዲስ አበባ ህዝብ በአንድነት ወጥቶ ለዓለም ህዝብ በመስቀል አደባባይ በቃኝ ወያኔ በማለት ይገልጽ ነበር፤ በአግዓዚ ጦርና በመከላከያ
ሰራዊት ብዛት ከቤት ባልተቀመጠም ነበር። ለወያኔም የሥልጣን ማብቂያው የአዲስ አበባ ህዝብ በቃኝ “እምቢ አልገዛም” “ሞት ለወያኔ” “የስርዓት ለውጥ ያስፈልጋል” ብሎ በግልጽ
ሲቃዎም ነው።
·
ማህበራዊ ግንኙነቱ የላላ ስለሆነና ለሚስጢራዊ
ውይይት አስቸጋሪ መሆኑ
ህወሓት ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የአዲስ አበባን ህዝብ በከተማ ልማት ስምና በተለያዩ ምክንያቶች ከለመደው ቀየ እያፈናቀለ
ወደ ማያውቀው አካባቢ በማዘዋወሩ ህብረተሰቡ እንደድሮው የጠነከረ ማህብራዊ ግንኙነት የለውም። ብዙ ጎረቤታሞች የማይተዋወቁ ከመሆናቸው
ጋር ተያይዞ በመተማመን ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረግ ይቸግራቸዋል። ማን ምን እንደሆነም ለማዎቅ በጣም ከባድ ነው፤ ጆሮ ጠቢ
ይሁን ጤነኛ፣ ባንዳ ይሁን ሰው፣ ተላላኪ ይሁን መልእክተኛ፣ ሰላይ ይሁን ተሰላይ መለየት አስቸጋሪ ነው። የጠነከረ ማህበራዊ ግንኙነት
አይደለም ለሀገር ጉዳይ ለቤተሰብ ጉዳይም ትልቅ ፋይዳ አለው። ስለዚህ በማህበራዊ ግንኙነተ መሳሳት የተነሳ ሰዎች እንደልባቸው እንዳይወያዩ አድርጓቸዋል፤ ወያኔንም በነቂስ ወጥቶ እንዳይቃዎም አንዱ እንቅፋት የማህበራዊ
ግንኙነት መዳከም ነው።
·
ህወሓት ወያኔ በአዲስ አበባ ላይ ይበልጥ የበላይነቱን
ስለያዘ
በዚህ ላይ ብዙ ነገር መናገር አስፈላጊ አይመስለኝም። ከቀበሌ እስከ ክፍለ ከተማ፣ በሚኔስተርም ሆነ መለስተኛ ስልጣን የህወሓት
ነው። ለይምሰል ካልሆነ በቀር ምንም አይነት ስልጣን ለሌላ አካል ተላልፎ አይሰጥም። ከአንድ ሚኔስተር ለሌላ ብሄር ይልቅ አንድ
ተራ የህወሓት ካድሬ በከተማዋ ብሎም በሃገር ጉዳይ ፈላጭ ቆራጭ ነው። አንድ ወያኔ መጥቶ የፈለገውን ማድረግ ይችላል፤ በንግዱም፣ በትምህርቱም፣ በግብርናውም፣ በግንባታዉም
መስክ እነርሱ ብቻ ተቆጣጥረውታል። መርካቶን የገብያ መዓከል ለአብነት ብንመለከት ነባር ነጋዴዎች ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ ህውሓታዊያን
ተቆጣጥረውታል። ስለዚህ አዲስ አበባን ወያኔ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፍ ስለጠቆጣጠሩት በሁሉም ቦታ እነርሱ አሉ። ይህን
ሰብሮ ለመውጣት ህዝቡ የተቸገረ ይመስላል። ግን ለጊዜው ነው እንጂ
የወያኔ የበላይነት ህዝቡን ከተቃውሞ ሊያስቀረው አይችልም።
·
የኑሮ ውድነቱ ፡ ከነጻነቱ ይልቅ ለእለት
ዳቦ ፍለጋ መሮጥ
የኑሮ ውድነት በማህበራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ዘርፍ ቀላል የሚባል ተጽኖ አያሳድርም። ሰው በልቶ ለማደር እንኳ እጅግ ከባድ
የሆነባት ከተማ ሆናለች አዲስ አበባ። በውሸት ፕሮፓጋንዳ 11% እድገት
አስመዝግባለች የምትባል ኢትዮጵያ በኢቢሲ/EBC ህዝቡን ከማሰልቸት በስተቀር አንድም ጠብ ያለ ነገር የለም። ብዙዎች የእለት ዳቦ እንኳ ለመብላት እጅግ አዳጋች ሆኖባቸዋል። ይህን ደግሞ ያደረገው ህወሓት ሆን ብሎ አንድም የአዲስ አበባን ህዝብ የ1997 ቁጭትና ንዴት ለመበቀል፤ አንድም
ህዝቡ በችግር ሲጠበስ ለእለት ጉርሱ እንጂ ለመብትና ነጻነቱ ለመታገል አቅምም ጊዜም አይኖረውም ብሎ አስቦ ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የእራሱ ሰዎች በሃብት የበለጸጉ ከሆኑ በሃብታቸው እንደፈለጉ ማድረግ የሚችሉ
መስሎ ስለሚታያቸው ነው። ይህ ግን የሞኝነትና የቅዥት ህልም መሆኑን ገና ወያኔዎች የተረዱ አይመስልም። ዛሬም በቁም ቅዥት ይዋኛሉ።
ሆኖም ግን ለጊዜው የአዲስ አበባን ህዝብ በአንድነት ለተቃውሞ እንዳይወጣ የኑሮ ውድነቱ በቂ ባይሆንም እንደምክንያት የሚናገሩ ጥቂቶች
አይደሉም። ግን የኑሮ ውድነትም ይሁን ድህነት ህዝብን ከተቃውሞ አያግደውም።
·
ወጣቱ በአነስተኛና ጥቃቅን አደረጃጀት
ስም ስለወደቀ
ህወሓት ወያኔ በተለይ ከ1997 ዓም ወዲህ ማንኛውንም የህብረተሰብ
ክፍል አፍኖ ለመያዝ፣ ለመደለል፣ በተለያዩ ማሰርያ መንገዶች ለማጥመድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። የወጣቶች ሊግ፣ የሴቶች ሊግ፣
ጥቃቅንና አነስተኛ ፣ አንድ ለአምስት፣ በአጋር ድርጅት ተብየዎች (ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴን፣ ህወሓት)በማለት
ህብረተሰቡን ለመያዝ ሙከራ አድርጓል። ዘረኛውና አንባ ገነኑ ወያኔ የተሳካለት እስኪመስል ድረስ ብዙ አባላት እንዳሉት ሲናገር መስማት
አዲስ ነገር አይደም።
ምንም ይሁን ምን በተለያየ መንገድ የተወሰኑ ወጣቶችን ሊባል በማይችል መልኩ ለማጥመድ ሞክሯል በተለይ በአዲስ አበባ። እነዚህ
ወጣቶች ከልባቸው ወያኔን ደግፈው እንዳልሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር
ይቻላል፤ ነገር ግን ጊዜያዊ የስጋ ምኞትን ለማሳካት፣ ለመብላት፣ ለመጠጣትና ሆዳቸውን ሞልተው ለማደር ሲሉ የወያኔ ተላላኪ ሆነዋል።
ይህ ደግሞ ለሀገራቸው ቆርጠው የሚታገሉ ጀግና ወጣቶች ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ነው። በርካታ ወጣቶች በእስርና በእንግልት ለነጻነት
የሚታገሉትን ለፍርፋሪና ለጥቅማጥቅም ብለው አሳልፈው ሰጧቸው። የትም ለማያደርስ ነገር በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የወያኔን
ተልዕኮ ፈጻሚ ሆነዋል በወጣትነት እድሜቸው። የአዲስ አበባ ወጣቶች
ብቻ በአንድነት ቢወጡ ወያኔን ድራሹን ማጥፋት የሚችል አቅም ነበራቸው።
ወጣቶች ደግሞ በቀላሉ እርስ በእርሳቸው መግባባት ይችላሉ።
ለማህበራዊ መገናኛ ዜዴዎች እጅግ ቅርብ ስለሆኑ መረጃም ሆነ ማስረጃ
በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ስለዚህ ወጣቶች ሆይ እራሳችሁን በመፈተሽ ነግ በነጻነት የምትኖርባትን ሀገር ገንባ። የአማራና የኦሮሚያ
ወጣቶች እየሞቱ ያሉት ለነጻነት ነው። ከወንድሞችህ ጋር ቶሎ ብለህ ህዝባዊ አመጹን ተቀላቀል!
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ህዝብ የተለያዩ ምክንያቶችን ወደጎን በመተው ህዝባዊ አመጹን በአስቸኳይ መቀላቀል አለበት። በመጀመርያ
አረመኔያዊ፣ ዘረኛና ጎጠኛ አንባገነን አገዛዝን ከስሩ ነቅሎ መጣልና ቀጣይ ሀገሪቱ ላይ ምን አይነት ስርዓት መምጣት አለበት ለሚለው
ወሳኝ ጥያቄ የሁሉም አካባቢ ህዝብ የሚወስነው ጉዳይ ነው። የሽግርግር መንግስት መስርቶ ሀገራችን ዘላቂ የሆነ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት እንድትሆን ማድረግ
ይቻላል። ከዚያ በፊት ግን ወያኔን አሽቆንጥሮ መጣል ያስፈልጋል።
እንደ ሌሎች አካባቢዎች ወያኔ በቃ በማለት ክፍለ ከተሞችንና ቀበሌዎችን ከወያኔ ማጽዳት ለነግ የማይባል ተግባር ነው።
በጎበዝ አለቃም ለማስተዳደር ወስኖ መነሳትም ሌላኛው አማራጭ ነው።
ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንዲሉ አግዓዚ፣ መከላከያ
ሰራዊት፣ ወታደር፣ ፖሊስ ፈርተን ነጻነታችንን አጥተን መኖር የለብንም። የጀግና ሞት ሞተንም ቢሆን ለወገናችን ነጻነትን ለማውረስ
ቆርጠን መነሳት ይገባል። ይህ ደግሞ ለአዲስ አበባ ህዝብ ከባድ የሚሆን
አይመስለኝም። የንግድ እንቅስቃሴውን ለአንድ ሳምንት ቢያቆም ወያኔን ሽባ አድርጎ ከጥቅም ውጭ ማድረግ ይችላል። አዲስ አበባ ለዓለም
አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እጅግ ቅርብ ስለሆነች የዓለምን ትኩረት በቀላሉ የመግዛት እድል ይኖረናል። ስለዚህ ሙሉ ኃይላችንን አጠናክረን
ነጻነትን ለመቀዳጀት መነሳት ይኖርብናል፤ ለሌሎች ህዝባዊ አመጾችም ድጋፋችንን እናሳይ።
ስለሆነም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል
Ø
የቤት ውስጥ አድማ
Ø
የንግድ እንቅስቃሴን ማቆም
Ø
የስልክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ለተወሰነ ቀናት ማቆም
Ø
ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት አለመስጠት፣ አለመጠቀም
Ø
በየክፍለ ከተማው ህዝባዊ አመጽ መጀመር እና የመሳሰሉ የትግል ስልቶችን ማድረግ በአስቸኳይ
ከአዲስ አበባ ህዝብ ይጠበቃል።
Sunday, 14 August 2016
Saturday, 13 August 2016
ትግላችን የመብትና የፍትህ ብቻ ሳይሆን
የስርዓት ለውጥ ነው!(በኤልሳቤጥ ግርማ ከኖርዌይ)
በመጀመርያ በሰሞኑ በወያኔ አገዛዝ ውድ ይወታቸውን ላጡ ወገኖቼ የተሰማኝ ሀዘን ከመጠን
በላይ መሆኑን ሳልገልጽ አላልፍም!ከሰማዕታት ወገን ጨምረን ለዘላለም
ስናከብራቸው እንደምንኖር ሳስብ ደግሞ ሃዘኔ በመጠኑም ቢሆን ይታደሳል! አምላክ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን!
ኢትዮጵያ ሃገራችን እንዳለመታደል ሆኖ ህዝቦቿን የሚያስተዳድርላትን፣ዳር
ድንበሯን የሚያስከብርላትን መንግስት ወይም ስርዓት በሰላም ቀይራ አታውቅም። ገዢዎች በኃይል ወደ በትረ ስልጣናቸው ይመጣሉ በኃይል
ደግሞ ከስልጣናቸው ዳግም ላይመለሱ በህዝብና በአዲስ መጤው ስርዓት ጉልበት የበላይነት ይቀየራሉ። በተለይ የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ስርዓቶች
የዚህ ቀጥተኛ ምሳሌዎች ናቸው። የጃንሆይን ንጉሳዊ ስርዓት ደርግ በወታደራዊ አምባ ገነናዊ አገዛዝ ቀየረው። ህዝብ የተሻለ ይመጣል
ብሎ ሲጠብቅ ከመቸውም በላይ የከፋ ለህዝብ የማይጠቅም ጨካኝ መሆኑን ሲረዳ ወያኔን ግባ ቤተ መንግሥት ከደርግ ከተሻልክ ብሎ ስልጣኑን
አደላድሎ አስረከበው።
ወያኔ ግን እንኳን ከደርግ የተሻለ አስተዳደር ሊያሰፍን ቀርቶ
እጅግ የባሰና የሃገርን ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ የከተተ አስተዳድር ሆነ። ከዚህ ክፉ ተግባሩ እንዲመለስ ለ25 ዓመታት እድል ቢሰጥም
አገዛዙ ግን አጥብቀህ ግዛን፣ ግድያንና ዘረፋን የዘወትር ተግባሩ አድርጎ ቀጠለ። አሁንም የወያኔ አረመኒያዊ ድርጊት ሲበዛ ህዝብ ምህረቱንና ትዕግስቱን እያበዛ አገዛዙን ቀይሮ ለህዝብ የቆመ መንግስት
እንዲመሰርት መከረ አስመከረ። በየአምስት ዓመቱ በሚያደርገው የይስሙላ ምርጫ ጨው ከሆንክ ጣፍጥ አለባለዚያ ድንጋይ ነህ ተብለህ
ወደ ባህር ትወረወራለህ በሚመስል ህዝብ በተለያየ መልኩ ሃሳቡን ገለጸ። ስርዓትህ ሊቀየር ይገባል፣ የአንድ ዘር የበላይነት ይቁም፣ኢትዮጵያ
የሁላችንም ናትና ጥቅሟም ጉዳቷም፣ ደስታዋም ሃዘኗም፣ ወንዟም ተራራዋም፣ ህዝቧም ዳር ድንበሯም ይመለከተናል፤ ያገባናል ብሎ በተደጋጋሚ
ጠየቀ።
የህወሓት እኩይ ተግባሩን ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ እኔ ከሞትኩ
ሰርዶ አይብቀል በሚል ጎጂ ፈሊጥ የሀገሪቱን አንጡራ ሃብት ሙሉ በሙሉ አሟጦ ለመጠቀም በማንአለብኝነት ማንኛውንም የስልጣን እርከን
ተቆጣጠረ፤ ህዝቦቿን ለስደትና ለከፋ ርሃብ ዳረገ። ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ከህዝብ ላይ በአደባባይ ገፈፈ። የኢትዮጵያንና
ኢትዮጵያውያንን ክብር በዓለም ሁሉ አዋረደ፤ የተናቀች ሀገርና የተናቁ ህዝቦች እንዲሆኑ ህወሓት ሳይሰለች ከበርሃ ጀምሮ ስራውን
ሰራ። ብዙዎችን ከቦታቸው አፈናቀለ፤ ሃብት ንብረታቸውን ዘረፈ። ይህን እኩይ ድርጊት በህዝብና በሀገር ላይ ሲፈጸም ያዩ ህሊናቸው ያላስቻላቸው ንጹሃን ዜጎች ድርጊቱን ሲኮንኑ
ህወሓት በእነዚያ ዜጎች ላይ ካለምንም ርህራሄ ሞት፣ እስርና እንግልት በይፋ ፈጸመባቸው፤ እየፈጸመባቸውም ይገኛል።
ዛሬ ላይ ግን ህዝብ ለወያኔ አምባ ገነንና ዘር ገነን አገዛዝ
ከ25ዓመት በላይ እድሜ ለመስጠት በፍጹም ፍቃደኛ አይደለም። ትዕግስቱና ኢትዮጵያዊ ጭዋነቱ ተሟጧል። “አጥብቆ ዝምታ ለበግም አልበጀ
አስራ ሁለቱን በግ አንድ ነብር ፈጀ” እንደተባለው የህዝብ ዝምታ ለሀገር ጥፋትና ለዜጎች እልቂት ምክንያት ስለሆነ ከእንግዲህ በቃ
ብሏል። ህዝብ ከምስራቅ እስከ ደቡብ፣ ከሰሜን እስከ ምዕራብ የወያኔ ስርዓት ከዚህ በኋላ በሃገሪቱ ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይገባም
አለ። በተግባርም ወያኔን የማሶገድ ስራ በይፋ ጀምሯል።
በአራቱም አቅጣጫ ጾታ፣ እድሜ፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና የቦታ አቀማመጥ
ሳይወስነው ሁሉም ህዝብ በአንድነት በህወሓት አገዛዝ ላይ ተነስቷል። ትዕግስት ፍርሃት አለመሆኑን አሳይቷል። ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ሊመልሰው እንደማይችል በሚገባ ለወያኔ አጻፋዊ
መልስ ሰጧል። ለነገሩ ህዝቡ ሞትን፣ እስራትን፣ እንግልትንና ስደትን ለ25ዓመት ተለማምዷል ማንንም አይፈራም ሆ! ብሎ ተነስቷል።
ዝምታ ፍርሃት እንዳልሆነ በሚገባው ቋንቋ ማሳየት ጀምሯል። እሾህን
በእሾህ እንዲሉ ጦርን በጦር፣ ጥይትን በጥይት መመለስ እንደሚችል ህዝብ በግልጽ አሳይቷል። ሞት ላይቀር ገለን እንሞታለን በማለት
ህዝብ ዝምታውን ሰብሮ ሁሉም በያዘው ዱላም ሆነ ድንጋይ፣ ጦርም ሆነ ጠብ መንጃ ወያኔንና ተላላኪውን መበቀል ጀምሯል።
ህወሓት መረዳት ያቃተው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ሊቀይር አለመቻሉን
ነው። ኢትዮጵያዊ እኮ ለአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የነበረ ህዝብ
ነው፤ ነጮችን በጎራዴና በጦር አንበርክኮ የመለሰ ጀግና ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ እኮ ጣሊያንን ከእነ ሙሉ ትጥቁ ድባቅ መቶ ሰንደቅ
ዓላማውን በዓለም ህዝብ ፊት የአውለበለበ ታላቅና ኩሩ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ በማንነቱ የማይደራደር፣ ለሃገር ዳር ድንበር ህይወቱን
አሳልፎ የሚሰጥ ቆራጥ ህዝብ ነው። ኢትዮፕጵያዊ እኮ ተሸናፊነትን
መቀበል የማይችል፣ ጠላቱን ጊዜ ጥብቆ የሚያጠቃ ጥበበኛና አስተዋይ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ ታጋሽና ጨዋ ህዝብ እንጂ ፈሪና ውርደትን
መቀበል የሚችል ህሊና ቢስ አይደለም። ታሪኩን፣ ባህሉን እና ሃይማኖቱን የማያስነካ የተከበረ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ እኮ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ለሚመጣበት ማንኛውም ነገር አጻፋዊ ግብረ መልስ ከመስጠት
ወደ ኋላ የማይል ታሪካዊ ህዝብ ነው።
ወያኔ/ህወሓት የኢትዮጵያን ህዝብ ማንነቱንና ምንነቱን ዘንግቶት
አገዛዙን አጠናክሮ በህዝቡ ላይ መከራና ስቃይን ቢያበዛም፣ ህዝብን
ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ከጫካ ጀምሮ ቢሰራም፣ ህብረተሰቡን ለዳቦ እንጂ ለመብትና ለፍትህ እንዳያስብ በኑሮ ዝቅተኛ ለማድረግ ቢጥርም፣
የተማሩና ለሃገር ይጠቅማሉ የሚባሉ ዜጎችን ለእስርና ለስደት ቢዳርግም፣
ትውልድ ገዳይ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ ትውልዱን እውቀት አልባ ለማድረግ ቢሞክርም፣ በዘር ፣በሀይማኖት፣ በጎሳና በቋንቋ ከፋፍሎ
ለመግዛት ቢጥርም፣ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ዲሞ ክራሲ፣ ፀረ-ሰላም እያለ ንጹሃን ዜጎችን በይስሙላ የሽብርተኛ ህግ ወንጅሎ እውነተኛ ትግልን
ለማኮላሸት ቢጥርም፣ ነጻ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ወያኔያዊ ተቋም ቢያደርጋቸውም
ህዝብ ግን ከዚህ በኋላ በምንም መልኩ የወያኔ ስርዓት ለተጨማሪ ጥፋትና እልቂት በስልጣን ላይ መቆየት እንደሌለበት በሰላማዊ መንገድ
ደጋግሞ ጠይቋል፤ ዛሬም አጥፊዎችና አምባ ገነኖች ቦታ እንደሌላቸው አስረግጦ እየተናገረ ነው።
ህዝብ ለ25 ዓመታት የህወሓት አገዛዝን በሰላማዊ መንገድ የጠየቃቸው
ጥያቄዎችን ለአብነት ያክል ብናነሳ፡
- · በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደራዊ ስርዓት ይዘርጋ
- · ስልጣን የህዝብ እንጂ የእናንተ አይደለምና ከማንአለብኝነት ተቆጠቡ
- · አድሎ፣ ሙስናና ዘረፋ በግልፅ ይቁም
- · በብሄር ስም ሆን ብላችሁ ጥላቻን አትፍጠሩ
- · ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ መንግስት በህጋዊና ፍትሃዊ ምርጫ ይረጋገጥ
- · ስልጣን በህዝብ በጎ ፈቃድ እንጂ በሃይልና በጉልበት ለማራዘም አትሞክሩ
- · ህዝብን ከትውልድ ቦታ በግፍ ማፈናቀል ይቁም
- · የሃገርን ዳር ድንበር እንደ መንግስት አስከብሩ
- · በየትም ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ጥብቅናና አለኝታ ሁኑ
- · ፖሊሲው ይፈተሽ፣ ህገ መንግስት በህዝብ ጸድቆ ተግባር ላይ እንዲውል ይደረግ
- · በነጻ ተቋማት(በፍትህ፣ በፖሊስ፣ በሃይማኖትና ማህበራት) ውስጥ ጣልቃ አትግቡ
- · አገዛዙን ለማራዘም ማንኛውንም ኃይል ከመጠቀም ተቆጠቡ እና ወዘተ በማለት ህዝብ ሳይሰለች ደጋግሞ መፍትሄ የሚሻቸውን ጉዳዮች ምንም እንኳ ወያኔ ጆሮ ባይሰጥም በሰላማዊ መንገድ ለሩብ ክፍለ ዘመን ጠይቋል።
ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ጥያቄ ህወሃት መፍትሄ ይሰጣል ብሎ ህዝብ የሚጠይቀው ጉዳይ የለም፣ አይኖርምም። ምክንያቱም መፍትሄ ከህወሃት
አይጠበቅም። አሁን ጥያቂያችንና ትግላችን የስርዓት ለውጥ ብቻ ነው። ህዝብ በአንድነት ወጥቶ ኢትዮጵያን ሊመራና ሊያስተዳር የሚችል፣
ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚሰማው፣ ህዝቦቿንና የሃገርን ሉዓላዊነት ሊያስከብር የሚችል፣ የቀደመ ታሪኳን፣ ሰንደቅ ዓላማዋን፣ ባህሏንና
የህዝቦችን ማንነት ሊያከብር ሊያስከብር የሚችል ዲሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት ይገባል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሀገር እንደ ሃገር
፣ ህዝብ እንደ ህዝብ በነጻነትና በእኩልነት መኖር የሚችለው።
ለዚህ ዲሞክራሲያዊ መንግስት የመመስረት ታላቅ ተግባር ላይ ደግሞ
ጥቃቅንና አነስተኛ ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን አድርገን ህዝብ በህብረት በመጀመርያ ወያኔ የሚባል ሰው በላ አገዛዝን ማሶገድና ለጥያቄዎቻችንና
ለችግሮቻችን መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል አካል መመስረት ለነግ የማይባል ታላቅ ተግባር መሆኑን ተገንዝበን ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል።
ይህን ማድረግ ከቻልን ብቻ ነው ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ ልትቀጥል የምትችል።
በኢትዮጵያ ደግሞ የማንደራደር ህዝቦች መሆናችን አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን
ከስክሰው ክቡር ህይወታቸውን ሰውተው ለኛ አስረክበውናልና ወያኔ የሚባል ባንዳ ከፋፍሎ ለመግዛት የሚያደርገውን ከንቱ ጥረት በማኮላሸት
በአማራና በኦሮሚያ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመጽ ወያኔን እንዲያቃጥለው ሁላችንም ቤንዚን የማርከፍከፉን ስራ መስራት አለብን፤ ትግላችን
የስርዓት ለውጥ፤ ጥያቂያችን የአገዛዝ ለውጥ ነውና ወያኔ ከዚህ በኋላ
የሚያመጣውን ማንኛውንም የአማልዱኝ ጥያቄ እንደማንቀበል የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ የሃይማኖት አባቶች የተባበሩትም ሆኑ
የአውሮፓ ህብረት፣ የመብት ተሟጋቾችም ሆኑ ማህበራት ሊገነዙቡ ይገባቸዋል! እኛ ኢትዮጵያውያን በቃን የስርዓት ለውጥ
እንፈልጋለን! የወረቀትና የይስሙላ ሳይሆን ፍጹም ዲሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል!
ስለዚህም ይህን የተቀጣተለውን ህዝባዊ አመጽ በአንድነት ሊያስተባብርና ሊመራ የሚችል አካል መሰየም፣ ህዝባዊ አመጹን ሊያስተጓጉል የሚችል ማንኛውንም ነገር
በአስቸኳይ ማውገዝ፣ የመከፋፈልና የኢ-ኢትዮጵያዊነት ስሜትን ማስወገድ፣ ሊያታግሉ የሚችሉ ስልቶችን መንደፍ፣ ለትግሉ የገንዘብና
የቁሳቁስ እርዳታ ማድረግና ከስርዓት ለውጥ በኋላ ለሚመሰረተው ዲሞክራሲያዊ መንግስትና ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ ከወዲሁ መዘጋጀት
የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮችን በተግባር ላይ አውለን የተጀመረውን ወያኔን ለማሶገድ የሚደረገውን ትግል አጠናክረን ከቀጠልን ድሉ ቅርብና
የህዝብ እንደሚሆን ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም!
ትግላችን የስርዓት ለውጥ ነውና የወያኔ አምባ ዘር ገነን ስልጣኑ እስኪያከትም ድረስ
በጽኑ እንታገላለን!!!
ግድያና አፈና ከትግላችን ወደኋላ
አንድ እርምጃ አይመልሰንም!!!
Tuesday, 24 May 2016
ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ ምኑ ነው?(በኤልሳቤጥ ግርማ ከኖርዌይ)
በዚህ በያዝነው ወር በየዓመቱ ስለግንቦት 20 በተለያየ መልኩ ይሰበካል፣ ይገለጻል። ለሀገራችን ኢትዮጵያ ታምራዊ ለውጥ እንዳስመሰገበ ሁሉ ወሩን ሙሉ ሲተረክ መስማት እንደ ሀገራዊ መዝሙር የተለመደ ሆኗል:: በተለይ የሥርዓቱ ባለቤቶችና ደጋፊዎች ምስኪኑን ሕብረትሰብ ሳይቀር በማስገደድ ቀኗን “ልዩ ቀን” “የድል ቀን” “የስኬት ቀን” በማለት ሰይመው በአስረሽ ምችው ሲከበር ማየት ድፍን 25 ዓመታትን አስቆጠረ።
ጀግናው የኢህአዲግ ሰራዊት ደርግ ኢሰፓ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬዲዮ ጣቢያ ተቆጣጥሮታል ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሦስት ብለው እንዳበሰሩን በእርግጥ ለጥቂቶች ግንቦት 20 የድል ቀን ነው:: ምክንያቱም ሀገሪቱን በአንባገነናዊ አገዛዝ ለማስተዳደርና የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት መሰረት የጣሉባት እና የአስራ ሰባት ዓመት የልፋት ዋጋቸውን ያገኙባት ልዩ ቀን ናትና:: በዚች ቀን ህብረተሰቡን በምስጢራዊ የአገዛዝ ስልት ለማስተዳደርና ስልጣናቸውን ዘላለማዊ ለማድረግ የነበራቸው ሕልም እውን የሆነባት ቀን ናትና በልዩ አከባበር ቢያከብሯት ሲያንሳት እንጂ አይበዛባትም::
የተወሰኑ የስራዓቱ አቀንቃኞችም ስለቀኗ መልካምነትና ከዚያች ቀን በኃላ አገራችን ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና የገስገሰች፣ የዜጎች አኩልነት የተረጋገጠባት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሰባዊ መብቶች የተከበሩባት፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የታየባት፣ ህብረተሰቡን በእኩል የሚያስተዳድር መንግስትና ሕግ መንግስት የተመሰረተባት አገር እንድትሆን ግንቦት 20 ታሪካዊ የድል አሻራ እንደጣለች በኩራት አፋቸውን መልተው ይናገራሉ:: ይባስ ብለው ከውጭ ወራሪ ወይም ቅኝ ግዛት ኢትዮጵያን ነፃ ያወጧት ይመስል ግንቦት 20ን የነፃነት/ሀገራዊ ቀን ለማድርግ የሚሞክሩ ብልጣብልጥ የስራዓቱ ደንገጡሮችም አሉ::
በእርግጥ የደርግ አንባገነን መንግስት የአጼ ኃይለ ስላሴ መንግስትን ገርስሦ በምትኩ ወታደራዊ ጁንታ በመመስረት ስሙን በመቀያየር አገዛዙ ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን በብዙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተለይ ሀገሪቱን መለወጥ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡትን 60 ሚኒስተሮች በመረሸን፣ ነጭና ቀይ ሽብር በማለት ሀገር ተረካቢ ትውልድን በማስጨፍጨፉ የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግን ስርዓት አንቅሮ ተፍቶት ነበር። የለውጥ ያለሽ ብሎ በመጮህ ከደርግ አረመኔያዊ የጭካኔ አገዛዝ ነጻ ሊያወጣው የሚችል መለኮታዊ ኃይል እስኪፈልግ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ለውጥ ፈላጊ ሆነ።
ህወሓት የህዝቡን ብሶትና እሮሮ ተጠቅሞ 17 ዓመት ጫካ ውስጥ ያረገዘውን መርዝ ለመርጨት ግንቦት 20 ደርግን ገርስሦ በትረ ስልጣኑን ጨበጠ። እዚህ ላይ ወያኔ የደርግን ስርዓት ሳያይና በትንሹም ቢሆን ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ሳያደርግ ለትግል ወደ ጫካ መግባቱ ሀገራዊ ለውጥ አሳስቦት ሳይሆን የብሄር ፖለቲካ ጥማት እንደሆነ በትክክል መገንዘብ ይቻላል፤እያየነውም ነው። የብሄር ፖለቲካ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን ለምታስተናግድ ሀገር ቀርቶ ለየትኛውም የአለም ሀገራት የማይበጅ መሆኑ የታወቀ ነው። ኢትዮጵያም የከፋፍለህ ግዛውና የጎሳ ፖለቲካ እንደማይጠቅማት ከዘመነ መሣፍንት ትምህርት ቀስማ ነበር። ዳሩ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግን ሥርዓት ጥላቻና ሽሽት ዘረኛው ወያኔን ግንቦት 20 በሩን ከፍቶ እጁን ዘርግቶ ተቀበለ።
ወያኔዎች የደርግን ሥርዓት ገርስሰው መንግስቱ ኃይለ ማርያምን ወደ ዝምባብዌ ካስኮበለሉ በኋላ ሥልጣናቸውን ለማጽናት የይስሙላ ህገ መንግሥት አርቅቀው አጸደቁ። ለተወሰኑ ዓመታትም የነጻነት በርን ለመከፈትና ስላምና መረጋጋትን ለማስፈን የመጡ እስኪመስል ድረስ ሰላምን ሰበኩ። ከደርግ ጋር ንክኪ አላቸው ተብሎ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በሙሉ እስር ቤት ወረወሯቸው። ከገጠር እስከ ከተማ ህብረተሰቡ ለራሱ መጠበቂያ ብሎ የገዛዉን ትጥቅ ሳይቀር በሙሉ አስፈቱ። የኢትዮጵያ ህዝብ ግንቦት 20 በየዓመቱ “የድል ቀን” እያለ እንዲዘምር ተደረገ።
በእውኑ ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ ምኑ ነው? ይህ ጥያቄ በተለያየ መልኩ በሁላችንም አይዕምሮ ውስጥ እንደሚመላለስ እርግጠኛ ነኝ። መልሳችን ግን በራሳችን ምዕናባዊ እይታ ስለምንመለከተው የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን ከሁለት አማራጮች ሊዘል አይችልም። ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔዎች እንደሚሉት “የድል ቀን” ወይም ብዙዎች እንደሚስማሙበት “የውድቀት ቀን” መሆን አለበት። ወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው ግንቦት 20ን “የድል ቀን” ማለታቸው በእርግጥም ትክክል ናቸው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የአንባገነን ስልጣናቸውን ያፀኑበት እና በሦስቱም ዘርፍ ማለትም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩበት ቀን ነውና።
እውነታው ሲገለጥ ግን ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የውድቀት እና የውርደት ቀን እንጂ በምንም መመዘኛ የድል ቀን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ለአንድ ሀገር የድል ቀን ሲባል ዜጎቿ እኩል ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል በጎ አጋጣሚ ወይም የኩራት ምንጪ ሲፈጠር ብቻ ነው። ግንቦት 20 ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑን ግልጽ ሊያደርግ የሚችል ብዙ ማሳያዎች ከመኖሩም ባሻገር በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ችግር ዘርዝሮ መናገር ይቻላል።
“የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
የኢትዮጵያ ህዝብ ከግንቦት 20 የተቀበላቸውን ገጸ እርግማኖች ለማሳያ ያክል እንደሚከተለው እናያለን፤
1. የብሄር ፖለቲካ የተፀነሰበት
የህወሓት ማፍያ ቡድን ገና ከጅምሩ ሃገራዊ ፍቅር ሰንቆ እንዳልመጣ ከስሙ መረዳት ይቻላል። የትግራይ ነጻ አውጪ ቡድን ብሎ መሰየሙ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ እንዳልቆመ ለመረዳት ነብይነት አያሻውም ነበር። የከፋፍለህ ግዛው መርህን በማንፌስቶው ይፋ አድርጎ ይንቀሳቀስ እንደነበር ሰነዶች ህያው ማስረጃ ናቸው። ለስልጣን ማራዘሚያ በዋናነት የተጠቀመበት ዋናና ትልቁ አጀንዳ የብሄር ፖለቲካን ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ካልሆነ በስተቀር ከስልጣን ሊወርድ የሚችልበት ምንም አይነት አጋጣሚ እንደሌለ በሚገባ ያውቃልና። የብሄር ፖለቲካ እያራመደ እርስበርሳችን እንዳንተማመን በብሄር ለያይቶናል። ይሄ የናንተ መሬት ነው፣ ይህ ደግሞ የነሱ ነው ወዘተ እያለ በቡድን ከፋፍሎናል። በብሄሮች መካከል መግባባት እንዳይኖር እነእገሌ እንዲህ አደረጓቹህ፣ ታሪካችሁ እንዲህ ነው በማለት መጀመርያ መምጣት ያለበት ብሄር ነው ወዘተ እያለ የብሄር ጥላቻ እንዲሰፍን ሀውልት ሰርቶልናል። አንድ ዜጋ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከማለት ይልቅ በውሸት የብሄር እኩልነት ስም ኦሮሞ፣አማራ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እያለ በየቦታው እራሱን እያዋረደ እርስ በእርሳችን በጥላቻ እንድንናቆር ማድረጉ የወያኔ የብሄር ፖለቲካ ውጤት ነው። ስለዚህም ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የድል ቀን ሳይሆን የብሄር ፖለቲካ የተፀነሰበት የውርደት ቀን ነው። “የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
2. ትውልድ ገዳይ ሥርዓተ ትምህርት የተቀረጸበት
ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሀገር ተተኪ ዜጋ ፈጣሪ ተቋም እንደመሆናቸው መጠን የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ ታሪክንና ባህልን ከማሳወቅ ባለፈም በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥራት ያለው ዜጋ ለማፍራት የሚቀረጸው ሥራተ ትምህርት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ነገር ግን ወያኔ የቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት ግን ትውልድን ገዳይና የተማሪዎችን አይዕምሮ ለምርምርና ጥናት የማይጋብዝ ዘላቂና አስተማማኝ ያልሆነ ጥራት የጎደለው ሥርዓተ ትምህርት ነው። ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎችን በጥሩ ሥነ ምግባርና ባህልን ከማሳዎቅ አንጻር አስተምሯቸው ዝቅተኛና ከዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ለትውልዱ መጥፋት ሌላው የወያኔ የስርዓቱ ውጤት ነው። ትምህርት ቤቶችን ስንመለከት ከተቀረጸላቸው ሥርዓተ ት/ት ጀምሮ ትውልድን ለመቅረጽ ቀርቶ በዜግነት ደረጃም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚናገር ትውልድ እንዲጠፋ በማድረግ ረገድ ግንቦት 20 የራሷን ጥቁር ጠባሳ ጥላለች። አንዳንድ የዘመነ ወያኔ ተማሪዎች የሀገረን ታሪክ በሚገባ ካለማዎቅ የተነሳ ቅኝ ግዛት በተገዛን ኑሮ ሲሉ መስማት የሥርዓተ ትምህርት ውድቀቱን ማሳያ አንዱ መንገድ ነው።
3. የሃገር ዳር ድንበር የተደፈረበት
አንድ ሀገር የድል ቀን የምታከብር ከሆነ ለሀገርና ለህዝብ የሚቆረቆር መንግሥት አላት ማለት ነው። መንግሥት ካለ ደግሞ የሃገር ሉዓላዊነት ተጠብቆ፣ ታሪኳ ሳይበረዝና ሳይፋለስ ለትውልድ መተላለፍ ይችላል ማለት ነው። ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ግን የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ዳር ድንበሯ የተደፈረባት፣ ወደቧን ያጣችበትና ታሪኳ የተበረዘበት ዘመን ነው። ድሮ አባቶቻችን ቅኝ አንገዛም በማለት ታሪካችንና ባህላችን ሊበረዝ ከቶ አይችልም ብለው አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ ውድ ህይወታቸውን ሰውተው ዳር ድንበሯን ከነሙሉ ክብሯ ያቆዩልንን ሀገር ወያኔ ለአረብና ህንድ ባለሃብቶች ማቀራመቱ ሳያንሰው ሱዳን የድርሻሽን ውሰጅ ብለው በመማጸን ላይ እንደሆኑ ስንሰማ በእውነትም ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የውርደትና የውድቀት ቀን ነው። ዜጎቿ በሄዱበት ሞትና እንግልቱ ሳያንሳቸው በእራሳቸው ሀገር በሌላ ዜጋ እንደ እንስሳ ደማቸው ሲፈስና ህጻናት በገፍ ተግዘው ሲሄዱ ከማየት በላይ ምን የተለየ ውርደትና ውድቀት ይኖራል። “የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
4. ህዝቦቿ ለሞት፣ለስርና በስደት ለውርደት የተዳረጉበት
በወያኔ አገዛዝ ከ1983 እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከግንቦት ወር ጀምረን በግፍ ውድ ህይወታቸውን በስውርና በአደባባይ የተቀሰፉ፣ ለስር፣ ለእንግልትና ለስደት የተዳረጉ ዜጎችን የሰማይ አምላክ ይቁጠራቸው እንጂ በአኃዝ ማስቀመጥ እጅጉን ይዘገንናል። ተፈጥሯዊና ሰባዊ መብቶች በይፋ ተገርስሰዋል። የስርዓቱ አባል፣ ደጋፊና አገልጋይ ካልሆነ በስተቀር በሀገሩ ምድር ቀና ብሎ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት እና የመስራት መብቶች ፈጽመው መገደባቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ወያኔዎች ግንቦት 20ን የድል ቀን ብለው ማክበር ከጀመሩ ጀምሮ በሀገሪቱ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈሷል። ህዝቦቿ በሄዱበት ሁሉ የውርደት ካባ እየተከናነቡ ተቆርቋሪ ያጣ ዜጋ በመሆኑ ዋይታና ልቅሶው ከመቸውም በላይ ጨምሯል። “የድል ቀን ሆይ የት ነሽ?ምንጭሽስ ከቶ ከወደየት ይገኛል?”
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አገራችን የተለያየ መልክና መገለጫ ያላቸው በርካታ መንግሥታትን ያስተናገደች አገር ብትሆንም ለዘመናት ታሪኳን፣ ባህሏን፣ እምነቷን፣ አንድነቷን፣ ድል አድራጊነትን እና ዳር ድንበሯን ጠብቃ አስጠብቃ የኖረች እና መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ዘርንና ጎሳን መሰረት ሳታደርግ ለዘመናት የቆየች የጀግኖች አገር ነበረች። ነገር ግን ግንቦት 20 የለገሰን የአሳርና የግፍ ፍሬዎች በቀላሉ የማይሽሩ እኩይ ተግባር ናቸውና ታሪካዊ አገራችንን አደጋ ላይ ጥሏታል። ስለሆም ጊዜ ሳንሰጥ “የድል ቀን” የሚለውን ተረት ተረት ወደ ጎን በመተው በአንድነትና በህብረት ዛሬውኑ የውርደትን ቀን ወደ የድልና የክብር ቀን ሊቀየር ይገባል። ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ የድል ቀን ሳይሆን የሞት፣የውድቀትና የውርደት ቀን ተብሎ ይስተካከል!ምነው ሽዋ! ድንቄም የድል ቀን............
Subscribe to:
Posts (Atom)