Thursday, 5 December 2013

ኢትዮጵያን በሙስና ከሚታወቁ የዓለም አገሮች ተርታ ያሰለፈው ሪፖርት ይፋ ሆነ




corruption index
ትናንት ኅዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በመላው ዓለም ይፋ የሆነው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ተቋም የሙስና አመላካች ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ከሙስና ጽዱነት ተርታ ውጭ ከሆኑና በሙስና ተግባር በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈረጁ አገሮች አንዷ ሆና መገኘቷን ይፋ አደረገ፡፡
ሪፖርቱ በሚከተለው የሙስና መለኪያ ሚዛን መሠረት፣ ከሙስና ጽዱ የሚባሉ አገሮች ከዘጠና እስከ መቶ ነጠብ የሚያገኙት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቶባቸዋል፣ የሙስና ጎሬ ሆነዋል ተብለው የሚታሰቡ አገሮች ደግሞ ከመለኪያው ከ50 በመቶ በታች የሚያስመዘግቡት ናቸው፡፡ በመንግሥት ተቋሞች ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቶባቸዋል ተብለው ከተለዩት ውስጥ ኢትዮጵያ 33 ከመቶ የመለኪያውን ነጥብ በማስመዝገብ ከከፍተኛ ሙስኞች ተርታ እንደምትሰለፍ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ ከ177 አገሮች ውስጥ 111ኛውን ደረጃ መያዟም በሪፖርቱ ይፋ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው አገሮች ለሙስና ተጋላጭነት ከሚለኩባቸው መመዘኛዎች መካከል፣ የፕሬስ ነፃነት፣ የተጠያቂነትና የሰዎች የመደመጥ መብት፣ የፍትሕ አካላት ከተፅዕኖ ነፃ መሆን፣ የሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ ልማት መለኪያና ሌሎችም ጠቋሚዎች እንደሚካተቱ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በድረ ገጹ ይፋ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ከ179 አገሮች 127 ደረጃን በመያዝ የፕሬስ ነፃነት ከሌሉባቸው አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ በፍትሕ አካላት ነፃነትና ከተፅዕኖ ውጭ ካልሆኑ አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን ከ142 አገሮች ውስጥም 93ኛ መሆኗ ይፋ የተደረገው ዓምና ነበር፡፡
ተቋሙ 177 አገሮችን በሙስና እንደሚጠረጠሩበት ደረጃቸው በመመዘን ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገሮች 90 ከመቶው ለሙስና በሚያስጠረጥራቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሆነው አግኝቷቸዋል፡፡ ቦትስዋና ከሰሐራ በታች አገሮች ዝቅተኛ የሙስና ወንጀል የሚፈጸምባት ስትሆን፣ ሶማሊያ ከሁሉም አገሮች በታች በመሆን ሙስና የተንሰራፋባት ተብላለች፡፡ በዓለም ላይ ከ177ቱ ውስጥ 69 ከመቶ አገሮች ከፍተኛ የሙስና መናኸሪዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያረጋግጣል፡፡
ከሰሐራ በታች የሚገኙትን አገሮች በሙሰኝነት ተፈርጀው የሚመሩት የምሥራቅ አውሮፓና እስያ አገሮች ሲሆኑ፣ 95 ከመቶ በላይ አገሮች ከፍተኛ ሙሰኞች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡
በዓለም ላይ ከፍተኛ ሙስና ከተንሰራፋባቸው አሥር አገሮች ስድስቱ ከሰሐራ በታች አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ (ሪፖርተር)

የመስቀል ክብረ በዓል የዓለም ቅርስ ሆነ

mesqel


የኢትዮጵያው የመስቀል ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ዩኔስኮ አስታወቀ፡፡ ዩኔስኮ የመስቀል ክብረ በዓልን (Commemoration feast of the finding of the True Holy Cross of Christ) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ኅዳር 25 ቀን ይፋ ያደረገው፣ በኢንታንጀብል (መንፈሳዊ) ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና ክብካቤ ላይ የሚሠራው ኮሚቴው ስምንተኛውን ጉባኤ እያካሄደባት ካለው የአዘርባጃኗ  ባኩ ከተማ ነው፡፡
ስለቅርሱ የመረመረው ኮሚቴ ባቀረበው ውሳኔ ሐሳብ ላይ እንደተመለከተው፣  የመስቀል ክብረ በዓል የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን የያዘ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ መምጣቱና በአገሪቱ ማኅበራዊ አንድነትንና የርስ በርስ ትስስርን፣ ብዝኃነትንም የሚያንፀባርቅ፣ በበርካታ ብሔረሰቦች ባህሎች መካከል ትስስርን የፈጠረ በመሆኑ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን አሟልቷል ብሎታል፡፡
የዩኔስኮ ኮሚቴው በረቡዕ ስብሰባ ውሎው  ከመስቀል ሌላ ከተለያዩ አገሮች 13 መንፈሳዊ ባህላዊ ቅርሶችን በሰው ዘር ቅርስነት መመዝገቡንም በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መስቀልን ጨምሮ እ.ኤ.አ. በ2013 የተመረጡትን የ14ቱ መንፈሳዊ ባህላዊ ቅርሶች ገጽታ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችና ፎቶዎችም በዕለቱ በድረ ገጹ ላይ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በመላ አገሪቱ በአደባባይ ደመራ የሚከበረው የመስቀል ክብረ በዓል የመጀመርያው መንፈሳዊ (ኢንታንጅብል) ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበላት ኢትዮጵያ፣  ዘጠኝ  ግዙፍ (ታንጀብል) ቅርሶች ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡(ሪፖርተር ፎቶ: Mekonnen Ayele Wollo)

ሰበር አስዛኝ ዜና !!! ከወደ ደቡብ አፍሪካ !! ታላቁ አፍሪካዊ መሪ ክቡር ኒሰን ማዴላ ከዚህ አለም በሞት ተለዩን

ሰበር አስዛኝ ዜና !!! ከወደ ደቡብ አፍሪካ !! ታላቁ አፍሪካዊ መሪ ክቡር ኒሰን ማዴላ ከዚህ አለም በሞት ተለዩን ! BBC – South Africa’s Nelson Mandela dies
Mr Mandela, 95, led South Africa’s transition from white-minority rule in the 1990s, after 27 years in prison.
He had been receiving intense home-based medical care for a lung infection after three months in hospital.
In a statement on South African national TV, Mr Zuma said Mr Mandela had “departed” and was at peace.
“our nation has lost its greatest son,” Mr Zuma said.
The Nobel Peace Prize laureate was one of the world’s most revered statesmen after preaching reconciliation despite being imprisoned for 27 years.
He had rarely been seen in public since officially retiring in 2004.
“What made Nelson Mandela great was precisely what made him human. We saw in him what we seek in ourselves,” Mr Zuma said.
“Fellow South Africans, Nelson Mandela brought us together and it is together that we will bid him farewell.”
Earlier, the BBC’s Mike Wooldridge, outside Mr Mandela’s home in the Johannesburg suburb of Houghton, said there appeared to have been an unusually large family gathering.
Among those attending was family elder Bantu Holomisa,
A number of government vehicles were there during the evening as well, our correspondent says.
Since he was released from hospital, the South African presidency repeatedly described Mr Mandela’s condition as critical but stable.
He was awarded the Nobel Peace Prize in 1993 and was elected South Africa’s first black president in 1994. He stepped down after five years in office.
source : BBC  NEWS

‹መለስ ዛሬ የለም፡፡ አዲስ ጊዜ ነው፡፡ ደስ ብሎኛል፤ ቪዛዬም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተሰጥቶኛል፡፡››...አና ጎሜዝ የሸፈተው የአና ጎሜዝ ልብ?!

‹‹መለስ ዛሬ የለም፡፡ አዲስ ጊዜ ነው፡፡ ደስ ብሎኛል፤ ቪዛዬም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተሰጥቶኛል፡፡››...
(… Meles has gone! This is a new timing. I am pleased I was granted visa without preconditions.)
ይህንን ያሉት በምርጫ በ1997 የአውሮፓ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ሆነው የመጡት ሚስስ አና ጎሜዝ ሰሞኑን ከአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡
የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ መሰንበቻውን ካስተናግደችው ጉባኤዎች መካከል የአፍሪካ ካሪቢያን፣ የፓስፊክና አውሮፓ የጋራ የፓርላማ ስብሰባ አንዱ ነበር፡፡ ጉባኤው የመንግሥት ሚዲያ ቀልብ ይሳብ እንጂ የሕዝቡን ቀልብ የሳበው ግን ሌላ ነው፡፡ ሪፖርተርን ጨምሮ የግሉን ሚዲያና የሕዝቡን ቀልብ የሳበው የሚስስ አና ጎሜዝ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ነው፡፡ 
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከመንግሥት ጋር የተወዛገቡት የአና ጎሜዝ መምጣት የበለጠ አስገራሚ ያደረገው እሳቸው በዚሁ ጉባኤ በአዲስ አበባ መገኘታቸው ብቻ አይመስልም፡፡ እሳቸው በአባልነታቸው የሚታወቁበት አውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ለኢትዮጵያ 5.5 ቢሊዮን ብር በዕርዳታ መልክ መለገሱን ኢቲቪ ዘግቧል፡፡ በአመዛኙ የምርጫ 97ን ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን ቢናገሩም፤ ከአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ግልጽ ውይይት ማድረጋቸውና አዲስ የለውጥ ነፋስ አየሁ ማለታቸውም ሌላው አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል፡፡ 
አና ጎሜዝና ምርጫ 97
ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ ቢያንስ በመርህ ደረጃ የሕዝብ ይሁንታ የሚረጋገጥበት ሕዝባዊ ሥልጣን በምርጫ የሚያዝበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ታውጇል፡፡ ኢሕአዴግ አብዛኛው የፓርላማ መቀመጫውን በምርጫ ስም (ገለልተኛ ታዛቢዎች እንደሚሉት) መቆጣጠር ይዞት የመጣው ባህል፣ በሦስተኛው ዙር የ1997ቱ አገራዊ ምርጫ ተሰብሮ ነበር፡፡ በወቅቱ እንደ አሸን የፈሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለት አውራ ጥምረቶች (ኅብረትና ቅንጅት) በመፍጠር ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ መፈታተን ችለው ነበር፡፡ ኋላ ኋላ ጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሄዱት ምሁራን እንደሚሉት በሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት፣ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት አደገኛነቱ የሚያመዝን ቢሆንም፣ የግል ሚዲያው በአገሪቱ ታሪክ ተጠናክሮ የመጣበት ወቅትም ነበር፡፡ መንግሥት የሰነዘራቸው ከፍተኛ ትችቶች ሳይዘነጉም የአገር በቀልና የውጭ ሲቪክ ማኅበራትም በፖለቲካው የላቀ ሚናቸውን ተጫውተዋል፡፡  
ይኸው የ97ቱ ምርጫ በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የራሱ የሆነ የማይረሳ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች ግንኙነት ላይ ያስከተለው ሕመምም አሁንም ድረስ አልተፈወሰም፡፡ ምርጫውን ተከትሎ ለተፈጠረው ቀውስም፣ በዋና ተዋናዮቹ ሁለቱ ወገኖች ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ 
ኢሕአዴግ እንደሚለው፣ አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የተንቀሳቀሱ የ‹‹ኒዮሊበራል›› ኃይሎች በገንዘብም ሆነ በሞራል ጫና ለመፍጠር ክፍተቱን ተጠቅመው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ይህ በማናቸውም አገሮች የሚፈጠር ቀውስ ለውጭ ኃይሎች በር መክፈቱ ግን በኢትዮጵያም በሌሎች አገሮችም እንግዳ አይደለም፡፡ በምርጫም ሽፋንም ሆነ በኃይል በመፈንቅለ መንግሥት፣ በተለይ ምዕራባውያን ኃይሎች የማይፈልጉትን አካል ለመጣልና የሚፈልጉትን ወገን ደግሞ ለማንገሥ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነት ከማድረግ አይቦዝኑም፡፡ የሚያስከትለው ውጤት ከአገር አገር ይለይ እንጂ፣ በተለይ በድሀ አፍሪካ አገሮች የእነዚህ ኃይሎች እጅ ረዘም ያለ ነበር፡፡ ዋና አጀንዳቸው ባይሆንም ለዲሞክራሲ መስፋፋት ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖራቸውም ግን አይባልም፡፡ 
ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ስማቸው በቀላሉ ከሕዝብ አእምሮ ከማይጠፋው ጥቂት የፖለቲካ ሰዎች እኩል የሚታየው፣ የውጭ ሰዎች ግንባር ቀደሙ ደግሞ የሚስስ አና ጎሜዝ ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤና ከአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ዕርዳታም በላይ፣ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ የሚመስለው፡፡ ወይዘሮዋ በአሁኑ ወቅት በተለይ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ቀልብ የሳቡት ከምርጫው ቀውስ ዘጠኝ ዓመት በኋላ ወደ ከተማይቱ ሲመጡ ለመጀመርያ ጊዜ በመሆኑ ብቻ አይመስልም፡፡ ያሳዩት የአቋም ለውጥ ጭምር እንጂ፡፡ 
የአና ጎሜዝ ልብ ዛሬ ወዴት ነው?
ከሁለት ዓመት እስር በኋላ በይቅርታ የተፈቱ የቅንጅት አመራሮች፣ የሚዲያና የሲቪክ ማኅበራት የፖለቲካ አራማጆችም፣ በምርጫው ወቅት ያሳዩትን ጉልበት ይዘው መቀጠል አልቻሉም፡፡ በተቃዋሚዎች ላይ ተስፋ የቆረጡት ግን የአሜሪካ መንግሥት (ቀጥሎ የመጣው የኦባማ አስተዳደር) እና የአውሮፓ ኅብረት ብቻ አልነበሩም፡፡ በምርጫ ውጤት እንደታየው፣ መራጩ ሕዝብ በተቃዋሚዎች ላይ ተስፋ መቁረጡን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ማሳያው በ1997 ምርጫ መቶ በመቶ ቅንጅትን የመረጠው የአዲስ አበባው ሕዝብ፣ ከአንድ ወንበር በስተቀር በ2002 ዓ.ም. ኢሕአዴግን መርጧል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የትግል ጽናት የላቸውም ብሎ ተስፋ የቆረጠባቸው የተቃዋሚዎች አመራሮች ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰናል›› በሚል ይቅርታ መጠየቃቸው ብቻም አይመስልም፡፡ መሪዎቹ ከእስር ከወጡ በኋላ በሁለት እግሩ መቆም የሚችል ድርጅት ይዘው መቀጠል አለመቻላቸውም ጭምር ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ምትክ፣ በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት ወደተራ ድብድብ እስከመግባት የደረሱ ነበሩ፡፡ መንግሥት ይህንን ክስተት ለፕሮፖጋንዳ በስፋት ተጠቅሞት ነበር፡፡ 
በቅርቡ አዲስ አበባ የመጡት አና ጎሜዝ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረጋቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር ምንም ንግግር አለማድረጋቸው ይነገራል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ድንገተኛ ሕልፈት አገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንድታደርግ እንደ መልካም አጋጣሚ የተመለከቱት አና ጎሜዝ፣ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ለማየት የጓጉ ይመስላሉ፡፡ 
በዚሁ ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ‹‹አዲስ ነፋስ አለ›› ያሉት መንግሥት ለእሳቸው ያለምንም መንገላታትና እንቅፋት ቪዛ ስለሰጣቸው የአወንታዊው ለውጥ ምልከታቸው ቀዳሚ ነው፡፡ አሁንም ከ97 በኋላ የፖለቲካ ምህዳሩን በተመለከተ ችግሮች መኖራቸው አስረግጠው የተናገሩት አና ጎሜዝ፣ በአጠቃላይ ግን አገሪቱ በተለየና አዲስ አመራር ውስጥ መሆኗን ይናገራሉ፡፡ ያዩዋቸው ለውጦች ምን ምን እንደሚያካትቱ በዝርዝር ባያስረዱም፡፡ አንድ ትልቅ ለውጥ የተመለከቱት የሶሻል ሚዲያ መስፋፋት ሲሆን፣ ያንንም ከመንግሥት ቁጥጥር በላይ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ በሙሰኞች ላይ የተወሰደ ዕርምጃም አድንቀዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ላይ እኔ ምንም የኢኮኖሚ ሆነ ምንም ግላዊ ፍላጎት የለኝም›› የሚሉት አና ጎሜዝ፣ አንዳንድ ባለሥልጣናት በግልጽ ለመነጋገር መፍቀዳቸውንም እንደ ለውጥ ሳይመለከቱት አልቀሩም፡፡ ‹‹እኔን ለመስማት መፈለጋቸው ራሱ ጥሩ ይመስለኛል›› ብለዋል፡፡ ‹‹በሽብርተኝነት የታሠሩት ጋዜጠኞች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም›› ለሚለው ሙግታቸው ማስረጃ እንዲያቀርቡ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ጋዜጠኞች መሆናቸውን ነው የማውቀው›› ከማለት ውጪ የማቀርበው ማስረጃም የለኝም ብለዋል፡፡ 
በወቅቱ ከቅንጅት አመራሮች አንዱ የነበሩት ዶክተር ኃይሉ አርአያ፣ የአና ጎሜዝን መምጣት በበጎ ጎን አይተውታል፡፡ ‹‹መቀራረቡ በእኔ በኩል ገንቢ ነገር ነው፤››  የሚሉት ዶክተር ኃይሉ፣ ‹‹በአገሪቱ ተለውጧል ያሉትን ነገር ግን እሳቸው ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እሳቸው በወቅቱ ይዘውት ከነበረው አቋም አሁን ምንም የተለወጠ ነገር አላየሁም፡፡ አቋማቸውን የሚያስለውጥ መሠረታዊ ለውጥ አላየሁም፤›› ብለዋል፡፡ ዶክተር ኃይሉ እንደሚሉት፣ በአገሪቱ እሳቸውም የማይክዱት ልማት እየመጣ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከዚያ ውጪ ግን በፖለቲካ መስክ ምንም የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ቪዛ ስለተሰጣቸው ብቻ አዲስ ለውጥ አለ ማለት ግን አግባብ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ 
የቀድሞ አምባሳደር ተስፋዬ ሀቢሶ በበኩላቸው በ1997 ዓ.ም. በካምፓላ (ኡጋንዳ) አምባሳደር የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩን በቅርበት ይከታተሉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አና ጎሜዝ በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቋም የግላቸው እንዳልነበር በአጠቃላይ የምዕራባውያን መንግሥታት አቋም እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ፣ ኒዮሊበራሊዝምን አክርረው የሚቃወሙት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን እንደ ‹‹የወገብ ቅማል›› አድርገው ነበር የሚያዩዋቸው ብለዋል፡፡ በወቅቱ ከኢትዮጵያ የተባረሩት አራት የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም የተቃውሞ እንቅስቃሴውን በገንዘብ ሲደግፉ እንደነበር ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ አና ጎሜዝ ብቻም ሳይሆኑ እነ ክርስቶፈር ክላፋም፣ ክሪስ ቦርና የኤችአር 2003 ሕግ አርቃቂ ዶናልድ ፐይን የመሳሰሉትም በተመሳሳይ ይጠቅሳሉ፡፡ እሳቸውም እንደ ዶክተር ኃይሉ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አቋም የሚያስለውጥ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፤›› በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ 
አና ጎሜዝ ከመንግሥት ጋር መታረቅ የፈለጉበት ምክንያት ግን ‹‹ታክቲክ›› እንደሚሆን በመገመት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ያለው አቋም መለወጡን ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ይገምታሉ፡፡ ‹‹ከወደቀ ጋር መሆን ማን ይፈልጋል?›› በማለት፡፡ ‹‹አሁን በ60 ዲግሪ አቋማቸው ተለውጧል ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፣ ግለሰቦች የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም ያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተዉት ፖሊሲና ርዕዮተ ዓለም እየተተገበረ ስለሆነ ምንም አቋም የሚያስለውጥ ነገር የለም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ስህተታቸውን አምነው፣ ለውጡ ከልብ ተቀብለውት ከሆነ ግን መልካሙን እመኝላቸዋለሁ›› ብለዋል፡፡ 
በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላምና ልማት ተቋም ተመራማሪው አቶ አቤል አባተ በበኩላቸው፣ ‹‹የአና ጎሜዝ መለሳለስ ከአውሮፓ ውስጥ የደረሰባቸው መገለል ውጤት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ከ1997 ምርጫ በኋላ የኢሕአዴግ መጠናከርና መንግሥት በልማት ላይ ያሳያቸው ተጨባጭ ዕድገቶች የተቺዎቹን አፍ እየዘጋለት እንደሆነ በመግለጽ፡፡ ለዚህም ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ ምንም ዓይነት የፖሊሲም ሆነ የስትራቴጂ ለውጥ ባልታየበት የአና ጎሜዝ መለሳለስ ጥሩ ማሳያ ነው ብለውታል፡፡ 
‹‹ቀደም ሲል ከተቃዋሚ አመራሮች ጋር የነበራቸው መጥፎ ስም ለማደስ ፈልገው ይሆናል፡፡ ለአቋማቸው መለወጥ ዋነኛ ምክንያት ግን መገለላቸውና በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ምንም ዓይነት ተሰሚነትና ተአማኒነት ማጣታቸው ነው፡፡›› 
የባከኑ ስምንት ዓመታት
አና ጎሜዝ ሰሞኑን እዚሁ አዲስ አበባ እስከታዩ ድረስ፣ በተገኙ አጋጣሚዎች በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲከሱ፣ ሲወነጅሉና ሲያጣጥሉ ቆይተዋል፡፡ 
ከይቅርታ ጠያቂዎቹ መካከል ወደ አሜሪካና አውሮፓ የገቡ አንዳንድ አመራሮች ከውጭ በመሆን ከእነ ሚስስ አና ጎሜዝና ዶናልድ ፔይን (ከሦስት ዓመት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው) ጋር በመሆን ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ መንግሥትን በኃይል ለመጣል ከዳያስፖራ ድጋፍ እያሰባሰበ የሚገኘውና በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው ግንቦት ሰባት ሊቀመንበሩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ (በአገር ክህደት ክስ በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው) ጋር በቅርበት ሲሠሩ ከቆዩት መካከል፣ አሁን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ‹‹ግልፅ›› ውይይት ማድረጋቸውን የሚናገሩት ሚስስ አና ጎሜዝ ናቸው፡፡ በአውሮፓ ኅብረት አስተባባሪነት ኢትዮጵያን በሚመለከቱ መድረኮች፣ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የተለያዩ ተቃውሞአቸውን እንዲገልጹም ከማመቻቸት ባሻገር ራሳቸው በተለያዩ ወቅቶች ኅብረቱ በኢትዮጵያ ላይ እንዲጨክን ድምፃቸውን ሲያሰሙ ኑረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ክስ ተፈርዶባቸው በእስር የሚገኙት ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ መንግሥት ያፀደቃቸውን ሕጎች እንዲከልስ፣ ኅብረቱ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ዕርዳታም ሆነ ብድር እንዲያቋርጥ በተለያዩ መንገዶች ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የእሳቸው ጥረት፣ በአጠቃላይ የአውሮፓ ኅብረትና አባል አገሮች ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ዕውቅና እንዲነፍጉ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚያም አልፈው ወይዘሮዋ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ባለው የድንበር ግጭትም ጭምር አስተያየት የሚሰጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሄጉ ፍርደ ገምድል ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲያደርግ ለዚህም ኅብረቱ ጫና እንዲፈጥር ይጠይቃሉ፡፡ 
በተለይ አምና መጋቢት ወር ላይ ለኅብረቱ ባቀረቡት ስሞታ፣ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆሴ ማኑኤል ባሮሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በሚያነጋግሩዋቸው ወቅት፣ አገሪቱ ‹‹የፖለቲካ›› እስረኞቿን በአስቸኳይ እንድትፈታ የድንበር ውሳኔው በአስቸኳይ እንዲተገበርና በሶማሊያ የምታደርገውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንድታቆም ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ እሳቸው ማምጣት የሚችሉት ለውጥ እምብዛም ነው›› ያሉዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምንም የሥልጣን ሽግግር እንዲያደርጉ ፕሬዚዳንቱ ጫና ይፈጥሩ ዘንድ ተማጽነው ነበር፡፡ አውሮፓ ኅብረት ምርጫ 97ን ተከትሎ ያደረገው ለውጥ ካለ፣ ለአገሪቱ የሚሰጠው ዕርዳታ በመንግሥት በኩል መሆኑ ቀርቶ በፕሮጀክቶች አማካይነት በቀጥታ ለዜጎች እንዲውል ማድረጉ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በሶማሊያም ጉዳይ ሆነ በአካባቢው ደኅንነትና የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ዙርያ በጋራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህ ግን ለአና ጎሜዝ ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ኅብረቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ እስካሁንም አይዋጥላቸውም፡፡
በመጀመርያ አካባቢ የአውሮፓ ኅብረት በተለይ ደግሞ የኅብረቱ ዋና አከርካሪ ከሆኑት አባል አገሮች ግንባር ቀደም ከሆኑት መካከል እንግሊዝ በኢትዮጵያ ላይ የዕርዳታና ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት በቀጥታ እንዳይሰጥ በመከልከል የተሳካላት ቢመስልም የኋላ ኋላ ነገሮች እየተቀየሩ መጥተዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ የአሜሪካ መንግሥት፣ ተስፋ የጣለባቸው ተቃዋሚዎችና ‹‹አክቲቪስቶች›› ወደ እስር ቤት በመግባታቸው ተፅዕኖዋቸው እየቀጨጨ በመሄዱ የውጭ ኃይሎችም ተስፋ እየቆረጡ መጥተዋል፡፡ ወይዘሮዋም ‹‹አይዟችሁ›› ሲሉዋቸው የነበሩ አመራሮችን ከእስር አላዳኑዋቸውም፡፡ 
እንደ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ትንተና፣ በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስና መንግሥት የሰጠው አሉታዊ ምላሽ፣ የአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ጉዞን ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ምክንያት ቢሆንም፣ የውጭ ኃይሎች ግን ተስፋ የተጣለውን ያህል ተቃዋሚዎች የዲሞክራሲ ጉዞውንም የሚታደጉ አልነበሩም፡፡ ከውጭ ተፅዕኖ በአንጻራዊነት ነፃ መሆኑን የሚያምነው ኢሕአዴግም ሊቀመንበሩ አቶ መለስም፣ ክፍተቱን ተጠቅመው በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን የሰደዱ ኃይሎች በቀላሉ መቋቋም ችለዋል፡፡ 
የአና ጎሜዝ ድምዳሜና መዘዙ
የመለስ ዜናዊ አጠቃላይ ትንተና የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በ1997ቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ሐቀኛ ሪፖርት አላቀረበም የሚል ነው፡፡ በተለይ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን በመሩት ፖርቱጋላዊቷ አና ጎሜዝ ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞን ከመሰንዘር ባሻገር ዘለፋ አከል አነጋገሮችን ተጠቅመዋል፡፡ በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ለመጀመርያ ጊዜ በስማቸው ባወጡት ጽሑፍ ቡድኑ በሪፖርቱ ያካተታቸው ጥሬ ሐቆች ያሉት ቢሆንም፣ ድምዳሜው ሁሉ መሠረታዊ ችግር ያለበት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በሪፖርቱ በተካተቱ የምርጫ ጣቢያዎች ሁሉ ተስተዋሉ የተባሉትን ችግሮች በዝርዝር በማስታወስ ለችግሮቹ መንስዔ የሆኑትንና ሪፖርቱ በውል ያላጤናቸውን ነገሮች በመዘርዘር የሪፖርቱን ኢ-ሚዛናዊነት ያስቀምጣሉ፡፡ በተለይ በቡድን መሪዋ ላይ ካነሷቸው አበይት ነጥቦች መካከል ግለሰቧ የምርጫውን ሒደት ከመታዘብና ከመዘገብ ኃላፊነት አልፈው በድህረ ምርጫው በተነሱት ያለመግባባት ጥያቄዎች የመፍትሔ ሐሳብ ጠቋሚ ሆነው ቀርበዋል የሚል ነው፡፡ አና ጎሜዝ በሪፖርታቸው ምርጫው በተቃዋሚዎች አሸናፊነት መጠናቀቁን ገልጸው የተጋረጠውን አደጋ መመለስ የሚቻለው መንግሥትና ተቃዋሚዎች ወደ ጥምር መንግሥት የሚያመራቸውን የጋራ ስምምነት ማድረግ ሲችሉ እንደሆነ የሚገልጽ ንድፈ ሐሳብ ነበራቸው፡፡ 
በእነዚህና በሌሎችም ተጨማሪ ጉዳዮች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹በሪፖርቱ ያልተካተተ ነገር ግን የሪፖርቱ ችግር ምንጭ›› ያሉት አና ጎሜዝን የሚሸነቁጡ ንግግሮችንና ዘለፋዎችን ሰንዝረዋል፡፡ በምላሻቸው ማጠናቀቂያ ላይ የቡድን መሪዋን የመፍትሔ ሐሳብ ላቅርብ ባይነትን በነገር ሲወጉ ‹‹የተከበሩት ወይዘሮዋ ከምርጫው ጋር ተያያዥነት የለውም ብለው እንጂ ዘንድሮ ስላገኘነው ጥሩ የዝናብ መጠንም አስተያየት መስጠት ይችሉ ነበር፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ 
ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ምላሽ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው በጽሑፋቸው መጨረሻ ያሰፈሩት፣ ‹‹What’s love got to do with it›› የታዋቂዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ዘፋኝ ቲና ተርነር ዘፈን ወይዘሮዋን ሸንቆጥ ማድረጋቸው ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጽሑፍ እስካሁን በወይዘሮዋ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ይመስላል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኅልፈት ያደረባቸውን ስሜት እስከመግለጽ ደርሰዋል፡፡ 
አና ጎሜዝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ በእጅጉ መበሳጨታቸውን በመግለጽ ‹‹ከተቃዋሚዎች የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገልኝና ሌላ ሌላ አስመስለው ነው የገለጹኝ፡፡ በጣም ምርጥ ጭንቅላት ያለው ሰው ቢሆንም የሰው ሐሳብ የማምታታት ችሎታ የነበረው መሪ ነው፤›› ሲሉ ነው የገለጿቸው፡፡ 
ቪዛ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማግኘታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መሞት ያገናኙት አና ጎሜዝ የብሔር ጉዳይም ማንሳታቸው በኢትየጵያ ስላዩት መሻሻል እንዲነግሩት ለጠየቃቸው አዲስ ስታንዳርድ መጽሔት፣ በሰጡት ምላሽ ‹‹አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሚናውን ለመጫወት ቀላል አይሆንም፡፡ በውስጣቸው የሥልጣን ሽኩቻ እንደነበርም አውቃለሁ፤ እሱ ከትግራይ አይደለማ፡፡ የተሰጠኝን ቪዛ ትልቅ ትርጉም እሰጠዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ካድሬዎቻቸው በፓስፖት እና በቀበሌ መታወቂያ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ተገለፀ።

ሰሞኑንን ኢ.ቲ.ቪ አይናችን በሚል ፕሮግራሙ ባሰራጨው በዚህ ስፊ ዘግባ ላይ የኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ጉዳይ መምሪያ መቤ/ት እና የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት መዋቅር እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቀበሌዎች ውስጥ የተሰማሩ ካድሬዎች በመታወቂያ እና በፓስፖርት ህገወጥ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ከቀረበው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። 
በአንድ ቤት እስከ 40 መታወቂያ የሚወጣበት አጋጣሚ መኖሩን በተጨባጭ፡ያረጋገጠው የፕሮግራሙ አዘጋጅ የኤምግሬሽኝ እና ስደተኞች ጉዳይ መመሪያ ሃላፊዎች ለውጭ፡ሃገር ዜጎች ፓስፖርት በመሸጥ የአሰሪ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ከፍተው አያሌ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ወደ አረብ ሀገር በመላክ ለሞት እና ለስቃይ መዳረጋቸውን ጸሃይ የሞቀ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑ ቢታወቅም ኢቲቪ የተጠቀሱትን ባለስልጣኖች በግርድፉ የህገሪቱን ሰነድ አሳልፈው የሸጡ ብሎ አድበስብሷት አልፎል። 
እንደሚታወቀው ከዛሬ 4 አመታት በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ለሳውዲ አረቢያ የቤት ሰራተኛ ለማቀረብ በገባው ውል መስረት አንዳንድ ከፍተኛ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ባለስልጣናት በውጭ፡ሃገር ዜጎች ስም በእጅ አዙር ሰራተኛ እና አስሪ ኤጀንሲዎችን ከፍተው ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተጓዥ እስከ 7መቶ ዶላር በማስከፈል በወር ከ 45 ሺህ ያላነሱ እድሜያቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ኢትዮጵያውያንን ህጻናት እህቶቻችንን ጭምር ያለምንም የህይወት ዋስትና ወደ ሳውዲ አረቢያ በመላክ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ.መንግስት ባወጣው ህግ ሸፋን በወገኖቻችን ደም ንግድ ላይ ተሰማርተው መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ ። የሳውዲ አረቢያ መንግስት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ወደ ሃገሩ እንዳይገቡ የመግቢያ ቪዛ ማገዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የተጠቀሱትን ኤጀንሲዎች ላልተወሰነ ግዜ መዝጋቱን ለማረጋገጥ ተችሏል። 
Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ

መድረክ የጠራው ሰልፍ ተከለከለ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም ለማድረግ ያሳወቀው ሰልፍ ተከለከለ፡፡ መድረክ ሰልፉን ለመጥራት በሀገራችን መሰረታዊና ወቅታዊ የሆኑ ችግሮችን እንዲሁም በሰውዲና በአለም ዙሪያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ መሰረቱ የስደት መንስኤው ላይ በመሆኑ መንግስትን በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ እንደነበር ለማወቅ ችለናል፡፡

ሰልፉን ለማድረግ የታቀደው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ በር ፊት ለፊት ከሚገኘው የመድረክ ቢሮ በመነሳት በአምስት ኪሎና ስድስት ኪሎ አድርጎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ድረስ ለመጓዝ ነበር፡፡ ነገር ግን የአድስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንትባ ፅ/ቤት “ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እውቅና የጠየቃችሁበት ስፍራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ አሰራር ስነ-ስርዓት አንቀፅ አምስት ሀ እና መ የሰላማዊ ሰልፍ የማይካሄድባቸው ቦታዎች ተብለው የተጠቀሱ በመሆናቸው የተጠየቀው የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና መስጠት የማንችል መሆናችንን እንገልፃለን” ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው የመድረክ ስራ አስፈፃሚና የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሀፊ አቶ አስራት ጣሴ “መልሱ የመድብለ ፓርቲ ቅልበሳ ከመሆን አይዘልም” ይላሉ፡፡ አስተዳደሩ ጠቅሶ እውቅና ለመንፈግ የተጠቀመበት ደንብ ማንም የሚያውቀው መሆኑን የተናገሩት አቶ አስራት በማያውቁት ህግ እንደማይደኙ ገልፀውልናል፡፡ በተጨማሪ በዚህ ጉዳይ ላይ የወጣው አዋጅ መወቅ ቢችሉ እንኳ በተባለው ደንብ እንደማሻር አክለዋል፡፡

በ1983 ዓ.ም የወጣው የሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 3 1983) የተከለከሉ ብሎ የሚጠቅሳቸው ቦታዎች እንደሌሉና ከኤምባሲዎች፣ ት/ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የሀይማኖት አምልኮ ስፍራዎች፣ በገበያ ቀን (ከገበያ ስፍራ) መቶ ሜትር መራቅ እንዳለበት ማዘዙን አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከጦር ካምፕና የደህንነት ተቋማት 500 ሜትር መራቅ እንዳለበት አዋጁ ማስገደዱን ያስረዱት አቶ አስራት ከዚህ ቀደም አንድነት መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም በጠራው ሰልፍ ይህንን አዋጅ በመሻር በጦር ካምፕና በደህንነት መስሪያቤቶብ በተከበበው ጀንሜዳ እንድንወጣ ነግረውናል ብለዋል በተሰጠው መልስ ላይ አቋም ለመያዝ የመድረክ አመራር እንደሚሰበሰብ ከአቶ አስራት ጣሴ ለማወቅ ችለናል፡፡

መድረክ ህዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም መድረክ ለጠራው ሰልፍ አስተዳደሩ ከተደራራብ የስብሰባ ጫና የተነሳ የፖሊስ ሀይል ስለሌለኝ ጥበቃ ለማድርግ አልችልም በሚል እውቅና መንፈጉ ይታወቃል፡


ጅጅጋ በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ስር ናት

esat

ህዳር (ሃያ ስድስ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-8ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለማክበር በሚል የጅጅጋ ከተማ በፌደራል ፖሊስ  አባላት መወረሯን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማውን ከተቆጣጠሩት በሁዋላ ልዩ ፖሊስ እየተባሉ የሚጠሩት ሀይሎችን ወደ ዳር የገፉዋቸው ሲሆን፣ ፖሊሶቹ በየተወሰኑ ሜትሮች ቁጥጥር እያደረጉ ነው። የጸጥታ ጥበቃው በሄሊኮፕተር ላይ በሚደረግ ቅኝት የታጀበ ሲሆን፣ በየ አቅጣጫውም በዙ 23 እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ጥበቃ እየተደረገ ነው። ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከሶስት ቀናት በፊት የአካባቢው የጸጥታ አጠባበቅ ምን እንደሚመስል ጎብኝተው መመሪያ ሰጥተው መሄዳቸው ታውቋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በቅርቡ በእጅ ስልካቸው ላይ ከአልሸባብ መልክት እንደደረሳቸው መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በትናንትናው እለት ደግሞ እንግዶች ከሚያርፉበት የክልሉ መስተዳድር ግቢ ውስጥ 4 የተቀበሩ ፈንጆች በአነፍናፊ ውሾች መገኘታቸውን ጅጅጋ የሚገኙ የውስጥ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። ፈንጂዎቹ እንደተገኙም እንግዶቹ ” ተረፍን” ሲባባሉ ተሰምቷል። ሁኔታው በበአሉ ላይ ለመገኘት በሄዱ የክልል ባለስልጣኖች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩንም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።
ለበአሉ ከክልሎች የመጡ ዋና ዋና እንግዶች የመስተዳድሩ መስሪያ ቤቶች ተዘግተው፣ በመስተዳድሩ ግቢ ውስጥ አልጋ ተዘርግቶላቸው እንዳረፉ መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ዝግጅት በወጪ ደረጃ  አምና በባህርዳር የተካሄደውን ዝግጅት በ50 ሚሊዮን ብር እንደሚበልጥ ለማወቅ ተችሎአል። ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሞበታል በተባለው በዚህ ዝግጅት ላይ አርቲስቶች በተለይም የህወሀት ሰዎች ከፍተኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያሳያል። አርቲስት ኪሮስ ወልደስላሴ የማስታወቂያውን ስራ ለመስራት 8 ሚሊዮን ብር ውል የተፈራረመ ሲሆን፣ የባዛር ዝግጅቱን እና በባዛሩ ላይ ለሽያጭ የቀረቡት᎐ አብዛኞቹ የህወሀት ኩባንያዎች ምርቶች መሆናቸው ታውቋል።
ውድ ተመልካቾቻችን በክልሉ ውስጥ የህወሀት ጄኔራሎች ስለገነቡት የሀብት ኢምፓየርና ለበአሉ እንዲደርስ ተሰርቶ  በዛሬው እለት እንደፈረሰ በተነገረለት የመለስ ሀውልት ዙሪያ ላይ  በነገው እለት ተጨማሪ ዘገባ ይዘን እንቀርባለን።