Friday, 18 October 2013

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግስት ላይ ተቃውሞ አሰማች

ጥቅምት ፮(ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው መንበረ ፓትሪያርክ ስብሰባ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ባለው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በቤተክርስቲያኑዋ ታሪክ  ተሰምቶ የማያውቅ ተቃውሞ ተከስቷል። አንድ በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አባት እንደገለጹት በስብሰባው ላይ ”  ይህ መንግስት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ እንደተነሳ በስፋት ተነግሯል።
የፌደራል ጉዳዮች የሀይማኖት ክፍል ሃላፊዎች ዛሬ ስለ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ገለጻ ለመስጠት በተገኙበት ወቅት ነው ተቃውሞው የተሰማው።
እድሉን ያገኙት 6 ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም የሰሜን ወሎ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቄርሊዮስ ፣ የምእራብ ወለጋ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ ሄኖክ፣ የጋሞ ጎፋ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤሊያስ ፣ የወላይታ ዳውሮ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የምስራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ ብጹ አቡነ ማርቆስ ፣ የደቡብ ጎንደር ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንድሪያስ የመንግስትን ፖሊሲ እያነሱ ትችት አሰምተዋል።
በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ፣ ግድያና ጫና መጨመሩን የተነጋሩት አባቶች ፣ ፓትሪያርኩም እውነት ነው ይህ ሁሉ ጫና አለብን በማለት በሊቀ ጳጳሳት የቀረቡውን ሀሳብ ደግፈዋል።
ከመላው አለም የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀይማኖቱ መሪዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት የኢትዮጵያን የሀይማኖት ታሪክ በማሳነስ ባቀረቡበት ወቅት  የሀይማኖት አባቶች ስሜት በተቃቀለበት ሁኔታ መልስ ሰጥተዋል።
የህዝቡን መሬት ነጥቃችሁ ፣ ህዝቡንም መሬቱንም የመንግስት ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ፣ ኢትዮጵያዊው ሀብትና ንብረት እንዳይኖረው አደረጋችሁት እናንተ ናችሁ፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩት መንግስታት በባሰ ህዝቡን ያስጨነቀ ይህ መንግስት ነው በማለት አባቶቹ ተናግረዋል።
“በአጼዎችም ዘመን ቢሆን ይህችን አገር  ስትረከቡ እስከ ታሪኩዋ ነው፣ ታሪኩዋን አላጠፋችሁም ወይ?” በማለት ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ ሲናገሩ ከተሰብሳቢው ከፍተኛ ድጋፍ ተችሮአቸዋል።
የሀይማኖት አባቶች የቤተክስርቲያኑዋን ታሪክ አዛብታችሁዋል፣ ቤተክርስቲያኑዋንም ታሪኩዋን አጥፍታችሁዋል በማለት ወጥረው መያዛቸው ታውቋል።

Wednesday, 16 October 2013

ለአፍሪካ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ፍትሕ አይቀሬ ናት

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ
ማስታወሻ ለአንባቢው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐተታዬ ‹‹የዘር አደን›› በሚል አሉባልታዊ ክስ  የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በተሰነዘረበት ክስ ደግፌው ተሟግቼለታለሁ፡፡ በዚህም ሳምንት ድጋፌን በመቀጠል እነዚህ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች የፈጠሙትን ግፍና በደል ጭቆና በመዘርዘር ራሳቸውን ነጻ በማድረግ የአይ ሲ ሲን (የኣለም ወንጀለኛ ፍርድ ቤት) ስም በማብጠልጠልና የቆመለትን ዓላማ የሳተ በማስመሰል ገዢዎችና አስፈጻሚዎ ቡችሎቻቸው ያነሱዋቸውን ማስረጃ ቢስ ውንጀላዎች በተጨባጭ ማስረጃ ድርጊቶታቸውንና ሸፍጣቸውን ይፋ ለማድረግ ወስኛለሁ፡፡ የኦክቶበር 11-12, 2013 የአፍሪካ አንድነት ‹‹መሪዎች›› የጨረባ ስብሰባ የተጠራውም ቴአትራዊ የልብ ወለድ ሴራ ለማካሄድና ነጻ ለመምሰል የሚያስችላቸውን ቅጥፈት ለማናፈስ ነው፡፡international criminal court
በኔ እምነት አይ ሲ ሲ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ሕግጋት ትክክለኛውና ጠንካራው ምልክት ነው፡፡ አይ ሲ ሲ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ስራውን በማከናወን ላይ ነው፡፡እስካሁን ያስመዘገባቸው ውጤቶች ጥቂት ቢሆኑም ለወደፊቱ ግን ያሻቸውን በደልና ግፍ ፈጥመው ግድያና አስገድዶ መድፈርን ሰብአዊ መብት በደልን አዘው በማስፈጸም በሥልጣናቸውም አላግባብ ባልገውና ተጠቅመው፤ ሃገርን አራዉተው፤ ሕዝብን በበደልና ግፍ ጫና አጉብጠውና አንበርክከው፤ በነጻ ሲቀመጡና ሲንደላቀቁ የነበሩትን እያጋለጠ ለፍርድ ለማቅረብ የሚችል ጠንካራ ተቋም እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡  የአፍሪካ ጨቋኝና የግፍ በደል ባለቤት የሆኑት ገዢዎች በሕዝቡ ላይ ሊኩራሩና ሊደነፉ፤ የሕግ የበላይነትን በመጨፍለቅ ሊቀጥሉ ይጥሩ ይሆናል፤ አሁን ግን አይ ሲ ሲ ስለመጣባቸውና ለሕዝቡ ወግኖ ስለቆመ ስሙ በተጠራ ጊዜ እየተርበደበዱና መግቢያ እያጡ በመሄዳቸው የአይ ሲ ሲን ስም በማጉደፍ ነጻ ለመሆን ቢጥሩ መንገድ ሁሉ፤ በደላቸው ሁሉ፤ ግፋቸው ሁሉ አይ ሲ ሲን እየቀሰቀሰባቸው በመሆኑ ኦክቶበር 13 2013 የቁም ተዝካራቸው ማውጫ አድርገው ሊሰባሰቡ ነው፡፡
በኦክቶበር 11-12,  2013 አድመኞቹ የአፍሪካ ‹‹መሪዎች›› አስተጋቢው የእንግዳ መቀበያ የአፍሪካ አዳራሽ በመሰባሰብ አብዛኛዎቹ በሮም ከጸደቀው ደንብ (አለም ኣቀፍ ዉል) በመውጣት በደስታ ተሞልተው የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን የሞት ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ ቀብሩንም ለማስፈጸም የኢትዮጵያ የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ  አንድነት ተዘዋዋሪ የ2013ቱ ሊቀመንበር ሃይለማርያም ደሳለኝ ነው፡፡ ስብሰባውንም ሲከፍት ‹‹ዛሬ በዚህ የምጽዋት አዳራሻችን የተሰባሰብነው አይ ሲ ሲን ለማወደስ ሳይሀሆን ልንቀብረው ነው….›› በማለት ይሆናል፡፡ የዚህ የቀብር ጥድፍም ሰበቡ የኬንያው ፕሬዜዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኬንያ በተካሄደው የ2007 ምርጫ ወቅት በፈጸመው የሰብአዊ መብት ግፍ ለመጠየቅ ኖቬምበር 12 2013 ለፍርድ ሊቀርብ በመሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ ወንጀልም ምክትሉ ዊሊያም ሩቶ ፍርዱ በሄይግ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ መታየት ከጀመረ ሁለተኛ ወሩ ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት በኬንያታ እና በሩቶ ላይ የተመሰረተውን ክስ ዘዴ ፈልጎ ካላነሳ በስተቀር ‹‹የኑክሊየር ፈንጂ መቃወሚያውን›› በመጠቀም ከአይ ሲ ሲ አባልነት ለመውጣት እንደሚችልም በማስፈራራት ላይ ነው፡፡
ላለፉት ጥቂት ወራት ሃይለማርያም በአይ ሲ ሲ ላይ የቃል ጦርነት ሲያካሂድ ነበር፡፡ ባለፈው ግንቦት የጃጀዉና በቅዠት ዓለም ያለው ሮበርት ሙጋቤን በመደገፍ በአይ ሲ ሲ ላይ ውንጀላ አካሂዷል፡፡ ግልጽና ማስረጃው ከመጠን ያለፈውን ግፍ ለፈጸመ የአፍሪካ ገዢ ጥብቅና መቆምና ሕዝብን ለባሰ ግፍ ማብቃት የሃይለማርያም የአፍሪካ ወቅታዊ ሊቀመንበርነት ተግባር ሆኗል፡፡ ሃይለማርያም ቃላትን በማሰባሰብና ከጀርባ ባሉት ሽነቋጭ አለቆቹ በመመራት ግራ የገባውን አባባል በመጠቀም አይ ሲ ሲ ‹‹99 በመቶ›› የሆኑት በደለኛ ተከሳሾች አፍሪካውያን በመሆናቸው  የዘር አደን ላይ ነው የሚል መሰረተ ቢስ ወሬ እየነዛ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው 68ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ባሰማው ወሬው፤ አይ ሲ ሲ የኬንያታንና የሩቶን ክስ በማንሳት ጉዳዩ በኬንያ ባለስልጣናት እንዲታይ ማድረግ አለበት በማለት የማይገባ  የድፍረት ጥያቄ አንስቷል፡፡ ሆኖም ኬንያታ ከተሰነዘረበት ወንጀል ነጻ ሳያደርገው፤ ማድረግ ያሰበው ግን ኬንያታ ራሱ በሚያዘውና መመርያ በሚሰጠው ችሎት ይዳኝ ለማለት ነው፡፡ አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ይላሉ ሲተርቱ፡፡ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያና ናይጄርያ  ለአይ ሲ ሲ ይግባኝ ሰሚ የኬንያው ክስ እንዲነሳ ያቀረቡትን የጽሁፍ ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ሃይለማርያም የዚህ ተቀባይነት የሌለው አሳፋሪ ጉዳይ አፈጉባኤ ሆኖ የመገኘቱ ምጸታዊ መነሾ አስገራሚ ነው፡፡ 34 የአፍሪካ ሃገራት የሮምን ደንብ/ዉል የፈረሙበት ሲሆን (አይ ሲ ሲ ሰን በማቋቋም ወንጀሎችን በመመርመር ሰብአዊ መብት ጥሰትን የዘር ጭፍጨፋን ግፍ በማጥራት ለፍርድ እንዲያቀርብ ውክልናና ስልጣን ሰጥቶታል):: እስከሁንም ኢትዮጵያ የዚህ ሕግ አባል ለመሆን ፊርማዋን ነፍጋ ቆይታለች፡፡ የሃይለማርያም የሥላጣን አባት ይህን ሕገ ደምብ ላለመፈረም ወስኖ ያቆየው ምናልባትስ አይ ሲ ሲ እንደማይለቀውና ወንጀሉን አጥርቶ እንደሚፋረደው ተገንዝቦ ይሆን? ለፊርማውም ችግር የሆነበት ሰበብ ሕጉን ፈርሞ ከተቀበለው የፊርማው ቀለም ሳይደረቅ በሰራቸው ሕገ ወጥ ተግባራት በፈጃቸውና ባስፈጃቸው ንጹኃን ዜጎች ሳቢያ አይ ሲ ሲ በሩን እንደሚያንኳኳና ለሕግ እንደሚያቀርበው ጠንቅቆ በመረዳቱ ነው?  እነዚያስ 34 ሃገራት ሕጉን አጽድቀው አይ ሲ ሲን ሲያቋቁሙ አይ ሲ ሲ የአፍሪካ ጋሻ መከታ ሆኖ ወንጀለኞችን አላንዳች አድልዎ እያደነ ለፍርድ እንደሚያቀርባቸው አልተገነዘቡትም ነበር?
አይ ሲ ሲን በአፍሪካ አለሳልሶ የመግደል ጥበብ የሃይለማርያም ተንኳሽና የሚያስቆጣው ክሱ የሚያሳየው፤ አይ ሲ ሲን ከአፍሪካ በድል በማስወጣት እራሱን ‹‹ጭራቅ
ገዳዩ ጀግና›› ላመሰኘት የተነሳሳ መስላል፡፡ (የሱ ቀደምት የሥልጣን አባቱም ‹‹የአዲሱ ትውልድ አፍሪካዊ መሪ›› በሚል መጠርያ ለራሱ የፈረስ ስም ሰጥቶ፤ ታላቅ በመሆን በሽታ ተለክፎ ለማይለቅና ለማይድን እጀሰብ ተዳርጎ ነበር::) የነገሩ እውነታ መሰርት ግን በዚህ አካሄድ የሃይለማርያምና የጸረመስቀል ተዋጊዎቹ አካሄድ በኬንያዊያን ባለስልጣናት ላይ የተመሰረተውን ክስ ለማስነሳት፤ በብዛት ከአይሲ ሲ አባልነት መውጣትን እንደማስፈራሪያና ማገቻ በማድረግ ወንድሞቹን ኬንያታንና ሩቶን ከአይ ሲ ሲ ማነቆ በማላቀቅ፤ ወደፊት በእነሱ ላይ ሊደርስ የማይችለውን አይቀሬውን ህጋዊ የክስ እርምጃ አስቀድሞ ለመዝጋት የሚያደርገው የአልሞት ባይ ተጋዳይ የሕልም ሩጫ ነው፡፡ አፍሪካን በሚገባት ከፍተኛ የአመራር ስልጣን ላይ ላመስቀመጥ የሚጥረውን አይ ሲ ሲን ለማጥፋት ከንቱ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ሃይለማርያምና መሰል ግፈኛ ገዢዎች ራሳቸውን ከግፍ ባህሪና ልምዳቸው በመመለስ እንደሰው በማሰብ ለሰብአዊ ፍጡራን ተገቢውን አገልግሎት ለማከናወን ቢተጉ ይበጃቸዋል፡፡
በኦክቶበር 11-12 2013 በአፈሪካ አንድነት ስለ አይ ሲ ሲ ቀብር ስለሚደረገው ንግግር ቅድመ ትርኢት
የአፍሪካ ‹‹ገዢዎች›› በኦክቶበር 11-12 2013 በአፍሪካ አንድነት በሚሰባሰቡበት ጊዜ ስለሚያካሂዱት እብደት ቀረሽ ጸረ አይ ሲ ሲ  ዘመቻ በቂ ግንዛቤ አለን፡፡ የንግግራቸው መነሾና አካሄየ አይ ሲ ሲን ወኔ ለመገድልና ተግባሩን ለማገድ አስቀድሞ ንድፉ በአምባሳደር ቋሚ ተወካይ ማቻሪያ ካማው፤ በኬንያ በተባበሩት መንግስታታ ቋሚ ሚሲዮን በኩል ለአምባሳደር ሜናንካዶ (የሴኪውሪቲ ካውንስል የሜይ ወር 2013 ሊቀመንበር) በተዘጋጀው ባለ 13 ገጽ ሚስጥራዊ ሰነድ ተዘርዝሯል፡፡
1. መላ የሌለውና ቅጥ ያጣ እርማት የተካሄደበት የካማው ሚስጥራዊ ሰነድ፤
ኬንያታን ሩቶ ከአይ ሲ ሲ ማነቆ ሊላቀቁ ይገባል ምክንያቱም እነሱን ለክስ ማቅረብ የኬንያን ልኡላዊነት ነጻነት የሚጥስ ነው፡፡ እንደ ካማው አባባል ‹‹የኬንያታና የሩቶ ክስ ራሱን ለሚያስተዳድረው መንግስታችን በውስጥ ጉዳያችንና በሃገራችን ኬንያና በልኡላዊነታችን ላይ የተቃጣ ውርደት ነው በማለት ይከራከራል፡፡ የኬንያ ልኡላዊነት ከኬንያ ውስጥና ውጭ የተለያዩ ተዋንያንን በመጠቀም ለወቀሳ እየተዳረግን ነው፡፡እንዳለፈውና እንደተለመደው የሲቪሉን ማህበረሰብ በማነሳሳት የራሱን ፖሊሲ እንዲቃወም በመደረግ የሮምን ስምምነት ሰበብ በማድረግ አይሲሲን በአስፈጻሚነት እየተጠቀሙበት ነው፡፡›› ነጻነት ለአፍሪካውያን ጨካኝና አረመኔ ገዢዎች የመጀመርያው ስደተኛ ነው፡፡ አሁን የአፍሪካን ነጻነት ለማስከበር በማለት የሚንደፋደፉት አስመሳይ የአፍሪካ ጨቋኞች በኖቬምበር 2010 ምርጫ ወቅት ፈረንሳይ በቀጥታ በአይቮሪኮስት ግጭት ጣልቃ በገባችበት ወቅት፤ ገዳም እንደገባች አይጥ ተሸጉጠው ትንፍሽ ሳይሉ ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቷን መልሳ ስተወር አንዲት ቃል አልተነፈሱም፡፡ የአፍሪካ አንድነትም ቢሆን በዝምታ ተቀምጦ ጠበይ ተመልካች በመሆን ከጎን ሆኖ ከመመልከት አላለፈም፡፡ በጃንዋሪ 2013 ፈረንሳይ የሰሜን ማሊን ከሽብርተኞች ወረራ ነጻ ለማውጣት ጣልቃ ሲገባ የአፍሪካ መሪዎች የፈረንሳይን ጦር ለማስወጣት የነጻነትንና የልእልና ማስከበርን ጉዳይ አላነሱም፡፡ አሁንም እንደገና የአፍሪካ አንድነት ከተመልካችነት አላለፈም፡፡
በወንጀል ፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት፤በጦር ወንጀለኛነት፤በዘር ማጥፋት ለሚሰነዘር ክስ ሉአላዊነት ሕጋዊ መከላከያ አለያም የፖለቲካ ውይይት ሁኖ አይቆምም፡፡ አሁን በአፍሪካ ፈላጭ ቆርጫ ገዢዎች የሚነሳው የሉአላዊነት ጥያቄ አይ ሲ ሲ የተጣለበትን አደራ ላማዘናገት ሆን ተብሎ የተነሳና ቀድሞ ከነበሩት የንጉሳዊ ገዢዎች በምድራዊ ዳኝነት እንጠየቅም ሥዩመ እግዚአብሔር ነን እንደሚሉት ለመሆን የታቀደ ዘዴ ነው፡፡ ሕገ ወጥ የሆነውን የአፍሪቃ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ሊዳኘው የሚገባውና የሚችለው ሌላው ሕገወጥ አፍሪካዊ ገዢ መሆን አለበት ነው የሚሉት፡፡
2.      ኬንያታና ሩቶ ከክስ ነጻ የመሆን መብት አላቸው ምክንያቱም በማርች 2013ቱ ምርጫ ‹‹ንጹህ›› ናቸው ስለተባሉ፤ካማው ኬንያታና ሩቶን በተመለከተ ሁለቱ ሰዎች ንጹሃን ብቻ ሳይሆኑ በክፍተኛው የመንግስት ስልጣን ላይ ስለተቀመጡ ሃለፊነትም አለባቸውና ክሱ ሊሰረዝላቸው ይገባል በማለት ይሞግታል፡፡ አይ ሲ ሲ የከፈተው የክስ
መዝገብ የሚዘጋበት ምክንያት ኬንታና ሩቶ የፈጸሙት የሰብአዊ መብት ድፍረትና ጥሰት በፍትህ አደባባይ ቆሞ ስለሚመሰክርባቸውና ለፍርድ ሊያቀርባቸው ስለሚችል የንጹሃን ግፍና በደል በነሱ የስልጣን ወንበር መያዝ ተቻችሎ ነጻ ሊሆኑ ይገባል ነው፡፡  እነዚህ ሁለት ዋናና ምክትል ገዢዎች የኬንያውያን ሁሉ መተሳሰርያ በመሆናቸውና ሕዝቡም በፍቅር ስለመረጣቸው፤ 86 በመቶ ድምጹን ሰጥቶ መንበራቸው ላይ ስላስቀመጣቸው ክሱ ሊሰረዝላቸው ግድ ነው፡፡ ካሙ ክርክሩን በመቀጠል፤ የሮሙ
ስምምነት ኬንያታንና ሩቶ ሊያካትት አይገባም፤ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛውን የሃገሪቱን አመራር በዋናነትና በምክትልነት የያዙ በመሆናቸውና የኬንያ ሪፑብሊክ የመከላከያ አዘዦች በመሆናቸው፤ነው ይለናል፡፡ ካሙንን ግራ ያጋበው ነገር ኬንያታና ሩቶ ንፁህነታቸውን ለማረጋገጥ መመረጥ አያስፈልጋቸውም፡፡ ማንም ሰው ቢሆን በፍርድ ሸንጎ ወንጀለኛ እስካልተባለ ድረስ ንጹህ ነውና፡፡ ስለዚህም በተጠረጠሩበት ወንጀል ኣይ ሲ ሲ የሚለው ችሎት ፊት ቀርበው ንጸህናቸውን በነጻ የፍትሕ ስርአት ያረጋግጡ ነው እንጂ ወንጀለኞች ናቸው ብሎ አልደመደመም፡፡ የሁለቱ ባለስልጣናት በአጥጋቢ ውጤት ከመመረጣቸው ጋር የተሰነዘረባቸው ተጠርጣሪነት አንዳችም ግንኙነት የለውም፡፡ ጥያቄው በ2007-08 በስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ተፈፀሙ በተባሉ ወንጀሎች ነው፡፡ ኬንያታና ሩቶ የሃገሪቱ መሪዎች መሆናቸው ከሕጉ ጋር የሚያገናኘው ሰበብ የለውም፡፡ የሮም ስምምነት አንቀጽ 27 ማንኛውም ተጠርጣሪ አይሲሲ ችሎት ቀርቦ ንጽህናውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ይላል፡፡ ስምምነቱ ማንንም በእኩል ደረጃ ይመለከታል፡፡ ማንንም ከማንም በስልጣን ደረጃ አያመዛዝንም ለአይ ሲ ሲ ምንኛውም ተጠርጣሪ እኩል ነው፡፡ ተመራጭ ፕሬዝዳንትም ይሁን የፓርላማ አባል የመግስት ባለስልጣንም ሆነ ተራ ዜጋ ለአይ ሲ ሲ ችሎትና መመርያ ሁሉም እኩል ናቸው፡፡
በኬንያታና በሩቶ ላይ የተመሰረተው ስንኩል ክስ (የተባበሩት መንግሥታት ሴኩሪቲ ካውንስልና በኬንያም መንግሥት ወንጀል መስራታቸው ሳይተላለፍለት ነው) በአግባቡ ምርመራና ማጣራት ሳይካሄድበት ነው ይላሉ፡፡ የአይ ሲ ሲ ክስ ተቀባይነት የሌለው ምስክሮቹንም አስጠንተው ያቀረቧቸው ናቸው፡፡ ተጠቂ ነን ብለው የቀረቡትም ሃሰተኞች አለያም ተመርጠው የተሰየሙ ናችው፡፡ የምስክርነት ቃላቸውም ደካማና የማያሳምን ነው፡ በማለት ካሙ ይከራከርላቸዋል፡፡ ምስክሮች  በመደለያ የተገዙ ያንንም ነው አይደለም ብሎ የሚወስነው የአይ ሲ ሲ ችሎት ነው፡፡ ምናልባትም ምስክሮቹ ተአማኒነት የሌላቸው በጥቅማ ጥቅም የተገዙ ናቸው የሚባልም ከሆነ የካሙስ መንግስት ማስረጃውን በማቅረብ ሊቃወም ይችላል፡፡
4.      የአቃቤ ሕግ ቢሮ ሚዛናዊ ባልሆነ መልኩ በኬንያታና በሩቶ ላይ የክስ ምስረታውን ተከሳሾቹን በሚጎዳ መልኩ እያካሄድ ነው ለፍትሕ በእኩል መልኩ የተከናወነ አይደለም በማለት ተጠርጣሪዎቹን ተከሳሾች ፍትሕ በአግባቡ ነጻ ናቸው አይደሉም ከማለቱ ይልቅ አይ ሲ ሲንና የአቃቤሕግ ቢሮን በሃሰት በመወንጀልና ፍትሕ ገደል ይግባ ለኛ በሚመቸን መልኩ የማይሰራም አይ ሲ ሲ ፍርስርሱ ይውጣ የሚል ነው የካማው ቅጥ ያጣ ሙግት፡፡ ፍትሕ ለመዛባቱ የካማው መንግስት ማስረጃ ካለውና በፊትም ሆነ አሁን ኬንያታንና ሩቶን ፍትሕ ይነፍጋቸዋል ብሎ ካሰበ ወደ ፍርዱ መድረክ በማቅረብ ሕዝብ እንዲያውቀው ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ በተቃራኒው ካማውና የአፍሪካ መሪዎች ሊያደርጉና ለማድረግም በመጣር ላይ ያሉት አንዳችም እውነትነት የሌለው የክስ ዳውላ በመዘርገፍና እርፍት የለሽ የድረሱልን ጥሪ በማሰማት ዓለምን ሊያሳምኑ በመጣር ላይ ናቸው፡፡ እውነት ካላቸው እነካማው አለን የሚሉትን የፍትህ ግድፈት አደባባይ ያውጡት፡፡
5. አይ ሲ ሲና የአቃቤው ሕግ ቢሮ ማንም የማይቆጣጠረውና ከሕግ ውጪ ለማንም ተጠያቂ ያልሆነ ባለሥልጣን ነው ለመጀመርያ ጊዜ ቋሚ ዓለም አቀፋዊ ተቋም የሃገራትንና የዜጎቿን ሕጋዊ ግዴታ ለመመልከትና ለመወሰን ወንጀልም ሲያገኝባቸው በአግባቡና በስርአት ቅጣት ለመጣል ተመስርቷል፡፡ አይ ሲ ሲ ብቃቱን በተመለከተ በማንኛውም መልኩ ለዓለም አቀፍ ሕግጋት ምን እንደሚያስፈልገው ሲረዳ የመከራከሪያው የመጨረሻ ቃላት አይ ሲ ሲ ሲወስን በማንኛውም መንግስት ቁጥጥር ስር አለያም ትእዛዝ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሕግጋት በሚመሩበት ስርአት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ካሙ የሚያውቀውና የሚለውም ሆነ አይ ሲ ሲ ያድርግ የሚለው አለቆቹ በሚወነጀሉበት ጥፋታቸው ሁሉ አስቀድሞ እነሱ የሚያዙት ችሎታቸው ጉዳዩን ይመርምር ነው፡፡ የሚያውቀውና የሚከተለው አሁን ምርመር ይደረግባቸው የተባሉት አለቆቹ ሲያስሩ ሲገድሉ ሲያሰቃዩ ፍርድ አልነካቸውምና አሁን እንዳይነካቸው ይደረግ ነው፡፡ ካሙ ችግሩና በሽታው አለቆቹ የሚመሩበት ያልተጻፈ ሕግና ያልተሰጣቸውን ስልጣን መጠቀም ስለሆነ በዚያው መሰረት ይዳኙ ነው፡፡ አይ ሲ ሲ የሚታዘዘውም ሆነ የሚመራው በዓለም አቀፉ የፍትሕ ስርአት ነውና ማንንም አይጠላም ማንንም ከማንም አስበልጦ አያፈቅርም፡፡ ካሙ ለምን አንድ አቃቤ ሕግ ብቻውን ያጣራው ጉዳይ ተቀባይነት ያገኛል ነው፡፡ አይ ሲ ሲ ደግሞ አቃቤ ሕግ ግድፈት አለበት የሚል ማንኛውም ተጠርጣሪ አለያም ዜጋ መስረጃውን አቅርቦ ሊሞግተው ይችላል ነው፡፡
የአፍሪካን ዲክታተሮችና ጭፍሮቻቸው ስለ ‹‹ቁጥጥር አልባ ሥልጣን›› ሲያወሩ ማዳመጥ የአዞ እንባ እንዲሉ አይነት ነው፡፡ የኬንያን ባለስልጣነት መጠን የለሽ የስልጣን ክልል በመጠኑም ቢሆን ለመቆጣጠር ያስቻለው በ2010 የወጣው ሕገመንግስት ነው፡፡ በኬንያ ስርአት አልበኝነትን ሕገወጥነትን ለመከላከል ሲባል የወጣው አዲሱ ሕገመንግስት  ነው መሰረት የጣለው፡፡ ማንም ሊረዳው የሚገባው አዲሱ የኬንያ ሕገመንግስት በ2007 በተከሰተው የምርጫ ውዝግብ ሳቢያ በተካሄደው ውይይት ላይ ተመስርቶ መረቀቁና መጽደቁ ነው፡፡ ኬንያታና ሩቶ በዚያው ሕገመንስት ደንብና ስርአት  ውስጥ በተካተተው መመርያ መሰረት ነው ለፍርድም ሊቀርቡ ማዘዣ የወጣባቸው፡፡
በአፍሪካ የሕግ የበላይነት እነ ካማው መሰረተ ቢስ የሆኑ በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳት ሕዝብንና መንግስታትን በማታለልና መንገድ በማሳት አለቆቻቸውን ነጣ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ እነ ሃይለማርያም ደሳለኝ የአይ ሲ ሲ አካሄድ ማንም ግፈኛና ወንጀለኛ ከነጉድፉ ተሸሽጎ እነዳይኖርና ግፍና በደሉን በማር ቀብቶ ለማስመሰያነት እንዳዋለ እንዳይኖር  የማድረግ ስልጣኑ ማነህ ባለሳምንት ይለናል በማለት አስቀድመው ለራሳቸው የሚጠቅም ከለላ ለመፍጠር ነው ጥረታቸው፡፡ የዓለም ሕግ ተፋለሰ ሲሉ እስከ ዛሬ ድረስ እነዚህ የኡኡታ አሰሚዎች የፈጸሙትን የሕግ መፋለስ በመዘንጋት ሳይሆን አውቀው ትክክለኛ መስለው ለመታየት እንጂ በአይ ሲ ሲ አካሄድ የተፋለሰ አንዳችም ሕግ የለም፡፡ አለ ከተባለ ደግሞ ከነማስረጃው ማቅረብ እንጂ ከንቱ የጋጋኖ ጨኸት የትም አያደርስም፡፡ የአፍሪካ አንድነት ደንብም ቢሆን በአፍሪካ ውስጥ ሰብአዊ መብት ሊከበርና ሊጠበቅ እንደሚገባው ይደንግጋል፡፡ ስለመልካም አስተዳደርም በደንቡ ላይ አስፈሯል፡፡ ማንም ከወንጀል ነጻ ሊሆን እንደማይችል ደንቡ ያናገራል፡፡
በኦክቶበር 13 ለቁጥር የሚጣክቱት መሪዎች ከሮሙ ስምምነት ለመውጣት ማሴር ማለት ሕግ አልበኝነትና የራሳቸው የአፍሪካ አንድነት የሚተዳደርበትን ደንብ መጣስ መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡ ተጠያቂነትን ያወጁ ሃገራት ተጠየቁ ሲባሉ ሕጉን ያወጣነው ሕዝብን ለመቅጣት እንጂ እኛ ልንጠየቅበት አይደለም ማለት ምን የሚሉት፡፡ በጣም ቀላል የሆነና የማይቀር ምርጫ አለን፡፡እነዚህን በአፍሪካ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ሆነው ግፍን በመፈጸምና ሃላፊነትን አላግባብ በሚጠቀሙ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ከሮም ውልና ስምምነት የመውጣት አድማቸው ላይ አቋም በመያዝ መመጎት ቢያንስ  የነዚህን እኩዮች አድማ የሚቃወሙትን ተቆርቋሪ ወገኖች ማገዝ ነው፡፡ ለዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት መቆምና መወገን ማለት አፍሪካ ውስጥ በመግዛትና ግፍ በመፈጸም ያሉትና ባለስልጣናት መሞገት ነውና አብረን ሆነን ከአፍሪካ ጫንቃ ላይ እንዚህን ጋሬጣዎች እንንቀስ! አይ ሲ ሲን የመደገፊያው ወቅት አሁን ነው::

አለማቀፍ ጠበቆች የኢትዮጵያን ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ጀመሩ



በወጣት አብዱላሂ ሁሴን አማካኝነት በኢትዮጵያ የኦጋዴን ክፍል የተፈጸመውን የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፊልም የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በስዊድን ቁጥር አንድ ቴሌቪዥን በትናንትናው እለት መቅረቡን ተከትሎ አለማቀፉ ጠበቆች ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀመረዋል።
ወጣት አብዱላሂ ለኢሳት እንደገለጸው ፊልሙ ከተላለፈ በሁዋላ ሚዲያዎች ሸፊ ሽፋን የሰጡት ሲሆን፣ ስቴላም የተባሉ የ አይ ሲ ጄ ጠበቃ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ በሬዲዮ ይፋ አድርገዋል።
የስዊድን የጦር ወንጀል ኮሚሽን ፍርድ ቤትም ማስረጃዎችን በመመርመር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከወጣት አብዲ ጋራ ቀጠሮ ይዘዋል። ጠበቆቹ ጄኔቫ ካለው አይሲጄ ጋር እና ከሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደሚሞክሩ ተናግሯል።
ትናንት በተላለፈው ፊልም ውስጥ ከዚህ በፊት በኢሳት ያልቀረቡ መረጃዎች መቅረባቸውን ወጣት አብዲ ገልጿል።
ልዩ ፖሊስ እየተባለ በሚጠራው ሀይል የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያሳይ መረጃ መካተቱትን፣ የክልሉን ፕሬዚዳንት የተቸች አንዲት ሴት በኦበነግ አባልነት ስትፈረጅ የሚያሳይ መረጃ ተካቶበታል ። የክልሉ ፖሊስ ሀላፊው በእስር ላይ የሚገኙትን ሴቶች በመድፈር ብዙ ህጻናት በእስር ቤት ውስጥ መወለዳቸውን በፖሊሶች በራሳቸው ሲነገር የሚያሳይ ፊልም መካተቱትን ወጣት አብዱላሂ ገልጿል።
ፊልሙ ” የዲክታተሮች እስረኞች” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል።
ጉዳዩን በማስመልከት የአለማቀፍ የህግ ባለሙያዎች ኮሚሽን በእንግሊዝኛ ኢንተርናሽናል ኮሚሽን ኦፍ ጁሪስትስ ኮሚሽነር የሆኑት ስቴላ ጋርደ ለኢሳት እንደገለጹት የወንጀሉን ፈጻሚዎች ወደ ፍርድ ለማቅርብ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ወንጀል ( ICC) ፈራሚ አገር ባለመሆኑዋ ማስረጃውን በቀጥታ ለፍርድ ቤቱ መላክ እንደማይቻል የገለጹት ኪሚሽነር ጋርደ፣ ይሁን እንጅ ሰቆቃን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴ ( Committe Against Torture) ፈራሚ አገር በመሆኑ ጉዳዩን በዚሁ በኩል ለመከታተል እና የስዊድን ፖሊስ ምርመራ ጀምሮ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ለኢሳት ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ መብት ኮሚቴ እነዚህን ማስረጃዎች እንዲያገኙ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የኖርዌይ የቴሌቪዥን ጣቢያም ፊልሙን በቅርቡ ያሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል። ፊልሙ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ይቀርባል።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው አስተያየት የለም።
ምንጭ:- ኢሳት

እባብ ለእባብ፣ ይተያያል በካብ – ከወንድሙ መኰንን፣ ለንደን

London Ethiopian Orthodox church controversy

ወዲያ ማዶ ሁኖ አንድ ሰው ተጣራ
ወዲህ ማዶ ሁኖ ሌላ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ አንድ በሉ ይኽ ነገር ለኛ ነው።
የለንደኑ ጸረ-ሕዝብ አመጸኛ፣ አንድ እርምጃ ሲወስዱ፣ ሕዝቡ ሁለት እርምጃ ቀድሞአቸው ይጠብቃቸዋል። ሲበዛ ተንኰለኛ በመሆናቸው፣ አንድ ቀን ተሳስተውም ደግ ነገር ሠርተው ቢገኙ፣ የሚያምናቸው ሰው አይኖርም። በዓይነ ቁራኛ ነው እንቅስቃሴአቸውን የምንቆጣጠረው። በዕውነት ተጸጽተው እንኳን ቢያለቅሱ፣ የአዞ ዕምባ ብሎ ነው ሰው የሚሸሻቸው። አሁንም ተነቃቅተናል።
አባ ተባዩ አስመሳይ መነኵሴ፣ የሚጠቅማቸው መስሎአቸው፣ ለወየኔ የመሽሎኪያ ቀዳዳ አበጀተውለት አስጠቁን። “የአስተዳደር መዋቅሩ አይሻሻልም፣ እኔም ከሥልጣኔ አልወርድም” – እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ሁኖባቸው ለወያኔ ወደው ገብተው እኛን በሶልዲ ሸጡን። ከአፈርኩ አይመልሰኝ ሁኖባቸው ነው መሰለኝ፣ የወያኔን ሴራና ሸር የምንቃወምዉን በሙሉ፣ የደርግ ባለሥልጣኖች ብለውን፣ በጠራራው ሜዳ ላይ በቪዲዮ እየተቀዱ “ንጉሳቸውን የገደሉ! ፓትርያርካቸውን የገደሉ![1]”  ብለው ተሳልቀውብን ለወያኔ ታማኝነታቸውን አረጋገጡ።  እነዚህናን የመሳሰሉትን የየጊዜውን ክስተቶች ብዙ ጸሐፊዎች፣ እኔም እንዳቅሚቲ ፣ ጭብጡን አያይዘናችኋል። ነገሩ አሁን አክርረው፣ በጣም አስቀያሚ አድርሰው አደገኛ የሆነ ፍልሚያ ቅዳሜና እሑድ 12th and 13th October 2013 ጠንሠው ተጋፍጠን ተርፈናል። እግዚአብሔር የመስገን!
aba gebreal london
የአዋሳ ገብርኤልን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጥሩ በኋላ፣ አቡነ ገብርኤል (በስተግራ) የለንደኗን ደብረጽዮን ቅደስት ማርያምን በቀሰሙት የትግል ልምድ በክርን ደቁሰው ቁጥጥራቸው ውስጥ ሊያስገቡን የደቡብ አፍርካውን አቻቸውን አቡነ ያዕቆብነ አስከትለው እየገሰገሱ ለሁለተኛ ጊዜ፣ ከተፍ አሉብን። ገና ከአዲስ አበባ ሳይነሱ፣ ሊማርኩን እና “እጅ ወደ ላይ ሊሉን”፣ ሲያስቡ፣ ከዚህ አባ ተባዩ አጭበርባሪ የቀበሮ ባህታዊ፣ ዝግጀታቸውን አጧጧፉ። ብዙ ሺ ብር አፍስሰው ዘማናዊ ቴክኖሎጂ፣ ወደፈለጉበት አቅጣጫ አዙሮ፣ ዙም አድርጎ ተንቀሳቃሽ ምስል መቅረጽ የሚችል ካሜራ ከሕግ ውጪ አስተከሉ። ትልቅ ኪሣራ!!! እንደ የጆርጅ ኦርዌሉ ናፖሊዩን ለዚህ ጉዳይ የሠለጠኑ (brainwashed) የተሸወዱ ወጣቶች እና በወያኔ የደኅንነት ነብሰ በላዎችን ለድብድብ አዘጋጁልን። ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ቴክስት መለዋውጥ ጀምሩ። እነሱ ባላሰቡት መንገድ መልዕክቶቻቸው እጃችን ገባ! “ቤተክርስቲያናችሁ ከአዲስ አበባ በመጡ “ብጹአን” አባቶች ቅዳሜ ዕለት ሊከፈትና እሑድም አገልግሎት ሊሰጥ ነው፣ ዕልል በሉ” ተባለ። አሽቃባጮቻቸው “ለዚህ ያደረሰን እግዚአብሔር ይመሰገን” እየተባባሉ በቴክስትና በፊስ ቡክ እንኳን ደስ ያለህ/ሽ መልዕክት መለዋውጡ ጀመሩ። አይ እግዚአብሔርን አለማወቅ! ለእግዚአብሔር የሚሰጥው ትልቁ ስጦታ “ምስጋና” ነው ሲባል፣ ምስጋንውን አስቀድመው እንደ ጉቦ አቅርበው አረፉ! ከማንስ ይማሩ? “አይ አለማወቅሽ አገር መራቁ” አለ ሰዉዬው። የኛም ሰው ተደዋውሎ ምን መደረግ እንዳለበት ከተስማማ በኋላ መሪዎቻችንና የሚችሉ አባላት ማታ ተገናኝተው ዕቅድ አውጥተው ጨረሱ።
ከስብሰባ መልስ 8 የሚሆኑ አባሎቻችን እኩለ ሌሊት ገደማ ቤተክርስቲያን ተሳልመው፣ ወዲያው ሁኔታዎችን ቃኝተው ለማለፍ ሲሄዱ፣ እነ አባ ተንኵሉን ሽር ጉድ ሲሉ ደረሰቡቸው። እንኳን መመንኰስና ሽታውም ሽው ያለለባቸው የዓለም ሰው አባ ተባዩ፣ የግቢውን በር በሰንሰለት ግጥም አድርገው በታማኝ ደንገጡሮቻቸው ሲያሳስሩና ሲይስቆልፉ አገኟችው! አንዱ ወንድማችን አልፎ ወደ ቤተክርስቲያን ዘልቆ ሊሳለም ሲሞክር የአባ የቅሌት ዘበኞች ተረባርበው ሠፈሩበት። የሚሰነዘሩበትን ጡጫ ተቋቁሞ፣ የሚችለውን ያህል ተከላክሎ በዝተውበት ካሰበው ሳይድረስ አቆሙት። ስልክ ቢደወልልንም በዚያን ሰዓት ከሩቅ ቦታ ልንደርስላቸው አልቻልንም። ሌላውን ወንድማችንን አንዱ የአባ ደንገጡር እጁን መትቶ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ወድቆ ተሠበሮበት ሊያመልጥ ሲሮጥ፣ ፖሊሶች ደርሰው ያዙት። አይ አባ ተባዩ! በተንኰል ባይሳካ፣ በጉልበት ገቡበት? አሁን ከእግዚአብሔር ቤት ማን ሊለየን ይችላል? እንኳን የሳቸው ሰንሰለትና፣ መትረየስም ቢደገንብን፣ በእመቤታችን ስም ከሚጠራው፣ ከአባታችን ቤት ሊነቀነቀን የሚችል አንዳችም ኃይል አይኖርም። እንዲሁ በከንቱ ነው የሚለፉት! ለማኛውም ነገሩ በዚያው በፖሊስ ጉልበት በርዶ ወደየቤታቸው ሁሉም ሂዱ።
አሁን ይኽ ሁሉ አተካሮ ለምን አስፈለገ? ነገሩ እንዲህ ነው! በOctober 21, Charity Commission ሁለቱንም አካል ሊያደራድር ጠርቷል። ወያኔና አባ ተባዩ፣ በዩኬ ሕግ ሳይሆን በአዲስ አበባው ሲኖዶስ ሕግ ብቻ ነው የምንተዳደረው ብለው ድርቅ ብለዋል። ቻሪቲ ኮሚሺን ይዘው የሚቅርቡት መደራደሪያ ሃሳብ የላቸውም። በሕግ ከተሄደ ቤተክርስቲያኑ ሊያመልጣቸው ሆነ። አስቀድሞ፣ አባ ተባዩ ተንደርድረው ቤተክርስቲያኗን ባይዘጉ እንዲህ ዓይነት ጣጣ ውስጥ ባልተገባ! “አንዴ ወድቄአለሁ፣ ጭቃው ላይ ልንከባለል” የሚሉ ይመስላሉ። ከዘጉም በኋላ፣ በወያኔ አይዞህ ባይነት ይኸን ሁሉ በደል ባላደረሱብን ነበር። አሁን ጉዳዩ በቻሪቲ ኮሚሺን ተይዞ ወደ ሕግ በሚገሰግሥበት ሰዓት ከአዲስ አበባ ሲኖዶስ ጳጳሳት አስመጥተው በራሳቸው ፍላጎት የዘጉትን ቤት ያንን ሁሉ ሕዝብ ውጪ አግደው ለመክፈት በከንቱ ለፉ! አቅማቸውን አለማወቃቸው፣ ይግርመኛል። “ለማይረባ አዕምሮ አሳልፎ ሰጣቸው” ነው የሚለው መጽሐፉ (ሮሜ.፩፡፳፰)?፡እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ ስለሚመለከት ሀሳባቸው ከንቱ ሆነባቸው! ከንቱ! የከንቱ ከንቱ!
አባ ተባዩ የሚኖሩበትን አገር ጨርሶ የሚያውቁት አይመስሉም። ዛሬም ኢትዮጵያ የሚኖሩ ነው የሚመስላቸው። የእንግሊዝ ፓስፖርት ይዘው፣ በኢትዮጵያ ሕገ-አራዊት ሊያስተዳድሩን ነው የሚመኙት! ጊዜው በገፋ ቁጥር፣ ወደ አዕምሮአቸው የተመለሰላቸው አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች ምንም የማያዋጣ አዘቅት ውስጥ ገብተው እንደሚዳክሩ ስለገባቸው፣ አንድ በአንድ ጥለዋቸው ሂደዋል። የቀሩት በሙሉ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ወያኔ የደኅንነት አባላት፣ ቀጥሎ፣ አሽቃባጮቻቸው፣ ከዚያም አሸሻ ገዳሜን እንጂ ምንም የማያውቁትን በጣት የሚቆጥሩ ወጣቶች ነው። አሁን ትግሉ፣ እነሱ በፊት ሊያስቀምጡት እንደሞከሩት፣ ቤተክርስቲያኗን ኮምፓኒ የማድረግና ያለማድረግ ሳይሆን፣ ቤተክርስቲያኗን ለወያኔ ከማስረከብና ካለማስረከብ ሁኗል። “ሕጋዊ ሲኖዶስ!” የሚሉት ነገር አላቸው። ደንቄም! ወያኔ እንደፈለገው የሚያሽከረክረው፣ የአዲስ አበባውን ማለታቸው ነው። እነዚህ አሁን “አለንልህ” የሚሏቸው ጳጳሳት፣ ከአባ ተባዩ ጀርባ የሚሏቸውን ቢሰሙ፣ በጠላቶቻቸው መከበባቸውን ማን በነገራቸው! አንዱ የተከበሩ አቡን፣ “አይ ግርማን ተወው! ለዚህ ያደረሰን እሱ መሆኑን መች አጣነው! ብቻ መጀመሪያ ቤቱን እንረከብና፣ እሱን የምናደረግውን እኛ እናውቃለን” ሲሉ ተደምጠዋል። በሬ ካራጁ ጋር ይውላል አይደል የሚባለው!
የአሁኑ የአባ ተባዩ እንቅስቃሴ የሞት የሽረት መሆኑን ሕዝቡ ተረድቷል። በሕግ ሳይሆን በጉልበት ለመውሰድ የተነሱ ቀማኛ መሆናቸውን አውቆ ሕዝቡ ቅዳሜ በማለዳ ቤተክርስቲያኑን ለመከላከል ሄደ።  ከዝግጅቱ መሀል አንዱ፣ እኛ ዘለን እንዳናልፍ ተከራይተው ያመጡት መክላከያ መሰናክል (barrier) የኛ ልጆች፣ ሄደው በሰንሰለት ግጥም አድረገው ቀስረው ቆልፈውላቸው ስለነበር፣ የአባ ተባዩ ደንገጡሮች ሊያንቀሳቅሱት አልቻሉም። ሌላ ልፋትና ኪሳራ!!! እነሱው የቆለፉትን የመግቢያ በር ሰንሰለት ፖሊስ “ከሕግ ውጭ ነው” በማለት ቆርጠው ቆራርጠው ጣሉላቸው! እዚያ ቤት ዕውር እውሩን እየመራ ገደል ተጎታትተው እየገቡ ነው። ኤድያ! ኪሳራ በኪሳራ! ገና ምን አይታችሁ! እግዚአብሔር የመጨረሻቸውን ያሳየናል። የግቢው በር በዚህ አኳኋን ሲከፈትለት፣ ሕዝቡ ግር ብሎ ገባ። ይኸኔ የአባ ተባዩ ዓይን ፍጥጥ ጥርስ ግጥጥ አለች! በሰው ብዛት አጠፍናቸው። ከገብሬኤል (ለትግሬዎች ተለይቶ የተደራጀ)፣ ከሥላሴ (ትግሬ ላልሆኑ ወዶ ገቦች በመፍቅረ ጳውሎሱ አባ ሙሴ ተመሥርቶ፣ በአባ እንጦስ የተደረጀ) ጸርሀ ጽዮን (ጃማይካ) ቤተክርስቲያኖች አባላት እስኪደርሱላቸው ድረስ ያን ሁሉ ሕዝብ ምንም ማድረግ ስለማይችሉ፣ እንደተተኰሰባት ድኵላ ደንግጠው፣ ጥግ ጥጋቸውን ይዘው ቆሙ። ሕዝብ ተመመ። መዝሙር ተዘመረ። አባ ተባዩ ፓሊሶችን አግባብተው ከጎናቸው ለማሰለፍ ሞከሩ። እኛን ወንጀለኞች ለማስመሰል፣ እንሱ ጨዋዎችን ለመምሰል ሞከሩ። ፓሊስ ያመናጭቀን ያስፈራራን ገባ! “እሱን ዲሲ” ነበር ያለችው ሴትዮዋ! በስደት ኖሮአችን እስከምን ፖሊሶቹን ልንጋፋ እንደምንችል ጠንቅቀን እናውቃለን። አባ ተባዩ ቪካሬጅ (ሕልፊኝ በሉት) ሲገቡ ሕዝቡ ተከትሎ ሊገባ ሞከረ። ፖሊስ ተሟሙቶ አገደን። ፖሊስ ከዚያ ውጡ እያለ ያዘናል።እኛ ደግሞ ያ ቤተክርስቲያናችን ነው የተም ንቅንቅ አንልም ብለን ተጋተርን። አባ ተባዩ ቀማኛ መነኵሴና እና ተከታዮቹ ከዚያ ሲወጡ እኛም ትዕዛዙን አክብረን እንደምንወጣ እቅጩን ነገርናቸው።
አባ ተባዩ እራሳቸው መጥተው በሩን መክፈት ፈርተው ይመስላል፤ ፖሊስ መግቢያ በሩን ሊቆጣጠርና ከፍቶ ጳጳሳቱን ሊያስገባ ተጠጋ። ነገሩ ገባን። ክርስቲያን እህቶቻችን ከዚህ በፊት አይቼው በማላውቅ ጀግንነት ግልገሏን ከነጣቂ ጅብ ልተከላከል እንደምትወረወር አራስ ነብር ተንደርድረው በሩ ላይ ተረባረቡ። ፖሊስ ቢጋፋ ቢያሽቀነጥር፣ ቢጮህ፣ ኃይል ቢጠቀም ምን ቢል እህቶቻችንን አልቻለም። የእህቶቻችንን ጀግንነት ያየን ወንዶች ዘለን ገባንላቸው። መሬት ላይ ቁጭ አልን። ፖሊስ እየተግተለተለ ቢመጣ፣ ወይ ፍንክች የአባ ብለዋ ልጅ! የእግዚአብሔር ኃይል ተጨምሮልን በምን ሊቋቋሙን! ኃይል የእግዚአብሔር ነው! የአባ ተባዩ ደንገጡሮች፣ ፖሊሶች እያነቁ ይወስዱናል ብሎ ከመመኘት በስተቀር፣ ምንም ማድረግ አልቻሉም! በእግዚአብሔር ኃይል ሁሉንም ቻልነው። ፓሊሶቹን በጥሞና አነጋገርናቸው። ያቺን ቤተክርስቲያን አባ ተባዩ በአቀዷት መሠረት ላትከፈት፣ ሕግ ሳንተላለፍ በሕይወታችን የቆረጥን መሆናችንን ሲገነዘቡ፣ “በቃ! በቃ! ቤተክርስቲያኗ በምንም ዓይነት በዚህ ሁኔታ ዛሬ አትከፈትም” ብለው ወሰኑ። “እናንተ ብቻ ሂዱልን” አሉን። እኛ የምንሄደው፣ አባ ተባዩ እራሳቸው፣ ከሥላሴ፣ ከገብርኤል፣ ከጸርአ ጽዮን (የጀመይካዎቹ) ቤተክርስቲያናት የወረሩን ወያኔና የወያኔ ወኪሎች፣ እና የአባ ተባዩ ደንገጡሮች እንዳሉ ካልወጡ አንሂድም አልን። አባ ተባዩ ወጥተው የሚሂዱት፣ “እናንተ ስትወጡ ነው” ተባልን።
በዚህ ክርክር ላይ አንዳለን አንድ ነገር ተከሰተ። ዞር ብለን ስናይ አባ ተባዩ ጠረንገሎ ጠረንገሎ የመሰሉ የደኅንነት ጥበቃ ዘበኞችን በሺህ የሚቆጠር ፓውንድ ከፍለው፣ ቀጥረው አምጥተው አገኘናቸው። ጉድ! ጉድ! “ጉድና ጅራት”  ከበስተኋል ነው የሚባለው? ዞር ብለን ስናያቸው፣ ሰዎች ሳይሆን ጉማሬ ጉማሬዎች ይመስል የሚንጎማለሉ መሰሉን። አንዳንዶቻችን “እነዚህ ወጠምሾች ቅዱስ ሚካሄል፣ ቅዱስ ገብሬል፣ ቅዱስ ሩፋኤል ወይስ ሌሎች ከአደጋ የሚከላከሉ መለዕክት ይሁኑ?” ስንል፣ በስላቅ ለጠየቅነው ጠያቄ፣ ሌሎች “አይ መላዕክት አይመስሉም፣ ክንፍ የላቸውም” ብለው ቀለዱባቸው! በአማርኛ ስለምናወራ፣ ፖሊስ ሳቃችን አልገባብውም። አባ ተባዩ፣ ዞሮባቸዋል ማለት ነው። ጡንቻው ያበጠ፣ ልቡ ያበጠበት የእግዚአብሔርን ልጆች አ-ያ-ሸ-ን-ፍ-ም! ኩርርርር!!!! አይሰሙም እንዴ! አሁን በሞቴ፣ እስከ አፍጢሙ የታጠቀ ፖሊስ ያልቻለንን እነዚህ ወጠምሾች ይችሉናል ብለው ነው፣ ገንዘባቸውን ያባከኑት? ከኛ ጋ የቆመው ከእነሱ ጋ ከቆመው የበለጠ ኃይለኛ አምላክ ነው (1ኛው የዮሐንስ መልዕክት፣ ም4 ቁ4)። ተጨማሪ ኪሳራ! ቀድሞውን መቸ በእግዚአብሔር መላዕክት ይመኩና። እሳቸው የሚመኩት፣ አይዘዎት በሚለው የወያኔ እምባሲ፣ እፍኝ በማይሞሉ ደንገጡሮቻቸውና ገና ተበልቶ ባላለቀው የጉርምስና ጉልበታቸው ነው። ውርደታቸውም እሱ ነው። አዙሮ አለማየት! ሰው መናቅ! ኢትዮጵያ ውስጥ ብንሆን እኚህ ሰውዬ በመትረየስ አስረሽነው ጨርሰውን ነበር። አሁንስ ቢሆን ጠብ ያለሽ በዳቦ በሚሉ፣ ምንም ዓይነት የክርስትና ጸባይ በማይታይባቸው ወጣቶች ካሰደቡን፣ ካስደበደቡን ምን ቀራቸው? እግዚአብሔር ብቻ እኚህን ከራስፑቲን የባሱ አመጸኛ ሰው ይገላግለን። የሰው ፍርድ ዋጋ የለውም!
ከፖሊስ ጋ ስንጋፈጥ ብዙ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል። ወንድማችን አሥራት ይግለጡ በአንድ የወያኔ ቅጥረኛ ተመታ!። በኋላ ላይ እመጣበታለሁ። ፖሊሶች “ውጡ እያሉ” ሲገፈታትሩን፣  “ቢያንስ ቢያንስ እነዚያ ከሌላ ቦታ የወረሩን እና ደንገጦሩቹ ይውጡ ብለን” ለመብታችን ተሟገትን። አሁንም ፖሊስ በዘዴም ቢሆን አታሎ ከግቢው ሊያስወጣን ስላልቻለ፣ የአባ ተባዩን ጦር ከነወያኔ ወኪሎቻቸው ጋር ሲያስወጣ እኛም ሕግ አክብረን ከግቢው ወጣንላቸው። ወደ ቤት እንድንሄድ ፖሊስ ያላደረገው ጥረት አልነበርም። የማይቻል መሆኑን ነገርነው። አባ ተባዩ እንደኪራይ ቤት ውልቅ ብለው ጥርግ ሲሉ በዓይናችን ካላየን ላንነቃነቅ ዕቅጩን ነገርናቸው።
ቅዳሜ ዕለት፣ ያንን ሁሉ ተጋድሎ አድርገን፣ ከመውጣታችን በፊት፣ ለትውልድ የሚተላለፍ፣ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ናቸው፣ ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት የማይታይባቸው ወንጀለኞች የሠሩትን እዚህ መመዝግብና ማስተላለፍ አስፈላጊ ነው። አዲስ አባባ ላይ፣ ወጣቶች ተደራጅተው፣ ወያኔን ይጋፈጣሉ። ይታሰራሉ፣ ይወድቃሉ ይነሳሉ። የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ የሕዝብ ደጀን፣ የሕዝብ ተከላካዮች ናቸው። ወያኔ አግዓዚ የተባለውን ጦር፣ ወይ ፌዴራል ፖሊስ የተባልውን ኃይል ተጠቅሞ ሕዝባችንን ሲጨፈጭፍ፣ የመጀመሪያ ገፈቱን ቀማሾች፣ የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው። ዛሬ ጎጃምና ጎንደርም ያሉ ወጣቶች፣ወያኔን ለመጋፈጥ፣ የአማራ ወጣቶች መከላከያ ኃይል ፈጥረው በረሀ ገብተው በመፋለም ላይ ናቸው። በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶቻችን ወያኔን እየተጋፈጡ ታሪክ ሰርተው በማለፍ ላይ ናቸው! ለንደን ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ወጣቶች ግን ኢትዮጵያን የሚወዱትን ሰዎች እየተተናኮሉ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜ ቱባ፣ ቱባ የወያኔ ባለሥልጣናት መቀሌ ሳይሆን ቨርጂኒያና ዋሽንግተን ለመመካከር ተሰብስበዋል። እዚያም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እየተጋፈጧቸው ነው።  ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ ነፍሰ ገዳዩን ወያኔ ስብሐት ነጋን ስታርባክስ ቁጭ ብሎ በነጻነት ቡና ሲጠጣ አግኝቶት ተጋፍጦታል[2]። መስፍን የተባለ ሌላ ኢትዮጵያዊ፣ ቨርጂኒያ ውስጥ ስብሀትን አግኝቶ ሲጋፈጠው[3]፣ ከስብሀት ጋር የነበረ ሌላ ወያኔ፣ መስፍንን መትቶት ሲያመልጥ ሁለት መኪናዎች ገጭቶ በማምለጡ ይኽ ጽሑፍ ሲጻፍ ፖሊሶች ለመያዝ እያሳደዱት ነው። ሌላ ቦታ ያሉት የኢትዮጵያ ወጣቶች እንዲህ ታሪክ እየሰሩ ነው። በተለይ ኖርዌይ ያሉት ወንድሞቼ ሁሌ ያኮሩኛል! ለንደን ግን ታሪኩ በሌላ ተቀይሯል። እናንተ ከወያኔ ጎን የቆማችሁ ወጣቶች! ለንደንን አታሰድቡ። ብትሞቱ ይሻላችኋል!
አብዛኞቹ ወጣቶች፣ ልክ አዲስ አበባ እንደሚደረገው ከወያኔ ነጣቂዎች ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው፣ ከሕዝቡ ጎን ተሰልፈው መስዋዕትነት እየከፍሉ ነው። ከ20 እስከ ሰላሳ የሚደርሱ ወጣቶች ግን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ወያኔ ጎን ተሰልፈው ይኸ ነው የማይባል ግፍ በወገኖቻቸው ላይ እያደረሱ ይገኛሉ። በእሑዱና በቅደሜው ትንቅንቅ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱብን የቻሉት እነዚህ ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ የወያኔ ቅልብ ወጣቶች ናቸው። ከዚህ በፊት፣ ከሀዲውን አስመሳይ መነኩሴ በቃል ከማጋለጥ አልፈን በእንቁላል እስከመደብደብ ደርሰን ነበር። ግቢውንም እንዳይገቡ ያገትንበት ጊዜ ነበር። እነዚህን ወጣቶች በምን እንደመረዟቸው ሳናውቅ አምጥተው ሲያፈሱብን፣ ከነሱ ጋር ስንተናነቅ ፖሊስ ልቅም አድርጎ ዘብጥያ እንዳያወርዳቸው በመሳሳት፣ ወይ ወደ አገር ቤት አንቆ እንዳይመልሳቸው በመስጋት፣ ወገናዊነት አስገድዶን፣ ተመካክረን እነሱን የሚቀሰቅስ ምንም እርምጃ ላለመውሰድ፣ ብዙ ወንድሞችና እህቶች እየተቃወሙን አካሄዳችንን አለስልሰን ሕጉን ብቻ ተከትለን ነበር። “ፈሩን” ብለው ጨፈሩ! ይሁን አልን። የልብ ልብ ተሰማቸው። መስማት አይፈልጉም። ዘፈናቸው አንድ ናት። አባቶችን አዋረዳችሁ፣ ቤተክርስቲያን ደፈራችሁ እያሉ መንተክተክ ነው። እራሳቸውን እንጂ ሌላውን አይሰሙም። ታገስናቸው፣ ታገስናቸው፣ ታገስናቸው። በውስጣቸው ያሉ ወያኔዎች አየሉ።
እዚህ ፎቶግራም ላይ የተነሱት፣ “ለአስመሳዩ መነኩሴ አባታቸው” ለመሞት የማሉ ናቸው። ይኸን ፎቶ ለማስታወሻ ተነስተው በፌስ ቡክ የለጠፉት ለኔ መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር። መለዕክቱ ደርሶኛል፣ አመሰግናቸዋለሁ። እሲቲ ይኸን ፎቶግራም ራስፑቲን ከተባለው የአባ ተባዩ ብጤ ሀሳዊ መነኵሴ ከአሻቃባጮቹ ጋር ከተነሳው ጋር እናወዳድር። ከጊዜው መራራቅ በስተቀር ምን ልዩነት አለው? እነዚህን ወጣቶች የሚሠሩት በደል የሚያስጠይቃቸው ነው፣ እያልን ለማስረዳትም ብንሞክር፣ “እናንተ ፖሊቲከኞች ናችሁ፣ ደርግ ናችሁ፣ ግንቦት 7 ናችሁ፣ አንድነት ናችሁ …” እያሉ ወያኒኛ እየተናገሩ፣ ሊያዳምጡን አልፈለጉም። ተውናቸው። ከዓርብ ማታ ቅዳሜና እሑድ ያደረሱት ጉዳት ግን በምንም ዓይነት ይቅር የማይባልላቸው፣ በየትኛው መድረክ ልንፋረዳቸው የሚገባን በደል ፈጽመውብናል።
በለንደን ውስጥ ላለፉት ብዙ ዓመታት በቆራጥነት ወያኔን መጋፈጣችን ይታወሳል። በነዚህ ጊዜያት በሙሉ አንድ በዓለም ድምጹን ያላስተጋባንለት ግንባር ቀደም ሁኖ ትግሉን ከማገዝ አልፎ እስከመምራት የደረሰ አሥራት የሚባል መመኪያ ወንድም አለን። አሥራት ጤንነቱ የተሟላለት አይደለም። ለመራመድ እንኳን በምርኩዝ ተደግፎ በግድ ነው የሚንቀሳቀው። ዳሩ ግን ማናችንም ጤንነታችን የተሟላልን የአሥራትን ያህል ለዚህ ትግል አስተዋጽኦ አላደረግንም። ደፍሮ “እኔ ከአሥራት በላይ አድርጌአለሁ” የሚልም ከኔ ጀምሮ አይኖርም። የትግላችን ሞተርና አንቀሳቃሽ እሱ በመሆኑ፣ አንዳንዴ ሕመሙን ጨርሶ እንረሳለን። እንዲያው አንባቢዎቼ ፍቀዱልኝና፣ ስለዚህ ጀግና በሕይወቱ እያለ ትንሽ ልበል። ይቅርታ አሥራቴ!
አሥራት ልዩ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። ገና በወጣትነቱ ጀምሮ በረሀ ገብቶ ደርግን የተፋለመ ጀግና ነው። ከዕውቁ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ምሑር፣ ከነዶር ጌታቸው በጋሻ ጋር ሁኖ ለወገኑ መብት ደሙን አፍስሷል። የኢትዮጵያ ጉዳይ እስከዛሬ የሚያንሰፈስፈው ጀግና ነው። አሁን እንኳን ጤንነቱ እንደዚያ ተቃውሶበት፣ አንዲት ቀን ሳያርፍ፣ ባለችው መኪና የቤንዚን እንኳን ሳንከፍልለት የትግል መኪና አድርጓት፣ ሰላማዊ ሰልፍ ስናደርግ እንደልባችን የምናዘው ዕቃ አመላላሽ፣ እንግዳ ሲመጣብን አድራሽ፣ እኛ ስንዘናጋ፣ አስተዋሽ፣ ስንሰንፍ ቀስቃሽ፣ ወደ አውሮፓ ከተሞች ለሰልፍ ወይም ልስብሰባ ከተነሳን፣ በመኪናው የቻለውን ጭኖ አድርሶ መላሽ፣ ከጠዋት እስከማታ ለኢትዮጵያ ጉዳይ እንደባከነ ነው የኖረው። ዝግጅቶች ሁሉ ላይ አሥራት የሌለበት አልነበረም፣ የለም፣ አይኖርም። በዚህ አንቱ በሚባልበት ዕድሜው እንደ ልጅ ነው የሚታዘዘን። ኢትዮጵያዊ የተባለ ስብሰባ ላይ አንድም ቀን ሳይቀር፣ በጣም ጠቃሚ ሀሳቦችን እያፈለቀ እየመራንና እየመከረን የሎንደንን ትግል አንዲት ቀን እንዳትቋረጥ የረዳን፣ ሳይማረርብን እዚህ ያደረሰን ወንድም ነው። አንድም ቀን እንኳን እኛ ስንበላ ስንጠጣ አብሮን ቁጭ ብሎ ተዝናንቶ አያውቅም። ሁሌ ሥራ ነው። ድፍን ለንደን ኢትዮጵያው (ሲቀነስ ወያኔና ጀሌአቸው) የሚኮራበት ወንድም ነው። እነዚህ ወያኔዎች የዘረገፈብን ሰላዮቹና የጠለፏቸው የዋሆች አድብተው አድብተው ጠብቀው ቅዳሜ ዕለት ምርኵዙን ተደግፎ ከቆመበት ሳያስበው ዓይናችን እያየ እግሩን ከሥር በኃይል ሲመቱት ወደቀ እና እራሱን ተመታ። መቺው ጨካኝ አረመኔ ከደጊቱ ምድር ከትግራይ የተገኘ ወጣት ነው። እኛ ተደናግጠን ወንድማችንን ለማንሳት እየተሯሯጥን ስንጯጮኽ፣ ልክ አንበሳ ታግለው እንደጣሉ (ዕውነቱን እንናገር ከተባለ፣ አሥራት የአንበሳም አንበሳ ነው) ዙሪያውን ከበው በሳቅ ሲያሽካኩ ስናያቸው፣ ፖሊስ በቦታው ባይኖርና እየገፈታተረ ባያቆመን አንድ በአንድ ጎሮሮ ለጎሮሮ በተናነቅን ነበር። እነሱ እያፌዙ፣ እኛም አንጀታችንን እያረረ ዝም አልናቸው። አሥራት ሆስፒታል ተወስዶ ከሁለት ቀን ሕክምና በኋላ ተርፎልናል።
ይኸ ሁሉ ሆኖ ከግቢው ለመውጣት የተስማማነው፣ ፖሊስ አባ ተባዩን ጨካኝ ሰው  እንደሚያስወጣ ቃል ገብተውልን ነበር። ዳሩ ምን ይሆናል ፖሊሶች ቃላቸውን አጠፉ። ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ አልወጡም። የባሰውኑ፣ በጓሮ በር አቡነ ገብርኤልን፣ አቡነ እንጦስን፣ አቡነ ያዕቆብን፣ ተወልደ ወልደማርያም የተባለውን የወያኔ የአውሮፓ የሀይማኖት ሹም አስገብተው እርፍ አሉ! በወያኔ መከበባችን አወቅን። ልንሄድ የነበርን በሙሉ ተመልሰን ፍጥጫው ቀጠለ። ከግቢ ውጪ ሁለቱም ቡድን ቁመናል። ቀሚስ በማስረዘማቸው፣ ፖሊስ አከበራቸው መሰለኝ፣ ወጥተን ቡራኬ ሰጥተን እንሂድ አሉ ተባልን። አብዛኛው “አንፈልጋቸውም። ከነሱ የሚመጣ ቡራኬ በአፍንጫችን ይውጣ። በመጡበት አኳኋን ይመለሱ” ስንል፣ ከየወያኔ ቤተክርስቲያናት የመጡ በአንደኛው ወገን የቆሙ የወያኔ አገልጋዮች እና የተገዙ የአባ ተባዩ ደንገጦሮች፣ አባቶቻቸው፣ ፓብልኪ በሆነው ሥፍራ ቁመው ቡራኬ እንዲሰጧቸው፣ የመናገርና የመስማት መብታቸው እንዲከበር ጠይቁ። የፈረደበት ፖሊስ ሆዬ፣ እነሱን አስገብቶ እኛን ውጪ አስቀረን። በሚያስገርም ፍጥነት ያኔ በሙሉ እንዳለን ዋናው መንገድ ላይ ወጥተን ተነጥፈን። ትራፊክ ቆመ። የለንደኗ በተርሲ መንደር ቀውጢ ሆነች። ቢቢሲ ሬዲዮ፣ የአካባቢው ሬዲዮ በዚያ አትለፉ የሚል መልዕክት ከዳር እስከዳር አስተጋባ። ፖሊስ በገዛ እጁ ጭንቀት ውስጥ ገባ። ምድር ተናወጠች። ፖሊስ እኛን ለማንሳት ያ ሁሉ ኃይላቸው ባለመቻሉ በሩን ከፍተው ወደግቢ እንድንገባ ልመና ገቡ። መጨረሻ ላይ ተነስተን ገብተን ልንቀላቀላቸውና ጉዳቸውን ልናፈላ ስንሄድ ፖሊስ ግድግዳ ሠርቶ ጳጳሳት ተብዬዎቹ ጋ እንዳንደርስ ከዓይን ሰወር ባለ ቦታ ቁመው እርኩሶቻቸውን እንዲባርኩ ተደረጉ። ፓሊሶችን ገፍቶ ማለፍ ሕግ መተላለፍ ስለሆነ ቁመን ጮኸታችንን አቀለጥነው። “ሌባ ሌባ” በጩኸት ቦታውን ስናናውጠው፣ አንዲት እህት ከመካከላችን ድምጿን ከፍ አድርጋ ሕዝቡን “እንዴ ነውር ነው። ትክክል አይደላችሁም”። ምንም ቢሆን አባቶች ናቸውና ሌቦች አትበሏቸው” አለች። ታዲያ ምን እንበላቸው ብለን መልሰን ስንጮኽባት፣ አሁንም ድምጿን ከፍ አድርጋ “መነኮሳት አባቶች! ሂዱና ልጆቻችሁን አሳድጉ!” እየለች መጮኽ ጀመረች። ተቀብለን አስተጋባን። ግማሾቻችን ግን ሆዳችንን ይዘን ሳቃችንን አቀለጥነው። የነሱ ቡራኬ የኛን ድምጽ አልፎ አልተሰማም። ቡራኬ አትበሉት! የድፍረታቸው ድፍረት፣ የእግዛብሔርን የሕዝብ ጥያቄ የመናቃቸው ድርጊት፣ ለውርደት ዳረጋቸው። ወደመጡበት ተመለሱ! ቅዳሜ በዚህ ዓይነት ኢትዮጵያዊ ቆራጥነትና ጀግንነት አለፈ። ነገም እኛው ነን። በእግዚአብሔር ኃይል እንደግመዋለን!
ድንገት በነጋታው ተጨማሪ ውርድት ለመከናነብ ሽተው አሁንም “እንክፈት” ብለው ይሞክሩ እንደሆን በማሰብ እሑድ ዕለት ሕዝቡ ከቅዳሜው ሁለት እጥፍ ግልብጥ ብሎ ቤተክርስቲያን ከቸች አለ። የግቢውን በር ፖሊሶች ዘግተውት ጠበቁ። የአባ ተባዩ ልጆች (30 ገደማ ቢሞሉ ነው)፣ የዓይናውጣው መነኵሴ ነኝ ባይ የቅሌት ዘበኛ ሁነው ጠበቁን። ስላሴም፥ ገብርኤልም፣ ጸርአ ጽዮንም ተስፋ ቆርጠው ዝር አላሏትም። ሕዝቡም ጋጠወጦቹም ወደ ግቢው ገብተው እነሱም የድሮዋን ኮርነራቸውን ይዘው፣ ሕዝቡም ከፊለፊት ሰፈው ሚዳ ላይ ተንጣሎ፣ ዝናም ዶፉን እያወረደ ያለምንም ግርግር እንዲጸልይ ከፖሊሶቹ ጋር ተደራደሩ። ፖሊስም ነገሩን አውጥተው፣ አውርደው፣ በቂ ዝግጅት አድርገው፣ በኛም በኩል ያሉት ካህናት ገብተው፣ አባ ተባዩና አፍቅሪ ወያኔ ካኅናት ገብተው የየግል ጸሎት አለቀ። በተገባው ቃል መሠረት፣ ጸሎቱ አልቆ ሕዝቡ በሰላም ከግቢው መውጣት ጀመረ። ፖሊስ የኛ ወገን ብዛት እና ቆራጥ የትግል ዘዴአችን ስላሳሰበው፣ በኛ ላይ ብቻ ነበር ትኩረቱ። የአባ ተባዩን ውሪዎች ከምንም አልቆጠራቸውም።
እንሱ ግን እኩይ ዕቅድ ነበራቸው። እነዚያው አሳፋሪ በጣት የሚቆጠሩ ወጣቶች ተብዬዎች ሳይታሰብ ዘለው ከሕዝቡ መሃል አንዳንድ ሰው ላይ ሠፈሩ! በዚህ አጋጣሚ፣ ወንድማችንን፣ ገጣሚና ጸረ-ወያኔ አክቲቪስቱን፣ ጌታቸው ሙላቱን (የአያልነህ ሙላት ታናሽ ወንድም – አንዳንድ ግጥሞቹን በራሱ ፌስ ቡክ የግል ድረ-ገጽ https://www.facebook.com/Getachewmulatu?hc_location=streamማየት የቻላል) ሳያስበው፣ ማንኛውም ማጅራት መቺ  እንደሚያደርገው አሸምቀው ፊቱን ባልታወቀ ነገር መትተውት ደሙን አፈሰሱት። በፊቱኑ ዕቅደ አውጥተው ኑሮ፣ የተወሰኑት ሆን ብለው ግብግብ ሲፈጥሩ ፖሊሶቹ ወደአንድ አቅጣጫ ሲመለከቱ፣ ሊሎቹ የዚህን ትግል መሪዎች ናቸው የሚሏቸውን ለማጥቃት መንቀሳቀስ ጀመሩ። አንድ የትግሉን ዋና መሪ አዛውንትን ሰባት ሆነው ከበቧቸው። እቅዳቸው አዛውንቶችን እግር እግራቸውን መውጋት እንደሆነ አውቀነው ስለነበር ለአንዳንድ ሰዎች አስጠንቅቀን ነበር። አዛውንቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተከላከሉ። አንደኛው እንደምንም በዕቅዳቸው መሠረት እግራቸውን ለመምታት ሞከረ። እሳቸው ግን በሚያስደንቅ አኳኋን የተሰነዘረባቸውን ሲመክቱ፣ አንዱ እሳቸውን እመታለሁ ብሎ የሰነዘረው ኃይለኛ ምት፣ ጓደኛውን አጉኖት ሰማይ አድርሶት አፈረጠው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሊደርስላቸው ቢሞክር ፓሊስ ገትሮ ያዘው። ግን እየጮኹ ወደ ተከበቡት አዛውንት ሲያመለክት፣ አንድ ጎበዝ ፖሊስ ዘሎ ገብቶ አዛውንቱን ከመሀል ጎትቶ አወጣቸውና እነዚያን ሲምቢሮ-ሲምቢሮ የመሳሰሉ ጨበሬውችን በታተናቸው። ፖሊስ ታክቲካቸው ገብቶት እኛን በዓይነ ቆራኛ እያየን እነሱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አተኮረ። ይኸኔ ነበር ዕቅዳቸው መክሸፉን ሲያቁ ውሪዎቹ ያበዱት። ሕዝቡና እነሱ መሀል ፖሊሶች አሉ፡፤ ድብድቡ አልተሳካላቸውም። እንዳበዱ ውሾች ጮኹ። ፖሊሶቹ ላይ ጉልበታቸውን ሊሞክሩ ወሰኑ። አንዱ ዱሩዬ ሙት ሲለው ዘሎ አንዱን ፖሊስ ረገጠው። ይኸኔ እልሁ ያለቀ ፖሊስ አንስቶት መሬት ላይ ፈጠፈጠው። ስድስት ገደማ ሁነው እንደቅሪላ ቀጠቀጡት! እራሱን በጉልበታቸው ከምድር አጣበቁትና በካቴና አሰሩት። ከትግራይ ሰልጥኖ የመጣው የወያኔ ቅጥረኛ የመጀመሪያ የፖሊስ ሰለባ ሆነ። መነሳትም አልቻለም። በካቴና ጠፍረው ወዲያ ሲወስዱት፣ ሌሎቹ አብሾ እንደጠጣ ወይም ዕጸ ፋርስ አጢሶ አንዳበደ ፌንጣ መዝለል ጀምሩ። ፖሊሶቹ ሊያስትግሷቸው ቢሞክሩ፣ እኛ ባፈለው ቀን ጥያቄአችንን ለማስከበር የተጠቀምነውን ታክቲክ ኮርጀው፣ ያለምንም ምክንያት መንገድ ላይ ተኙ። አንደኛ በቁጥር በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ፖሊስ እያንዳንዷን ድመት ግልገሏን በአንገት ቆዳ አንጠልጥላ እንደምትሄድ አንጠልጥለው ሊወስዷቸው ይችላሉ። ሁለተኛ የሚያቀርቡት ጥያቄ አልነበረም። ሶስተኛ መንገዱን ፖሊስ ቀድሞውኑ ዘግቶት ስለነበረ፣ መንገድ አስዘግተው ቀውጢ መፍጠር የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም። እያንዳንዷን ፌንጣ ፖሊስ በአንገት እያንጠለጠለ አነሳ። ያ ሁሉ ሲሆን፣ አባ ተባዩና አንድ የቀሰሰ ሰይጣን ጉዳቸውን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ከሩቅ ይቀርጹ ነበር። እንግዲህ፣ እነዚህን ጅሎች፣ በሚመጣው እሁድ ሲሰበሰቡ፣ አባ ተባዩ “እናንተ ሰማዕታት ናችሁ” ብለው ለመስበክ አርዕስት አገኙ። ለሌላ ዙር አመጽ እንዲዘጋጁ ለመቀስቀስ ቪዲዮውን ይጠቀሙበት ይሆናል። ተመልከቱልንማ! ዕውነተኛ መንኵሴ በሱ ምክንያት አንዲት ነፍስ እንዳትወድቅ፣ ሱባኤ ይገባል። አንድ ሰው እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ያደርጋል። ካልሆነ፣ እያለቀሰ፣ አምላኩን ይቅርታ እየለመነ ወደ ወደ ገዳሙ ይመለሳል። የኛ የለንደኑ የቀበሮ ባህታዊ ግን፣ “በሉ! ተሟሟሙት! በርቱ!” እያለ ምንም የማያውቁትን እምቦቅቅላ ወጣቶችን ለመስዋትነት ያዘጋጃል! ኧረ የትኛው ገዳም ነው እንዲህ ዓይነቱን አጭበርባሪ፣ ግብረ አልባ ሰው ሳይበቃ ያመነኰሰ? መነኵሴ እንዲህ ነው እንዴ! አሁንም ቢሆን፣ የወያኔ ምልምሎቹ ሰላዮች፣ ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹን አጋፍጠው ሹልክ ብለው አምለጠዋል።
ፖሊስ በዚህ አኳኋን ሁኔታዎቹን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ፣ ሕዝቡ ወደየመጣበት ተመለሰ። ዕለቱ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን ከናይጄሪያ ጋር የሚጋጠምበት ዕለት ስለነበረ፣ አለባቸው ደሳለኝ የሚባል የወጣለት ፎቶ ጆርናሊስትና አንድ ቁጥር የወያኔ ተፋላሚ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ሰብሳቢ ወንድማችን፣ ሁኔታውን በተርሲ ለታሪክ ሲቀርጽ ውሎ፣ ከጓደኞቹ ጋር ጨዋታውን ለመከታተል ማራቶን ሬስቶራንት ሄደ። እነዚያ መሠርይ የወያኔ ቅጥረኞች ተከታተሉት። እንግዶቹ ምሳ አዘው እንደተቀመጡ፣ ጋጠ ወጦቹ ተከታትለው ገብተው፣ አለባቸውን ተጋፈጡት። እየሰደቡት ለመማታት ሲጋበዙ፣ ምን እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው። ቪዲዮ አንስቶአቸው የለጠፈውን ከድረ-ገጽ እንዲያነሳ ነገሩት። ከይትኛው ድረ-ገጽ ነው ብሎ ቢጠይቃቸው፣ መልስ አጡ እና ወደ ተራ ስድብ ወረዱ። ይኸኔ የሬስቶራንቱ በለቤት መጥቶ በጥሞና ደንበኞቹን እንዳይረብሹ ለመናቸው። ወደሱ ዙረው፣ እሱም ተባባሪ በመሆኑ እንደሚዞሩበት ሲጮኹበት ትቶአቸው ወደ ውስጥ ገብቶ ፖሊስ መጥራት ጀመረ። እነሱም ምግብ ቤቱን ለቀው እየወጡ ሳለ፣ የበሩን መስታወት በብረት ቦክስ ቡጢ ሰበሩት። ፖሊስ መጥቶ ብዙም ሳይርቁ ሶስቱን ሌጊዜው ማገት ቻለ። የዚህ ሁሉ ድራማ video፣ ዓርብ ኦክቶበር 18 ይለቀቃል። ልጆቹንም ዓለም ያያቸዋል። ልጆቻችሁ ብቻ እንዳይሆኑ ኢትዮጵያ የምትኖሩ አንባቢዎቼ፣ አጥብቃችሁ ጸልዩ!
የተቀሩት ጥቂት ዱሩዬዎች የሄዱት፣ በቀጥታ ወደአዲስ አበባ ሬስቶራንት እንደነበረና፣ ባለቤቱን ለመተናኰል እንደሞከሩ መረጃ ደርሶናል። ኧረ ምን ዓይነቶቹ ጉዶች ናቸው?
እስካሁን ፖሊስ 9 ከአባ ተባዮ ወጣቶች ከአንዱ ጥጋበኛ በስተቀር አስሮ ፈትቷል።የፈታቸውንም በሚፈለጉ ጊዜ ሊቀርቡ መዝግቦአቸው ለቆአቸዋል። ከኛ መሀል አንድም ሰው አልተያዘም። ሰላማዊ ነና! ያ የሚያሳየው፣ አባ ተባዩ የጠነሰሱት ሴራ አድጎ ተመንድጎ፣ ሕግ እንደማያዋጣቸው ሲረዱ፣ ወደ አመጽና ወንጀል አምጥቀውታል። ለደረሰው ጥፋት፣ ለልጆቹ ጉዳት፣ ተጠያቂው አባ ተባዩ ስግብግብ ሰው ናቸው። ፖሊሶቹ ትላንት ከገረማቸው ትልቁ ነገር አንዱ፣ ሕዝባችን በቁጥር እነሱን በብዙ እጥፍ ሲያጥፍ፣ አንዳችም ነገር ለማድረግ አለመንቀሳቀሱና፣ ፖሊሶቹን አለማስቸግሩ ነው። አንዲት ሴት ፖሊስ ለሌላው ፖሊስ ስትናገር፣ እነዚህ በጣም ዲሲፕሊን ያላቸው ሲሆኑ፣ እነዚያ በጣት የተቆጠሩ ወጣቶች ግን እንዲህ ማስቸገራቸው የሚግርም ነው ብላ ስትናገር ተሰምታለች። እንግዲህ፣ የአባ ተባዩ ጦር ሥነ-ሥርዓት የጎደለው መሆኑ በግልጽ በዩኬ ባለሥልጣኖች እየታወቀ መጥቷል። ይኸንን አመጽ ከኋል ሁኖ የሚሸርበው የወያኔ እምባሲ እንደሆነ ለአንዲት ደቂቃ እንኳን መዘንጋት የለብንም።
ከ30ዎቹ፣ አብዛኛው ወጣት ዝም ብሎ መናጆ ሲሆን አንቀሳቃሽ ሞተሮቹ ግን የወያኔ ቅጥረኞች ናቸው። ወያኔ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሥራ ፈት ወጣቶችን ለደኅነነት አሰልጥኖ እንዳስመረቃቸው እናውቃለን። በብዙ መቶ የሚቆጠሩትን፣ በተለያየ መልኩ ስደተኛ አስመስሎ ወደ ውጪ በማስወጣት በየዲያስፖራ እንደበተናቸው ብዙ መረጃ በእጃችን ላይ ይገኛል። ይኽ ድርጊቱ በኛ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም በግልጽ እየታወቀ መጥቷል። ወያኔ፣ ሰላዮቹን በግልጽም በስውርም እያሰውጣ ነው። በስውር ወደዚህ አገር የሚያስግባቸው፣ በትምህርት፣ በጉብኝት እያለ እያለ ነው። አንዴ እዚህ ካደረሳቸው በኋላ ፓስፖርታቸውን ደብቆ በመርከብ በሶማሌ ደላሎች ተመርተን መጣን እያሉ እጅ እንዲሰጡ፣ እራሱ ወያኔ ሲያሳድዳቸው እንደነበረ የሚገልጽ ሀሰት ሰነድ ሁሉ እየሰጣቸው፣ በሎንደን አማርኛ፣ “ያስረፍጃቸዋል”። ሌላውና ግልጹ ስደተኛ መስሎ የመውጣቱ መንገድ፣ ከዚያው ከኢትዮጵያ “የኤርትራ ስደተኞች ናቸው” እያስባለ ነው። ለኤርትራውያን ስደተኞች፣ ወደሶስተኛ አገር ”resettlement” የሚባል ፖርግራም አለ። ወያኔ ከእውነተኞቹ ትግራይ ውስጥ በቁጥጥሩ ሥር ከሚገኙት የኤርትራ ስደተኛ ካምፖች፣ የስደተኞች ዕድሉን እየነጠቀ ለሕወሀት የደኅንነት አባሎች እየሰጠ፣ ወደውጪ አስወጥቶ እመሀላችን ሰግስጎአቸዋል። መረጃውን ከኢሳት ሬዲዮ የOctober 9 ፕሮግራም http://ethsat.com/2013/10/09/esat-radio-oct-09-2/ ማግኘት ይችላል። ሲመጡ ለስሙ ኤርትራውያን ናቸው። ትግርኛ (ኤርትራዉያን ኤርትርኛ ይሉታል) የናታቸው ቋንቋ በመሆኑ፣ እንኳን ለውጪው ዜጋ እኛም ወንድሞች እና እህቶቻቸው ልዩነታቸውን አናውቅም። እዚህ ከደረሱ በኋላ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን ብቅ አድርገው ይቀላቀሉናል። ከዚያማ ወጣት ለወጣት መግባባት ቀላል ነው። የእግር ኳሱ አለ፣ ሙዚቃው አለ፣ የምሽት መዝናናቱ አለ፣ ጫት አለ፣ …። የወያኔ ዓላማ፣ እኛ ታላላቆቹ ስደተኞች ሙተን ስናልቅ፣ የሚተኩን አፍቅሪ ወያኔ እንዲሆኑ ልዩ የወደፊት የዲያስፖራ ደጋፊው ዚጎች ለማትረፍ ን እው። ለረጅም ጊዜ ያቀደው ስትራተጂ መሆኑ ነው። ታዲያ የሚያስፈልጋቸውን ጊዜያው ዕርካታ ሁሉ ወያኔ በቀላሉ እያቀረበላቸው፣ ዕወነተኞቹን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ልብ ይሰልባል። በቃ ተገናኝቶ ቸበርቻቻ መምታት ነው። ወያኔ ሲፈልጋቸው፣ ተቀጠሩት መሪነት፣ እዚሁ የተመለመሉት እና ሳያውቁ የተዶሉበትም አብረው ሆ ብለው መዝመት ነው። ለንደን ቤተክርስቲያን ላይ የዘመቱት፣ እኔ በግሌ የማውቃቸው ደህና ከመሀል አገር የመጡ ወጣቶች ሁሉ ተዱለውበታል። በጽሞና ሳነጋግራቸው፣ “እናንተ ፖሊቲከኞች ናችሁ። እኛ ፖሊቲካ አይገባንም። እናንተ የደርግ ባለሥልጣኖች ነበራችሁ፣ እያሉ ወያኔ የጋታቸውን መልሰው ያቀረሹብናል። ስንቶቻችን ከደርግ እንደተፋለምን ስንነግራቸው፣ “ፖሊቲከኞች ቤተክርስቲያናችንን ሊነጥቋት ነው፣ መነኵሴ ደበደቡ ስንባል፣ እንዴት ዝም ብለን እንቀመጣለን ብለን ነው የገባንበት” ይሉናል። እኔ በበኵሌ፣ ለማስረዳትም አልቻልኩም። መዝናናቱ ይቀርባቸዋላ! እድሜ ለአባ ተባዩ፣ አሁንማ በወንጀል የማንታወቅ ኢትዮጵያውያና ወንጌል ሳይሆን ወንጀል መታወቂያችን ሁኗል።
እሑድ ዕለት ከፖሊስ ጋር ሲከሳከሱ፣ አንድ የማውቀው ወጣት፣ “We are not Woyyane! We are not Woyyane!” እያለ ሲጮኽ ተሰምቷል። ልክ ነው። እሱ ወያኔ ላይሆን ይችላል። ዳሩ ግን አባ ተባዩ ምን ቢደግሙበት ይሆን እነተወለደን የመሳሰሉ ወያኔዎች በተሰበሰቡበት “ይቅርታ ያድርጉልኝ! በፊት ተሳስቼ ነበር”[4]ያሉትን በዓይኑ እያየ፣ ሙሉጌታ አሥራተ ካሳ በግልጽ ቤተክርስቲያን ድረስ መጥቶ፣ መመሪያ እየሰጠ እያየ፣ እነሰብሀት ነጋ ከመለመሉት ሲኖዶስ የመጡ ጳጳስት ሕንጻ ቤተክርስቲያናችንን ሊነጥቁ ሲያሰፈስፉ እያየ “እኔ ወያኔ አይደለሁም” ማለት! ጲላጦስ ክርስቶስ ላይ የሞት ፍርድ ፈርዶ፣ “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ” ካለው በምንም አይለይም። በወያኔ መናጆ የሆናችሁ ወጣቶች ንቁ። አለበለዚያ ስማችሁ የወንጀል ሪኮርድ ውስጥ አንዴ ከተመዘገበ፣ እንጀራ ገመዳችሁ መበጠሱን ተረዱት! ትምህርት አይኖርም! ሥራ አይኖርም! በራሳችሁ አትፍረዱ! አባ ተባዩ ነገ ተሹመው ከሂዱ እኛ እና እናንተ እዚችው እንደተፋጠጥን ልንቀር ነው። አንዴ ሪኮርድ ከተያዘባችሁ በሆነው ባለሆነው እንደጥጃ ጎትተው ያስሯችኋል። በአጠፋችሁትም ባላጠፋችሁትም በዓይነ ቁራኛ ፖሊስ እየጠበቃችሁ ቁም-ስቅላችሁን ይሳዩአችኋል።
የመጨረሻው መልዕክቴ ለሸረኛው አባ ተባዩ እና ለወያኔ ነው። ለአባ ተባዩ ዓይናውጣ አጭበርባሪ አስመሳይ መነኵሴና ለወያኔ ደጋፊዎቻቸው የምናስተላልፈው መልዕክት አለ። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ይኸን ሕንጻ ቤትክርስቲያን ለመንጠቅ የምትሞክሩትን በሙሉ አቁሙ። ወጣቶቻችንን መጠቀሚያ መሣሪያ አታድርጓቸው። ከሕግ ውጭ የምትሠሩት መጥፊያችሁ መሆኑን ዕወቁት። የሕግ የበላይነት የተከበረበት አገር ውስጥ መኖራችሁን አትዘንጉት። ንግስቲቱም ሳትቀር ለሕግ ተገዢ ናት። የአገሩ መንግሥት ሳይቀር ከሕግ በታች ነው። ሕጉ ከሰጣችሁ፣ ለሕግ እንገዛለን። ትተንላችሁ እንቀመጣለን። ውሰዱት። ሕግ ከሰጠን፣ የሕዝብ ንብረት ስለሚሆን አንዳችም ነገር ማድረግ አትችሉምና አትፈራገጡ። መፈራገጥ እንደእሁዱ ጉዳችሁ ለመላላጥ ብቻ ነው። ስለዚህ ያላችሁበት አገር ደንብ ጠንቅቃችሁ ዕወቁ። ወጣቶቻችንን መርዛችሁ መልሳችሁ እኛው ላይ አታዝምቱ! ወጣቶቻችን ሲጎዱ ማዘናችን ባይቀርም፣ ቢያሳዝነንም ታዲያ ተኝተን እንደማንታረድላችሁ ዕውቁ! ለንደን አዲስ አበባ አይደለችም! ለሕግ ተገዙ። የምትሠሩትን እናያለን! እንሰማለን! አንድ እርምጃ ስተውስድ ቀድመን እንጠብቃችኋለን። እባብ ለእባብ ይተያያል በካብ!

Monday, 14 October 2013

ስንቱን አጣን! (ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም)


Pro Mesfin
እንደኢትዮጵያ ባለ ኋላቀር አገር አገር ውስጥ መሠልጠን ብዙ ችግር አለበት፤ እኔ ራሴ በኮምፒዩተር መጻፍ ከጀመርሁ ሠላሳ ዓመት ሊሆነኝ ነው፤ ታዲያ መብራት ጠፋና የምሠራው ባጣ የቆዩ ወረቀቶችን ሳገላብጥ አንድ እአአ በዲሴምበር 26 1965 ከዱሮ ተማሪዬ የተጻፈልኝን ደብዳቤ አገኘሁ፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በነበረ ከአንድ በጣም ጎበዝ ወጣት የተላከልኝ ነበረ፤ ከተመረቀ በኋላ በአንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ለጥቂት ዓመታት ሠርቶ ትምህርቱን ለመቀጠል ወደአሜሪካ ሄዶ በሎዝ አንጄለስ አካባቢ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር፤ ደብዳቤውን የጻፈልኝ ከዚያ ነው፤ ደብዳቤው ሰባት ገጾች አሉት፤ ከሰባቱ ገጾች አምስቱ ስለኢትዮጵያ ያለውን ስጋት የሚገልጽ ነው፤ በሎዝ አንጀለስ አካባቢ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት በሚያደርግበት ጊዜ ሁሉ ብዙዎቹ የሚያሳዩት የመንደረኛነት ስሜት እያበሳጨው የተማሩት ሰዎች በእንደዚህ ያለ ማኅበረሰባዊ ኋላቀርነት ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዴት መራመድ ትችላለች? እያለ ይሰጋ ነበር።
ደብዳቤውን ላቋርጥና ስለሰውየው ትንሽ ልናገር፤ ተማሪ ሆኖ ክፍል ውስጥ ምንም ነገር የማያሳልፍ በጣም ተከራካሪ ተማሪ ስለነበረ አደንቀው ነበር፤ አንድ ጊዜ እንዲያውም የዘውድ መንግሥት ደጋፊ ነኝ አልሁና አንዴት በትከሻው ላይ ጭንቅላት ያለው ሰው ዓመቱን በሙሉ የዘውድ አገዛዝ የሚያደርስብንን በደልና ችግር ሲነግረን ቆይቶ አሁን ደግሞ ያንን ደጋፊ ነኝ ይላል ብሎ ወረፈኝ፤ ልጁን ስለማውቀው አነጋገሩ አሳቀኝ እንጂ አላስቆጣኝም፤ ጥያቄህ ይገባኛል፤ ግን እኔን ሳትወርፈኝ መጠየቅ ትችል ነበር በዬ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ለጥያቄው መልሱን ሰጠሁት፤ በኋላም ጥሩ ጓደኛዬ ነበር።
ከአሜሪካ ትምህርቱን ጨርሶ እንደመጣ ተገናኘንና ወደቀድሞ ሥራው ወደወንጂ ተመልሶ እንደሆነ ስጠይቀው ‹‹እንዴት ብዬ! ዕድሜ ልኬን የፈረንጅ አሽከር ሆኜ መኖር አልፈልግም፤ አሁን ደግሞ ያስተማረኝን ሕዝብ ላገልግል እንጂ!›› ነበር ያለኝ፤ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በወንጂ ባሉት ደመወዞች መሀከል ከፍተኛ ልዩነት ነበረ፤ ቁም-ነገረኛነቱን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ታማኝነት፣ የግል ጥቅሙን ቀንሶ ኢትዮጵያን ለመርዳት ባሳየው ተግባራዊ አርአያነት የማደንቀው የወታደር ልጅ ነው።
ይህ ሰው በደርግ ጊዜም አልሸሸም፤ በአንድ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሥልጣን ቦታ ላይ ነበር፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ ወንበሩን ሲይዝ እንደዚህ ያሉ ሰዎች የማይፈለጉ መሆናቸው ሲታወቅ አገሩን ጥሎ ተሰደደ፤ በትልቅ ዓለም-አቀፍ መሥሪያ ቤት ጥሩ ሥራ አግኝቶ ዕድሜው ለጡረታ እስቲደርስ ቆየ፤ ወደሚወዳት አገሩ ለመመለስ አልቻለም፤ ከአንድ የትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር ግንኙነት እንዳለው አውቃለሁ፤ አንድ ቀን ስለዚሁ የጋራ ጓደኛችን ስናወራ ለምን ወደኢትዮጵያ እንደማይመለስ ጠየቅሁ።
የዚህ ወጣት አጎት በወታደርነት ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ በክብር ያገላገለ ነው፤ ይህ ሰው ወያኔና ሻቢያ በተጣሉ ጊዜ ዜግነታቸው በጉልበት እየተገፈፈ ከአገራቸው እንዲወጡ ከተደረጉት ሰዎች አንዱ ነው፤ በዚያን ጊዜ በሌላ የኤርትራ ተወላጅ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ራሱ ሰውዬው በአሜሪካ ድምጽ ራድዮ ሲናገር የሰማሁት የሚከተለውን ነው፤– ‹‹ለኢትዮጵያ በአለኝ ሁሉ አገልግያለሁ፤ ኢትዮጵያን ሳገለግል አንድ እግሬን አጥቻለሁ፤ አንድ ሰው ለአገሩ ከዚህ የበለጠ ምን ያደርጋል?›› ብሎ ሲናገር አስለቅሶኛል።
የኔ የቀድሞ ተማሪና ወዳጅም ለምን ወደኢትዮጵያ እንደማይመለስ ሲጠየቅ ‹‹ለጋሼ (ማለት ለአጎቱ) ያልሆነች ኢትዮጵያ ለእኔ አንዴት ትሆነኛለች? በማለት በጥያቄ መለሰ አሉ፤ አባቱ ያገለገላትን፣ አጎቱ የለፋላትን፣ አያት ቅድመ-አያቶች የሞቱላትንና የደሙላትን አገር እንዲህ በቀላሉ ማጣት ነፍስን ያቆስላል፤ የነዚያን ሰዎች ሁሉ መስዋእት ያከሽፋል፤ ያረክሰዋል፤ ይህንን የተገነዘቡና ያዘኑ፣ ያለቀሱ ሰዎች ናቸው –
እናት ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!

ሸህ መሀመድ ሁሴን አል ዓሙዲ ቤቶችን ተነጠቁ

ጥቅምት ፩(አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከመንግስት ጋር ባላቸው ከመጠን ያለፈ ወዳጅነትና ቅርበት የሚታወቁት ሼህ መሀመድ ሁሴን አል-አሙዲ ለእግዶች ማረፊያ የተከራዩዋቸውን  ቤቶች እንደተነጠቁ የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ሼሁ፤ ከውጪ አገራት ለሚመጡባቸው እንግዶች በአያት ሲ.ኤም. ሲ   25 መኖሪያ ቤቶችን ለውጪ አገር ጎብኝዎች በተሰላ ሂሳብ ተከራይተው +በዶላር ምንዛሬ እየከፈሉ ሲገለገሉባቸው መቆየታቸውን የጠቀሱት እነዚሁ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ  ምንጮች፤ መንግስት ባልተገለጸ ምክንያትና የኪራይ ውሉን በማፍረስ  25ቱንም   ቤቶች ሰሞኑን እንደነጠቃቸው አመልክተዋል።
ባለሀብቱ አገር ውስጥ በሌሉበትና ባላወቁበት ሁኔታ የተወሰደው እርምጃ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ የሚድሮክ ሠራተኞችንና የባለሀብቱን ወዳጆች ማስደንገጡ ታውቋል።  አል-አሙዲ በኪሳራ ምክንያት የተዘጋውን የካራቱሪን እርሻ ጠቅልለው ሳይገዙት አይቀርም የሚል ወሬ በስፋት እየተሰራጨ ባለበት ጊዜ  መንግስት በድንገት ይህን እርምጃ መውሰዱ ከመለስ ሞት በሁዋላ የባለህብቱና-የመንግስት ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን ጠቋሚ ነው ብለዋል-ዜናውን ያደረሱን ወገኖች።

በ1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና በ12 ድራፍት ብርጭቆ – እውነትና ከሕደት………(ከ ይድነቃቸው ከበደ)


ooohhhh
(የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ሀላፊ)
ኪነ-ጥበብ ምኞታችን፣ደስታችን፣አዘናችንን እና ክፋታችን የምናይበት እና የምናዳምጥበት የህይወታችን ነፀብራቅ ነው፡፡ ኪነ-ጥበብ ህይወትን ቀለል አድርጎ ከማዝናናት ባለፈ በገለሰብ አስተሳሰብ ላይ የራሱ የሆነ በጎ ወይም በጎ ያልወነ አስታውጾ የሚያበረከት ጥበባዊ ሃይል ነው፡፡ይህ ሃይል በመልካም አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ ወደ ህብረተሰቡ ውስጥ ሲገባ የሚኖረው አገራዊ ፋይዳ እጅግ በጣም የበዛ ነው፤፤ በመሆኑም ኪነ-ጥበብ እንዲህ አይነቱ ጠቀሜታ እንዲኖረው የሚያደርጉት በጥበብ ሙያ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ናቸው ፤እነኚህ ባለሙያዎች ሙያቸው ከመሬት የፈለቀ ሣይሆኖ በልምድና በት/ት የዳበረ ጥበባዊ ተስጥኦ ነው፡፡
ከኪነ-ጥበብ ዘርፎች ውስጥ ከሚመደቡት አንዱ ቴአትር ነው፤ ቴአትር በአገራችን ያለው ተቀባይነት ቀላል የሚባል አይደለም ፤ቴአትር አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ የቴአትር ባለሙያዎች የከፈሉት ዋጋ ከዕድሜቻው፣ ከገንዘባቸው እና ከዕለት ተዕለት ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ጎምዶ ያስቀረባቸውን የሚያውቁት ዋጋውን የከፈሉት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ቢሆንም በቴአያትር ጥበብ የዝወትር እንቅስቃሴችን መጥፎዉንና የተሸለውን በመለየት ጥበባዊ በሆነ መንገድ እየተዝናናን እንድንማርበት ለሚያደርጉ የቴአትር ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ስንመለከትና ስናደምጥ እውነትም ለሙያው እድገት የተከፈለ ነገር እንዳለ ያስገነዝበናል፡፡
ስለሆነም ለቴአትር ባለሙያዎቻችን ከትላንት ዛሬ የምንሰጣቸው ከበሬታና አድናቆት የሚበረታታና የሚያስደነቅ ነው፤ይህ ደግሞ ለቴአትሩም እድገት የሚጠቅም ነው፡፡ይሁን እንጂ በቀርብ በብሔራዊ ቴአትር ቀደምት ባለሙያዎች ላበረከቱት አስታዋጽኦ በማስታወስ የሽልማት ፕሮግራም የተዘጋጀ ቢሆንም ዝግጅቱ እውነትና ከሕደት የተቀላቀለበት ነበር፡፡
‹‹……. ቀደምት ባለሙያዎች እንዲገናኙና ባለፈው ላደረጉትም አስታውጽኦ ሽልማት መሰጠቱ ተገቢነት ያለው ድርጊት ነው፡፡ባለሙያዎቹ ሲገናኙና በመነፋፈቅ ፈቅራዊ ሰላምታቸውን ሲለዋወጡ ስመለከት እጅጉን ደስ ብሎኝ ነበር የምከታተለው፡፡ እየቆየሁ ሲሄድ በውስጤ ቅሬታ ተሰማኝ በብሔራዊ ቴአትር በተከናወነው ስርአት ላይ በሞት የተለዩትን ተነሱ፤ በነፍስ ያሉት ግን ተገኝተው የሚመሰገነው ተመሰገነ፤ የሚሸለመው ተሸለመ እዚህ ላይ ነው ቅድም የጀመረኝ ቅርታዬ የበረታብኝ፡፡………. ››
በማለት በብሔራዊ ቴአትር ቤት የተካሄደውን ሽልማት ስነስርአት በኢቲቪ ፕሮግራሙን ሲከታተል የነበረ ሰው ትዝብቱን እና ቁጭቱን በሎሜ መፅሔት በባለፈው ሳምንት ዕትም ላይ ያስነበበን፡፡
እኔም የሰውዬውን ትዝበት እና ቁጭት አብዝቼ የምጋራው ነው፤ አርቲስት ደበበ እሸቱ በሙያው ከበሬታን ያተረፈ ለብሔራዊ ቴአትር ቤት እድገት የተቻለውን አስታውጾኦ ያበረከተ እና በህይወተ ከቀሩልን አንጋፋ አርቲስቶች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ማንኛውም ሰው የሚሰጠው ምስክር ነው፡፡እውቁ አርቲስት ደበበ እሸቱ ተዋናይ፣ኮሜዲያን፣ አዘጋጅ ሆነ ለረዥም ዓመታት አገልግሏል፡፡ በመድረክ ፣ በሬዲዩ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም ስራ እና በጋዜጠኝነት ሙያ ሠርቷል፡፡ ቤተ መንግስት ተገኝቶ አፄ ኃይለሥላሴን ከሥልጣን ሲወርዱ ያነጋገራቸው ጋዜጠኛ ደበበ እሸቱ ነው፡፡ የተለያዩ ሃላፊነቶችን ይዞ ሠርቷል ፤ በአፍሪካ የመድረክ ሙያተኞች ማህበር በሊቀመንበርነት መርቷል እንዲሁም በአትላንታ አንድ ቀን በስሙ ተሰይሞለታል፡፡ የአርቲስት ደበበ እሸቱ የጥበብ እረዥሙ የህይወት ጉዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኪነጥበባት ወ ቴአትር ተጀምሩ በብሔራዊ ቴአትር የቀጠለ ሲሆን በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ያበቃ ነው፡፡
ስለ አርቲስቱ ካነበብኩት እና ከማቀው ይህን ብልም ከእኔ እውቀት ማነስ ያስቀረውበት መልካም የሆኑ ስራዎቹ እንደሚኖሩት ተስፋ አደርጋለው፡፡ በመሆኑም በብሔራዊ ቴአትር ቤት በተካሄደው የማስታወስ እና የሽልማት ስነስርአት ላይ አርቲስት ደበበ እሸቱን ለማስታወስም ሆነ ለመሸለም አለመቻሉ ከምን እንደመነጨ አንድ ለበዓሉ ዝግጅት ቅርብ የሆነ ለሆዱ ያደራ አርቲስት በ1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና በ12 ድራፍት ብርጭቆ በፈጀ ወጪ እውነትና ክሕደትን ዘርዝሩ የተናገረው፡፡ ይህን ሰው ሆድ አደር ያልኩበት ምክንያት የሚያውቀውን እውነት በፍራቻ ምክንያት በአደባባይ አለመግለፁ እንዲሁም የዝግጅቱ አስተባባሪ ከሆኑት ውስጥ አንዱ እንደመሆኑ መጠን የራሱን እምነት ወይም አቋም በዝግጅቱ ሂደት ላይ ምንም ሳይገልፅ ሌሎችን ለመኮነን የሄደበት መንገድ ነው፡፡
ይህ ለበዓሉ ዝግጅት ቅርብ የሆነው አርቲስት የቀረበለትን ምግብ እና መጠጥ እየጠጣ አርቲስት ደበበ እሸቱ በሙያው አንቱታን ያተረፈ ለቴአትር ሙያ እድገት አስታውጾኦ ያበረከተ መሆኑ እና በቀድሞ የሙያ አጋሮቹ ፍቅርና ከበሬታ ያለው መሆኑን ምግብና መጠጥ ለጋበዘው ሰው ገልጾአል፡፡ ንግግሩን ሲቀጥል ‹‹ ደቢሾ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ስለሆነ በፕሮግራሙ ላይ እንዲሳተፍ አልተፈለገም ፤ በሱ ጉዳይ ላይ ስንቱ አፈ ልጉም ሁሉ ልወደድ በሚል አፉን ፈታ መሰለህ፡፡ የሚገርመው ግን ደቢሾ ወደ ቴአትር ቤት አንድ ሁለት ጊዜ መጥቶ በነበረ ጊዜ ሁሉም እንዴት እየተንደረደሩና እላዩ ላይ እየተጠመጠሙ እንደሚስሙት አይ ነበር እነዚያው ሰዎች አሁንም እንዳይጠራ ብለው ሲሞግቱ በጣም ነው የተገረምኩት ፡፡ ዋናው ደግሞ ስራ አስኪያጁ እንዴት እንደተቃወመና በጭራሽ ሊጠራ አይገባም ፤ እሱ የሚጠራ ከሆነ እኔ በበዓሉ አልገኝም ስራዬንም እለቃለው አለ ! በቃ ያንን ስንሰማ ሁላችንም ፈራን……….. ስማ እንግዲህ ይህ በእኔና ባንተ የሚቀር የግል ጨዋታ ነው፤ የኔን ስም በጽሁፍም ሆነ በግልም ለደቢሾም ቢሆን እንዳታነሳ፤ አደራህን ነገ የሚሆነውን ማን ያውቃል ? ›› በማለት የነገሩን ሂደት ሰፋ አድርጎ የገለፀው፡፡
ውድ አንባቢያን 1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና 12 ድራፍት ብርጭቆ የፈጀ ወጪ በመሸፈን በብሔራዊ ቴአትር ቤት የተካሄደውን የሙያ ክሕደት እውነቱ እንዲወጣ ያደረገው አርቲስት እና ምግብና መጠጥ አሸንፎት እውነቱን የተናገረው ሌላኛው አርቲስቲ ሙሉውን ታሪክ መስከረም 18 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው ሎሚ መፅሔት ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡
ወደ መነሻዬ ልመለስ እና አርቲስት ደበበ እሸቱ እድሜ ልኩን በሙያው ያገለገለ እውቅ አርቲስት ነው ፡፡ በዚያው መጠን አሁን ባለው በገዢው ስርዓት ለታየው ብልሹ አስተዳደር ግንባር ቀደም በመሆን ሲተች እና ሲታገል ነበር በዚህም ምክንያት ለተደጋጋሚ እስር እና ለተደጋጋሚ ይቅርታ ጥያቄ ተዳርጓል፡፡ ይህ ግለሰባዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ላበረከተው በጎ አስታውጾ በየትኛውም በኩል መመዘኛ ሊሆን አይገባም !!! እርግጥ ነው ገዢው መንግስታችን ለልማታዊ አርቲስቶች ያለው ድጋፍ ቀላል የሚባል አይደለም ፤ ልማታዊ አርቲስቶችም ለኢህአዴግ መንግስት ያላቸው ድጋፍ ወደር አይገኝለትም፡፡
አርቲስቶቻችን ሰው እንደመሆናቸው መጠን የራሳቸው የሆነ የሃሳብ ነፃነት ያላቸው ሲሆን በዚህ መብታቸው በመጠቀም የሚፈልጉትን የፖለቲካ አስተሳሰብ የመደገፍ ሳይመስላቸው ሲቀር የመተቸትና የመቃወም መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ተፈጥራዊ የሃሳብ ነፃነት መብት በሃይል ወይም በጥቀማጥቅም በመደለል እና በማስገደድ የአንድ የፖለቲካ ስርአት ብቻ ደጋፊና አቀንቃኝ ማድረግ የሞራል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
በመሆኑም እንዲህ አይነቱ አካሄድ ለአርቲስቱም ሆነ ለሙያው እድገት ጉዳት እንጂ ጠቀሜታ የለውም፡፡ በአገራችን የፖለቲካው ስርአት ሲለወጥ የአገር መከላኪያ ሠራዊት ( ጦሩ) እየተለወጠ በአዲስ መልክ እየተቋቋመ ተቸግረናል ፡፡ አሁን ደግም የመከላኪያ ሠራዊት ( ጦሩ) ብቻ ሳይሆን አርቲስቶቻችንም ከፖለቲካ ስርአታችን ጋር እየተቀየሩ በአዲስ መልክ ልናያቸው ይሆን ? ፡፡ እንዲህ አይነቱ አደገኛ ከስረት ውስጥ ከመግባታችን በፊት የነገሩን አካሄድ ሊመረመር ይገባል ፡፡
በመሆኑም በአርቲስት ደበበ እሸቱ ላይ የተፈጸመው የሙያ ከሕደት እጅግ በጣም የሚያሳዝን እንዲሁም የሚያሳፍር ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አገርን አስተዳድራለው ከሚል መንግስት እንደሰፈር ጉልበተኛ ጎረምሳ እልህ በመጋባት በአርቲስቱ ላይ የሙያ ከሕደት እንዲፈፀም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ አስታውጾኦ በመንግስት ካድሬዎች በመፈጸሙ ሌላኛው አሳፋሪ እንዲሁም አስቂኝ ነገር ነው፡፡
ስለዚህም ለእውነት ያደሩ ሙያተኞች እንዲህ አይነቱን አሳፋሪ ተግብር ለህዝብ ከማጋለጥ ባለፍ ለሙያቸው እና ለእራሰቸው እድገት የሚበጀውን ቀና መንገድ ለማምጣት ውጫዊ እና ውስጣዊ ሙያዊ ትግል ሊያካሂዱ ይገባል፡፡ በተጨማሪ በቀብር ስነስርአት ላይ ጥቁር ለብሶ እና በእመም ጊዜ ለመታከሚያ ገንዘብ ለመሰብሰብ ከመታየት በለፈ በሙያቸው እውቅ የወኑትን አርቲስቶች በህይወት እያሉ በማሰብ እና በማበረታታት ሙያዊ አጋርነታቸውን ለእውነት የቆሙ አርቲስቶች ሊያሳዩን ይገባል፡፡