ጥቂት ከትግራይ ክልል የሆኑ የአገራችን ሕዝቦች መለስ ሲነካ ትግሬ ተነካ ብለው በየአደባባዮ ሲናገሩ እና አቧራ ሲያስነሱ ይደመጣሉ። መለስ ሲነካ ትግራይ እና የትግራይ ተወላጆች የሚነኩበት ወጥነት ያለው ግልጽ እና ቀጥተኛ ምክንያት ሊታየኝ ስላልተቻለ ሁልጊዜ እገረማለሁኝ። ለመለስ ዜናዊ እና ለስርዓቱ ድጋፋቸውን ከሚሰጡት ግለሰቦች መካከል አብዛኛዎቹ ሰዎች መለስን እና ስርዓቱን የሚደግፉበት ምክንያት ሲጠየቁ የሚሰጡት ምላሽ የደም ንክኪ ስላላቸው እንደሆነ በግልጽ እና በተዘዋዋሪ መንገድ እና አገላለጽ ያስቀምጡልናል።
ታዲያ እኔ ስለዚሁ ጉዳይ ጥያቄዮን በግሌም እንዲሁም ከሌሎች ጋር መጠየቄ አልቀረም ግን ቆይ ደም ፣ ዘር ቆጥረን ነው የምንደግፈው የምንደጋገፈው ከተባለ ታዲያ መለስ ሲነካ የትግራይ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ኤርትራዊያንም ተነክተናል ሊሉ በተገባ ነበር ማለት ነዋ። እንዲሁም መራራ ሲነካ ኦሮሞ፣ ፕ/ር አስራት፣ ዶ/ር ታዮ ወልደሰማያት፣ አሰፋ ማሩ ሲነካ የአማራ ተወላጆች አማራ ተነካ ማለት ይገባቸው ነበር፣ ብርቱኳን ሚደቅሳ ስትነካ አማራም ኦሮሞም ተነክተናል ባሉ ነበር ።
አረ ደግመን ወደ ሕወሃት እንመለስ …. አንድ ብሔሩ ከትግራይ የሆነ ግለሰብ ሲነካ ትግራይ እና ትግሬ ተነካ የሚል መደምደሚያ ላለው ሰው እንዲህም ልጠይቅ እነስዮ ሲገፉ ሲገፈተሩ ትግራይ ተነካች ወይንም ትግሬ ተነካ ለምን አላሉም? ሻዕቢያ እና ወያኔ በሚስጢር በመጣመር ሓየሎምን ባለተሰናዳበት ወቅት ሲገድሉት ለምን እነዚሁ የትግራይ ጥቂቶች አንተ ጀግና ልጃችን አረገፉህ….አንተ ጀግና ወንድማችን ተበቀሉህ ብለው ሊደግፉት እና ተነካን ሊሉ ስለምን አልወደዱም? እነ ኢያሱ በርሔ ድንገት ክልትው ሲሉ ማን ነካህ ወንድማችን …አንተን የነካ እኛን የነካ ነው የሚልለት ስለምን ጠፋ?
አንድ ጊዜ ቆም ብለን ነገሩን ግራ እና ቀኝ እንመዝነው ታዲያ እነ ሓየሎም እነ ኢያሱ ሲነኩ ተነካው የሚል ሰው ከጠፋ እና እነመለስ እና አንጃዎቻቸው ሲነኩ ተነካን የሚሉ ደጋፌዎች ካሉ ነገሩ ከደም፣ ከቋንቋ ያለፈ ሰበብ አለ ማለት ነው። እነሓየሎም እነ ኢያሱ በትግሉ ወቅት መራራ መስዋዕትነት የከፈሉ አይደሉምን? ታዲያ ዘርን ቆጥሮ ድጋፍ የሚሰጥ ካለ ስለ ሓየሎም ድጋፍ ለመስጠት እነዚህ ጥቂት የትግራይ ልጆች ስለምን ዝም አሉ? መቼም ቢሆን መቼ ከመለስ ይልቅ ሓየሎም ለትግራይ ሕዝብ በደም ሙሉነት ይቀርባል። እኔ እነዚህ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች እነመለስን እና አሁን በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን የሚደግፉበት ምክንያት የትግራይ ልጆች ስለሆኑ ብቻ አይደለም ብዮ ልከራከርም የምወደው ለዚህ ነው፤ በእርግጥ በጥቂቶች ፕሮፓጋንዳ ተታሎ ድጋፉን እየሰጣቸው ያለ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የግለሰብ ስብስብ ስለመኖሩን አልክድም።
እውነቱን ለመናገር እነ መለስ ሲነኩ የትግራይ ሕዝብ እንደተነካ ተደርጎ እንዲቆጠር የሚጥሩ ጥቂት በስርዓቱ የተጠቀሙ ግለሰቦች ብቻ ናቸው፤ የሕወሃት ሰዎች ሲነኩ የሚነካውም ከስርዓቱ ጥቅም የተጋሩ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የስርዓቱ ተጠቃሚዎች እነዚሁ ጥቂቶቹ ናቸው እንጂ መላው የትግራይ ሕዝብ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። እንደውም ነገሩን ወደውስጥ ጠለቀ ብለን እንመልከት እነ አርከባ፣ እነ አዜብ፣ እነ በረከት፣ እነ ስብሃት ነጋ፣ እነ ደብረጽዮን፣ እነ ታደሰ ሃይሌ፣ ሌሎቹም ቀንደኞቹ የሕወሃት ምንደኞች ዘረፋቸውን የሚያካሂዱት ከእነ ማን ጋር ነው? ከጥቂት ትግሬዎች (እንደ እንይ ሪል እስቴቶቹ ባለቤቶች እና መላው ሕወሃት ፖሊት ቢሮ አባላት ቀድሞው እና አሁኑ በጠቅላላቸው )፣ ከጥቂት አማራዎች(የሰንሻይኑን ባለቤት ሳሙዔል ታፈሰ፣ ሼክ ሁሴን ዓሊ መሃመድ አላሙዲንን፣ አያት ሪል ስቴቱ አያሌው፣ የስታር ቢዝነሶቹ ጌቶች እን ምንውዮለት አጥናፉ፣ ) ከእነ የምሩ ነጋ(ደምበል)፣ የኬ.ኬ ትሬዲንጉ ከተማ ከበደ እና ከመሳሰሉት ስርዓቱ ተጠቃሚዎች ጋር ነው። ስለሆነም የሕወሃት መለካት የእነ ሳሙዔል ታፈሰ፣ የእነ አርከበ፣ የእነ አላሙዲን፣ የእነ በረከት፣ የእነ ደብረጽዮን መነካት እንጂ የትግራይ ልጆች መነካት የሚሆንበት ሒሳብ የለም ሊኖርም አይገባም።
ነገር ግን እነዚህን ወንጀለኞች የሚደግፍ ማንኛውም ግለሰብ ወይንም ድርጅት ነገ ፍትሕ ስፍራዋን ስትይዝ መጠየቃቸው አይቀርምና ዛሬ የትግራይን ህዝብ ከለላነት ይጠቀማሉ፤ በማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን የሚዘረፈው ገንዘብም የኢትዮጵያ ገንዘበብ ከሆነ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግራዮ እና ሌላውም ገንዘብ ነው፤ ዝርፊያውን የሚያካሂዱት ደግሞ የትግራይን ልጆች ድጋፍ እና እገዛ ያገኙ በማስመሰል ስለሆነ እና የትግራይን ልጆች በማታለል መጠቀሚያ በማድረግ ስለሆነ የትግራይ ልጆች ይህን ዘራፊ የወያኔ ቡድን ከማናቸውም ብሔር በላይ አምርረው እንዲታገሉት ግድ አለባቸው።
እዚህ ጋር አንድ ወዳጄ የነገረንን ላውጋችሁ ወቅቱ 1997/98 ነው በምርጫው ግርግር ወቅት 200 ሰዎች በተገደሉ ወቅት ወዳጄ በስራ ምክንያት በቢሮው ሰበብ በተባበረችው የአሜሪካን ግዛት ለ1 ወር ስልጠና ሄዶ ነበር፤ እናም አሁን ቦታውን በትክክል ባላስታውሰውም ዋሽንግተን ዲ.ሲ ውስጥ እንደሆነ ግን ወሬውን አልዘነጋሁትም፤ የ1997/98 ጭፍጨፋ አስመልክቶ የወያኔን ቡድን የሚደግፍ እና የሚቃወም ትዕይንት ተመልክቶ ነገሩ ስለሳበው ነገሩን ሊመለከት አብረውት የነበሩትን ሐበሻ ወዳጆቹን ግድ ብሎዋቸው የሁለቱንም ቡድን ጥያቄ ለመስማት ወደ ቡድኖቹ መቀላቀል፤ ከወያኔ ደጋፊዎ በኩል የሚሰማው የከበሮ ድምጽ ደጋፊዎቹ ለመስቀል ወይንም ለጥምቀት ወይ ደግሞ ለእንቁጣጣሽ ጃንሜዳ የወጡ ይመስል ነበር አለኝ። ወደ መካከላቸው ዘልቆ ሲገባም የሚናገሩትን ቋንቋ ሰምቶ በአመዛኙ ከትግራይ ክልል ስለ መሆኑን አስገነዘበኝ እና ወደ መካከላቸው ዘለቀ …..እውነቴን ነው የምላችሁ ግለሰቡ ሲያወራኝ ለመስማት የከበደኝን ብዙ ወሬ እርሱ በአካል ሰምቶ መመለሱ በራሱ አስገረመኝ፤ ኢትዮጵያዊያን እንደዚህ አይነት አቋም ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም ነበርና። ለጆሮ እጅግ የሚሰቀጥጥ ስድብ እና ፉከራውንማ ተዎት…ስለ ሕጻን ነቢዮ መሞት ከወያኔ ተቃራኒ ወገን በተቃውሞ ሲነሳ…. ከወያኔ ደጋፊዎች በኩል አንዱ ገና መዋዕለ ሕጻናችሁን ቤንዚን አርከፍክፈን ነው የምንፈጃችሁ አለ…አጠገቡ የነበሩትም አይባልም ተው ከማለት ይልቅ ሳቁ፤ የሚቃወመው አንድም አለመኖሩ አንገበገበኝ አለኝ፤ ሌላኛውም አስከትሎ ገና ምኑ ተንክቶ ነው የምትንጫጪው አርፈሽ ካልተቀመጥሽ እንፈጅሻለን .....አጥነንታችን ከስክሰን ልጆቻችን ገብረን የ ተገኘን ስልጣንማ በካርድ እና በአመጽ እንዲህ በቀላሉ አንሰጥም አለ…. ሌላኛይቱም አማራን ሙልጭ አድርጋ ስትሰድብ አማራ ብቻ በመሆኔ እንዲህ ለምን እንደምሰደብ አልገባ እያለኝ ... የእነዚህ ሰዎች የጥላቻ ልኩ እያስፈራኝ ከመካከላቸው ወጣሁኝ እና ወደሌላኛው ቡድን ተቀላቀልኩኝ አለኝ።
በእርግጥ 50 የማይሞሉ ጥቂት የወያኔ ደጋፊዎች 4 ሚሊየኑን የትግራይ ሕዝብ እንደማይወክሉ ብረዳውም ነገሩን ከሰማሁነበት ቀን ጀምሮ ግን እረፍት ነሳኝ…አንዱ ብሔሩ ትግሬ የሆነ ግለሰብ አንዲህ አለ… ሕወሃት ባጠፋው ቁጥር አብሬ ልጠየቅ አልችልም፤ እኔ ህወሃት ያጠፋውን ሂሳብ በምንም መልኩ የማወራርድበት ምክንያት የለም ሕወሃት በትግራይ ልጆች ስም ከለላነት የትግራይን ህዝብ ጨምሮ መላውን ኢትዮጵያ ህዝብ እየመዘበረ ነው አለኝ፤ የወዳጄን ንግግር ሊሰመርበት እወዳለሁኝ።
ስለዚህ ይህንን ኢ- ፍሕታዊነት መታገል ደግሞ የሁሉም ድርሻ ነውና ሁሉም የ ኢትዮጵያ ህዝብ ሊታገለው ያስፈልጋል። የአማራው ፍትሕ ተጓድሎ የኦሮሞው ፍትህ ሊጠበቅ የሚችልበት አግባብ በምንም መልኩ የለም። የኦሮሞ ልጆች መብት እየተረገጠ በምንም መልኩ ሊከበር የሚችል የትግሬ መብት የለም። የአንዱ ፍትሕ ሲጓደል የሚጓደለው ፍትሕ የሁሉም ኢትዮጵያ ነውና ሁሉም ኢ-ፍትሃዊነትን … ዝርፊያን .. ንጥቂያን …. ግድያን.. አፈናን... ሊቃወም ይገባል። ድል ለመላው ሕዝብ!!!
ለምን አንቃወም? ለመቃወማችን ሰበቡ…. ብዙ ነው BS/ምኒልክ ሳልሳዊ
http://minilik-salsawi.blogspot.no/2013/02/blog-post_9818.html
No comments:
Post a Comment