Sunday, 26 April 2015

“የምንታረድበት ቀን ደርሷል፣ ጓደኞቻችን ታረዱ፤ እኛም አሁን ተራችንን እየጠበቅን ነው”

ሰሞኑን በሊቢያ በኢትዮጵያኖች ላይ የደረሰው አረመኔያዊ ድርጊት ሁላችንንም መሪር ሃዘን ውስጥ ከቶናል። እንቅልፍ ነስቶናል። መደበኛ ስራችንን ሳይቀር ማከናወን ተስኖናል። ምክንያቱም ድርጊቱ በሰው ልጅ ላይ ሊደረግ ቀርቶ የማይታሰብ ሰይጣናዊ ድርጊት ነውና። በህይወት የሚገኙትን ከዚህ አሸባሪ ሰይጣናዊ ቡድን ማዳን አለመቻላችን ደግሞ ሃዘናችንን እጥፍ ድርብ አድርጎብናል። በሰማዕትነት ላለፉት ክርስቲያን ወንድሞቻችን አንብተናል፣ አልቅሰናል፣ ውስጣችን ደምቷል፤ እኛም እንደ እነሱ በመንፈስ ታርደናል።
ብዙዎች በተለያየ መልኩ ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው። ለዚህ ያበቃንን መንግስት ነኝ ባዩን በመኮነን ላይም እንገኛለን። ለብዙዎች የስደት ዋናው ምክንያት የወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ መሆኑ የታወቀና የተረጋገጠ ነው። በመተባበር ለአገርና ለህዝብ ጠላት የሆነውን ወያኔን ማሶገድ  ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደሚገባም ብዙዎቻችን እንስማማለን።
እስከዛው ግን በስቃይና በመከራ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚቻለው ሁሉ መታደግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብዬ አምናለሁ።
ዛሬ በቅርብ ከማውቀው ሰው ከሊቢያ በቫይበር መልእክት ደረሰኝ። ስደውልለት ማናገር እንደማይችል መልእክት ላከልኝ።  ፎቶግራፉን ሲልክልኝ ማመን አቃተኝ። እጅግ በጣም ተጎሳቁሏል፣ የሐዘን ስሜት ይነበብበታል። እኔም የት እንዳለ እና በምን ሁኔታ እንደሚገኝ ጠየኩት። ተስፋ በቆርጠ አነጋገር “የምንታረድበት ቀን ደርሷል፣ ጓደኞቻችን ታረዱ፤ እኛም አሁን ተራችንን እየጠበቅን ነው” አለኝ። እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ነው ማጽናናት እንኳ የማይቻልበት ወቅት። እኔም ግራ ገባኝ እንደማነኛውም ሰው ሐዘን ተሰማኝ ይበልጥ ደግሞ  ምንም ማድረግ አለመቻሌን ሳስበው።
37 ኢትዮጵያውያን በአንድ ጠባብ ቤት በሊቢያ እና ሱዳን ጠረፍ ደንጉላ በምትባል ስፍራ ታስረው እንዳሉ ገለጸልኝ። ሊወጡ የሚችሉበት መንገድ  እንዳለም ጠየኩት፤ ለእያንዳንዳችን 2000 የሱዳን ገንዘብ መክፈል ከተቻለ የመለቀቅ እድል እንዳላቸው ነገረኝ። ያን መክፈል ካልተቻለ ግን ለአይ ኤስ አይ ኤስISIS) አሳልፈው እንደሚሰጧቸው አስረዳኝ። ብዙ ኢትዮጵያውያን ጓደኞቻቸው በዚህ መልኩ እንዳለቁ ነገረኝ። እንዴትና በምን መልኩ ገንዘብ ሊደርሳቸው እንደሚችል ጠየኩት፤ ሱዳን በሚገኝ ደላላ አማካኝነት ለአሳሪዎቹ ገንዘቡ ሊደርሳቸው ይችላል አለኝ። የደላላይ ስልክም ተቀብዬ ደጋግሜ  ብደውልም ላገኘው  አልቻልኩም። አማራጭ ስልክ እንዲሰጠኝ በጠየኩት መሰረት በደላላው የቅርብ ጓደኛ ደጋግሜ ደውዬ ሳናግረው ገንዘብ መክፈል ከተቻለ እንዲለቀቁ እና ወደ ሱዳን እንዲመለሱ  ማድረግ እንደሚቻል አረጋገጠልኝ።
ይህን መረጃ ለኢሳት ለማስተላለፍ ወደ ዲሲ ስቲዲዮ ደጋግሜ ደወልኩ ግን የስራ ቀን ባለመሆኑ ስልኩ ሊነሳልኝ አልቻለም። አሁን ብቸኛ አማራጭ ሁኖ  ያገኘሁት ይህን መረጃ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ለኢትዮጵያውያን ማድረስ  ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን፦ በሰማዕትነት የተሰውትን ነፍሳቸውን በክብር ከቅዱሳን ጋር ይደምርልን እኛንም አምላከ ቅዱሳን መጽናናቱን ይስጠን ከማለት ውጭ ምንም ማድረግ አንችልም። ስለዚህ በሞትና በህይወት መካከል በብዙ ስቃይና መከራ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚቻለን አቅም እንድረስላቸው። የሰው ደም ከጠማው አረመኔና ጨካኝ አይ ኤስ አይ ኤስ አሸባሪ ቡድን እንታደጋቸው። ቢያንስ አንድ ንጹህ  ሰው ማትረፍ ለህሌናችን ትልቅ እረፍት እናገኛለን።
ወገኖቼ ምን እናድርግ??? እርዳታችንን በግል ከምናደርገው በህብረትና በመመካከር ቢሆን ብዙ ነፍስ ማድን እንችላለን በማለት ወደ እናንተ  ማድረሱን ወደድኩ።
አስፈላጊ መረጃዎቹንስልክ ቁጥሮችንእርዳታ ለማድረግ ለሚፈልግ ሁሉ እሰጣለሁ።  ለቤተሰብ እና ለአንዳንድ ጥንቃቄዎች ሲባል ስልክ ቁጥርና ፎቶ ግራፉን እዚህ ላይ ከማውጣት ተቆጥቢያለሁ።

ይበልጣል 
http://yibeltalethiopia.blogspot.no/2015/04/blog-post.html

No comments:

Post a Comment