Sunday, 10 May 2015

ምርጫው አዲስ “ጠቅላይ ሚ/ር” አግኝቷል



“የተለቀቁት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እናጣራለን?” ኢህአዴግ
freed ethiopians

በሊቢያ ታፍነው የነበሩ ወደ 30 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በግብጽ ጦር ኃይል ነጻ አውጪነት መለቀቃቸውን የግብጽ መንግሥት አስታወቀ፡፡ የግብጹ ፕሬዚዳንት አልሲሲ የተለቀቁትን ኢትዮጵያውያን አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመገኘት አቀባበል አደረጉላቸው፡፡ ኢህአዴግ እንደተለመደው “የተለቀቁት ኢትዮጵውያን መሆናቸውን አጣራለሁ” እንደማይል ተገምቷል፡፡ “ተይዘን የነበረው በሊቢያ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ነበር” ከተለቀቁት አንዱ ኢትዮጵያዊ፡፡
በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ሐሙስ በተሰራጨው የዜና መረጃ መሠረት በሊቢያ ደርና እና ምስራታ በተባሉ ከተሞች ታፍነው የነበሩ 30 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በግብጽ ጦር ኃይል እና በሊቢያ ድጋፍ ነጻ መለቀቃቸው ተሰምቷል፡፡
ዜናውን ከካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ የግብጽ የዜና አውታሮች በቀጥታ ለአገራቸውና ለዓለም ሕዝብ እንዲሰራጭ አድርገውታል፡፡ ኢትዮጵያውያኑን የጫነው የምስር (አልምስሪያ) አውሮፕላን መሬት ሲነካ ከፓይለቱ ክፍል አካባቢ የግብጽ ሰንደቅ ሲውለበለብ ተመልክቷል፡፡ ቀጥሎም የተለቀቁት ከአውሮፕላኑ ከመውጣታቸው በፊት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ እስኪመጡ እንዲጠብቁ ተደረገ፡፡ እርሳቸውም እንደደረሱ ኢትዮጵያውያኑ የግብጽን ሰንደቅ እያውለበለቡ ሲወጡ ፕሬዚዳንቱ እያንዳንዳቸውን “እንኳን ለምስር አፈር አበቃችሁ” በሚል ፈገግታ እየጨበጡ ተቀብለዋቸዋል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያውያን በግፍ ከታረዱ በኋላ በዚያ ስለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ሁኔታ ግብጽ በጥልቀት ስታስብ ነበር፤ ለዚህም ነው እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ወደቤታቸው እንዲመለሱ በጣም ጥረት ስናደርግ የነበረው” በማለት የቀድሞው የጦር ጄኔራል አልሲሲ እዚያው አየር ማረፊያው የተለቀቁትን ኢትዮጵያውያን ከኋላቸው አድርገው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡
ይኸው ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ግድያ እጅግ ያሳመማቸው መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በህይወት አስለቅቆ ወደ ግብጽ ለማምጣት የተፈለገው ጥረት ሁሉ መደረጉን በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ “የግብጽ (የጦር ሠራዊትና የደኅንነት) አገልግሎቶች በዚህ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን በመከላከል፣ በማዳንና በማስለቀቅ ተግባር ተሳትፈዋል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “በሊቢያ የሚከሰተው ነገር ሁላችንንም ይመለከተናል” ብለዋል፡፡
ዜናው እንደተሰማ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት “ከመጪው ምርጫ አኳያ ይህ የግብጽ ተግባር እና የፕሬዚዳንቱ ቁርጠኝነት እንዲሁም ደመላሽነት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በመጪው ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቢሆኑ ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም” በማለት ከአዲስ አበባ አካባቢ በላኩት ዋዛ አዘል መልዕክት አስታውቀዋል፡፡
የወገኖቻችን አሰቃቂ ግድያ እንደተሰማ “ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እያጣራን ነው” በማለት ሲያላግጥ የነበረው ኢህአዴግ ሦስት ቀን “ብሔራዊ ሃዘን” በማለት ቢያውጅም ከአንድ ቀን በላይ መቀጠል አለመቻሉ ብዙዎችን ያጠያየቀ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዚህም ሌላ ደርግን “በጦርነትና በጀግንነት” አሸንፈን “ነጻ አወጣን”፣ “ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ” ነን የሚለው ህወሃት “ካስፈለገም ጦርነትን እንሰራለን” ሲል እንዳልኖረ ሁሉ 30ኢትዮጵያውያን በግፍ ከታረዱ በኋላ ምንም ዓይነት የጀግንነት፣ የአርበኝነት ወይም የጦረኝነት ምላሽ ቢያንስ እንኳን ለማሳየት አለመቻሉ ከመጀመሪያውኑ ባዶ ጀግንነት የተሸከመ በምዕራባውያን ድጋፍ የራሱን ወገን በመሸጥ ሥልጣን ላይ የተቀመጠ፤ ኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ ኩራትና ወኔ የሌለው በከንቱ ጀብዱ የተሞላ ባዶውን የቀረ ቀፎ ድርጅት መሆኑን አስመስክሯል፤ ለዚህም ነው ለሃዘን የወጣው ሰልፈኛ “ያገር አንበሳ የውጭ ሬሳ” ብሎ የፈከረው በማለት ብዙዎች ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ከርመዋል፡፡
ከዚህ ዜና ጋር በተያያዘ የግብጽ ሚዲያ ኢትዮጵያውያኑ ከታፈኑበት ተለቀቁ ቢልም ከተፈቱት መካከል አስተያየቱን የሰጠ አንድ ኢትዮጵያዊ እንደተናገረው ተይዘው የነበረው በሊቢያ የጸረ ሕገወጥ ኢሚግሬሽን አካል እንደነበረና የግብጽ መንግሥት መጥቶ እንዳስለቀቃቸው ተናግሯል፡፡
ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጽ/ቤት የተለቀቀው መረጃ እንደጠቆመው ፕሬዚዳንት ሲሲ “የመጀመሪያውን ዙር ከሊቢያ ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ወንድሞችን” መቀበላቸውንና ይህም በቀጣይነት የሚካሄድ ዘመቻ መሆኑን አመላክቷል፡፡
http://www.goolgule.com/egypt-rescued-ethiopians-from-libya/

No comments:

Post a Comment