ነጻነትን በተለያየ መልኩ ትርጓሜ መስጠት ይቻላል። ለምሳሌ፦ ተፈጥሯዊ፣ ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ
እንዲሁም ሀይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ነጻነት በማለት መተንተን ይቻላል። ነጻነት የሚለው ቃል በቀላል አገላለጽ ሲገለጽ
ከማነኛውም ተጽኖዎች መውጣት፤ ከግዞት ወይም ከባርነት መውጣት እና በራስ መወሰን ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የጾታ፣ የእድሜና የአካል
ልዩነት ሳይገድብ ወይም ማንም ሌላ አካል ሳያስገድደን እና የማንንም መብት ሳንነፍግ በነገሮች ላይ በራስ ወይም በጋራ መወሰን መቻል
ነው፡፡ በትክክል ከተረዱት ዲሞክራሲም ሊባል ይችላል፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ
ነጻነትን ለማስፈን የሁሉም ህብረተሰብ አስተዋጾ ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ለበለጸጉ ሀገሮች ነጻነት፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ መስፈን የሴቶች
ድርሻ በቀላሉ ሊታይ የማይችል ነው። ዛሬም በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና በምጣኔ ሃብታዊ መስክ የሴቶች አስተዋጾ ከፍተኛ ነው። ካለ ሴቶች አስተዋጾ የሀገር ለውጥ በታሪክ አጋጣሚ ተዘግቦ
የተቀመጠ አላየሁም። ምናልባትም የሴቶችን ድርሻች አጉልቶ ካለማሳየት የመጣ ካልሆነ በስተቀር። የብዙ ሴቶችን ቀጥተኛ ተሳትፎ ብንተወው እንኳ በእናትነት፣ በእህትነትና በሚስትነት
ለነጻነት ትግሉ ትልቅ አስተዋጾ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ።
በማነኛውም መስክ ውጤታማ ለመሆን በጥሩ ሥነ ምግባር አንጻ፣ ተንከባክባና አስፈላጊውን
ድጋፍ ልታደርግ የምትችል እናት፣ አይዞህ የምትል እህት እና ስነ ልቦናዊም ሆነ አካላዊ ብቃት የምትገነባ፣ የደስታ ምንጭ የሆነችና
እና ጥበበኛ ሚስት ያስፈልጋል። ሴቶች ትውልድን የመግደልም ሆነ የማዳን ችሎታውና እድሉ አላቸው። እኛ ሴቶች ሁኔታዎች ከተመቻቹልን
ሀገርን ሊጠቅም የሚችል ትውልድ ማፍራት እንችላለን፤ ነጻነትና ፍትህን የማስፈን ብቃቱና ችሎታው ያንሰናል ብዬ አላምንም። ይህን
ያደረጉ እናቶቻችን በታሪክ ተዘግበው እናገኛቸዋለን። ለአብነት ያክልም ኢትዮጵያውያንን እትጌ ጣይቱን እና ንግሥተ ሳባን ማንሳት
ይቻላል።
እትጌ ጣይቱ በነበረችበት ዘመን የወንድ የበላይነት በእጅጉ የነገሠበት ቢሆንም የነበረው
ሕግና ባህል ሳይገድባት በፖለቲካው መስክ የነበራት ተሳትፎ ቀላል አልነበረም። ታሪክ እንደሚያስረዳን እቴጌ ጣይቱ በዘመኑ በነበረው
ባህልና ወግ መሰረት የአጼ ምኒሊክ ታማኝ ሚስትና የቤት እመቤት መሆኗ ወደ ኋላ ሳያስቀራት የወታደር መሪ፣ የጦርነት ስልት ቀያሽ፣
ታላቅ ሥልጣን የነበራት እና የሴቶችን እኩልነት በተግባር ያሳየች እናትና ወታደር እንዲሁም ባለስልጣንና አስተዋይ መሪ ነበረች።
ኢትዮጵያ ሀገራችን በቅኝ እንዳትገዛ አፄ ምንሊክ የውጫሌን ውል በመቅደድ/በመሰረዝ ሀገሪቱ በጣልያን ላይ ጦርነት እንዲታወጅና ድልን እንድትቀዳጅ ጠንካራ አቋም
እንዲወሰዱ ያደረገች ጀግናዋ ጣይቱ ስለመሆኗ ታሪክ ህያው ምስክር ነው። እቴጌ ሁሉም
ኢትዮጵያዊ ለመብቱ፣ ለነፃነቱና ለክብሩ የጣሊያንን ወረራ መመከት እንደሚገባው በአጽንኦት አሳስባለች፡፡ በጦርነቱ ወቅትም ጣይቱ
በርካታ ወታደር በብቃት መምራቷ፣ አስተማማኝ የሆነ ወታደራዊ ስልት በመንደፍ እና ለጣሊያን የውኃ ምንጭ የነበረውን የውኃ ግድብ
በወታደር አስከብባ ጣሊያን እንዲዳከም ማድረጓ፣ ከዚያም ኢትዮጵያውያን ሴቶች በተዋጊነትና በጦርነቱ የተጎዱትን ወታደሮች የህክምና
እርዳታ እንዲሰጡ በማድረግ የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጋለች። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሀገራችንን በዓለም ከአስጠሩ ነገሥታት
መካከል ንግሥተ ሳባ በእንስትነት ቀዳሚውን ቦታ በመያዝ በታሪክ መዘክር ለዘላለም ስትወሳ ትኖራለች።
አገራችን ኢትዮጵያ የሴቶችን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ተሳትፎ ዋስትና ለመሰጠት የሚደረጉ
ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለመፈረም ብዙ ችግር የለባትም። በተጨማሪም የሚሊኒየም ግብ እንፈጽማለን ከሚሉ ሀገሮች መካከል እንደሆነች
በወረቀት ደረጃ ለማስመሰል እየሞከረች ነው። አገራችን የጾታ መድሎን ለማስቀረት እና የጾታ እኩልነትን ለማስፈን በተለያዩ ብሔራዊና
ክልላዊ ፖሊሲዎች ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ እንዲካተት ማድረጓ ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን አድሎው፣ ጭቆናው፣ የጾታ ጥቃቱ እና ከባድ
ማኅበራዊ ኃላፊነት መሸከሙ እንዲሁም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽኖዎች በዘመናዊ መልክ ተጠናክሮ ከመቀጠል ባሻገር ኢትዮጵያ
ውስጥ በተግባር የሴቶችን ዋስትና ማረጋገጥ አልተቻለም። ሴቶች በአደባባይ ሲደፈሩ፣ ሲዋረዱ፣ በስደት ማንነታቸው ሲገፈፍ እና ተቃውሞ
ለመግለጽ ሲሞከር ሕጉ ከለላ ሊሰጠን አልቻለም። በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው የሴቶችና የሕጻናት መብት፣ የቤተሰብና የወንጀል ሕጉ
የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ አልሆነም።
ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማለት ገዥውን ፓርቲ ብቻ መደገፍ፣ ለወያኔ መላላክ፣ ለወያኔ አሽከር
መሆንና ለባለ ሥልጣን ሚስት፣ እናትና እህት መሆን ሳይሆን በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ የመወሰን፣ በሙሉ ነጻነት የመምራት፣ ሃሳብን በነጻ
የመግለጽ፣ የመደራጀት እና የመቃዎም መብት ሲከበር ብቻ ነው። ፖለቲካ ማለት መደገፍ ብቻ ሳይሆን መቃዎምም ነው። ፖለቲካ ማለት በሀገር ጉዳይ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ማለት ነው። ፖለቲካ ማለት ነጻነት፣ፍትህና
ዲሞክራሲ እንዲሰፍን መታገል ማለት ነው እንጂ እንደ ወያኔ ለስልጣን
ብሎ ህዝብን ማሰቃየት፣ ሀገርን መሸጥ፣ በብሄር፣ በቋንቋ ከፋፍሎ መግዛት እና የሀገርን ሀብት ንብረት ጠቅልሎ መያዝ ማለት አይደልም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት፣ ፍትህ፣ የሰባዊ መብት መከበርና ዲሞክራሲ የሚባል ነገር
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል። ሴት፣ ወንድ፣ወጣት፣ አዛውንት፣ የተማረ፣ ያልተማረ እና ንጹሃን ዜጎች ሳይባል እስር፣ እንግልት፣
ስደትና ሞት በይፋ እና በስውር በወያኔ ባለስልጣናት ይደርስባቸዋል። በሀገራችን ላይ የሰባዊ መብት ጥሰቶች፣ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው
ግፍና ጭቆና ከሚባለው በላይ ጨምሯል። የሴቶች መደፈርና የወሲብ ንግዱም በእጅጉ ተባብሶ ቀጥሏል። አለም ዓቀፍ ድርጅቶች ይህንን በገሀድ እየገለጹ ይገኛሉ። ሆኖም
ግን የህወሓትን ማፍያ ቡድን ተቋቁመው ብዙዎች በብዙ ስቃይና መከራ ለነጻነት ዋጋ እየከፈሉ ነው። ሴት እህቶቻችንም በዚህ እውነተኛ
ትግል ውስጥ ሰማዕትነትን እየተቀበሉ ይገኛሉ። ብዙ እህቶቻችን በእስር ቤት ውስጥ ስቃይ፣ መከራና ጾታዊ ጥቃት ያስተናግዳሉ። ርዮት
ዓለሙን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። እነ ማህሌት ፋንታሁን፣ ወይንሸት አስፋውን እና ሌሎች በእስር ቤት ለነጻነት ሲሉ ስቃይና መከራ
የሚቀበሉ እንስት እህቶቾን ሳላወሳ ማለፍ አልፈልግም።
ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ በሃገራችን ለማስፈን፣ ሰባዊ መብትን ለማስከበር እና ዘላቂ
ልማትን ለማረጋገጥ የእኛ የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ተፈጥሮና ባህል ለሴትም ለወንድም የተለያየ ኃላፊነቶችን ሰጥተውናል፡፡ በዚህም
መሰረት ሴት ልጅ በተፈጥሮ ልጅ በሆዷ ዘጠኝ ወር ተሸክማ መውለድ እና የማጥባት ስራ የሷ ብቻ ነው፡፡ ይህን ምንም ልናደርገው የማንችለው
ተፈጥሮ የለገሰችን ጸጋና ኃላፊነት ነው።ነገር ግን በተፈጥሮ የተሰጠን ጾታ እና ማንነት ከትግል ሊበግረን አይገባም። በይበልጥም
እኛ ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኩል እንደወንዶች የመወሰን እና የመምራት ኃላፊነት ቢኖረን በተሻለ
መልኩ ሀገርን መለወጥና ትውልድን መቅረጽ እንችላለን። ስለሰባዊ መብት መከበርም ተግተን እንሰራለን፤ ምክንያቱም ርህራሄና ሰባዊነት
ተፈጥሮ በለገሰችን በእናትነት አማካኝነት እንዲሁም አመራርንና ማስተዳደርን በማህበራዊ ህይወታችን በሚገባ እናውቃለንና።
ስለዚህ ፖለቲካዊ ተሳትፎ፣ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ መታገል በተፈጥሮ ለወንድ ብቻ የተሰጠ
አይደለም። እኛም ሴቶች የሀገር ጉዳይ ያገባናል። በትዳር ደስተኛ ሁኖ ለመኖር፣ ልጆቻችን ስደትን ከመናፈቅ ይልቅ በሰላም በሀገራቸው
ታሪክና ባህል ይኮሩ ዘንድ፣ ዜጎች በእኩልነት ተከባብረው ይኖሩ ዘንድ እና ወጣት እህቶቻችን የወሲብ ንግድ እንዳይፈጸምባቸው ለማድረግ
በመጀመርያ እኛ ሴቶች ለነጻነት ትግሉ በምንችለው አቅም አስተዋጾ ማበርከት ይጠበቅብናል። ዝናር ታጥቀው፣ ብረት አንግበውና ጋሻ
አንስተው ነጻነት ፍለጋ በርሃ የወረዱ እህቶቻችን ቆራጥነትና የዓላማ ጽናታቸውን እኛም ልንላበሰው ይገባል። በእያለንበት ትግሉ ወደፊት
ይሄድ ዘንድ እና ትውልድ ሁሉ በነጻነት በሀገሩ ይኖር ዘንድ የድርሻችንን እንወጣ። ወንድ አደባባይ ሴት ወደ ቤት የሚለውን የማይጠቅም ኋላ ቀር ብሂል ወደ ጎን
ትተን በአንድነት፣ በመደራጀትና ዘመናዊ ስልት በመንደፍ ከፋፋይና ዘረኛ ወያኔን ከህዝብ ትክሻ ላይ ለማስወገድ እንትጋ። እኛ ሴቶች
ለነጻነት ትግሉ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረግ እንደምንችል በተግባር ማሳየት አለብን። ምክንያቱም ለነጻነት ትግሉ የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ
ነውና።
ፍትህና ነጻነት
ለታሰሩ ወገኖቻችን! ፍትህ ለርዮት፣ ለማህሌት፣ ለወይንሸት!!!
No comments:
Post a Comment