Wednesday, 3 September 2014

ኑና እንወያይ

ኑና እንወያይ

የወያኔ ዘረኞች የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌን ፍጹም ህገወጥ በሆነ መንገድ አስሮ ማሰቃየት ከጀመሩ እነሆ ሃምሳ ቀኖች ተቆጥረዋል። ሠላማዊ ዜጎችን ሽብርተኛ ብለዉ ካሰሩ በኋላ የፈጠራ ታሪክ እየጻፉ የቴሌቪዥን ድራማ መስራት የለመዱት ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በአቶ አንዳርጋቸዉ ላይም በዉሸት የተቀነባበረ ድራማ ሰርተዉ የዚህን ጀግና ሰዉ ተክለሰዉነት ጥላሸት ለመቀባት ሞክረዋል። ሆኖም ቆሻሻ ፈብራኪዎቹ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ተቋሞች ያሻቸዉን ድራማ ቢሰሩም በአለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአንድ ድምጽ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” እያሉ ትግሉን በመቀላቀል ግንቦት 7 የዕልፍ አዕላፍት ድምጽ አንጂ የአንድና የሁለት ሰዎች ድርጅት አለመሆኑን በተግባር ለወዳጅም ለጠላትም አሳይተዋል። በእርግጥም ግንቦት 7 ወያኔ አንዳርጋቸዉን ካሰረ በኋላ ህዝብን ለማታለል እንደሞከረዉ ያበቃለት ድርጀት ሳይሆን ወያኔና ቆሻሻ ስርዐቱ ተጠራርገዉ ቆሻሻ መጣያ ዉስጥ እስካልገቡ ድረስ በየቀኑ እያደገ የሚሄድ ህዝባዊ መሠረት ያለዉ ድርጅት ነዉ።
ዛሬ ኢትዮጵያን ጨምሮ በየአህጉሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአካል ሲገናኙም ሆነ በማህበራዊ ሜዲያዎች ሲሰባሰቡ አንድነታቸዉን የሚገልጹበትና የትግል ቃልኪዳናቸዉን የሚያድሱበት ቃል “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” የሚል ቃል ነዉ። ባለፉት ሃምሳ ቀኖች በዚህ መልኩ በወያኔና በተላላኪዎቹ ላይ ቁጣዉን ሲገልጽ የሰነበተዉ በዉጭ አገሮች የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ወያኔን ባስቸኳይ ለማስወገድ በሚቻልበት መንገድ ለመምከርና ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ ያለዉን ፍቅር በተግባር ለማሳየት ከፊታችን እሁድ ነኃሴ 24 ቀን እስከ መስከረም 4 ቀን ባሉት ሦስት ተከታታይ እሁዶች በ26 ታላላቅ የአለም ከተማዎች ዉስጥ በአይነቱ ልዩ የሆናና ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማያዉቅ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ያደርጋል። የእነዚህ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” በሚል መሪ ቃል የተጠሩ ስብሰባዎች ዋና አላማ አንዳርጋቸዉና ከሱ በፊትም ሆነ ከሱ በኋላ ለእናት አገራቸዉ ኢትዮጵያ አንድነት፤ ሠላምና ብለጽግና ሲሉ የታሰሩና የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ኢትዮጵያዉያን የቆሙለትን አላማ ከግብ ለማድረስ ምን ማድረግ አለብን የሚለዉን ትልቅ ጥያቄ በጋራ ለመመለስ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱና ለነጻነቱ የሚያደርገዉ ትግል ወደመጨረሻዉና ፈታኝ ወደሆነዉ ወሳኝ ምዕራፍ ዉስጥ መግባቱን ሁሉም ኢትዮጵያዉ የተገነዘበዉ ይመስለናል፤ ሆኖም በጋራ ለሚደረግ ህዝባዊ ትግል ህዝብ ቁጭ ብሎ በጋራ ካልመከረበትና ተስማምቶ ለድል የሚወስደዉን ጎዳና በጋራ ካልቀየሰ ትግላችን ወሳኝ ደረጃ ላይ መድረሱን መገንዘቡ ብቻ በራሱ ፋይዳ ይኖረዋል ብለን አናምንም። ስለሆንም በአነዚህ ብዙዎችን አቀራርበዉና አወያይተዉ ለህዝባዊ ትግሉ የሚበጁ ጠቃሚ ሀሳቦችን ያፈልቃሉ ብለን በምናምንባቸዉ ስብሰባዎች ላይ የአገሬ ጉዳይ ከግል ጉዳዬ በላይ ነዉ ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተገኝቶ የበኩሉን አስተዋጽኦ አንዲያደርግ የዝግጅት ክፍላችን በዚህ አጋጣሚ አገራዊ ጥሪ ያደርጋል።
ለመሆኑ በአለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ድምጻቸዉን ከፍ አድርገዉ በየአደባባዩና በየስብሰባ አዳራሹ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” እያሉ ሲጮኹ ምን ማለታቸዉ ነዉ? ወያኔ ስልጣን ይዞ በቆየባቸዉ ባለፉተረ ሃያ ሦስት አመታት ዉስጥ አያሌ ኢትዮጵዉያን የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ አርበኞች ታሰረዋል፤ ዘግናኝ በሆነ መልኩ ተገርፈዋል ብዙዎች ደግሞ ተገድለዋል። ኢትዮጵያዉያንን እያፈሱ ማሰር በአንዳርጋቸዉ አልተጀመረም አንዳርጋቸዉ ስለታሰረም አያበቃም። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች እኛ በቃ ብለን ካላቆምናቸዉ በቀር እኛን ማሰርና መግደል በስልጣን ላይ የመቆየት ዋስትናቸዉ አድርገዉ ስለሚመለከቱ መግደላቸዉንና ማሰራቸዉን በፍጹም አያቆሙም። እንግዲህ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” ስንል ኢትዮጵያ ዉስጥ በዘፈቀደ ዜጎችን ማሰርና መግደል እንዲቆምና አናሳዎች በሀይል የጫኑብን ዘረኛና አግላይ ስርዐት ተደምስሶ ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ ስርዐት እንዲፈጠር ማድረግ የምንችለዉን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም ማለት ነዉ። ይህ ማለት ደግሞ አንዳርጋቸዉ ጽጌ፤ እስክንድር ነጋ፤ ኡስታዝ አቡበከር፤ በቀለ ገርባ፤ ሠላማዊት ሞላ፤አዚዛ መሐመድ፤ ርዕዮት አለሙና ሌሎችም ለአገር አንድነትና ለህዝብ ነጻነት ሲታገሉ የዘረኞች ሰለባ የሆኑ ጀግኖቻችን የቆሙለትን አላማ አንግበንና ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን ወደማይቀረዉ ድል እንጓዛለን ማለት ነዉ።
ዛሬ ሁላችንም በግልጽ እንደምንመለከተዉ ኢትዮጵያዉያን በያሉበት ቦታ ሁሉ ትግሉን እንዴት እንቀላቀል፤ ምን ላድርግ ወይም እንዴት ትግሉን ልርዳ የሚሉ ጥያቄዎችን በየቀኑ እየጠየቁ ነዉ። እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ አንዳርጋቸዉ ስለታሰረ ብቻ ሰኞ ተረግዘዉ ማከሰኞ የተወለዱ ጥያቄዎች ሳይሆኑ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሆድ ዉስጥ ከሃያ አመታት በላይ ታፍነዉ የቆዩና በአንዳርጋቸዉ መታሰር ፈንድተዉ የወጡ ጥያቄዎች ናቸዉ።
የወያኔ ተላላኪዎች አንደሚከስሱን የአገር ጥላቻ ሳይሆን የአገር ፍቅር ጥያቄዎች ናቸዉ፤ ዘረኝነትና ጎሰኝነት የቀሰቀሳቸዉ ጥያቄዎች ሳይሆኑ ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዘረጋዉን ያጋጠጠ የዘረኝነት ስርዐት ለማፍረስና በቦታዉ ሁሉንም የአገሪቱ ዜጎች በእኩልነት የሚመለከት ስርዐት ለመፍጠር የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸዉ። ግንቦት ሰባት በሃያ ስድስት ከተማዎች ዉስጥ የጠራቸዉ ህዝባዊ ስብሰባዎች እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን የሚመልሱ ስብሰባዎች ናቸዉ። እነዚህ ስብሰባዎች ከዚህ ቀደም እንደተለመደዉ ከመድረክ ላይ የሚወረወሩ ሀሳቦችን ብቻ አስተናግደዉ የሚበተኑ ስብሰባዎች አይደሉም። እነዚህ ስብሰባዎች የስብሰባዉ አዘጋጆችና የስብሰባዉ ተሳታፊዎች በአንድ መንፈስ ሆነዉ ይህንን የተበታተነ ህዝባዊ ትግል የሚያስተባብርና ትግሉን በተቀናጀ መልክ እንዴት ለድል ማብቃት እንደምንችል የምንመክርባቸዉ ሁሉን አቀፍ ስብሰባዎች ናቸዉ።
በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ወያኔ ግምገማ ወይም ስልጠና እያለ እንደሚያዘጋጃቸዉ መድረኮች ካድሬዎች መመሪያ እየሰጡ ህዝብ ደግሞ ወደደም ጠላ መመሪያዎቹን ተግባራዊ የሚያደርግበት የአንድዮሽ መድረኮች ሳይሆኑ ህዝብ በአገሩ ጉዳዮች ላይ በሚወሰኑ ዉሳኔዎችና በተግባራዊነታቸዉ ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተሳትፎ የሚያደርግባቸዉ የሁለትዮሽ መድረኮች ናቸዉ። በሃያ ስድስቱም ከተማዎች ላይ የሚሰበሰበዉ ህዝብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል? ከምሁራን ምን ይጠበቃል? ከሴቶች ምን ይጠበቃል? ከወጣቶች ምን ይጠበቃል ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ ዘረኞች ጋር የሚያደርገዉ የሞት ሽረት ትግል በአንድ ምዕራፍ የሚገባደድ፤ በጥቂት ሰዎች የሚሰራ ወይም አንዱ ታጋይ ሌላዉ ገላጋይ ሆኖ የሚታይበት ትግል አይደለም። ይህ ትግል ብዙ ምዕራፎች ያሉት፤ እልፍ አዕላፋት የሚሳተፉበትና ሁሉም የየራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግበት የጋራ ትግል ነዉ። ግንቦት ሰባት ይህንን እዉነታ የሚረዳ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወደእነዚህ ስብሰባዎች በብዛት በመምጣት በአገሩ የወደፊት ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ አገራዊ ጥሪ ያስተላልፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
እናሸንፋለን!!

No comments:

Post a Comment