ሰኔ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :- ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲ ፍትሀዊ እና ግልጽ በሆነ ምርጫ ተመርጠው ለአንድ አመት ያክል በስልጣን ላይ ከቆዩ በሁዋላ በህዝብ ተቃውሞና በወታደራዊ ግፊት ከስልጣን እንዲወርዱ ተደርጓል።
ፕሬዚዳንቱ በአንድ አመት የስልጣን ጊዜያቸው ፣ እርሳቸውን ለስልጣን ያበቃውን የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባላትን ከመጥቀም ባለፈ የፈየዱት ነገር የለም በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ቆይቷል። በአገሪቱ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን ስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት እና የጸጥታ ችግር ተከትሎ በርካታ የግብጽ አብዮታዊ ወጣቶች ” ለዚህ ነበር የታገልነው” በማለት ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አንደኛ አመት የስልጣን ጊዜያቸውን ለማክበር ሽር ጉድ በሚሉበት ጊዜ “ታማሮድ” ወይም አመጸኞች በማለት ራሳቸውን ሰየሙ የግብጽ ወጣቶች ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲነሱ የሚጠይቁ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፊርማዎችን ከመላው አገሪቱ አሰባሰቡ። ከፊርማ ባለፈ ተቃውሞአቸውን በአደባባይ ማሰማት ጀመሩ። ሺዎች ወደ አደባባይ ጎረፉ። የህዝቡን ስሜት የተረዱ የሚመስሉት ወታደራዊው አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ፕሬዚዳንቱ የተቃዋሚዎችን ድምጽ እንዲሰሙ ጠየቁ። ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱን እንዳልወደዱት ቢገልጹም፣ በሁዋላ ሁኔታው እየገፋ መሄዱ ስላሰጋቸው ጥምር መንግስት የማቋቋም ሀሳብ አቀረቡ። ተቃዋሚዎች ግን የሚቀበሉት ሆኖ አልተገኘም።
ጄኔራል ሲሲም ለውጥረቱ ማስተንፈሻ የሚሆን አዲስ አቅጣጫ መቀየሳቸውን አስታወቁ። በዚህ መሰረት የአገሪቱ ህገመንግስት ፈረሰ ፕሬዚዳንት ሙርሲም ከስልጣን ተነሱ።
የፕሬዚዳንት ሙርሲ ከስልጣን መነሳት የአለምን ህዝብ እያወዛገበ ነው። አንዳንድ ወገኖች በዲሞከራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መሪ ከስልጣን መውረድ የሚገባው በህዝብ ተቃውሞና በወታደራዊ መንገድ ሳይሆን በምርጫ ብቻ ነው በማለት ድርጊቱን ከመፈንቅለ መንግስት ጋር ሲያይዙት ፣ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ወታደሩ ስልጣኑን ለፍትህ ሚኒሰትሩ አል ማንሱር በጊዜያዊነት በማስረከቡ መፈንቅለ መንግስት ነው ተብሎ ሊታይ አይገባውም በማለት ይሞግታሉ።
ምእረባዊያን አገራት እርምጃውን መፈንቅለ መንግስት በማለት አለመጥራታቸውን ተከትሎ በሙርሲ ከስልጣን መነሳት የተደሰቱ ይመስላሉ የሚሉ አስተያየቶች በብዛት እየቀረቡ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም 2ኛውን አብዮት “መፈንቅለ መንግስት” ብሎ ከመፈረጅ ተቆጥቧል።
አብዛኞቹ የአረብ አገራት ድርጊቱን ሲደግፉት ፣ በውስጥ ችግሩ እየታመሰ የሚገነው የሶሪያ መንግስት አስተያየት ግን ያልተጠበቀ ሆኗል። ፕሬዚዳንት በሽር የግብጽን ወጣቶች አወድሰው፣ እስልምናን ለፖለቲካ ስልጣን መያዢያ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሀይሎች እንደማያስካላቸው ያመላከተ ነው በማለት እርምጃውን ደግፈዋል።
ብዙዎች ” ሙርሲን ከስልጣን ማውረድ ፣ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ከስልጣን እንደማውረድ ቀላል ላይሆን ይችላል” ይላሉ። የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች እርምጃውን አንቀበልንም በማለት ትግላቸውን ከቀጠሉ በሶሪያ የሚታየው አይነት ደም መፋሰስ ሊከተል እንደሚችል እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ። እርምጃው የአብዛኛውን ህዝብ ድጋፍ ያገኘ በመሆኑ እና ምርጫ በፍጥነት ሊካሄድ የሚችልበት እድል ሰፊ በመሆኑ የተፈራው ችግር አይከሰትም በማለት የሚናገሩም አሉ።
No comments:
Post a Comment