የነፃነት ቀበኞች (ፀሮች) የተደራጁትም ያልተደራጁትም ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጡንቻቸውን አፈርጥመው፣ ክራንቻቸውን ስለው፣ ጥፍሮቻቸውን ወድረው ሊዘነጣጥሉ የሚችሉበት አቅምና ጉልበት አላቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ያ ጉልበት ስለሌላቸው፣ ቀበኛ ባሕሪያቸውን በጩኸትና በስም ማጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው ያከናውኑታል፡፡ በልዩ ልዩ መልክና ቅርጽ የተደራጁት “የመሠረታዊ ነፃነት ጠሮች (ቀበኞች)” ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ገሚሶቹ በገዢነት (በፓርቲነት)፣ አንዳንዶቹ በሃይማኖታዊ ማኅበራት ሽፋን፣ ሌሎቹ ደግሞ በአነስተኛና ጥቃቅን ቡድንነት የተደራጁ አዳሚዎችና አሳዳሚዎች ናቸው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በአንድ-ለአምስት ሕዋስ ሥር (as a gangster) የተደራጁ “የጎበዝ አለቆች” ናቸው፡፡ በነዚህ አካላት ጭፍን አካኼድ የተነሳ፣ የዜጎች መሠረታዊ ነፃነትና መብት ይደፈጠጣል፡፡ የሥልጣናቸውና የመጉዳት አቅማቸው መጠን የተለያየ ይሁን እንጂ፣ ሁሉም የመሠረታዊ ነፃነት ቀበኞች (ፀሮች) ናቸው፡፡ ለምን እንደሆኑና እንዴትስ ከዚህ ደረጃ እንደደረሱ ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ፡፡
የሥነ-መንግሥት ተመራማሪዎች፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ነፃነት አለ-ይላሉ፡፡ ሁሉንም ለመዘርዘር አልቃጣም፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ የሐሳብ መስጠት ነፃነት፣ አንድ ሰው አምላኩን ሃይማኖቱ በሚፈቅደው መንገድ የማምለክ ነፃነት፣ ተሰብስቦ የመወያየት ነፃነት፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት፣ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትና ነፃነት፣ የመሳሰሉት እያሉ ይዘረዝራሉ፡፡ ሁሉም ታዲያ “ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ነው የሚከወኑት” ይላሉ፡፡ አልተተገበረም አንጂ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 27 መሠረት፤ የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት የዜጎች መብት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 መሠረት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመድረግ ነፃነትና አቤቱታንም የማቅረብ መብትን በተመለከተ ነጩ ወረቀት ላይ ሰፍሯል፡፡ ግን አልተተገበረም፡፡ የከፋ በደል ነው፡፡ የበደልም በደል! (“የሰው ልጅ በሠለጠኑትም ሆነ ባልሰለጠኑት አገሮች መሠረታዊ ነፃነት እንጂ ፍፁም ነፃነት ሊያገኝ እንደማይችል የሚታወቅ ነው፤” ሲሉ ተመራማሪዎቹ ያክላሉ፡፡)
ስለ“መሠረታዊ ነፃነት” ምንን ከመጻፌ በፊት፣ ስለዚህ የነጻነት ዓይነት ለመፃፍ ያሳሰቡኝን ምክንያቶች ላነሣ እፈልጋለሁ፡፡ የመጀመሪያው የሩዶልፎ ግራዚያኒ ደጋፊዎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 30 መሠረት፤ “የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመድረግ ነፃነትና አቤቱታንም የማቅረብ መብትን” እንዴት በካልቾ እንደመቱት በመመልከቴ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ፣ አንዳንድ ሰዎች (በግልም በቡድንም ሆነው) እንዴት የሌሎችን መሠረታዊ ነፃነት እንደሚጣረሩ ለማሳየት ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሜ ግን፣ “ነፃነት ማለት ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም እሞክራለሁ፡፡ በአቦ ሰጡኝ የመጣልኝ መልስ፣ “ነፃነት የሰው ልጅ ከአላህ ወይም ከእግዚአብሔር (አዳላህ እንዳትሉኝና ከእግዚአብሔር ወይም ከአላህ) በተፈጥሮ የተሰጠውን ክብር መጠበቂያው ሚዛን ነው፡፡” የሚል ሆነ፡፡ መሠረታዊ ነፃነት የሌለው ሰው፣ በሰው ፊት ሰው የበለጠው፣ ከሰው በታች የሆነም ነው፡፡ ነፃነት የሌለው ሰው፤ በሰው ፊት የተዋረደ፣ የተናቀ፣ ሕቁር (Inferior) ፍጥረት ነው፡፡ ነፃነት የሌው ሰው በአፀደ ሕይወት ቢኖር እንኳን፣ መኖሩ እንደሰው ሳይሆን እንደዕቃ፤ እንደ“እንትና” ሳይሆን እንደ“እንትን” የሚታይና የሚቆጠር ፍጡር ነው፡፡ “እንትን” የሚል ቅጽል የሚሰጠው፣ መሠረታዊ ነፃነት ለሌለው ሰው ነው፡፡ እንትንነት ክብራቸውን በፍርፋሪ ለሸጡና መሠረታዊ ነፃነታቸውን ለተገፈፉ የሚሠጥ ቅጽል ነው፡፡ ለሕቁር ፍጥረታት የሚሠጥ ቅጽል ነው፡፡ እንደዔሳው የብኩርና ክብራቸውን በምስር ንፍሮ ለሸጡና ለለወጡ ፍጥረታት የሚሠጥ ስያሜ ነው፡፡ እነዚህ አምላክ/ፈጣሪ በተፈጥሮ የሰጣቸውን ክብር የቸበቸቡ ፍጥረታት ደግሞ፣ ሰላማዊ ሰልፎችን የሚከለክሉ፣ የመናገርንና የመጻፍን መብት ለመገደብ የሚንጠራወዙ፤ ፖሊስ ወይም የፀጥታና ደኅንነት ኃይል ተቀጣሪዎች ሲሆኑም ሌሎችን በዱላ የሚደበድቡ፣ የሚሳደቡና በተራ ስም አጥፊነት ተግባር የሚጠመዱ ናቸው፡፡ ኅቁር ፍጥረታት ክብር ስለሌላቸው፣ ማንንም አያከብሩም፡፡
ኅቁር ፍጥረታት ሰላማዊ ሰልፍ ሲሏቸው፣ እፊታቸው ድቅን የሚልባው የአመጽ ሰልፍ ነው፡፡ ለኅቁር የፀጥታና የዘመኑ ሹሞች የሚታያቸው፣ በሕግ ፊት ሰዎች እኩል መሆናቸው ሳይሆን፣ ተደብዳቢነታቸው ነው፡፡ ኅቁራን ሹሞችና አሽቃባጮቻቸው፣ ሰብዓዊ መብትን መጣስና መሠረታዊ ነፃነትን ማሳጣት የእንጀራ ገመዳቸው እንዳይበጠስ ማረጋገጫ ነው፡፡ ኅቁራን ባለሥልጣኖች፣ የጉልበት ሥልጣን እንጂ የመንፈስ ሥልጣን የላቸውም፡፡ ለኅቁር ፍጥረታት፣ ካላግባብ በአሸባሪን ስለታሰሩ ወገኖቻችን ሲነገራቸው፣ እንደሰረሰር ሰርሳሪ የቄራ ለማጅ፣ ዋናውንና ሙዳውን ስጋ ትተው አገጭና ሌንጬጭ ይፈልጣሉ፡፡ ኅቁራን ፍጥረቶች፣ “ለአህያ ማር አይጥማትም” እንደሚባለው፣ ትልቁ ዓላማ አይጥማቸውም፡፡ ለኅቁር ፍጥረታት፣ መሳደብና ስም ማጥፋት ቋሚ ተግባራቸው ነው፡፡ ለኅቁራን፣ መቼም ቢሆን የቃላት ስንጠቃና “ከቁንጫ መላላጫ” ማውጣት የተለመደ ተግባር ነው፡፡
እንደአለመታደል ሆኖ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ገዢዎች የዔሳው የመንፈስ ልጆች ናቸው፡፡ የእነሱ አጫፋሪዎችና ሎሌዎቻቸው ደግሞ የባሰባቸው “ኅቁሮች” ናቸው፡፡ ኅቁርነት፣ “ከመምህሩ ደቀ-መዝሙሩ” እንደሚባለው እየከፋና እየሰፋ የሚሄድ ነቀርሳ (Cancer) ነው፡፡ በቅርቡ ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት፣ ኅቁራን “በቆብ ላይ ሚዶ” የሚሽጡም ናቸው፡ በዚህ አላዋቂነትና ጠብደል መታወር ውስጥ እየኖሩ እንደምን የሌሎችን መሠረታዊ ነፃነት ሊያከብሩ ይችላሉ? ፈጽሞ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ስለሠጠው መሠረታዊ ነፃነት ስለማያውቁ፣ ወይም በያውቁም ሆን ብለው ስለሚክዱት፣ የሌሎችን ነፃነትና ክብር የገፋሉ፡፡ (ኋላ እመለስበታለሁ፡፡) አባቶቻችን አገራችን በተወረረች ጊዜ ነፃነትን አጥቶ ሆድን በፓስታና በሹታ ጎስሮ፣ ገላን በአቡጀዲና በጨርቅ ሸፍኖ ከመንቀዋለል ይልቅ፣ መሠረታዊ ነፃነትን ማጣት ምን እንደሚደርስባቸው ስላወቁ፤ “ነፃነት ወይም ሞት!” ብለው በጀግንነት ተጋድለው አለፉ፡፡ በፍርሃትና በጥቅመኝነት ታውረው፣ “ከመሞት መሰንበት” ያሉትም ቢሆኑ፣ ያለመሠረታዊ ነፃነት መኖር ምን ምን እንደሚል አሳምረው ቀምሰውታል፡፡ በዱር በገደል የተጋደሉትና በእስር አዚናራ የተጋዙት ምንኛ እድለኞች ነበሩ?
በነሐሴ 1960 ዓ.ም በወጣው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ ስለመሠረታዊ ነፃነት ሲያወሱ፣ “የባሕል ነፃነት ነው” በማለት ሊገልፁት ሞክረዋል (ገጽ 5 ላይ ይመልከቱ)፡፡ “በሀገራችንና በሕዝባችን ዘንድ የባሕል ነፃነት ወይም የመሠረታዊ ነፃነት ከነትርጉሙም አይታወቅም፡፡ ነገሩ ግን የሀገርን ነፃነት የማጣትን ያህል ደም የሚያፋስስ ነው፤” (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ነሐሴ 9/1960)፡፡ ይሄው የመሠረታዊ ነፃነትን የማጣትና የማሳጣት ተንኮል፣ ከጥንት ጀምሮ በምዕራባውያን (በቄሳራውያን ሃይሎች) ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ መሠረታዊ ነፃነት ገፈፋው ዘዴ በጣም ረቂቅና ስልታዊም ነው፡፡ ከባሕልና ከመሠረታዊ ነፃነት ገፈፋ ስልቶች መካከል አንዳንዶቹን ለመጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ የመጀመሪያው ዘዴ፣ የገዢዎችን መብት ለአንዳንድ ተገዢዎች መስጠት ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ተገዢዎች ማንነታቸውን ክደው፣ የሀገርና የብሔራዊ ስሜታቸውን ማስካድ ነው፡፡ ሦስተኛውና ዋናው ችግር ደግሞ፣ ተገዢው ባሕሉንና ወጉን እንዲንቅና በራሱ እንዳይተማመን የማድረግ የሥነ-ልቦና ክሽፈት ነው፡፡
ከመጀመሪያው ነጥብ ጀምሮ መተንተን ያለበት ነው፡፡ ገዢዎቹ ለአንዳንድ ተገዢዎች፤ “በብሔር፣ በዘር ወይም በሃይማኖት ተዋጽዖ ስም” የይስሙላ የገዢነት መብት ይሠጧቸዋል፡፡ የአገሩን ሰርዶም በአገሩ በሬ ማለት እንደዚህ ነው እያሉ ይደልሏቸዋል፡፡ ጣሊያን አንዴ ልጅ አያሱን ልጅ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የአፄ ዮሐንስን ወይም የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ልጆች ከተገዢነት አውጥታ ገዢ ልታደርጋቸው ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ገዢዎች የሚከተሉት ስልትና ብልሃት ተመሳሳይ ነው፡፡ መሠረታዊ ነፃነቱን የተገፈፈው ሰው፣ የነፃነት ገፋፊውን ቋንቋና አነጋገር በቅጡ እንዲኮርጅ ከተደረገ በኋላ፣ የነፃነት ገፋፊውን አገር ዜጎች ያላቸውን ክብርና የይስሙላ ማዕረግ ይሰጡትና፣ የትውልድ አገሩንና የወገኖቹን መሠረታዊ ነፃነት የሚንድ “ምልምል አሽከር” ይሆናል፡፡ እንደዚያ ለመሆን የሚጠበቁበት ነገሮች ቀላል ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ቋንቋውን ማጥናት፣ ሁለተኛ፣ የወራሪውን ሀገር ዜጎች አክባሪ መሆኑን ለማሳየት መስገድ/እጅ መንሳት፣ ሦስተኛ፣ የወራሪውን አገር ከትውልድ አገሩ በላይ እንደሚያፈቅርና እንደሚወድ ማሳየት ነው፡፡ በተቻለ መጠን የሀገሩ ሕዝብና የሀገሩን ፍቅር ክዶ የብሔራዊ ስሜቱን አንጠፍጥፎ ደፍቶ ሞራለ-ቢስ መሆን በቂው ነው፡፡ ያን ጊዜ፣ ከተገዢነት ወጥቶ፣ የፈረስ ስም ተሰጥቶት፣ (ማጆር፣ ወይ ሰር፣ አልያም ደግሞ አፈ-ቄሳር፣ ማንትሴ እየተባለ) የይስሙላ ገዢ/ሹም ይሆናል፡፡ እንዴት ዓይነት አዘቅት ነው ጃል!
ሌላው ከተገዢነት ደረጃ ወጥቶ ወደ ይስሙላ ገዢነት መብት የሚደርስ ሰው፣ ከአፋፉ ጫፍ ላይ ለመድረስ ክህደትን የሙጥኝ ማለት አለበት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የይሁዳ ሰው ሆኖ ሳለ፣ የገዢዎቹን ሮማዊነት መብት ያገኘውና ከእስር ቤት የተለቀቀው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ እንደጳውሎስ ያለውን መብት ያገኘ ሰው፣ ከእስር ቤት ወጥቶ ስለፎለለ ነፃነትን ያለገደብ ያገኘ ይመስለዋል፡፡ ለሌሎች ተገዢዎችም ትልቅ ሰው መስሎ ስለሚታያቸውና በየአደባባዩም ስለሚወጣጠርና ስለሚበጣጠስም ጭምር፣ እርሱን መስሎ ለመገኘትና እርሱ የደረሰበት የክህደት አፋፍ ላይም ለመቆም ብዙ ወገኖቹ በማመጽ ፈንታ ጀርባቸውን ለሸክም፣ ኅሊናቸውንም ለሎሌነት ይሰጡታል፡፡ ተገዢዎች መሠረታዊ ነፃነታቸውን ለማግኘት ከመታገል ይልቅ፣ የገዢነትን መብት ለማግኘት ይንጠራወዛሉ፡፡ ብዙዎችም ነፃነት የሚባለውን አኃዝ ከነመኖሩም ይረሱታል፡፡ ትግሉ ሮማዊ፣ እንግሊዛዊ፣ አሜሪካዊ፣ ፈረንሳዊ፣ ጣሊያናዊ፣ ሳዑዲአረባዊ ወይም ሊባኖሳዊና ኳታራዊ ምንትስ ለመሆን መንጠራራት ይሆናል፡፡ ገዢዎች ከሚሠሩት ሃጢያት ሁሉ እንዲዚህኛው ዓይነት በክፋት የተሞላና የረጅም ጊዜ ቀውስ የሚያስከትል መርዝ የለም፡፡
ነፃነት ገፋፊዎች ይሄንን ሳያደርጉ ሁለት ዓላማዎችን ይዘው ነው፡፡ 1ኛ) የገዢዎቹን (የራሳቸውን) ትልቅነትና የሌላውን ትንሽነት አሳምኖ የበላይም ሆኖ ለመኖር የተዘየደ ደባ ነው፡፡ 2ኛ) አገሩና ሕዝቡም የኋላ ኋላ የይስሙላ ነፃነት ሲሰጠው፣ የባሕል ተገዢ ሆኖ እንዲቀርና የመሠረታዊ ነፃነት ጣዕም ሳይቀምስ እንዲቀር ለማድረግ የተሸረበ ታክቲክ ነው፡፡ በመሆኑም ነፃነት ገፋፊዎች በእቅድና በብልሃት ወደ ዓላማቸው ይደርሳሉ፡፡ አንዱ ዘዴ ከላይ የጠቀስነው የገዢነት መብት መስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ የነሱንና የባሕላቸውን ትልቅነት እንዲሁም ከፍተኝነት የተገዢዎቹንና የባህላቸውን ትንሽነትና ዝቅተኝነት ከልጅነታቸው ጀምሮ በማስተማር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ትምህርት በአንድ ሕዝብ አእምሮ ውስጥ ሲቀረጽ ባሕል ለዘላለሙ ይጠፋል፡፡ አብሮትም መሠረታዊ ነፃነት ድራሹ ይጠፋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በየአውደ ምህረቱ፣ በየመስጂዱ፣ በየማኅበር ቤቱና በየመንዙማ ዝየራው፣ በየጽዋውና በየወዳጃ ቤቱ ሳይቀር የባሕል ወራሪዎቹ ትልቅነት ስለሚሰበክና ስለሚደሰኮ ዜጎች ከማይወጡት የመሠረታዊ ነፃነት እጦት ውስጥ ገብተው እንዲዘፈቁ ይዳርጋሉ፡፡ የፖሊስና የወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ስለገዢዎች የበላይነትና ስለሠልጣኞቹ የበታችነት በዘዴ እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ከዚያ ፀጥ-ለጥ ብለው ተገዢ ከመሆን ውጭ ምርጫ አይኖራቸውም፡፡ ጃስ ሲሉት የሚናከስ፣ ጭላጭ ሲያቀርቡለት የሚልስ ውሻና ድመት ይሆናል፡፡
የተገዢዎቹን ሥነ-ልቦናም የበለጠ ለማኮስመንም ሲባል፣ ገዢው በተገዢው ዓይን ከታምራት የማያንሱ ነገሮችን ሲሰራ እንደነበረና እየሠራም እንዳለ ተደርጎ በየመድረኩና በየአደባባዩ ይደሰኮራል፡፡ ተገዢው ሕዝብ የፈለገውን ያህል ቢማርና ጥበበኛ ቢሆን እንኳን፣ ገዢዎቹ የሚሠሩትን ምትሃት ከቶም የማይደርስበት “ራዕይ” መሆኑን እንዲገነዘብ ተደርጎ ይሰበካል፡፡ የገዢዎቹ ራዕይና አርቆ-አሳቢነት ከሞቱም በኋላ በመገናኛ ብዙሃን እየተደሰኮረለት፣ ለሙት መንፈስ ሳይቀር ታማኝ ሆኖ እንዲገዛ ይደረጋል፡፡ ዱሮ-ዱሮ “ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ” ነበር የሚባለው፡፡ አሁን ደግሞ “ከጓድ አብዮታዊ መሪያችን ጋር ወደፊት!” ወይም “ከባለራዕዩ መሪ ጋር ወደፊት!” በሚል ሽፋን፣ ሕዝቡ መሠረታዊ ነፃነቱን እንዳይጠይቅ፣ አልፎ-ተርፎ ነፃነቱን ሲገፈፍም ዝም ብሎ እንዲያይ፣ “አሜን” ብሎ እንዲገዛም ያመቻቹታል፡፡ (ብቻቸውን አይደለም፣ ጭፍራና ጀሌ አስከትለው ነው፤ ካድሬዎቻቸውን አስደግድገው ነው፡፡)
ፕ/ር ጌታቸው እንደጠቀሱት፣ ገዢዎች የሚፈጽሙት ሦስተኛው መቅሰፍት ከሁሉ የባሰ ነው፡፡ ተገዢዎች ነፃ ቢወጡ እንኳን ራሳቸውን ችለው የሚያድሩም እንዳይመስላቸው አድርገው በባዶ ፕሮፓጋንዳ ያሸብሯቸዋል፡፡ ገዢዎቹ (ከሃሊዎቹ) የሌሉበት ነገር እንደሚዘባረቅ፤ “እነርሱ ያልገዙት አገር እንደሚበታተን፤ ዜጎች እንደ ሩዋንዳና ቡሩንዲ እንደሚተላለቁ፣” ሟርትና ጥላቻን ይደሰኮራሉ፡፡ ባዶ ሟርትና ፕሮፖጋንዳ መሆኑን ለመረዳት ተገዢዎች ለማመን እስኪቸገሩ ድረስ ፕሮፓጋንዳ ይሠራባቸዋል፡፡ ያንንም ለማወቅ፣ “በእርግጥ ባህላችንና እምነታችን የተመቸ ነውን?” ብሎ የሚጠየቅ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜም፣ የገዢዎቹ ሟርትና ማስፈራሪያ በሥልጣን ከመቆየት የዘለለ ቁብ እንደሌለው ይረዳል፡፡ “ጠመንጃ ነካሾች፣ በሥልጣን ኮርቻው ለመፈናጠጥና ለመቆየት ብለው የሚነዙትን ሽብር ፋይዳ-ቢስነት ለመረዳት፣ በመጀመሪያ ባህልን ጠንቅቆ ማወቅ” እንደሚያስፈልግ ኤድዋርድ ሳይድ Orientalism በተባለው መጽሐፉ ይመክራል፡፡
ስለባህል ምንነት ለመረዳት የሚፈልግ ሰው ካለም፣ “ባሕል ማለት ቋንቋ፣ ዜማ፣ ዘፈን፣ የአለባበስ ዓይነትና ዘዴ፣ የጸሎት ወይም የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት፣ ከቤተሰብና ከጎረቤት ጋር ያለው ተራክቦ፣ በአረጋውያንና በልጆች ብሎም በወራዙት መካከል ያለውን ግንኙነትና ሥርዓት እንዴት ነው?” ብሎ መጠየቅና መመርመር አለበት (ፕ/ር ጌታቸው፣ 1960)፡፡ እስከምናውቀውና እከተረዳነው ድረስ፣ የኢትዮጵያውያን ባሕል በፈሪሃ እግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ነው በመሆኑ፣ ዕልቂትን አያስከትልም፡፡ እልቂት ቢከሰት እንኳን የእልቂቱና የግድያዎቹ ፈፃሚዎች ራሳቸውንና ሀገራቸውን ክደው፣ የገዢዎቹ ደረጃ ላይ ደርሰናል በሚሉት የነፃነት ገፋፊዎች ጭካኔ የሚፈፀም ነው፡፡ የእውነተኛ ኢትዮጵያውያን መዋግደ ኅሊና የተገራና ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለው በመሆኑ፣ ለጭካኔ ብርታት የለውም፡፡ ትክክለኛ ኢትዮጵያውያን ኅቁር ፍጥረታት አይደሉም፡፡ ከነፃነታቸውና ከሰብዐዊነታቸው ያለፈ፣ የሚያስቀድሙት ሃብትም ሆነ ሥልጣን የላቸውም፡፡ ኅቁር ፍጥረታት ከፈረሱ በፊት ጋሪውን ያስቀድማሉ፡፡ “ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ይቅደም!” ሲሏቸው፣ “መልካም አስተዳደር እናሰፍናለን!” ይላሉ፡፡
ምዕራባዊያኑም ሆኑ አንዳንድ የምስራቅ አገሮች በአገራችን ላይ የባሕልና የመሠረታዊ ነፃነት ገፈፋን ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ በከተሞቻችን አካባቢ እንደምናየው፣ ኦርቶዶክስሰ ክርስቲያኖቹ እንደሶሪያና ሊባኖስ ካህናት፣ ሙስሊሞቹም እንደ ሳዑዲና የመን ሼኪዎች፣ ካቶሊኮቹም እንደቫቲካን ቀሳውስት፣ ፕሮቴስታንቶቹም እንደጀርመንና አሜሪካን ፓስተሮች ለመሆን ይቸጋገራሉ፡፡ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎቹ፣ ራሳቸውን ክደው በሌሎች ባሕል ኮራጅነት ተጠምደው እሽቅድምድም ይዘዋል፡፡ ከራሳችን አለባበስ የእነርሱ አለባበስ፤ ከራሳችን ዜማና ዘፈን የነርሱ ጋጠወጥ ስልት፣ ከራሳችን የቤተሰብ ኑሮ የነርሱ ቤተሰባዊ ኑሮ፣ ከራሳችን ወግና ሥርዓት የነርሱ ወግና ሥርዓት፣ ከራሳችን አገር የነርሱ አገር የሚሻል መሆኑን ሊያሳምኑን ጥረዋል፡፡ የዚህ የዚህ ታዲያ፣ በዓድዋና በማይጨው ለምን የብዙ ኢትዮጵያውያን ንፁህ ደም ፈሰሰ? በሽንብራ ኩሬና በመተማ፣ በዶጋሊና በኦጋዴን ለምን ጀግኖች ተሰው? አገራችን እንዳትገዛና በእነርሱ እንዳትተዳደር አልነበረምን?!” እንጂ፤ “አገሪቱማ ሳትገዛና ሳትተዳደር መቼ አድራ ታውቃለች! ዋናው ምክንያት እነሱ በምንም መልኩ እንዳይገዙን መሰረታዊ ነፃነታችንን እንዳናጣ አልነበረም እንዴ? የራሳችን ባህል እንድንጠብቅና የነሱን ባህል እንዳንይዝ አልነበረምን?” አሁን ታዲያ ምን ነካን? ምን ዓይነትስ ጥንጣን በላን? ምን አነቀዘን? (ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ 1960፡፡)
ከላይ በጠቀስነው መጣጥፋቸው ላይ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ እንደገለጹት ከሆነ፣ “በማናቸውም ረገድና በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ መሠረታዊ ነፃነት እንጂ ነፃ ነፃነት የለም፡፡” ነፃ ነፃነት (Absolute Freedom) የሌለው፣ በነፃ ነፃነት ውስጥ መኖርም ስለማይቻል ነው፡፡ ነፃ ነፃነት አለ ካልን፤ የሕዝቡ የርስ በርስ ግንኙነት ባዶ (ዜሮ) ነው ማለታችን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኃላፊነትና ግዴታ እስካለ ድረስ “ነፃ ነፃነት” የለም፡፡ ያለው መሠረታዊ ነፃነት ነው፡፡ አንዱ ከሌላው የሚቀበለውና ለሌላውም የሚሠጠው እስካለው ድረስ ነፃ ባህልም የለም፡፡ አንዱ ከሌላው ይዋሳል፤ ያውሳልም፡፡ ነፃ ባህል የለም፤ ነፃ ነጻነትም የለም፡፡ ያለው መሠረታዊ ባህልና መሰረታዊ ነፃነት ነው፡፡ ግራዚያኒን ለመቃወም ሰልፍ መሰለፍ አትችሉትም የሚሉትና የሚያስሩት ወገኖች፣ የመሠረታዊ ነፃነት አፈና እያካሄዱ ነው፡፡ አንድ ሃሳብ ወይም አጀንዳ ሲነደፍ የሚጮኹና የሚፎክሩትም ወገኖች፤ መሠረታዊ ነፃነትን ለመግፈፍ በአነስተኛና ጥቃቅን ገዢነት ተግባር ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ሃሳቡን ሳይሆን አሳቢውን የሚዘልፉና የሚሳደቡም ኅቁራን ካሉም፤ አንድ ለአምስት የተደራጁ የገዢዎቹ አባሪዎችና ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ አይደሉም፡፡
መሠረታዊ ነፃነትን የሚገድበው መንግሥት የሚባለው አካል ብቻ አይደለም፡፡ የመንደር ጎረምሳ፣ የቀዬ ጠብደልና የአጥቢያም ጎበዝ አለቃ ጭምር ናቸው፡፡ በግሌ መሠረታዊ ነጻነትን የሚገፍን አገዛዝ፣ ሥርዓትና መንግሥታዊ መዋቅር ለማጋለጥና አላህ ወይም እግዚአብሔር የሰጠኝንም ነፃነት ለማስከበር እጥራለሁ እንጂ፤ በአንድ ለአምስት ወይም በአነስተኛና ጥቃቅን ከተደራጁ የመሠረታዊ ነፃነት ገፋፊዎች ጋር ቅንጣት ሴኮንድም አላጠፋም፡፡ በአንድ ለአምስት ወይም በአነስተኛና ጥቃቅን የጎበዝ-አድማ ላይ ለተሰማሩት ወገኖቼም ሆነ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን የምናገረው ሃይለ-ቃልም የሚከተለተው ነው፡፡ “እርስ በርስ መፎካከታችንን ትተን፤ መሠረታዊ ነፃነታችንን የሚገፉትንና እያወናበዱ እንግዛችሁ የሚሉንን፤ ካድሬ ሆናችሁ፣ ሎሌ ሆናችሁ ቋንቋችንን ተናገሩ፤ የእኛን ባሕል ተከተሉ፣ የእኛን ሃይማኖት እመኑ፣ እናንተ ምንም ስለማታውቁ፣ እኛ ሁሉንም እናውቅላችኋለን፤ በአጠቃላይ “እኛን ምሰሉ” ባዮችን የአገዛዝ ዘመን እናሳጥር፡፡ እርስ በርስ ስንቦቃቀስ፣ የገዢዎቻችን እድሜ አራዝመን የእኛንም ሆነ የሕዝባችን ስቃይ ከማራዘም፣ የመሠረታዊ ነፃነት ገፋፊዎችን ጎራ ከማጠናከር በስተቀር የምናተርፈው ቅንጣት ታክል ፍርፋሪም ሆነ ሰደቃ እንደሌለ ማወቅ አለብን፡፡ አይመስላችሁም ጎበዝ?!
(የሳምንት ሰዎች ይበለን!)