Friday, 26 April 2013

የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ በሙስና መጨማለቁን አንድ ጥናት አመለከተ


መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ የመንገደኞች የይለፍ ማረጋገጫ
አሰጣጥ እና የአገልግሎት ክፍያ ገንዘብ ገቢ አሰባሰብ የአሰራር ሥርዓት በሙስናና ብልሹ አሰራር የተጨማለቀ
መሆኑን ከፌዴራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን የተገኘ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
በመምሪያው በይለፍ ማረጋገጫ አሰራር ስርዓት ላይ ለሙስናና ብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ ተብለው በጥናቱ ከቀረቡት
ሁኔታዎች ውስጥ የመረጃ አያያዝና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደካማ መሆን፤የሙስናና ብልሹ አሰራር
መንሰራፋት፣የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመመደብ፣ግልጽ የስራ መመሪያና ማኑዋል ያለመኖር የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
ለሠራተኞች የሚያገለግል የሥነምግባር መመሪያ ባለመኖሩ ጠንካራና አስተማሪ የሆነ አስተዳደራዊና የዲሲፕሊን እርምጃ ለመውሰድ ባለመቻሉ  ደላሎች፣ የካውንተር ሠራተኞችና ኃላፊዎች ተባባሪና የጥቅም ተጋሪ በመሆን መንገደኞች በፎርጅድ ፓስፖርትና ቪዛ ከአገር እንዲወጡ ያደርጋሉ። ቪዛ በሕገወጥ መንገድ ከተለያዩ ኤምባሲዎች እንዲወጡና ቪዛ ከሌሎች አገሮች እንዲመጣ በማድረግ መሸጥ፣ ቪዛ የሚሰጡ አገሮች  ለተጓዦች የሰጡትን የቪዛ ሊስትና ቁጥር ለኢሚግሬሽን በሚልኩበት ጊዜ ቦሌ አንዳንድ የመ/ቤቱ ሠራተኞች ዝርዝሩን የመሰረዝና የመፋቅ፣ ከዚያም በማመሳሰል ቪዛውን ፓስፖርት ላይ በመምታት ገንዘብ እንደሚያጋብሱ ተመልክቷል።
እንዲሁም ደላሎችና የካውንተር ሠራተኞች በምን ሰዓት ማን እንዳለ በተለምዶ በመለየት መንገደኛውን በመላክና በሕገወጥ መንገድ እንዲያልፍ በማድረግ፣ ቪዛ በማያስፈልገው የኬንያን በመሳሰሉ ፓስፖርቶች በመጠቀም  መንገደኛው በቦሌ በኩል ካለፈ በኋላ ኬንያ ሲደርስ የሌሎችን አገሮች ቪዛ በመለጠፍ ትራንዚት ነን እንዲሉ በማድረግ፣ ከተለያዩ አገሮች የተባረሩ ተጓዦችን ኤርፖርት ከያዙና አስፈላጊውን መረጃ ከሰነዳቸው ላይ ከወሰዱ በሁዋላ ምርመራ መከናወን ሲገባው በጥቅማጥቅምና በቸልተኝነት እንዲበተኑ በማድረግ ገንዘብ እየተዘረፈ መሆኑ ተመልክቷል።
መ/ቤቱ ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ ከሚሰበስቡት ተቋማት መካከል አንዱ ቢሆንም  የፋይናንስ አስተዳደርና
ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ለማከናወን የሚችል የውስጥ ኦዲት የሥራ ክፍል የለውም፡፡ በዚህም የተነሳ ይላል ጥናቱ ወቅታዊና ድንገተኛ ኦዲት በአግባቡ ለማድረግ ባለመቻሉ የሚሰበሰበው ገቢ በትክክል ለመንግስት ገቢ መደረጉን ለማረጋገጥ አልተቻለም።  በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ወቅታዊ የማስተካከያ እርምጃ አለመውሰድ፣በፌዴራል ዋናው ኦዲተር መ/ቤት ዓመታዊ ኦዲት ሪፖርት መሠረት የማሻሻያ ሥራ አለማከናወን የአሰራር ስርዓቱ ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በመ/ቤቱ በሁለቱም የሥራ ክፍሎች ተመድበው የሚሰሩ አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ብቃታቸውና ክህሎታቸው አነስተኛ
መሆኑም ተመልክቷል።
ለሰራተኞች የስራ ላይ ሥልጠና የሚሰጥ ቢሆንም እንኳን የፎርጀሪና ማጭበርበር መንገዶች እንደ ወቅታዊ ቴክኖሎጂ ደረጃ የሚሻሻሉና የሚለወጡ በመሆኑ በብቃት ለመከላከል የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት አለመዘርጋቱን በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
የአሰራር ሥርዓት ችግሩን ለመፍታት በሥራ ክፍሎች አሰራር ሥርዓት ላይ በባለሙያ እጥረት ምክንያት እያጋጠመ
ያለውን ችግር ለመቅረፍ ብቃትና ክህሎት ያለውን ባለሙያ ለማስመደብ ወይም ለመቅጠር በቅድሚያ ለሥራ መደቦች
የሚያስፈልገውን የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ እንዲወጣለት በማድረግ ማሟላት፣ ከዚህም በተጨማሪ አዲስ
ሠራተኞች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ስለአሰራሩ በቂ ስልጠና የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸትና በሥራ ላይ እያሉ
የማጠናከሪያ ሥልጠና እንዲሰጥ ማድረግ በጥናቱ የተጠቆመ የመፍትሄ ሀሳቦች ናቸው፡፡
የ ተለያዩ የሥራ ክፍሎችን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች ሥራውን የሚመሩት በግልፅ መመሪያ ሳይሆን በልምድ፣ በቃል ትዕዛዝ እና በማስታወሻ መሆኑ፣ ይህ ዓይነቱ አሰራር ደግሞ ግለሰቦች እንደፈለጉት ሥራውን የሚመሩበት በመሆኑ በተፈለገው ጊዜ የሚሰራበት በማይመች ጊዜ እንዲቆም የሚታዘዝበት አሰራር ዘይቤ እንዲከተልና ለግለሰብ አመለካከት የተጋለጠ መሆኑም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
የይለፍ ማረጋገጫ አሰጣጥ አሰራር ሂደት በባህሪው በየቀኑ በርካታ ተገልጋዮችና መንገደኞች የሚስተናገዱበት የሥራ ክፍል ቢሆንም በአሰራር ሥርዓቱ ላይ የመንገደኛው የሀሳብ መስጫ አስተያየት ማቅረቢያ ቅፅም ሆነ ሳጥን አለመኖር፣ የቅሬታ ማስተናገጃ ክፍልም ሆነ ኦፊሰር አለመደራጀት፣ ተገልጋዩ በአቅራቢው ችግሩን የሚፈታበት ሥርዓት ያልተዘረጋ ስለሆነ ችግር ሲያጋጥመው ከቦሌ ወደ ዋናው መ/ቤት እንዲመጣ ማድረግና ማጉላላት ስላለ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በቀላሉ የተጋለጠ ሆኗል
ከአሰራር ጋር በተያያዙ የተጠቀሱት ሌሎች ችግሮች ከአገልግሎት የሚሰበሰብ ገንዘብ በየእለቱ ወደ ባንክ ገቢ
አለማድረግ፣ ከመጠን በላይ በካዝና ገንዘብ ማሳደር፣ የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢዎች በየዕለቱ የሚሰበስቡትን ገንዘብ
አግባብ ያለው ወቅታዊ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገበት ለባንክ ገቢ አለመሆን፣ የሂሳብ ምዝገባ በየቀኑ
ስለማይመዘገብ አግባብ ያለውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አለመቻልና የገቢ ሒሳብ ምዝገባ ሳይከናወን ለረጅም ወራት
ማከማቸት፣ የገቢ ሒሳብ እንቅስቃሴ መዝገብ በኮምፒውተር በየጊዜው ስለማይመዘገብ ሒሳቡን በወቅቱ አለመዝጋት፣
የገንዘብ መቀበያ ደረሰኞች አያያዝና አጠቃቀም ብክነት ያለበት መሆን እንዲሁም የሚሰበሰበው
ገንዘብና ወደ ባንክ ገቢ የሚሆነው ገንዘብ ከደረሰኞች ጋር በወቅቱና በዕለቱ ማመዛዘኛ /balance/
አለመሰራት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ከመረጃ አያያዝ ጋር በተገናኘ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ደግሞ ውዝፍ ሥራዎች በመብዛታቸው ምክንያት
ሥራዎችን በዘመቻ በመስራት የሥራ ጫና መኖር፣ ፋይሎች በዓመታትና በየወሩ ተለይተው በቀላሉ የሚገኙና የተደራጁ አለመሆኑ ምክንያት ለክትትልና ለቁጥጥር አለመመቸት፣ ከክልል ኬላዎች ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ጋር የተቀናጀ ግንኙነት ባለመኖሩ የሰበሰቡትን ገንዘብ በወቅቱ በባንክ በኩል ፈሰስ አድርገው ማስረጃውን እንዲልኩ አለማድረግና የገቢ ደረሰኝ በወቅቱ አለመስራት፣ ፋይሊንግ ሲስተሙ በዘመናዊ መልክ የተደራጀ አለመሆን፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ማዕከላዊ ሒሳብ መምሪያ ጋር ተናቦ ሪፖርቶችን በወቅቱ አለማዘጋጀት፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ባንክና በመሥሪያ ቤቱ መካከል ልዩነት መኖር ፣ የሚሉት ተካተዋል።
ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ፓስፖርት ለማውጣትም ሆነ
ለማሳደስ ዜጎች እስከ አራት ወራት የሚደርስ ቀጠሮና መጉላላት የሚደርስባቸው ሲሆን ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት
በነፍስወከፍ እስከ አምስት ሺ ብር ጉቦ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
መ/ቤቱ በቂ የትምህርት ዝግጅት በሌላቸው በቀድሞ የህወሀት / ኢህአዴግ ታጋዮች ከላይ እስከታች የተሞላ መሆኑም ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment