Friday, 26 April 2013

የህዳሴ ግድብ ኃይል ጣቢያ በ1 ቢሊየን ዶላር የቻይና ብድር ሊሠራ ነው


ከታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ የሚመነጨውን ኃይል የሚያስተላልፍና የሚያከፋፍል ጣቢያ ለመገንባት የሚያስችል የኮንትራት ስምምንት ተፈረመ። የማስተላለፊያና የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል።
የኮንትራት ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምህረት ደበበና የቻይናው ኤሌክትሪክ ፓወር ኢኩዊፕመንት ና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ዥያ ዥኪያንግ ፈርመዋል።
አቶ ምህረት በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከሚውለው ገንዘብ 85 በመቶ ከቻይና መንግሥት በብድር የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪው በኢትጵያ መንግሥት ይሸፈናል።
የጣቢያው ግንባታ በቀጣዮቹ 30 ቀናት ውስጥ ይጀመራል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ሥራው በ24 ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ጥናትና ዲዛይን ሥራ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መካሄዱን ገልጸው፣ በግንባታው ላይ የሁለቱም አገሮች ባለሙያዎች በጋራ እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።
የኃይል ማስተላለፊያ መሥመሩ ባለ 500 እና 400 ኪሎ ቮልት የመሸከም አቅም ያለው ሲሆን፣ አጠቃላይ ርዝመቱ 700 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።
አቶ ምህረት እንዳሉት መሥመሩ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኃይል ማስተላለፍ መስክ ለሚደረገው ግንኙነት ከፍተኛ ጠቀሜታም ይኖረዋል። ከግድቡ የሚመነጨውን ኃይል ከዋናው ብሄራዊ ሃይል ማዕከልር ለማገናኘት ከደዴሳ -ሆለታ፣ሰበታ ሁለት እንዲሁም ከሆለታ ወደ ሰበታ ከዚያም አቃቂ ወዳለው የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያ እንዲገባ ይደረጋል።
ሚስተር ዥኪያንግ እንዳሉት ኩባንያቸው ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ እንደሚያስረክብ ገልጸዋል።
በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
***************
Source: Ethiopian News Agency – April 26, 2013. Originally titled “የህዳሴ ግድብ የሚመነጨውን ኃይል የማስተላለፊያና የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ለማከናወን ስምምነት ተፈረመ”.

No comments:

Post a Comment