በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ ሲያጠምቁ የከረሙት አነጋጋሪው መ/ር ግርማ ወንድሙ እንዳያጠምቁ ታገዱ
(ዘ-ሐበሻ) በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ የማጥመቅ አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበሩት መምህር ግርማ ወንድሙ ካሁን በኋላ በደብሩ ውስጥ እንዳያጠምቁ በደብሩ አስተዳደር መልአከ ኃይል አባ ሚካኤል ታደሰ (ቆሞስ) ሚያዚያ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ታገዱ። የዘ-ሐበሻ የአዲስ አበባ ምንጮች ደብዳቤውን አግኝተው አድርሰውናል። ለ እገዳው ምክንያትነት የቀረቡት አካባቢው የቱሪስት ቦታ ስለሆነ ለጸጥታ እና ለንጽህና የሚሉ ይገኙበታል።
“በደብሩ ውስጥ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ እየፈጸሙ ያለውን የማጥመቅ ሥራ ማገድን ይመለከታል” በሚል ለመምህር ግርማ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ከዚህ በፊትም መምህሩ እንዳያጠምቁ ታግደው የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ ሳይፈጸም መቆየቱንና ከሚያዝያ 28 ጀምሮ ግን መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው እስጢፋኖስ ቤ/ክ እንዳያጠምቁ ታግደዋል።
እገዳው ለምን እንዳስፈለገ ደብሩ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “የብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ በ/አ/አ/ሀ/ስ የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሰኔ 8 ቀን 2003 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር 4290/90/03 የሰጡት የእገዳ ትዕዛዝ ያልተነሳና ያልተሻረ በመሆኑ፤ በግቢው ውስጥ ያለው ሁኔታ ለሃገርም ሆነ ለቤተክርስቲያኒቱ ሰላም አስጊ በመሆኑ፣ በተጨማሪም ደብራችን የአዲስ አበባ እንብርት በሆነው በመስቀል አደባባይ አካባቢ፣ በአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤትና በታላቁ ቤተመንግስት አካባቢ በመገኘቱ ምክንያት ሰላማዊ ቦታ መሆን እንዳለበት ከዚህም ሌላ በብዙ የውጭ ሃገር ዜጎች ቱርስቶችም በተደጋጋሚ ቦታው ስለሚጎበኝ በሰላም ገብተው እንዲገለገሉ እና እንዲጎበኙ፤ ንጽህናው የተጠበቀ፣ ሰላም እና ጸጥታ የተሞላ የጸሎት ስፍራ መሆን እንዳለበት ሰበካ ጉባኤው ስላመነ፤ አሁን እየተፈጠረ ካለው ችግር አንጻረና የተጀመረውም የማጣራት ሥራ ተጠናክሮ የማያዳግም ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከዛሬ ሚያዝያ 28 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለጊዜው የማጥመቅ አገልግሎትዎን እንዲያቆሙ የደብሩ አስተዳደር ሰባካ ጉባኤ ጽ/ቤት የ እግዳ ውሳኔ አስተላልፏል። ውሳኔውን ባለማክበር በቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ለሚፈጠረው ማንኛውም ችግር ዋነኛ ተጠያቂ መሆንዎን እናስታውቃለን” ይላል።
No comments:
Post a Comment