የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሬጂስትራር የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ አመራር አባላት ጠበቃን የክስ ማመልከቻ አልቀበልም ብለው መለሱ
ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት ጀሃዳዊ ሃረካት በሚለው ድራማ በመንግሥት የስም ማጥፋት ዘመቻ ተደርጎብናል ሲሉ ያቀረቡትን የክስ ማመልከቻ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሬጂስትራር አልቀበልም ማለቱ ተገለጠ።
የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በዚህ የክስ ማመልከቻ 8 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።
የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት ጠበቃ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ዛሬ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጡት የክስ ማመልከቻውን በሬጂስትራር ባቀረቡ ጊዜ የከሳሾቹን ስም ካዩ በኋላ “ምን ጣጣ አመጣችሁብኝ” በማለት ላለመቀበል መፈለጋቸውን አመልክተዋል።
የፍርድ ቤቱ ሬጂስትራሩ በየትኛውም ፍርድ ቤት ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ የክስ ማመልከቻውን ለፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ወስደው ካሳዩ በኋላ ማክሰኞ ተመለሱ ብለው እንደመለሷቸው ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ለኢሳት ገልጠዋል።
ከአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ በሕግ ሙያ በሀገር ቤትም በውጭም ሰርቻለሁ ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ የፍርድ ቤት ሬጂስትራሮች የክስ ማመልከቻ በእነሱ . . . የሚታይና ፎርማሊቲ ያሟላ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ አንቀበልም ያሉበት ጊዜ አጋጥሟቸው እንደሚያውቅ ይህም ያልተለመደና ከአሰራር ውጪ የሆነ መሆኑን ገልጠዋል።
የስም ማጥፋት ክስ፤ የስም ማጥፋቱ በለተደረገ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት የገለጡት ዶ/ር ያዕቆብ የሦስት ወር ጊዜ ሳይሞላ የቀረበው የክስ ማመልከቻቸው ለትናንት ማክሰኞ ቢቀጠርም ተቀባይ አጥተው መመለሳቸውን አመልክተዋል።
በዚህ የክስ ማመልከቻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት መ/ቤት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ውብሸት ሽፈራው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅቶች መክሰሳቸውንም ከዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ቃለ ምልልስ መረዳት ተችሏል።
እነዚህ የመንግሥት ተቋማት፣ ጅሃዳዊ ሃረካት በሚለው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተከሳሾች ላይ ሀገር ወዳድና የተማሩ ሰዎች ሆነው ሳለ አሸባሪ ተደርገው በመቅረባቸው ነው በስም ማጥፋት የተከሰሱትና መንግሥት የ8 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፍል የተጠየቀው::
No comments:
Post a Comment