የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት- የኔ ሀሳብ*
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር በዲሰምበር 1948 የመጀመሪያው የሰባአዊ መብት የአዋጅ ሰነድ በተባበሩት መንግስታት ሲጸድቅ ድምጽ ከሰጡ ሦስት አፍሪካዊ ሀገሮች አንዷ ነች:: ነገር ግን ከዚያ በኋላ ባሉት ስልሳ አመታት ለነዚህና ዘግይተው ለጸደቁ የሰባአዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መከበር በሀገር ውስጥ የተደረገው እንቅስቃሴ ዘገምተኛ ነው::
ዘግይተው ወደዚህ ክበብ የተቀላቀሉ ሁሉም የቅኝ ግዛት አፍሪካውያን ሀገሮች በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ከኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል:: ይህ በነጻነቱ ለሚኮራና ቅኝ ላልተገዛ ህዝብ አሳፋሪ ነው:: በዚህ ታሪክ ውስጥ እንድንቀጠል መደረግ የለብንም::ዲሞክራሲና የሰባዓዊ መብቶች አያያዝ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ የሚሄድ መሆን አለበት:: የማይሻሻል፤ ባለበት የሚረግጥና እየጫጨ የሚሄድ ዲሞክራሲና የሰባዓዊ መብት አያያዝ በቃን! እላለሁ::
በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣትና የመሰብሰብ መብት እንደሌሎች መብቶች ሁሉ ተከብሮ ማየት እሻለሁ:: የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ይመለስ ስል ሌሎቹን መብቶች ረስቻቸው አይደለም:: የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በሁለት ምክኒያት የተለየ ነው ብዬ ስለማስብ ነው::
አንደኛው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ባልተጻፈና በጊዜያዊነት በታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታገደ 8 አመት አሳልፏል::ለዚህ አዋጅ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች ምንም እንኳን የአብዛኛው ተቀባይነት ባይኖራቸውም የዚህን ያህል ጊዜ ቆይተዋል ብሎ ማሰብ የመንግስትን (የራሱን) አመለካከት ይጻረራል ብዬ አምናለሁ::ምክንያቱም ባንድ በኩል ‘ሰላም ሰፍኗል እና ከዚያ በኋላ ያለውን ምርጫ 99.6% አሸንፌአለሁ’ እያለ በሌላ በኩል ከ 8 ዓመት በፊት የነበረው ድንጋጤ እንዳልቀቀው የሚያሳይ ድርጊት ማስቀጠል አይጣጣሙም::
ሁለተኛ ቀስ በቀስ ይህ ልዩ ሁኔታ(exception)እንደ ቀጥተኛና የወትሮ ጊዜ ህግ ተወስዶ በሌሎች መብቶች ላይም ክልክላ ለማድረግ መነሻ ሆኗል:: ለምሳሌ ሌሎች ተቀራራቢ መብቶች በጥቃቅን ምክኒያቶች ክልከላ እየተደረገባቸው ነው:: በቤት ውስጥ የመሰብሰብና የመደራጀት መብትን መውሰድ ይቻላል::ከዚህ ሲከፋም በቤት ውስጥ የሚደረጉ ስብሰባዎችና በርከት ያሉ ግለሰቦች የሚገኙበትን የራት ግብዣዎች መከልከል እየተለመደ ነው::
የተሳታፊዎችንና የሌሎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተለያዩ ፕሮሲጀሮች(procedures)፤ ማስፈጸሚያ ስርዓቶች መቀመጣቸው በራሱ ችግር አይደለም:: ነገር ግን ይህን ተገን ተደርጎ መከልከልም ሆነ ሆን ተብሎ ሌሎች እክሎች እንዲፈጠሩ ማድረግ፤ ፍቃድ ከመከልከል እኩል ውጤት ነው ያላቸው::
መንግስትና አስፈጻሚ አካላት ፈቃድ ሳይሰጣቸው የሚውጡትን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ትጋትና ዝግጅት ያህል፤ ፈቃድን ያለምንም ተጨባጭ ምክኒያትና ማስረጃ በመከልከል ታማኝነታቸውን ለሚያረጋግጡ ካድሬዎችና በአጠቃላይ በሚከለክሉ ትናንሽ ባለስልጣናት ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግና ፈጣን የተጠያቂነት ሰንሰለት እንዲያወርድ እጠይቃለሁ:: ፈቃድ ሳይሰጠው መውጣት ህግ መተላለፍ ብቻ ሳይሆን ወንጀል ተደርጎ እየታሰበ ነው:: በኔ ዕምነት ፈቃድ መከልከል ፈቃድ ሳይሰጠው ከመውጣት በላይ ወንጀል መሆን አለበት::
በሀገሪቱ ዋነኛ ህግ -በህገ መንግስቱ ለይስሙላ አሳይቶ(አስቀምጦ) ተጽዕኖዋቸው በወጉ ባልተጠኑ ከህገ መንግስቱና ከተደነገጉት መብቶች ጋር በመንፈስም በይዘትም በማይስማሙ በትንንሽ የሰፈር ህጎች መብት መንፈግ ይቁም! የትንንሽ ማስፈጸሚያ ህጎቹ ዋነኛ አላማም ለመከልከል መሆን የለበትም::የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የምክር ቤት አካላትም ‘ከዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ልምድ ቀዳን’ እያሉ ለሀገሮቹ የተለዩ ሁኔታዎች የተዘጋጁና ከኢትዮጵያ ሁኔታዎች ጋር የጋራ ታሪክም ሆነ የሚመሳሰል አጠቃላይ መሰረት ለሌላቸው ጉዳዮች የተዘጋጁ አፋኝ የሆኑ ህጎችን መርጠው መቅዳት እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ::
የሀገሬ ሰዎች ነጻነትን የሚሹትና የሚያስፈልጋቸው ዋናው ምክንያት እነ የአለም ባንክና ሌሎች ሀገሮች ክበብ ለሚገኝ ጥቅም አይደለም::ይህ እንጭርጫሪ ጉዳይ ነው:: የሀገሬ ሰዎች ዲሞክራሲን የሚሹት ሰዎች ስለሆኑና የነጻነት ክበባቸው በሰፋ ቁጥር የሚያጋጥማቸውን መልካም ዕድል ለመጠቀም የሚያስችል ጉልበትና ክህሎት ስለሚሰጣቸው ነው::በተለምዶ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም ይባላል::ዸፋር መሆን የማህበረሰብ ውጤት ነው::ነጻ የመሆን ስነልቦና ውጤት ነው:: ያለአሸማቃቂና አሳሪ ባህል ወይም ህግ የመኖር ውጤት ነው:: በተለያዩ መስኮች ደፋር ሰዎች እንዲኖሩን ያስፈልጋል:: ህግ እየተበተቡ የሰውን መሰጠትና የመንፈስ ልዕልና መስበር ይቁም!
መብት ይከበር! በጋራ በሚያሳስቡን ጉዳዮች እንመክር ዘንድ መስብሰብ ይመለስ:: ስነቃላችን እንዲል ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ ነውና ሁለትም ከዚያም በላይ ሆነን ፤መምከርና መከራከር ፤ሃሳብን በሃሳብ ማሽነፍና በማያውቁን በማናውቃቸው ዜጎች ፊት አላማችንንና ራዕያችንን እናሳይ፤ የሌሎችንም እንመልከት፤ እንስማ፤ እንደማመጥ:: ይህ ሁሉ እንዲሆን መደራጀትንም፤ መሰብሰብንና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግን ባህል እንልመድ:: መንግስትና ባለስልጣናትም እንዴት የህዝብ መብቶች እንደሚታፈኑ ሳይሆን እንዼት ለነዚህ አይነት የህዝብና የግለሰብ ጥያቄዎችና መብቶች፤ መልስ እንደሚሰጥና ጥበቃ እንደሚደረግ፤ ይማሩ::ልምድ ይቅሰሙ::
ዸርሶ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣና የሚሰበሰብ ሁሉ ለመንግስት ክፉ አመለካከት ያለውና በሃይል ያለውን ህገመንግስት ለመናድ የሚጥር ነው ብሎ ከመፈረጅ ይልቅ በህገመንግስቱና በሌሎችም ሁኔታዎች እንዲከበሩ ለምንፈልጋቸው መብቶች፤ በጋራ መቆምን መለማመድ አለብን:: ይህ ሲሆን ህገ-መንግስቱ ራሱን የሚጠብቅ ሀይል ይኖረዋል:: በመሳሪያና በጦር ሰራዊት መጠበቅ አያስፈልገውም:: በያንዳንዳችን ህሊና የሚጠበቅና ሁላችንም ዘብ የምንቆምለት ይሆናል::
መብቱ ያልተከበረለት ህዝብ በወርቅ የተጻፈ ህገመንግስት ቢኖረው ፤እርሱን ተከትለው የተቋቋሙ ተቋማት ያለአድልዎ መብቱንና ጥቅሙን የምር እስካላስከበሩለት ድረስ፤ ጽላቱ እንዲሆን መጠበቅ የለበትም:: ህዝቡ የኔ ህገመንግስት ብሎ እንዲያወራና እንዲወስደው በህገ- መንግስቱ የተመለከቱት መብቶች መተግበር አለባቸው::ለዚህ እያንዳንዳችን የተሰማንን ከሚጋሩን ጋር እንድንመክር ፤ በመሰብሰብና በጋራም ጥሪ እንድናቀርብ፤ ዲሞክራሲን በጋራ በተግባር እናውል፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ይከበር! ይመለስ! እላለሁ:: ቸር እንሰንብት:
No comments:
Post a Comment