Wednesday, 11 December 2013

አንዱዓለም አራጌ ከእስር ቤት “እኔ እስሩ አልከበደኝም፤ በጣም ያሳዘነኝ ግን በኔ መታሰር ልትጠቀሙበት አልቻላችሁም” አለ

(ዘ-ሐበሻ) የ2005 ዓ.ም የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ምርጥ ተብሎ የተሰየመውና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የሚገኘው ወጣቱ ታጋይ አንዱዓለም አራጌ እስር ቤት ሊጠይቁት ለሄዱት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች መልዕክት አስተላለፈ። በጣም ማዘኑንም ገለጸ። ዕድሜ ልክ እስራቱን ተቀብሎ እስር ቤት የሚገኘው አንዷለም አራጌ “ይቅርታ አልጠይቅም” በሚል እስካሁን በእስር ቤት እየማቀቀ ሲሆን “በእኔ መታሰር ብዙ ልትጠቀሙበት ስትችሉ አለመጠቀማችሁ ያሳዝነኛል:: እኔ አሁን በእስር ባለሁበት ሰዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ የነፃነት ትግሉን ወደ ፊት ለመግፋት አጋጣሚ ሊሆንላችሁ ቢችልም አልተጠቀማችሁበትም ” ሲል የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን መውቀሱን የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች ገልጸዋል።
 
“እኔ መታሰሩና፤ በእስር ቤት እየደረሰብኝ ያለው ስቃይ አልከበደኝም። የከበደኝ ግን በኔ መታሰር ልትጠቀሙበት አለመቻላችሁ ነው። በኔ መታሰር መንግስት ብዙ ጫና ውስጥ እንዳለ ይታወቃል። በኔ መታሰር ብዙ ሥራ ልትሰሩበት፤ ትግሉን ወደፊት ልታስኬዱበት ስትሉ ይህን አላደረጋችሁም” ያለው አንዷለም አራጌ አሁንም የመንፈስ ጥንካሬው አብሮት እንዳለ በ እስር ቤት ካነጋገሩት ወገኖች መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።
 
አንዷለም አራጌ የፌደራሉ ማረሚያ ቤት የሚጠይቁህን ሰዎች ስም ዝርዝር አስመዝግብ ተብሎ ተጠይቆ የነበረ ሲሆን እርሱ ግን ማንም ሰው መጥቶ ሊጠይቀኝ መብቱ ነውና ስም ዝርዝር አውጥቼ አልሰጥም ሲል ፈቃደኛ አለመሆኑን ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም መዘገቧ አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment