Monday, 16 December 2013

በጅጅጋ የተካሄደው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ማለፉ በክልሉ ሰላም አለመኖሩን ያመለክታል ሲሉ አንድ ታዛቢ ተናገሩ

 (ስድስት)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-በመንግስት የሀላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ አንድ ስማቸው እንዳይገለጸት የፈለጉ ሰው ለኢሳት እንደተናገሩት በክልሉ በቆዩባቸው ቀናት የታዘቡት ነገር ቢኖር በክልሉ የሰላም እጦት ዋናው ችግር መሆኑን ነው።
ምንም እንኳ መንግስት ያለምንም ችግር በአሉ መጠናቀቁን ቢገልጽም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ እንደነበር ሃላፊው ይናገራሉ። በከተማዋ ዳርቻዎች ታንኮች፣ ከባድ መሳሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ፣ ልዩ ኮማንዶችና እና እስካፍንጫቸው የታጠቁ እግረኛ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት የ24 ሰአታት ጥበቃ ሲያደርጉ ፣ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ደግሞ የአየር ላይ ቅኝት ያደርጉ ነበር። ጥበቃው እስከ አዋሳኝ ወረዳዎች ዘልቆ እንደነበር የገለጹት ሀላፊው፣ መኪኖች በበአሉ ዝግጅት ወቅት እንዳይንቀሳቀሱ ታግተው እንደነበር ገልጸዋል።  የበአሉ አከባበር በስታዲየሙ ውስጥ ብቻ ይካሄድ እንደነበር የገለጹት እኝሁ ሀላፊ፣ ሌላው የጅጅጋ ክፍል የሞት ከተማ ይመስል ነበር ሲሉ አክለዋል። በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንኳ ቢሆን፣ በዚህ አይነት ወታደራዊ ጥበቃ ማንኛውንም አይነት በአል ማክበር እንደሚቻል የገለጹት ባለስልጣኑ፣ አካባቢውን የጎበኙ የውጭ አገር ዜጎችና ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው   ሰላም በኢህአዴግ እይታ ምን ማለት እንደሆነ በቂ ግንዛቤ ወስደዋል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በበአሉ ላይ ለመሳተፍ እንግድነት ተጠርተው ከሄዱት እንግዶች መካከል የኬንያውና የሩዋንዳው አፈ-ጉባኤዎች ተቀባይ አጥተው ሲቸገሩ እንደነበር እኝሁ ሀላፊ ተናግረዋል። የኬንያው አፈጉባኤ የተጋበዙት በአባ ዱላ ገመዳ ሲሆን፣ የሩዋንዳው ደግሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉበኤ ካሳ ተክለብርሀን ነበር። ይሁን እንጅ ሁለቱ ልኡካን ጅጅጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቶ አባ ዱላም ሆኑ አቶ ካሳ ተክለብርሀን አልተቀበሉዋቸውም፣ እነሱን የሚቀበል ሌላ ሰውም አላዘጋጁም። ልኡካኑ ግራ ተጋብተው በጅጅጋ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከቆዩ በሁዋላ፣ የጅጅጋ ፖሊስ በአንድ አሮጌ ፒክ አፕ የፖሊስ መኪና አሳፍሮ ጅጅጋ ሆቴል እንዲያርፉ አድርጓል። ልኡካኑ እንዲያርፉ የተደረገበት ሆቴል ደረጃውን የማይመጥን ነበር ሲሉ ባለስልጣኑ ገልጸዋል። የልኡካን ቡድኑ በመጡበት ወቅት አባ ዱላና አቶ ካሳ ተክለብርሀን በተዘጋጀላቸው የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ውስጥ በመዝናናት ላይ ነበሩ።
ልኡካኑ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሄደው ባለመቀበላቸው ማዘናቸው ሳያንስ በተያዘላቸው ሆቴል እጅግ ተበሳጭተው ነበር።  የሶማሊ ክልል አስተዳደር የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ለውጭ አገር እንግዶች ተገቢውን ክብር ባለመስጠታቸው ማዘኑን መግለጹም ታውቋል።

No comments:

Post a Comment