Thursday, 26 December 2013

የፌዴሬሽን ምክርቤት በአቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

በአቶ ካሳ ተክለብርሃን የሚመራው የፌዴሬሽን ምክርቤት ፍ/ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በሙስና ወንጀል በተከሰሱት
የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ
ለመስጠት የፊታችን ሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ታወቀ፡፡

የፌዴራሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል በመጠርጠር በሶስት የተለያዩ መዝገቦች ስር
ከባለስልጣናትና ባለሀብቶች ጋር ክስ የመሰረተባቸው አቶ መላኩ ፈንታ፤ ሚኒስትር በመሆኔ ጉዳዬ መታየት ያለበት
በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው በማለት ባቀረቡት መከራከሪያ መሰረት ችሎቱ ጉዳዩ የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል
ሲል ለፌዴሬሽን ም/ቤት የሕገመንግስት አጣሪ ጉባኤ መምራቱና ጉባዔውም በበኩሉ የውሳኔ ሃሳቡን ለፍ/ቤቱ ማሳወቁ
ይታወሳል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎቱ ላይ የቀድሞው
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ ያነሱትን ክርክር ተከትሎ ብይን
ለመስጠትና ጉዳያቸው መታየት ያለበት በከፍተኛው ፍርድ ቤት ነው ወይስ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚለው ጉዳይ
ለመወሰን ለታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል። በዕለቱም የሕገመንግስት አጣሪ ጉባዔ
የውሳኔ ሃሳብ የደረሰው ፍ/ቤቱ የፌዴሬሽን ም/ቤት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሰጥቶ እንዲያሳውቀው ትዕዛዝ በመስጠት
ለታህሳስ 22 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡

ፍርድ ቤቱ የአቶ መላኩ ፈንታን ጉዳይ የሕገ-መንግስት ትርጓሜ ያስፈልገዋል ብሎ በዝርዝር ትንታኔ እንዲታይ
ከማድረጉ በፊት የግራ ቀኙን የተከራካሪ ወገኖች ሀሳብ አድምጦና መዝገቦችንም አገላብጦ ባገኘው መረጃ መሰረት፤
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የስነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ መሰረት፣
ሚኒስትሮችን ጨምሮ የፌዴራል መንግስቱ ባለስልጣናት በስራ ኃላፊነታቸው ምክንያት ተጠያቂ በሚሆኑባቸው ወንጀሎች
በማናቸውም የወንጀል ጉዳዮች የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የስረ-ነገር ክርክር
ማስኬጃ እንዲሆን ስልጣን የተሰጠው መሆኑ በግልፅ ተደንግጓል ብሏል።
ሆኖም የነዚህ ሁለት አዋጆች ንዑሳን አንቀፆች ሕገ-መንግስታዊ ናቸው ወይም አይደሉም የሚለው የተጣራ ትርጉም ያስፈልገዋል በሚል በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ እልባት ለመስጠት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መምራቱ የሚታወስ ነው፡፡

የፌዴሬሽን ም/ቤት ታህሳስ 21 እና 22 ቀን 2006 ዓ.ም ተሰብስቦ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ
ወንጀል ችሎት ትእዛዝ በሰጠበት በአቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ላይ የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ የውሳኔ ሃሳብ ላይ
በመወያየት የመጨረሻ ውሳኔ በማሳለፍ ለፍ/ቤቱ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፌዴሬሸን ም/ቤት በሕገመንግስቱ መሰረት በፌዴራሉ መንግስት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች፣ሕዝቦች
የሚልኩዋቸው አባላት የሚወከሉበት ምክርቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment