Monday, 10 February 2014

ግንቦት 7 በአለም ዙሪያ ከሚገኙ አባላቱ ጋር መከረ

ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በተዘጋጀ የድርጅቱ የስራ እቅድ ላይ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ዓባላቶቹ ጋር አመርቂ ውይይት አካሄደ። ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የተደረጉትን እነዚህን አሳታፊ ውይይቶች የንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች እንደመሯቸውም ተያይዞ ተጠቅሷል።
በሁሉም ቦታ ፍጹም አሳታፊ የነበረውንና ሰአታትን የወሰደውን ይህን ውይይት የመሩት እነኝህ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ከድርጅቱ ምስረታ እስካሁን ድረስ ያለውን የድርጅቱን ጉዞ ባጭሩ ማብራራታቸውን የጠቀሰው ዘጋቢያችን ለቀጣይ ሁለት አመታት ምን መደረግ አለበት የሚለውን የስራ እቅድ ለተሳታፊዎች በማቅረብ ከፍተኛ ውይይት ከተደረገበት በሗላ በሁሉም ቦታ በአባላት ሙሉ ድምጽ ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁን ዘጋቢያችን ጨምሮ ገልጿል።
በስብሰባው ወቅት ለፍትህ፡ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ ከታሰበው እቅድ በላይ በፍጥነት እየተጓዘ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም በአባላቱ ከፍተኛ ቁርጠኝነት የተገኘ መሆኑ በየውይይቱ በአጽንኦት ተገልጿል። እኛ ከተባበርን የምንፈልገውን ከማድረግ የሚያግደን ሃይል የለም፣ የወገኖቻችን ስቃይ የሚያበቃበት የድሉ ምዕራፍ ላይም እንገኛለን ስለሆነም ሁላችንም በከፍተኛ የትግል መንፈስ ለመጨረሻው የድል ጉዞ በከፍተኛ ወኔ እንነሳ በሚል የትግል ጥሪም ተላልፏል።
በየከተሞች ከነበሩ የውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን አባላቱ በአዲስ የስራ መንፈስና ወኔ ለእቅዱ ስኬት እንደሚሰሩ መናገራቸውን የጠቆመው ዘጋቢአችን በአካል በስልክና በመሳሰሉት የመገናኛ መንገዶች ያነጋገራቸው በተለያዩ ከተሞች ውይይቱን የተሳተፉ አንዳንድ የድርጅቱ አባላት በተለይም በቀረበው የሁለት አመቱ የስራ እቅድ ደስተኞች በመሆናቸው ለስኬቱም ከምን ግዜውም በላይ እንደሚሰሩና ትግሉ ለሚጠይቀው ሁሉ መስዋእትነትን ለመክፈል ራሳቸውን ማዘጋጀታቸውን ዘጋቢያችን ጨምሮ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment