Saturday, 22 February 2014

የመከላከያ ተቋም ተግባር አገርን መጠበቅ ነዉ ወይስ አገርን መዝረፍ?



Ginbot 7 weekly editorialየአዉሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ሲቀራመቱ ባህር ተሻግረዉ በመጡ የነጭ ባዕዳን ኃይሎች መገዛትን መርጦ የአዉሮፓን ወራሪዎች በሰላም በሩን ከፍቶ ወደ አገሩ ያስገባ እንድም የአፍሪካ አገር አልነበረም፤ የኋላ ኋላ ተሸንፈዉ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር ቢወድቁም ሁሉም የአፍሪካ አገሮች እንደ አቅማቸዉ ከወራሪ ኃይሎች ጋር ተፋልመዋል። በአንድ ወቅት የቅርብ ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች በወራሪ ኃይሎች ተሸንፈዉ የቅኝ ገዢዎች ቀንበር ጀርባቸዉ ላይ ሲጫን አገራችን ኢትዮጵያ ብቻዋን የአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆና የኖረችዉ ጣሊያኖች፤ እንንግሊዞችና ፈረንሳዮች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለይተዉ ስለወደዷት ወይም ስላከበሯት አይደለም። ይልቁንም ነፃነታችንና የግዛት አንድነታችን ተከብሮ የኖረዉ ኢትዮጵያ እናት አገሩ በጠላት ስትደፈር ከሚያይ ምትክ የሌላት ህይወቱ ብታልፍ ደስ የሚለዉ የኩሩና የጀግና ህዝብ አገር በመሆኗ ነዉ። የሚገርመዉ ይህ ኩሩና ጀግና ህዝብ ጣሊያንን የመሰለ በዘመናዊ መሳሪያ የታጀበ ኃይል ዉርደቱን ተከናንቦ ወደመጣበት እንዲመለስ ሲያስገድድ እንደ ዛሬዉ የተደራጀ ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት አልነበረዉም። ዛሬ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ላይ የተተከሉት ሁለቱ ታሪካዊ ሀዉልቶቻችን የሚነግሩንም ይሀንኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናዊ መልክ የተደራጀ ሠራዊት ሳይኖረዉ የጎበዝ አለቃ እየመረጠ በጣሊያን ፋሺስቶች ላይ የተጎናጸፈዉን አኩሪ ድል ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘመናዊና የተደራጀ መከላከያ ሠራዊት ጥንስስ የተጣለዉ በዳግማዊ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት ሲሆን እሱም ቢሆን ከአድዋ ድል በኋላ ቆይቶ የመጣ ክስተት ነዉ። በአፄ ኃ/ሥላሤና በደርግ ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ ለአንድ ፓርቲና ይህ ፓርቲ እወክለዋለሁ ለሚለዉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሙያዊ ብቃት የነበረዉ፤ሙያዉን የሚያከብርና ለአገሩና ለወገኑ ታማኝ የሆነ የመከላከያ ሠራዊት ነበራት። የወያኔ ዘረኞች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ የመጀመሪያ ኢላማቸዉ አድርገዉ ካወደሟቸዉ ዋና ዋና የአገራቸን ተቋሞች ዉስጥ የመጀመሪያዉ ይሄዉ የአገርና የህዝብ ደጀን የነበረዉ ተቋም ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገር መከላከያ ሠራዊት እየተባለ የሚጠራዉ ተቋም ለጎጠኞች ጥቅምና የስልጣን መራዘም የቆመ፤ በዘረኝነት የተካፋፈለ፤ ይህ ነዉ ተብሎ የሚጠቀስ ሙያዊ ብቃት የሌለዉና የወገንና የአገር ፍቅር እንዳይኖረዉ ተደርጎ የተደራጀ ሰራዊት ነዉ። ይህንን ሠራዊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሳይሆን የወያኔ ሠራዊት እያልን የምንጠራዉም በዚሁ ምክንያት ነዉ።
ዛሬ ሙሉ በሙሉ በወያኔ ዘረኞች ቁጥጥር ስር የወደቀዉ የአገር መከላከያ ተቋም የሚታማዉ በዘረኝነት፤ በሙያ ብቃት ማነስና የአንድ ፓርቲ ጥቅም አስከባሪ በመሆኑ ብቻ አይደለም፤ ተቋሙ ከእነዚህ ዋና ዋና ጉድለቶቹ በተጨማሪ በቀድሞዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ተቋም ላይ በፍጹም ያልታዩ ሌሎች ትላልቅ ጉድለቶች አሉበት። ከእነዚህ ጉድለቶች ዉስጥ አንዱ የወያኔ የመከላከያ ተቋም ህገ መንግስቱ ከሰጠዉ ኃላፊነት ዉጭ በንግድና በንብረት ይዞታ ላይ ላይ መሰማራቱ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ከዚህ ፀባዩ ጋር ተያይዞ በመከላከያ ሠራዊት ተቋም ዉስጥ ከላይ እስከታች የሰፈነዉ ቅጥ ያጣ ሙሰኝነት ነዉ። ዛሬ የወያኔን የመከላከያ ተቋም፤ የህወሀትን ፓርቲና ኤፎርት በሚል ምህጻረቃል የሚታወቀዉን የወያኔን የገንዝብ ማምረቻ ድርጅት ነጣጥለን ወይም አንዱን ከሌላዉ ለይተን ማየት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።
በላፈዉ አመት ወያኔ እራሱ ያቋቋመዉ ፀረ ሙስና ኮሚሺን የገንዘብ ዝርፊያን፤የንብረት መባከንንና መዝረክረክን አስመልክቶ ለፓርላማዉ ባቀረበዉ ሪፖርት ላይ ከጠቀሳቸዉ መንግስታዊ ተቋሞች ዉስጥ ቀዳሚዉን ደረጃ የያዘዉ የመከላከያ ተቋም ነዉ። ሆኖም ፓርላማዉም ሆነ የወያኔ አገዛዝ ለዚህ ሪፖርት የሰጡት ምላሽ የመከላከያና የደህንነት ተቋሞች ከአሁን በኋላ ያሻቸዉን ያክል ገንዝብ ቢዘርፉ የሂሳብ መዝገባቸዉ “ለአገር ደህንነት” ሲባል በኦዲት ኮሚሺን አይመረመርም የሚል ምላሽ ነበር። እንግዲህ ይህ በሙሰኝነት የተጨማለቀ፤ ለህግ የማይገዛና መጠበቅና መንከባከብ የሚገባዉን የአገር ኃብትና ንብረት የሚዘርፍ ተቋም ነዉ ባለፈዉ ሳምንት “የመከላከያ ቀን” ተብሎ አመታዊ በዐል የተከበረለት።
መናገሻ ከተማችን አዲስ አበባ ዉስጥ በየቦታዉ የሚታዩትን ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ሰርተዉ የሚያከራዩት የወር ደሞዛቸዉ ከ2500 ብር የማይበልጥ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ የተሰገሰጉ የወያኔ ጄኔራሎች ናቸዉ፤ኢትዮጵያ ዉስጥ ትርፋማ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ትላልቅ ሆቴሎች፤ የአገልግሎት ተቋሞችና የንግድ ድርጅቶች ከፍተዉ ቁጥር ስፍር የሌለዉ ኃብት የሚያጋብሱት የወያኔ ጄኔራሎች ናቸዉ፤ ድሃዉና የወያኔ ዘረኝነት ሰለባ የሆነዉ ኢትዮጵያ ሰራዊት ለተመድ ተልዕኮ በተሰማራባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ተመድ የሚከፍለዉን የቀን አበል ኪሳቸዉ ዉስጥ እየከተቱ ሚሊዮነሮች የሆኑትና በየዉጭ አገሩ ዉድ መኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ተቋሞችን የሚገዙት የወያኔ ጄኔራሎች ናቸዉ። የወያኔ መከላከያ ተቋም ጉድ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ይህንን ወንጀለኛ ተቋም ቃላት እየደረደሩ ለመግለጽ ከመሞከር ይልቅ በጥቅሉ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ኃብትና ንብረት እንዳሻዉ መዝረፍ እንዲችል የኃይል ሽፋን የሚሰጥ ተቋም ነዉ ማለት የሚበቃ ይመስለናል።
ወያኔና ስር የሰደደዉ ዘረኛ ስርዐቱ ከኢትዮጵያ ምድር ላይ እስካልተነቀሉ ድረስ ወያኔ ዝርፊያዉን የወያኔ መከላከያ ተቋምም የወያኔንና የደገፊዎቹን ዝርፊያ በመሳሪያ ማጀቡ አይቆምም። የወያኔን ዝርፊያ ለማስቆምና አገራችንን ከተጋረጠባት አሳሳቢ አደጋ ለመታደግ ብቸኛዉ መንገድ ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ ብቻ ነዉ። ግንቦት 7 የፍትህ፤የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የጀመረዉ ህዝባዊ ትግል እንደ አገር መከላያከያ አይነቶቹ ቁልፍ የአገር ተቋሞች በሚሰሯቸዉ ስራዎች ሁሉ የአገርንና የህዝብን ጥቅም እንዲያስጠብቁ ለማድረግ ነዉ። የግንቦት 7 ትግል አላማ የመከላከያ፤ የደህንነት፤ የፖሊስና የፍትህ ተቋሞች የአንድ ፓርቲ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያዎች መሆናቸዉ አብቅቶ የአገርና የህዝብ አለኝታ እንዲሆኑ ነዉ፤ ሆኖም ይህንን ቅዱስ አላማ ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ተግባራዊ ማድረግ ስለማይቻል ነፃነት፤ ፍትህ፤ዲሞክራሲ፤ ሠላምና እኩልነት የናፈቀዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወያኔን በፍጥነት እናስወግድ ከሚለዉ የአገር አድን አላማ ጎን እንዲሰለፍ ግንቦት 7 የትግል ጥሪዉን ያስተላልፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!http://ecadforum.com/Amharic/archives/11144/

No comments:

Post a Comment