Wednesday, 19 March 2014

ውዳሴ መስከረም ወጽዮን

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
woman flag


በብዙ አገሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ የሴቶችና የወንዶች ቁጥር ብዙም አይለያይም፤ እኩል ለእኩል ይሆናሉ፤ ነገር ግን ይህ የቁጥር እኩልነት በኑሮአችን ላይ አይታይም፤ በ1983 የወያኔ ሠራዊት በየመንገዱ ይታይ በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን ወደሂልተን ሆቴል ስገባ አንዲት ልጅ ከቁመትዋ የሚረዝምና ከክብደትዋ የበለጠ ጠመንጃ ይዛ አየሁና ዕድሜዋን ብጠይቃት አሥራ አራት አንደሆነ ነገረችኝ፤ ይቺ ልጅ በዚህ ዕድሜዋ ስንት መከራ እንዳየች እግዚአብሔር ይወቀው፤ በዚያን ጊዜ እንደስዋ ያሉ ብዙ ሴቶች ወያኔዎች አይቻለሁ።
የመጀመሪያው ወያኔ/ኢሕአዴግ ያዘጋጀው ጉባኤ በተካሄደበት ጊዜ በጉባኤው ውስጥ አንዲት ሴት ብቻ ነበረች፤ እስዋም ከሠራተኞች ማኅበር የተወከለች ነበረች፤ እነዚያ ጠመንጃ እየተሸከሙ በእግራቸው አዲስ አበባ የገቡትና በየመንገዱና በየመሥሪያ ቤቱ በር ላይ ሲጠብቁ የነበሩ የወያኔ ሴቶች በጉባኤው ላይ በአንድም ሴት አልተወከሉም ነበር፤ ነገሩ በጣም ከንክኖኝ ለመለስ ዜናዊ ነገርሁት፤ ይህንን ጉድለት በማንሣቴ ደስ ባይለውም ስሕተት መሆኑን ተቀብሎ ወደፊት እንደሚታረም ነገረኝ፤ ከዚያም በኋላ ቢሆን ከነጻነት አስፋው ሌላ (የእስዋን አርበኛነት ባላውቅም) በመድረኩ ላይ የምትታይ ሴት አልነበረችም፤ ምናልባት እነዚያ ከጫካ የመጡት እንደ ነጻነት በአውሮፓና በአሜሪካ አልሠለጠኑም ይሆናል፤ እንዲያውም ትንንሾቹን ወያኔዎች ወደትምህርት ቤት ቶሎ ማስገባት ያስፈልጋል ብዬ በመናገሬ ነጻነት አስፋው አንተ ብሎ ለነሱ አሳቢ ብላ ቁጣዋን አውርዳብኛለች፤ ምናልባትም ተማሪዬ በነበረች ጊዜ የደረሰባትን ‹‹ግፍ›› ልትመልስ ይሆናል፤ ዋናው ነጥቤ ግን በወያኔ ዘመን ብዙው ሰው ሲያልፍለት እነዚያ ጠመንጃ ተሸክመው ያየኋቸው እንኳን ሊያልፍላቸው ለዓይንም የጠፉ ይመስላል፤ አሁን በቅርቡ አንዳንድ መደበኛ የትራፊክ ፖሊሶች ሆነው አይቻለሁ፤ በተቀረ ከላይ ተንሳፍፈው የምናያቸው የእንትና ሚስት ወይም የእንትና እኅት ናቸው ይባላል።
ነጻነት አስፋው
ነጻነት አስፋው
እንዴት እንዲህ ሆነ? ይህ እንግዲህ ከአገዛዙ በኩል የጎደለ ነገር መኖሩን ያሳያል፤  ሴቶቹ የተፈለገባቸውን ግዴታ ከወንዶቹ እኩል ከአከናወኑ በኋላ ከመድረኩ የወጡ ይመስላል፤ አገልግሎታቸውን ጨርሰው የወጡም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወንዶችም ወጥተዋል፤ ግን ይህ ብቻ አይመስለኝም፤ እንዴት እንደገቡ ስለማናውቅ እንዴት እንደወጡ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፤ ስለዚህ ወደሌላ አቅጣጫ ብናተኩር ኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ) ሲቋቋም ከመሥራቾቹ ቢያንስ ግማሹ ሴት እንዲሆን ያላደረግሁት ጥረት አልነበረም፤ ቢሮአቸው ወይም ቤታቸው ድረስ እየሄድሁ የለመንኋቸው ነበሩ፤ በመጨረሻም የኢሰመጉ አባሎች ውስጥ ሴቶች አሥር ከመቶም አልደረሱም፤ በኋላ ለኢሰመጉ አቤቱታውንና ኡኡታውን የሚያቀልጡት አብዛኛዎቹ ሴቶች ነበሩ፤ ቆይቶም ለቅንጅት እንቅስቃሴ ብዙዎቻችን በተቻለን መጠን የሴቶችን ቁጥር ለማበርከት ከፍተኛ ጥረት አድርገን ነበር፤ ውጤቱ ግን የማያረካ ነበር፤ ዛሬም ቢሆን በየፓርቲዎቹ የሚታዩት አብዛኛዎቹ ወንዶች ናቸው፤ ሴቶች ከአሥር በመቶ እንዳያልፉ የወሰኑ ይመስላል፤ ግን የትና እንዴት ተሰብስበው ወሰኑት!
በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ የሚጽፉም ቢሆን በእኔ ግምት ከአሥር በመቶ አያልፉም፤ በቃሊቲ እስር ቤት ከርእዮት ሌላ ሴት ጋዜጠኛ ያለ አይመስለኝም፤ እዚያም ቢሆን ያው ከአሥር አንድ ግድም ሊሆን ነው፤ እየፈሩና እያፈሩ ነው እንዳንል ይህንን የሚያስተባብሉ ሌሎች ምክንያቶች አሉ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች በማዝናኛው መስክ ያላቸው ድርሻ በጣም የላቀ ነው፤ በዘፈንም በጭፈራም ቢሆን ከወንዶቹ ጋር የማይተናነስ ቁጥር ያላቸው ይመስለኛል፤ በስፖርትም በወንዶችና በሴቶች መሀከል ያለውን ርቀት በጣም እያጠበቡት ነው፤ ሌላም ድርጅት ሴቶች በብዛት የሚገኙበት አለ፤ እድር፤ ታድያ ለሌሎቹ ማኅበራት ሲሆን፣ ለፖሊቲካና ሀሳብን ለመግለጹ ሲሆን ወደኋላ የሚይዛቸው ወይም እንዳይገቡበት ወደውጭ የሚገፋቸው ምን ዓይነት ኃይል ነው? ሌላ ትዝ ያለኝና የሚያስደስተኝ በሥጋ ቤት በላተኛነትም ሴቶቻችን የሚያሳዩት የነጻነትና የእኩልነት መንፈስ ነው፤ ይህንን የኢትዮጵያ ሴቶች በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አነስተኛ ተሳትፎ እንደትንሽ ነገር ሳንመለከተው ጥልቅና ትክክለኛ ጥናት ሊደረግበት የሚገባ ይመስለኛል፤ ይህንን ረጅም መንደርደርያ (እኔ አስተማሪ ሆኜ ይህንን ያህል መንደርደሪያ የሚጽፍ ተማሪ ፍሬ ነገሩ ጥሩ ቢሆንም ከD በላይ አያገኝም ነበር!) መንደርደሪያው ያነጣጠረው ዕድልና ጊዜው ያለው ሰው ይህንን ጉዳይ እንዲያጠና/አንደታጠና ለመቀስቀስ ነው፤ የጽሑፌ ዓላማ ውዳሴ መስከረም ወጽዮን ነው።Olympics Day 7 - Athletics
እንዳመጣጣቸው ቅደም-ተከተል ወይዘሮ መስከረምና ወይዘሮ ጽዮን ለፋክት መጽሔት ብርቅ ጽሑፍ አቅራቢዎች ናቸው፤ ብድግ ብዬ እጅ እየነሣሁ እንኳን ደህና መጣችሁ! ያበርታችሁ! እላለሁ፤ በሀሳብ ማሰራጫው ዓለም ለወጉም ቢሆን ከወይዘሮ መዓዛ ሌላ የለም፤ በማናቸውም የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለየብቻቸውም ሆነ በቡድን የሚሠሩ ሰዎች የኢትዮጵያን ወንዶች ይወክላሉ አልልም፤ በተጨማሪም ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሆኑትን ሴቶች አይወከሉም፤ ሁሉንምና ማናቸውንም የኢትዮጵያ ጉዳይ ወንዶች ብቻ ያውም ማንንም በትክክል የማይወክሉ ወንዶች (ወንዶች የምለው ሰዎች እንዳልል ነው፤)  ገርድፈው እያቀረቡት ሲወሰን አንድ አገርና ሕዝብ የሚሄድበትን አቅጣጫ ለመገመት አያስቸግርም፤ በምንም ተአምር ወደላይ ሊሆን አይችልም።
በበኩሌ ወይዘሮ መስከረምንና ወይዘሮ ጽዮንን የማደንቃቸው በአእምሮአቸው ለምነትና ንቃት ብቻ ሳይሆን በመንፈሳቸውም ጥንካሬ ነው፤ የቁልቁለቱ ኃይል በሚያስደነግጥ ሁኔታ እያደገ በመጣበት ዘመን ድምጽን ማሰማትና ለየት ያለ ሀሳብን ይዞ ወደአደባባይ መውጣት አስቸጋሪም አደገኛም በሆነበት ጊዜ የወይዘሮ መስከረምና የወይዘሮ ጽዮን ብቅ ማለት የወደፊቱን አመልካች የሆነ ልዩ ብርሃን ስለሚመስለኝ ደስ ይለኛል፤ የኤፍሬም ሥዩም የቅኔ ችሎታ ቢኖረኝ ለነዚህ ለፋክት አዳዲስ ብርሃናት መወድስ እቀኝላቸው ነበር፤ ወይም አላሙዲንን ብሆን ጠቀም አድርጌ እሸልማቸው ነበር፤ አግረ-መንገዴን አላሙዲን ስለሽልማት ማሰብ እንዲጀምር ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
የህንድን፣ የቻይናን፣ የታይላንድን፣ የመሀከለኛው ምሥራቅን ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ ስመለከት እቀናለሁ፤ የእኛዎቹን ምን ነካቸው እያልሁም ራሴን እጠይቃለሁ፤ በአፍሪካም ሴቶች ፕሬዚደንቶች ሲሆኑም እቀናለሁ፤ ለዚህ ነው መስከረምንና ጽዮንን ብርቅ ናቸውና ብርቅ አድርጌ የማያቸው።
የሴቶችን ተሳትፎ እኔ በቀላሉ አላየውም፤ ትግሉን በስሜት ስለሚገጥሙ የሚያይ ሁሉ ለመሳተፍ ያምረዋል፤ አባቶቻችን ትልቁን ቁም-ነገር አበላሽተው ሴት የላከው ሞት አይፈራም ያሉት በዚህ ምክንያት ነው፤ ፈረንጆች መለስ አድርገው በእያንዳንዱ ትልቅ ሰው በስተጀርባ አንዲት ሴት አለች ይላሉ፤ እንደየቴዎድሮስ ምንትዋብ፣ የምኒልክ ጣይቱ ማለት ነው፤ የምፈራው በዚህም በኩል ሳኡዲ አረብያና የመን እንዳይቀድሙን ነው፤ ሴቻችን ካልተነሣሱ ቆመን መቅረታችን ነው።

No comments:

Post a Comment