Saturday, 8 March 2014

አንድነት ሁለተኛውን ዙር “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት”ንቅናቄ ጀመረ

የመሬት ፖሊስን ለማስለወጥ እታገላለሁ ብሏል  
አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የመሬት ጥያቄን አጀንዳው በማድረግ ለሶስት ወራት የሚዘልቅ ሁለተኛ ዙር “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ንቅናቄ መጀመሩን ጠቁሞ መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆኑን በመቃወም እንደሚንቀሳቀስ ገልጿል፡፡
ፓርቲው በትናንትናው እለት በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋሉን በመቃወም የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ ጫና ለመፍጠር፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተመረጡ 14 የክልል ከተሞች ህዝባዊ ስብሠባ የሚያካሂድ ሲሆን ስብሠባዎቹ እንደቀድሞው በመንግስት የሚደናቀፉ ከሆነ ወደ ሠላማዊ ሠልፍነት እንደሚለወጡ አስታውቋል፡፡ በመሬት ጥያቄ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የፓርቲው የ3 ወር ንቅናቄ፣ በመጪው ሳምንት መጋቢት 7 አዲስ አበባ ላይ በሚካሄድ ህዝባዊ ስብሠባ ተጀምሮ፣ በሣምንቱ በደሴ እና በድጋሚ በአዲስ አበባ የሚደረግ ሲሆን በየ15 ቀን ልዩነት በሃዋሣ፣ አዳማ፣ ለገጣፎ፣ መቀሌ፣ ደብረታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ድሬዳዋ፣ ጂንካ፣ ቁጫ፣ አሶሣ፣ ነቀምት እና ጋምቤላ ከተካሄደ በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሚደረግ ማጠቃለያ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚቋጭ የፓርቲው አመራሮች ገልፀዋል፡፡ እነዚህ የክልል ከተሞች የተመረጡት ለገበሬው ቅርብ ስለሆኑ ነው ብሏል - ፓርቲው፡፡
አንድነት ባለፈው ዓመት ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2005 ዓ.ም ባካሄደው የመጀመሪያ ዙር “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ንቅናቄ የፀረ ሽብር አዋጁን፣ የፕሬስ ህጉን፣ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንና የዜጐች ከቀዬአቸው መፈናቀልን አጀንዳው አድርጐ በአዲስ አበባና 11 የክልል ከተሞች ባካሄዳቸው ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ወከባ ቢደርስበትም ንቅናቄው ስኬታማ እንደነበር መግለፁ  ይታወሳል።  

http://addisadmassnews.com/

No comments:

Post a Comment