Saturday, 8 March 2014

ፓትርያርኩ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በዩኒቨርስቲ ምሩቃን አትመራም›› ማለታቸው ቅሬታ ፈጠረ

  • ስለ ማኅበራት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት ተጠየቀ
  • ‹‹ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከል ይገባል›› መንግሥት
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፴፰፤ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
His hHoliness00የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ቤተ ክርስቲያንን እንምራ እያሉ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና ሥርዓት አላት፤ እንዲህ ማለት አይችሉም›› በማለት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት በንግግራቸው ቅር የተሰኙ የመንፈሳውያን ማኅበራት አገልጋዮች ጠየቁ፡፡
አገልጋዮቹ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ አቡነ ማትያስ ይህን አስተያየት የሰነዘሩት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋራ በመተባበር የካቲት ፳፩ እና ፳፪ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል የምክክር ጉባኤ በተካሔደበት ወቅት ነው፡፡
በምክክር ጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹በባዮሎጂና ኬምስትሪ እንቀድስ እያሉ ነው፤›› ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ‹‹ምን እያልኹ እንደኾን ይገባችኋል›› በማለት ስለማን እንደ ኾነ የማሳየት ያህል የጠቆሙበት አስተያየት ያልተለመደና ጥቂት የማይባሉ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ያሳዘነ እንደነበር የጉባኤው ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በምክክር ጉባኤው ላይ ለውይይት በቀረቡ ጽሑፎች፣ በአዲስ አበባ እስከ ሰማንያ ሺሕ የሚገመቱ መንፈሳውያን ማኅበራት በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እንደሚንቀሳቀሱ የተጠቀሰ ሲኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራቱ በሕግና በሥርዐት የሚመሩበት ደንብ አውጥታ እስካልተቆጣጠረቻቸው ድረስ እየተከሠቱና ሊከሠቱ የሚችሉ ችግሮች በቀላሉ እንደማይታዩ ተመልክቷል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፣ በማኅበር ሽፋን ለግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው የሚሯሯጡ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ሕጸጽ የሚታይባቸው ማኅበራት የመኖራቸውን ያህል ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ምእመናንን በማትጋት ለበለጠ ሀብተ ጸጋ የሚያበቁ ጠንካራ ማኅበራትም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ በምክክር ስም በሚዘጋጁ መድረኮችና በቤተ ክህነቱ ጉባኤያት እየታየ ያለው ‹‹ማኅበራት አላሠራ አሉን›› በሚልበጅምላ የመፈረጅና የመኰነን ዝንባሌ፣ አብዛኞቹ ማኅበራት ለሀገር በአጠቃላይና ለቤተ ክርስቲያን በተለይ እያበረከቱ ያለውንና በቤተ ክህነቱ ቀጥተኛ አቅም ሊሸፈን የማይችለውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በሚዛን ያላስቀመጠ ነው ብለዋል – የማኅበራት አገልጋዮቹ፡፡
‹‹በአሁኑ ጊዜ ማኅበራት የአባሎቻቸውን አስተዋፅኦና የበጎ አድራጊ ምእመናንን የገንዘብ፣ የዕውቀትና ሞያዊ አቅም በማስተባበር የገጠር አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ት/ቤቶች በተቀናጀ መንገድ እንዲረዱ ያደርጋሉ፤ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ዕድገት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ጥናቶችን ያካሒዳሉ፤ በጠረፍ የሀገሪቱ ክፍል በሚያከናውኑት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ምእመኑ በቋንቋው የሚገለገልበትን ኹኔታ ያመቻቻሉ፤ የቅዱሳት መካናት ተሳላሚዎችን የክብረ በዓላት ጉዞዎች በማስተባበር ሕዝቡ ቅርሱንና ባህሉን ዐውቆ እንዲጠብቀውና እንዲከባከበው ከማስቻላቸው ባሻገር ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መስፋፋትና መጠናከርም ያላቸው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤›› ሲሉ በበጎ ፈቃድ የሚሰበሰቡ ማኅበራትን አገልግሎትና ድርሻ አብራርተዋል፡፡
ማኅበራቱ አብዛኞቹን ተግባራት የሚያከናውኑት በየደረጃው ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሓላፊዎችና አባቶች ፈቃድ እያገኙና መመሪያ እየተቀበሉ መኾኑን የሚገልጹት አገልጋዮቹ፣ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. የማኅበራትን ቁጥር ስለ መቆጣጠር ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ በነበረ ጥናት መነሻነት ምልዓተ ጉባኤው ራሱን የቻለና ማኅበራቱን የሚያሠራ ሕግ እንዲዘጋጅ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበትደንብ አዘጋጅ ኮሚቴ ሠይሞ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የማኅበራት አደረጃጀትና የፋይናንስ ቁጥጥር መርሖን ጠብቆ እንደሚወጣሲጠበቅ የቆየው ደንብ ከሚገባው በላይ መዘግየቱ ችግሩ ከቤተ ክህነቱ እንጂ ከማኅበራቱ አገልግሎትና ብዛት አለመኾኑን እንደሚያመለክት ይከራከራሉ፡፡
ፓትርያርኩ አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማስተዳደር በዕለተ ሢመታቸው ቃለ መሐላ መፈጸማቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በምክክር ጉባኤው ላይ በተጠቀሰው አኳኋን የመናገራቸው ግፊት የተለያየ መነሻ ሊኖረው እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የመጀመሪያው መንሥኤ፣ የሙስናንና ብልሹ አሠራርን ችግር ለመቅረፍና ለማድረቅ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተሠራው የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ተቃዋሚዎች ‹የጥናቱ ባለቤት ነው› በማለት በሚከሡት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር አማካይነት እንዲፈጠር የሚሹት ጫና ነው፡፡
ኹለተኛው መንሥኤ ደግሞ በመንግሥት በኩል፣ ‹‹በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚታየው ህልውናቸውና ዓላማቸው ሃይማኖታዊና በሃይማኖቱ የበላይ ጠባቂዎች ይኹንታ በተቋቋሙ የወጣት ማኅበራት አደረጃጀቶች ውስጥ በመሸጉ አካላት ነው፤ ስለዚህም ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከሉ ይገባል፤›› የሚለው [በአንድ ማኅበር ላይ እንዳነጣጠረ ግልጽ እየኾነ የመጣው] የአክራሪነት ውንጀላና ክሥ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያሳደረው ማኅበራቱን በምዝገባና ክትትል የመቆጣጠር ጫና ነው፡፡
የአክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ምንነት መፍትሔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች በሚያብራሩት የመንግሥት ሰነዶች፣ የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ከሚባሉት ኹኔታዎች ውስጥ÷ ‹‹የሃይማኖት ተቋማቱ የሰው ኃይል አስተዳደርና የፋይናንስ ሥርዐት ለተከታዩ ሕዝብ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው መኾኑና ከዚኹ ጋራ ተያይዞ በሙስናና በአስተዳደር በደል ሳቢያ የሚፈጠር ግጭት፣ የሰው ኃይል አስተዳደር በዘመድ አዝማድና በጉቦ እየኾነ የሥራ ብቃት በሌላቸው ሰዎች የሚሠራበት፣ የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ የሚተችበትና አስተያየት የሚሰጥበት ሥርዐት አለመዳበሩ፣ ምእመናን የአክራሪነት ሰርጎ ገብ አስተሳሰቦችን የሚቋቋሙበት በሃይማኖት ዕውቀት የማስታጠቅ ክፍተት›› ይገኙበታል፡፡
በመንግሥት ትንታኔ መሠረት አክራሪነትን የመዋጊያው ቁልፍ መሣሪያ÷ የሀገር ልማትንና ዕድገትን ማፋጠን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን፣ የወጣቶችና ሴቶች ሥራ አጥነትን መቅረፍ፣ ሕዝቡን በሃይማኖታዊ ዕውቀቱ ማስታጠቅ ነው፡፡
የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጓቸዋል የተባሉት የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሠራር ችግሮች÷ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም ባልተሳተፈበትና በተቃዋሚዎች አላግባብ በሚከሠሥበት የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ትግበራን በማፋጠን እንዲኹም ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ በርካታ ማኅበራት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የገዳማትና የአብነት ት/ቤት ማኅበረሰቦችን በልማትና ተራድኦ ከመደገፍ ጀምሮ በሚያከናውኑት የሐዋርያዊ ተልእኮ ንቃት ሊወገድ እንደሚችል ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያምናሉ፡፡
ከዚኽም አንጻር ፓትርያርኩ ንግግራቸውን[ከንግግራቸው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከአዳራሹ ወጣ ብለው በተቀበሉት የስልክ ውይይት እንደተቀበሉት የተጠቆመውን] መልሰው በማጤን ማኅበራት አገልግሎታቸውን በተገቢው የአደረጃጀትና የፋይናንስ ቁጥጥር መርሖመሠረት አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችላቸው ኹኔታ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል፡፡
http://haratewahido.wordpress.com/

No comments:

Post a Comment