ጥቅምት ፲፫(አስራ ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ህግ አንድ ግለሰብ ከመንግስት በማስፈቀድ አንድ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ እንዲይዝ ቢፈቀደልትም ፣ በተግባር ግን አብዛኛው ህዝብ በመሳሪያ አሰሳ ስም የግል መሳሪያውን መቀማቱን በተለያዩ የመገናኛ ብሀን ሲዘገብ ቆይቷል።
በ1997 ምርጫ ወቅት የአንድ ብሄር አባላት በገዢው ፓርቲ ህወሀት ራስን የመጠበቂያ መሳሪያ እንዲታደላቸው መደረጉ በስፋት መዘገቡ ይታወቃል።
የፌደራል አቃቢ ህግ በቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋ/ዳይሬክተር መላኩ ፋንታ መዝገብ ላይ ባቀረበው ክስ፣ በህወሀቱ አባል ምክትል ዳይሬክተሩር አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት ውስጥ 2 ታጣፊና ባለእግር ክላሾች፣ 4 ማካሮቭ ሽጉጦች፣ 2 ኮልት ሽጉጦች፣እና አንድ ስታር ሽጉጥ በድምሩ 9 የጦር መሳሪያዎች መገኘቱን ጠቅሷል።በሌላው የህወሀት አባል በ24ኛው ተከሳሽ በቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አማካሪ በነበሩት በአቶ ወልደስላሴ /ሚካኤል ቤት ደግሞ 2 ባለሰደፍና ታጣፊ ጠመንጃዎች፣ አንድ ኡዚ ጠመንጃ፣ አንድ እስታር ሽጉጥ፣ አንድ የጭስ ቦንብ እና የተለያዩ ጥይቶችን ይዞ መገኘቱ ተገልጿል።
ግለሰቡ ከቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳላቸው በተቃራኒው ደግሞ ከደህንነት ሚኒስትሩ ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ለእስር መዳረጋቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሲዘግብ ቆይተዋል።
በተመሳሳይ ሴና ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መላኩ ፋንታ ባለትዳር በማማገጥ ወንጀል አቃቢ ህግ ክስ እንደመሰረተባቸው ሰንደቅ ጋዜጣ ዘግባል። ዐቃቤ ህግ አቶ መላኩ የስራ ኃላፊነታቸውን በመጠቀም ለስራ ጉዳይ የመጣችን ሴት፤ ትዳሯን ፈታና በትዳር ውስጥ ያፈራቻቸውን ሦስት ልጆች በትና አብራቸው እንድትሆን አድርገዋል ሲል ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ብሎአል። ሰንደቅ አቃቢ ህግን ጠቅሶ እንደዘገበው ” ወ/ሮ መቅደስ ለማ የተባሉት እኚሁ ሴት የቀድሞ ባለቤታቸውን ንብረት የሆነውን ሳንክቸሪ ኢንተርናሽናል ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር በ2001 ዓ.ም የስራ ግብር ለመክፈል ወደገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሲሄዱ 144 ሺህ ብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸውና በዚህም ምክንያት አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ለአንድ አመት ከ4 ወር መጉላላታቸውን ለማስረዳትና መፍትሄ ለማግኘት ወ/ሮ መቅደስ ለማ የአቤቱታ ደብዳቤ ይዘው ወደተከሳሹ ዘንድ በቀረቡበት ወቅት የፍቅር ግንኙነት” ጀምረዋል። ተከሳሽ የነበረውን ስልጣን መከታ በማድረግ ባለጉዳዩዋ ቀደም ሲል ከከፈሉት ብር ውስጥ አንድ መቶ ሺህ ብር ተመላሽ እንዲሆን አድርጓል፤ በትዳር ውስጥ ያለችን ሴትም አማግጧል ሲል አቃቢ ህግ ክስ አሰምቷል።
ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ “በጋብቻ ውስጥ ያለችን ሴት በመንግስት ተሽከርካሪና ነዳጅ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ክብረ በዓል ላይ እንድትገኝ ከማድረጉም በላይ ቀኑ በውል ባልታወቀበት ዕለትም፤ በጋብቻ ውስጥ የነበረችው መቅደስ ለማን በግል ሾፌሩ አማካኝነት ወደ ባህርዳር ከተማ እንድትሄድ በማድረግ ሰመርላንድ ሆቴል ለአንድ ሳምንት አብረው እያደሩ እና በሾፌሩ አማካኝነት ከተማ ውስጥ እንድትዝናና ” አድርጋል ብሎአል።
አቃቢ ህግ ባቀረባቸው በርካታ የወንጀል ዝርዝሮች ውስጥ የሼክ ሙሀመድ ሁሴን አላሙዲንና በጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው በመከላከያ ውስጥ የሚገኘው የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን እቃዎች ያለቀረጥ እንዲገባላቸው ቢደረግም፣ ሌሎች ኩባንያዎች ሲከሰሱ ሁለቱ ድርጅቶች እና የኩባንያው መሪዎች አልተከሰሱም። አቃቢ ህግ እነዚህ ሁለት ግዙፍ ኩባንያዎች በሙስናው ውስጥ እንዳሉበት መረጃ ቢኖረውም ለመክሰስ ለምን ፈቃደኛ እንዳልሆነ አልታወቀም።
No comments:
Post a Comment