Friday, 25 October 2013

የአውራምባ ታይምሱ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባል

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ Journalist Dawit Kebede
“እጅግ አስደንጋጭ ዜና ነው” ሀገር ቤት ያሉ ጋዜጠኞች

Ethiopia Zare (ዓርብ ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. Oct. 25, 2013)፦ በሀገር ቤት ይታተም የነበረው “አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ እና የድረ ገጹ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከሁለት ዓመት በሰሜን አሜሪካ የስደት ቆይታ በኋላ በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚበር ገለጸ። በጉዳዩ ላይ ከአቶ ያሬድ ጥበቡ ጋር በቪዲዮ ቃለምልልስ አድረጓል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ዛሬ ከዋሽንግተን መነሳቱንና ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገባ ገልጸዋል። የጋዜጠኛ ዳዊት ውሳኔን አስመልክቶ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የዚህ ዜና አጠናካሪ አነጋግሯል። እነዚሁ በሀገር ውስጥ የሚገኙት ጋዜጠኞች ዜናውን አለመስማታቸውን ገልጸው፤ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲጠየቁ፤ “እጅግ አስደንጋጭ ዜና ነው” በማለት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በተለይ በመንግሥት እና በደጋፊዎቹ መገናኛ ብዙኀን ከፍተኛ የሥም ማጥፋት ዘመቻ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ሲሰነዘርበት ስለነበር ለስደት መዳረጉንና በአሜሪካ ጥገኝነት ጠይቆ እንደነበር ይታወቃል። ጋዜጠኛ ዳዊት በዚሁ ቃለምልልሱ፤ “ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው፤ እነዚያን ጫናዎችና ፈተናዎች መቋቋም ይቻል ነበር ብዬ አምናለሁ። ያኔ የተሳሳተ ምርጫ አድርጌአለሁ” ሲል ገልጿል።
ከሀገር ቤት ሳይወጣ በፊት በእሱ ላይ ተከፍተው ለነበሩት ዘመቻዎች መንስዔ ነው ብሎ የሚያምነው፤ በሥልጣን ላይም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች በሚዲያው ጠንከር ያለ ትችት ሲሰነዘርባቸው ትችቱን ያለመታገስና የመቋቋም ክህሎት ስለሚያንሳቸው ነው ሲል ጋዜጠኛ ዳዊት ገልጿል።
ዛሬ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጠኞች እስር ቤት እያሉ ወደ ሀገር ቤት መመለሱ “ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት አለ” ለማሰኘት ነው በሚል ትችት ቢቀርብበት ያለውን ምላሽ ሲጠየቅ፤ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት ዓለሙ እሱ ከመሰደዱ ከ5 ወር በፊት መታሰራቸውን፣ እስክንድር ነጋ ደግሞ ከመሰደዱ 3 ወር በፊት መታሰሩን ገልጾ፤ የእሱ ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደቅድመ ሁኔታ ሆኖ መታየት የለበትም ብሏል።
“እኔ በግሌ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ እንዳለ አንድ ዜጋ የበኩሌን አስተዋጽዖ ማድረግ የምችለው (ውጤታማም ሆነ አልሆነ) ኢትዮጵያ ውስጥ በማኅበረሰቡ መሃል ሆኜ ነው የሚል ቁርጠኛ ሃሳብ ነው ወደ ኢትዮጵያ እንድመለስ ያደረገኝ እንጂ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፕሬስ ነፃነት ከመሻሻሉና ካለመሻሻሉ ጋር አይደለም። ከመሰደዴም በፊትም የታሰሩ ጋዜጠኞች ናቸው፤ አሁንም ስደት ላይ ሆኜም፣ በምመለስበት ጊዜም እስር ቤት ያሉ ጋዜጠኖች ናቸው። ስለዚህ መሻሻልን ያሳያል በሚል እየሸሸን የምንቀር ከሆነ፤ ተገቢ አይመስለኝም።” በማለት ለጥያቄው ምላሽ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በሚኖርበት በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ከተለያዩ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙኀን፣ … ጠንከር ያለ ትችት ሲሰነዘርበት፣ የሥም ማጥፋት ውንጀላ ሲደርስበት መቆየቱ፣ እሱም እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቱ፤ ወደ ሀገር ቤት በመግባቱ ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ እንዳላሳደረበት ገልጿል።
እ.ኤ.አ. 2010 ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የሲ.ፒ.ጄ.ን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት የተሸለመ ሲሆን፣ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ በወቅቱ “ኀዳር” የተሰኘውን ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ሲሠራ ስለነበር ከቅንጅት መሪዎች ጋር የዕድሜ ልክ እስራት ከተፈረደበት በኋላ በ”ይቅርታ” መለቀቁ አይዘነጋም።
ባላፉት ሁለት ዓመታት በስደት በቆየበት በሰሜን አሜሪካ በተለይም ከኢትዮ ሚዲያ ድረ ገጽ ጋር ለረዥም ጊዜ የዘለቀ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው እንደነበር አይዘነጋም። ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በተለይ በኢሳት እና በግንቦት 7 ላይ ይሰነዝር የነበረው ትችት ከብዙ ወገኖች ጋር አቋስሎት የነበረ ሲሆን፣ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ነው እስከመባል ከመድረሱም በላይ እስካሁን ድረስ አከራካሪ ከሆኑ ግለሰቦች ውስጥ አንዱ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።
አቶ ያሬድ ጥበቡ ከጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ያደረገው ቃለምልልስ ከዚህ በታች ቀርቧል።(ለመመልከት የማጫወቻ ቁልፉን 

No comments:

Post a Comment