Tuesday, 1 October 2013

የኢህአዴግ ባለስልጣናትን የሚያስተምረው ትምህርት ቤት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውዝግብ ውስጥ ገባ

576820_643438789017118_1777115518_n
መስከረም ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በፕሮፌሰር ባደግ በቀለ የሚመራውና የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን በተለይም የአመራር ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥ በማስተማር የሚታወቀው ኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ ኢንሰቲትዩት በትምህርት ሚኒስቴር ስር ካለው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት ጥራት ኤጀንሲ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ታውቋል።
የሁለቱ አካላት ውዝግብ መነሻ ምክንያቱ ተቋሙ ሳይፈቀድለት በዶክትሬት ዲግሪ ከፍተኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር በመጀመሩ ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ኢንስቲትዩት ሳይፈቀድለት ተማሪዎችን
በፒኤችዲ ዲግሪ መርሃግብር ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን በመጥቀስ ወቀሳ ያቀረበ ሲሆን የኢንስቲትዩቱ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ባደግ በቀለ በበኩላቸው ዕውቅና ያላገኙት በኤጀንሲው አቅም ማነስ መሆኑንና አቅም እስክንገነባ ድረስ ታገሱን መባላቸውን በመጥቀስ ወቀሳውን ያስተባብላሉ፡፡
“አንድ ተቆጣጣሪ አካል በአቅም በለጦ መገኘት እንጂ አቅም እስክገነባ ጠብቁኝ እንዴት ይላል? በማለት የኤጀንሲውን ትችት ማጣጣላቸውን አዲስዘመን ጋዜጣ ባልተለመደ መልኩ በትላንት ዕትሙ በፊት ገጹ ዘግቦታል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከ100 ኣመት በላይ ዕድሜ ካለውና በፊሊፒንስ አገር ከሚገኘው ቡልካን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት የሚሰጠው የፒኤችዲ ዲግሪ ዕውቅና እንዲሰጠው በ2004 ዓ.ም አመልክቶ ከአንድ ኣመት በኃላ አቅም አስክንገነባ ጠብቁ የሚል ምላሽ በማግኘቱ አዲስ ቅበላ ማቆሙን ማስተማር የጀመራቸውን ግን በውጪ አገርም ጭምር እያስተማረ መሆኑን በመጥቀስ የኤጀንሲውን ወቀሳ አጣጥለዋል፡፡
ኤጀንሲው በበኩሉ በፒኤቺዲ ዲግሪ እንዲያስተምር ፈቃድ የተሰጠው የግል የትምህርት ተቋም በኢትዮጵያ እስካሁን አለመኖሩንም አስታውቋል፡፡
ሆኖም ኤጀንሲው በሌሎች የግል ከፍተኛ ተቋማት ላይ ችግር ሲያገኝ ለመዝጋትና በሚዲያ ስም ለማጥፋት የሚሮጠውን ያህል በዚህ ኢንስቲትዩት ላይ ለዘብተኛ አቋም መያዙና ወደልመናና ልምምጥ ደረጃ መውረዱ የዘርፉ ባለሙያዎች አድሎአዊ አካሄድ ነው ሲሉ ነቅፈውታል።
በርካታ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በዚህ የትምህርት ተቋምና በውጭ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ትምህርቶቻቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment