Tuesday, 29 October 2013

የሁለት ኢትዮጵያውያን ሁለት አንቀጽ ወግ እና እኔ…(አቤ ቶኪቻው)

የሁለት ኢትዮጵያውያን ሁለት አንቀጽ ወግ እና እኔ…
ዳዊት ከበደ እና ተስፋሁን ጫመዳ
ተስፋሁን ጫመዳ የተባለ አንድ ወጣት ኢትዮጳያዊ ነበር፡፡ የገዢው ግንባር ኢህአዴግ ነገረ ስራ አልመችህ ቢለው በተለያየ አጋጣሚ ተው  ማለት ጀመረ፡፡ ኢህአዴግዬ ግን ተው ባይ አይወድምና በክፉ አይኑ ተመለከተው ይሄኔ ተስፋሁን የሚመጣበትን ጦስ ሸሽቶ መጪው ጊዜ መልካም እንደሚሆን ተስፋ አድርጎ እስኪያልፍ ያለፋል ብሎ ሀገሩን ትቶ ተሰደደ፡፡ ኢህአዴግ ግን ዝም አላለውም ከተሰደደበት ሀገር አፍኖ ወደ ሀገርቤት መለሰው፡፡ መመለስ ብቻም አይደለም እስር ቤት ዶለው፡፡ መዶል ብቻም አይደለም በቅርቡ ተስፋሁን በእስር ቤት በቂ ህክምና አጥቶ ህወቱን ተነጠቀ፡፡
ዳዊት ከበደ የተባለ ሌላ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነበር፡፡ እርሱም የገዢው ግንባር ኢህአዴግ ነገረ ስራ አልጣመውም እና መምከር ጀመረ፡፡ ኢህአዴግዬ ግን በሚመክሩት ላይ መከራ የሚያበዛ ነውና በክፉ አይኑ ተመለከተው፡፡ ይሄኔ ዳዊት ከጎልያድ ጋር ይጋፈጥበት ወንጭፍ በእጁ አልነበረምና ቀን እስኪልፍ ብሎ ሀገሩን ትቶ ተሰደደ፡፡ ኋላ ላይ ግን እንደ ተስፋሁን አፍነው ሳይወስዱትም ራሱ “እንደውም አልፈራችሁም” ብሎ ወደ ሀገርቤት ተመለሰ፡፡ “ይገሉኝም እንደሁ ይሰቅሉኝም እንደሁ ይሄው መጣሁልዎ ያለምጣም ኢህአዴግ ብዬ ሰደብኩዎ” ብሎ ሁሉ ልክ ልካቸውን ነገሯቸዋል ነው የሚባለው…  ነገር ግን እንደ ተስፋሁን እስር አልጠበቀውም፡፡  እንኳንስ ህወቱን ሻንጣውም አደጋ ላይ አልወደቀም፡፡
ሶስተኛ አንቀጽ እኔ
“አውቶብሱ መጣ ጎማው ሸተተኝ እኔም ከሰሞኑ ተሳፋሪ ነኝ” ብዬ ዥው ብዬ ወደ ሀገሬ ብሄድ የሚጠብቀኝ ምን ይሆን… እንደ ተስፋሁን ታስሮ ህይወት ማጣት፣ እንደ ውብሸት ታስሮ ይቅርታ ማጣት፣ እንደ ርዮት ታስሮ ጠያቂ ማጣት፣ እንደ እስክንድር ታስሮ ቤተሰብ ማጣት ወይስ እንደ ዳዊት ታስሮ አሳሪ ማጣት!? (በቅንፍም የሆነውስ ሆኖ ግን ስንት አመት ሰው ሀገር እቆያለሁ የሆነ ቀንማ ሄጄ መቀወጤ አይቀርም፡፡ (በሌላ ቅንፍም ደግሞ ሳላግጥ፤ ቢያንስ ግን ለጨዋታም ለቃለ ምልልስም እንዲመች የባቡር ግንባታው እንኳ ይለቅና እንተያያለን…!))

No comments:

Post a Comment