አሜሪካ የመጣችው ከ27 አመት በፊት ነበር። ሁለት ልጆች የወለደችለት ባለቤትዋ በሞት ሲለያት ታዳጊ ህጻናት ልጆቿን ይዛ በሱዳን በኩል አድርጋ አሜሪካ መጣች። ሳልዋ ትባላለች፤ የጠይም ቆንጆ ናት። በአሜሪካ ዲሲ ከተማ ብዙዎች የሚያውቋት በታታሪ ሰራተኛነቷ፣ በሳቅ ጨዋታዋ፣ እንዲሁም በመልካም ባህርይዋ ነው። ጥሩ ስራና ገቢ የነበራት ሳልዋ በፍቅር ከቀረበችው ሃበሻ ጋር በአብሮነት መኖር ይጀምራሉ። ለረጅም አመት ብዙዎችን የሚያስቀና ፍቅር እንደነበራቸው የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
በድንገት የሳልዋን ልብ የሚሰብር ሁኔታ ይፈጠራል፤ የምትወደውና ልጅ ያልወለደችለት ፍቅረኛዋ በድንገት በሞት ይለያታል። ሃዘኑን መቋቋም የተሳናት ሳልዋ ይባስ ብሎ ሁለቱ ልጆቿ ጥለዋት ወደ ሌላ ከተማ ሄዱ። ለ17አመታት ገደማ ጠይቀዋት አያውቁም፤ እሷም ልጆቿ የት እንዳሉ አታውቅም። ሶስት ነገር ያጣችው ሳልዋ ጤናዋ ተቃወሰ። አእምሮዋ ተነካ። ህይወት ፊቷን አዞረችባት። ለጎዳና ኑሮ ተጋለጠች። ሃበሻ በሚበዛበት መንገድ ከአንድ ሬስቶራንት ጥግ ኩርምት ብላ ታሳልፋለች። ያገኘችውን ሃበሻ « ነፍሴ..ወገኔ..ኑርልኝ!» እያለች በጣፋጭ አንደበቷ ሰላምታና መልካም ምኞቷን ትገልፃለች። ለመጀመሪያ ግዜ ካገኘኋት ከአምስት ወር በኋላ ዳግም ሳገኛት አልረሳችኝም ነበር።
የማስታወስ ችሎታዋን አደነቅኩላት። ኑሯዋ ግን እጅግ አሳዛኝ ነው። ስትናገር ቀልጠፍ የምትለው ሳልዋ እንዲህ አለች፥ « በእኔ የደረሰው በማንም አይድረስ። ወላድ ይፍረደኝ!! ሁለት ጊዜ ትዳር ብመሰርትም ፈጣሪ ነጠቀኝና ብቸኛ አደረገኝ። እንደገና የወላድ መካን ሆንኩ። እብድ እናት ስለሆንኩ አፍረውብኝ ይሆናላ!? ምን አደርግላቸዋለሁ!?..እስቲ ንገረኝ?…እ..እ…ንገረኝ ነፍሴ!?..» ቅዝዝ ብላ አተኩራ እየተመለከተችኝ።….በዲሲ ለ35 አመት የኖረ አንድ ሃበሻ ስለሳልዋ ሲናገር፥« እንዴት አይነት መልካም ሰው መሰለችህ!! ስራ በነበራት ጊዜ ሃበሻ እንዲህ ችግር ደረሰበት ሲባል ገንዘብ ቀድማ የምትሰጥ ደግ ሴት ናት።
እኔን ጨምሮ ለብዙ ሰዎች ገንዘብ ታበድረን ነበር። አንዳንዱ ሳይመልስላት ሲቀር ምንም አትልም። ሳልዋ እንዲህ መሆኗ..» ሳግ እየተናነቀው ሳይጨርስ ተወው። ሳልዋ አዘውትራ ከማትጠፋበት ጎዳና በ30ሜትር ርቀት የኮሚኒቲ ቢሮ አለ። ግን እሷን የሚያይ “አይን” የላቸውም።…
No comments:
Post a Comment