Thursday, 23 January 2014

ከቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶች በላይ የሚያንጸባርቁ ከዋክብት (ዳዊት ከበደ ወየሳ፣ አትላንታ)

ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)

(ይህ ጽሁፍ የርዕዮት አለሙ የልደት በአል በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት; ከውጭ አገር ንግግር እንዳደርግ በተጋበዝኩበት ወቅት… የስራ ባልደረቦቼን እስክንድር, ውብሸት እና ርዕዮትን በማሰብ የተዘጋጀ ነው)
ይህ ሳምንት የታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በመላ አሜሪካ የሚከበርበት ነው:: በአሜሪካ ከክርስቶስ ልደት ቀጥሎ ስራ እና ትምህርት ቤት ተዘግቶ ልደቱ የሚከበርለት አንድ ሰው ቢኖር ማርቲን ሉተር ኪንግ ብቻ መሆኑን ልብ ይበሉ:: የማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በሚከበርበት ወቅት በህይወት ዘመኑ ለጥቁር ህዝብ ነጻነት ያደረገው አስተዋፅኦ ይታወሳል:: በህይወት በነበረበት ወቅት ለሰው ልጅ እኩልነት ተሟግቷል; የነጻነት ቀንዲልን ለኩሷል:: ሆኖም እኩልነት እና ነጻነትን ሳያጣጥም በበርሚንግሃም እስር ቤት ተጥሎ ፍዳውን እንዲቆጥር ተፈርዶበት ነበር:: በመጨረሻም የሰውን ልጅ ክብር እና ነጻነት በማይደግፉ ሰዎች ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል – መልካም ስራዎቹ ግን አላለፉም::Reeyot Alemu, the 31 year-2012 Courage in Journalism Award winner.
ዛሬም በአገራችን ስለፍትህ, ስለነጻነት የሰበኩና የደሰኮሩ; የጻፉና የመሰከሩ… ለሃቅ ቆመው፣ ግፍ የተሰራባቸው፣ ከአገር የተሰደዱና የወጡ፤ በግፍ ሰንሰለት ለጨለማ እስር የተዳረጉ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው:: እስክንድር፣ ውብሸት፣ ርእዮት፣ አንዷለም እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በሰብአዊነት መሰረት ላይ ስላነጹ እና ሃሳባቸውን በነጻነት ስለገለጹ መጨረሻቸው እስር እና እንግልት ሆኗል::
እንደ እውነቱ ከሆነ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ… ብሎም የህዝብ ልሳን ሆኖ ለህዝብ የቤዛነት ዋጋ መክፈል የሚያስከብር እንጂ የሚያሳስር አልነበረም:: በመሆኑም ለነጻ ፕሬስ መክፈል የሚገባቸውን ዋጋ ከመጠን አሳልፈው የከፈሉት፤ ርዕዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ እና ውብሸት ታዬ… ሶስቱም ከአገራቸው አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል:: በአለም አቀፍ ደረጃም በልዩ ልዩ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማህበራትና ተቅውውማት ለሽልማት ታጭተው አሸናፊ ሆነዋል::
የ’ነዚህ የስራ ባልደረቦቼ ብዕር… ህዝብን ሳይሆን የተወሰኑ ወገኖችን አሸብሮ ሊሆን ይችላል:: እነርዕዮት አለሙ በዚህ አይነት ሰበብ አስባብ በቃሊቲ እና በቂሊንጦ እስር ቤት ታግተው፤ ነጻነታቸውን አጥተውና ህክምና ተነፍገው ይታሰሩ እንጂ፤  ለእውነት የቆሙ ወገኖች ግን ለመልካም ስራቸው ሽልማትን አልነፈጓቸውም::
ማርቲን ሉተር ኪንግ በበርሚንግሃም እስር ቤት ታስሮ ቢማቅቅም የአሜሪካም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አልዘነጋውም:: ቆይቶም ቢሆን የአለም አቀፉ ኖቤል ተሸላሚ እስከመሆን ደርሷል:: ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች የኖቤል ተሸላሚ ባይሆኑም አለም ግን አልረሳቸውም:: ከታሰሩበት የጨለማ ወህኒ ቤት ጀርባ፤ ከብረት ፍርግርግ እና ከግድግዳዎቹ ባሻገር በመቶዎች፣ በሺዎች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ጋዜጠኞች በመልካም ስራቸው ያስታውሷቸዋል; ይዘክሯቸዋል:: ስለሆነም የጻድቃን ሞት፤ የሰማዕትነት ጽድቅ ተደርጎ እንደሚቆጠረው ሁሉ… የነ እስክንድር፣ ውብሸትና ርዕዮት እስር፤ ከቶውኑ ዋጋ ቢስ እና ፍሬ አልባ ሊሆን አይችልም::
ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት በፕሬስ ጉዳይ ተደጋጋሚ የሆነ እስር ደርሶብኛል:: በ’ነዚህ የእስር እና እንግልት ጊዜያት ግን… ከጨለማው እስር ቤት ማዶ ለምን እንደታሰርኩ የሚረዱ ሺዎች በመኖራቸው ሁልጊዜ እጽናና ነበር:: በተደጋጋሚ እስር ቤት እየመጣ የሚጠይቀኝ እና የዋስ መብቴን አስጠብቆ ከእስር እንድወጣ ያደርገኝ የነበረው ወላጅ አባቴ፤ “የታሰርከው ሰርቀህ ወይም ሌላ ወንጀል ሰርተህ ሳይሆን፤ እውነትን ስለተናገርክ ነው:: ስለዚህ አንገትህን ቀና ልታደርግ እንጂ ልትሸማቀቅ አይገባህም::” የሚል አጽናኝ ቃል ሁሌ ይነግረኝ ነበር:: ዛሬ አባቴ በህይወት የለም:: ቃሉ እና ምክሩ ግን አብሮኝ አለ:: በእስር ላይ ለሚገኙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ “አንገታችሁን ቀና አድርጉ!” የሚለውን መልዕክት አጋራቸዋለሁ::
ዛሬ በጋዜጠኞቻችን ላይ የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸው መታሰራቸው ሳያንስ; ከታሰሩም በኋላ በሃሰት ሊወነጅሏቸው የሚሹ ብዙ ግራ ዘመም ሰዎች መኖራቸውን ታዝበናል:: በአሜሪካ ከፍተኛ የአየር ሽፋን አግኝቶ ዲሞክራቶችን በመሳደብ የሚታወቀው ራሽ ሊምቦ የተባለ ጋዜጠኛ በቅርቡ ኔልሰን ማንዴላ በሞት ሲለዩ… “ብታምኑም ባታምኑም ኔልሰን ማንዴላ አሸባሪ ነበሩ::” ብሎ ሰፊ ሙግት ፈጥሮ ነበር:: ይህ አባባሉ ለኛ እና ለሌሎች አፍሪቃውያን ሊገርመን ይችል ይሆናል:: ነገር ግን የራሳቸው አመዛዛኝ ህሊና ያልፈጠረባቸውና ይህን ሰው በጭፍን የሚከተሉት ሰዎች “አዎ ማንዴላ አሸባሪ ነበሩ” ብለው ቢሉ ሊገርመን አይገባም::
ዛሬም ባገራችን በተመሳሳይ መልኩ የነርዕዮት አለሙን መልካም ስም ጥላሸት ለመቀባት እላይ ታች የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ… እኛ ግን እንላለን:: “ወንጀል አልሰራችሁምና አንገታችሁን ቀና አድርጉ!” ስማችሁ ከቃሊቲና ከቂሊንጦ እስር ቤቶች በላይ፤ በጠራው ሰማይ ላይ ያንጸባርቃል፤ ቃለ ሃቃቹህ በአየር ናኝቶ… ኢትዮጵያዊያን ባሉበት ሁሉ በመላው አለም ላይ ተሰራጭቷል::
የማርቲን ሉተር ኪንግ ልደት ሲከበር መልካም ስራዎቹ እንደሚወደሱ ሁሉ፤ ዛሬም ሆነ ወደፊት የነርእዮት አለሙ ልደት ሲከበር መልካም ስራዎቻቸው በተደጋጋሚ ይነሳሉ ይዘከራሉ:: ዛሬ ማንዴላን አሸባሪ ብለው የሚከሱ ሰዎች እንደመኖራቸው መጠን; በተመሳሳይ መልኩ ለነርእዮት አለሙ ተመሳሳይ ስም የሰጡና ያሰጡ… ለመስጠት እና ለማሰጠት የሚጥሩ ሰዎች አሉ:: እኛ ግን የተለኮሱ ሻማዎች ይዘን ልደት ስናከብር; የብርሃናችን  ጮራ፤ ሌሎች የፈጠሩትን የጨለማ ድባብ ሰንጥቆ… አንዳች ብርሃን እንደሚፈነጥቅላቸው በማመን ነው:: ዛሬ የርዕዮት አለሙን የልደት ቀን ስናከብር፤ ያለፍትህ የታሰሩትን ፍትህ የሚፈልጉትን፤ ነጻነት የተጠሙትን ነፍሶች በማሰብ ጭምር ነው::
መልካም ልደት – ርዕዮት!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10805/

No comments:

Post a Comment