Thursday, 16 January 2014

ፕ/ር በየነ “የአካኪ ዘራፍ ትግል አክሳሪ ነው፤ የስሜት ፖለቲካ ያብቃ” አሉ

“ከኤርትራ ጋር መስማማት አግባብ ነው፤ ግን ፍርሃቻ አለኝ”

beyene petros


“የአካኪ ዘራፍ ፖለቲካና ከስሜት ያልጸዳ የፖለቲካ ትግል መሪውንም ሆነ አምኖ የሚመራውን ህዝብ ለድል” እንደማያበቃ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ። ከኤርትራ ጋር ስምምነት ቢደረግ መልካም መሆኑን፣ ነገር ግን ስምምነቱ የመሪዎችና የፖለቲከኞች ሳይሆን የህዝብን ስሜት የጠበቀ ሊሆን እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጋር በተለይ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕ/ር በየነ “አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስተዋይነት የሚፈልግ፣ ዘመናዊ የትግል ስልት የሚጠይቅ ነው” በማለት ተናግረዋል። በቃለ ምልልሳቸው ደጋግመው  “አሁን በተያዘው የአካኪ ዘራፍ መንገድ የትም አይደረስም” በማለት ምክንያታቸውን ዘርዝረዋል።
ትንንሽ ጠርዝ በመያዝ የትም የማይደርስ ትግል ከየአቅጣጫው እንደሚፈለፈል ፕ/ር በየነ አመልክተዋል። በዚሁ የተነሳ ስትራቴጂካልና ታክቲካል ጉዳይ የመለየት አቅም አናሳ በመሆኑ የፖለቲካው መንደር የርስ በርስ ንትርክና ውግዘት ሊሆን እንደቻለ ገልጸዋል። ለዚህም ተጠያቂዎችና ቅድሚያ ተወቃሾች ህዝብና አገር የምትፈልጋቸው የዘመናዊ ለውጥ መሪዎች መሆን ሲገባቸው የዳር ተመልካች የሆኑት የአገሪቱ ልሂቃን እንደሆኑም በግልጽ ተናግረዋል።
“ችግሩ በአገር ውስጥ ባሉት ልሂቃን ላይ ጎልቶ ቢታይም፣ በውጪው ዓለም ባሉት ምሁራኖችም ላይ ተመሳሳይ ችግር አለ” የሚሉት ፕ/ር በየነ “እነዚሁ ክፍሎች ትግሉን ከመቀላቀል ይልቅ እኛን በመውቀስ አገራዊ ሃላፊነታቸውን የተወጡ መስለው ይታያሉ” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
“የፖለቲካው መስመር ክፍተትን አይወድም” በማለት የሰከነ አመለካከት ላላቸውና ከስሜት ፖለቲካ ነጻ ለሆኑት ዜጎች መልዕክት ያስተላለፉት ዶ/ር በየነ፣ ሰዓትና በጀት በመመደብ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክፍሎች ሰድቦ የማሰደብ ተግባር ሲከናወን ማየታቸው በጅጉ እንደሚያሳዝናቸው ተናግረዋል። በጦር መሳሪያና በሃብት ብዛት መፎካከር ባይቻልም፣ በሰብአዊ ብቃት ኢህአዴግን መፎካከር እንደሚቻል የጠቆሙት ዶክተሩ የተቃዋሚው ሰፈር በተቃራኒው የተፈረካከሰ፣ እርስበርስ ለመባላት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ የትግል ስልቱም ሆነ አቅሙ ስትራቴጂካዊና ታክቲካል ጉዳዮችን መለየት በማያስችል ደረጃ የተዋቀረ መሆኑ ትግሉን ፍሬ አልባ እንዳደረገው ተናግረዋል።
beyene_petros“ለአውራነት/ኮርማነት የታሰበ በሬ ተመልሶ ላሚቱን ጠባ” በሚል በሃድያ የሚነገር ተረት በማስታወስ ሃሳባቸውን ያጠናከሩት ዶ/ር በየነ፣ የዚህ ሁሉ ችግር መንስዔው የልሂቃኑ ዝምታ እንደሆነ አመልክተዋል። አገራቸውን ወደ ተሻለ መንገድ ለማሸጋገር የሚችሉ ሁሉ ዝምታቸውንና ዳር ቆመው የሚመለከቱትን የአገራቸውን ውድቀት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል። ዶ/ር ነጋሶ የወሰዱትን ርምጃ በማንተራስ ስለ ፖለቲካ ጡረታም ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል።
“እናንተ አርጅተሃል ካላችሁ እንጂ እኔ አላረጀሁም። ጤነኛ ነኝ። የነጋሶን ያህል እድሜም የለኝም” በማለት መልሳቸውን ይጀምራሉ። በማያያዝም “ልተውስ ብል እንዴት ብዬ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “ልሂቃኑ ዳር ቆመው ተመልካች ሆነዋል። በዚህ ላይ የምመራቸውና ውህደት የፈጠሩት የደቡብ ህብረትና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ አደራውን ከኔ አላወረዱም። አሁን በቃኝ ማለት ሰራዊት በትኖ እንደሚፈረጥጥ መሪ የመሆን ያህል ነው።”
ኸርማን ኮህን በቅርቡ ይፋ ያደረጉትን የእርቅ ሃሳብ አስመልከቶ ማብራሪያ ሰጡት ዶ/ር በየነ “በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የሚደረግ ስምምነት ከቶውንም ቢሆን ተቀባይነት የለውም። ከኤርትራ ጋር እርቅ መልካም ቢሆንም በፖለቲከኞችና በውስን ሃይሎች ፍላጎት ተከናውኖ ሰዶ ማሳደድ እንዳይሆን እፈራለሁ” ብለዋል። ከዚሁ ጋር በማያያዝ አሜሪካ በኢህአዴግና በወያኔ የፖለቲካ እምነት ደስተኛ እንዳልሆነች ተናግረዋል። ድጋፍ የምትሰጠው ከፍቅር ብዛት እንዳልሆነ በማመልከት የተቃዋሚው ክፍል ይህንኑ ቀዳዳ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል። “ታዲያ” አሉ ፕ/ር በየነ “ታዲያ በማንጓጠጥና በዘለፋ ሳይሆን በሰከነ መንፈስና ስሜትን በገደለ አስተዋይነት” ሊሆን ይገባል። በመጪው ምርጫ የ1997 ምርጫ ዓይነት ሁኔታ እንዲፈጠር ዘመቻ መጀመሩንና የድጋፍ ፍንጭ መታየቱን የገለጹት ዶ/ር በየነ ስለ ሃይል አማራጭና ኢህአዴግ፣ በተለይም ህወሃት ውስጥ አለ ስለሚባለው የመፈረካከስ ችግር ተጠይቀው “ጦርነት የሁለት የጎበዝ አለቆች ጸብና ድብድብ ነው። ከአሁን በኋላ እኔ ላገሬ ጦርነት አልመኝም” በማለት ከምክንያታቸው ጋር አስቀምጠዋል። ህወሃትና ኢህአዴግ ውስጥ አለ ስለተባለ የመፈረካከስ ችግር “የዋህነት አይጠቅምም፣ በስሜትና በአካኪ ዘራፍ ፖለቲካ የሚመጣ ለውጥ ይኖራል ብዬ አላስብም” ብለዋል። ስለ ስጋታቸውም ተናግረዋል።
“ወያኔ የሚባለውና ተዘጋጅቶ አገሪቱን የተቆጣጠረ ሃይል ለሰበሰበው ሃብትና ንብረት ሲል ፖለቲካውን በበላይነት ለመምራት ከቀን ወደ ቀን የሚፈጽመው ጥፋት ህዝብ እያማረረ መጨረሻው አገሪቱን ወደ ጥፋት እንዳይወስድ ነው። የከፋቸው በጨመሩ ቁጥር ችግሩ መከሰቱ አይቀርምና በጥበብ ታግሎ ካሰቡት ለመድረስ እነሱ ከሚያስቡት በተለየ በልጦ ማሰብና መታግል አስፈላጊ ነው። ለዚህም የልሂቃኑ ዳር ቆሞ መመልከት መቆም አለበት” ብለዋል። በማያያዝም ዲያስፖራው አገር ውስጥ ለሚታገሉ ድርጅቶች ልዩነት ሳያደርግ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። ድጋፉም ሆነ እገዛው ሰክኖ ለማሰብ እንደሚመነጭም ገልጸዋል። ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ በተለይ ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ያደረጉትን ሙሉ ቃለ ምልልስ በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን።
http://www.goolgule.com/beyene-says-politics-of-emotions-should-end/

No comments:

Post a Comment