Wednesday, 12 June 2013

የዳውድ ኢብሣ ኦነግ ለተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ የጻፈው ደብዳቤ አማርኛ ትርጉም


dawd ibsa
አዳ ቢሉስማ ኦሮሞ (ኦነግ)
ይነጋል በላቸው
ሰሞኑን ለድረገፆች የላክኋትን አንዲት ትርጉም ቢጤ ተመርኩዘው ብዙዎች ሲቆራቆሱባት ታዘብኩ፡፡ የኢሣቱ ልጅ ተክሌ የሚላት ነገር ትዝ አለችኝና በዚህ አጋጣሚ እሷን አስታውሼ ወደድኩለት፤ በቀጥታ ላልጠቅሰው እችላለሁ – የምጽፈው ነገር አቧራ ካላስነሳ የጻፍኩ አይመስለኝም – ይላል ልጅ ተክሌ፤ እውነቱን ነው፡፡ እየበሉ እየጠጡ ዝም… የሚባለው የመደሰቻ ድግስ ብሂል እንኳን መብላት መጠጣታቸው ስለሚታይ ነው፡፡ የአንድ ጽሑፍ መነበብና አለመነበብ የሚለካው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሰላማዊ ውርክብ ሲታይ ነው፡፡ በነገር መነታረክ መጥፎ አይደለም፤ ከብዙ ተጨቃጫቂ መካከል አንድና ሁለት የሚማማር ሰው ማግኘት ቀላል አይደለምና፡፡ ፍሬና ገለባ ከሚለይባቸው መንገዶችም አንዱ ይሄኛው ነው፡፡ ‹ከአነጋገር ይፈረዳል፤ከአያያዝ ይቀደዳል› እንደምንል፡፡
ዛሬ ደግሞ በ‹ጠዓመኒ ድግመኒ› የትግርኛ ብሂል መሠረት አንዲት ነገር ተርጉሜ ማስነበብን ወደድኩ፡፡ የዛሬው ወደአማርኛ በከፊል የተመለሰ ጽሑፍ ቀደም ሲል ከድረ ገፅ ያወረድኩትና ለክፉ ቀን ሳይሆነኝ አይቀርም ብዬ እንዳይዘነጋኝ በ‹ሾርት ከት› የኮምቡጦሬ ደስክቶፕ ላይ ያኖርኩት አንድ አስደናቂ የኦነግ ደብዳቤ ነው፡፡ የደብዳቤ መለያውን ፍርማት(head letter) በኦሮምኛ፣ በዐረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ያዘጋጀው ይህ ግምባር የጌቶቹንና የጃዝ ባዮቹን የኤሪዎች ትግርኛ – የኛም ነው ለነገሩ – አለመጨመሩ ገርሞኛል፡፡ (ሰዎች እየተጃጃሉ የማያስፈልግ ግጭት ውስጥ የሚዘፈቁት እኮ ቋንቋን ልክ እንደ አንድ የምርት መገልገያ መሣሪያ ወይም ልክ እንደሸሚዝና ከናቴራ ከመቁጠር አልፈው በዘር ሐረግ ባሕርያዊ ውርስ ከአባት ወደ ልጅ እንደሚተላለፍ ትልቅ ቁም ነገር እየቆጠሩ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ በመግባታቸው ነው – እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በዚህም ላይ እመለስበታለሁ)፡፡
ትግርኛን አለመጨመሩ ድርጅቱ ዕድሜ ጠገብ በመሆኑ ሊሆን ይችላል ከወያኔ በተሻለ ይሉኝታን ያውቃል ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ግምባሩ ለተቦረቦሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ለሚስተር ባን ኪ ሙን የላከውን ደብዳቤ ሙሉ ቃል ሳይሆን የተወሰነውንና ከሀገራችን ወቅታዊ የመጋኛ ምች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለውን ይህን የተላላኪዎች ጦማር ተርጉሜ ላስቃኛችሁ ፈልጌያለሁና ለማንበብ ትብብራችሁን አትንፈጉኝ፡፡ ሁሉንም ያልተረጎምኩት ረጂም ስለሆነና ከወቅታዊነት አንጻር አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ነው፡፡ ለሁላችሁም መልካም ንባብና ለአንዳንዶቻችሁ በተለይ መልካም መናደድ ይሁንላችሁ፡፡
OROMO LIBERATION FRONT
Gaafa: 09-08-2011 Date:
ﺗﺎرﺦﻳ رﻢﻢ
His Excellency Ban Ki-moon
Secretary General of the United Nations,
The United Nations Organization,
New York, N. Y.
( በቀጥታ ለዋና ጸሐፊው ስለተጻፈ Your Excellency ቢባል ይሻል ይመስለኛል – ለማንኛውም እንደገባኝ ልቀጥል – በቅንፍ የሚገኙ ጭማሪዎችና ደብተራ የጫጫረው አሸንክታብ ያስመሰልኩበት ልዩ የቀለም አፅንዖት የኔ ናቸው፡፡)
ለተከበሩ ባን ኪ ሙን
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ
ይህን ደብዳቤ የምጽፍልዎ ሶማሊያንና ኢትዮጵያን የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት (ከአሁን በኋላ የተ.መ.ድ በሚል አሳጥረዋለሁ) የቁጥጥር ቡድን ፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ በጁን 21/2012 የተደረገውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ለማደናቀፍ ታስቦ ተጠነሰሰ የተባለለትን ሤራ (የኢሕአዲግ መንግሥት) አከሸፍኩ ማለቱን ተከትሎ ኦነግን በዚህ የሽብር ድርጊት ውስጥ ከሌሎች ኃይላት ጋር ለማካተት ሙከራ የተደረገበትን ሪፖርት በመቃወም ነው፡፡
ይህ ዜና በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በወጣበት ወቅት ኦነግ የአፍሪካ ኅብረትን ስብሰባ በቦምብ ለማጋየት ተጠንስሷል በተባለ በዚህ የሽብር ጥቃት ውስጥ (ከእውነት ተሞክሮና ከሽፎም ከሆነ) እጁ እንደሌለበትና እንዲያውም ይህን ዓይነቶችን ንጹሓን ዜጎችን ለዕልቂት የሚዳርጉ ተግባራትን እንደሚቃወም በጊዜው በማያወላውል ሁኔታ አስታውቋል፡፡ በብሉምበርግ የዜና ማዕከል የዜና ዕወጃ እንደተገለጸው “ኦነግ የአፍሪካ ኅብረትን ለማፈንዳት አላለመም ወደፊትም አያልምም”፡፡ እንደድርጅቱ ፖሊሲም “ኦነግ ሲቪሎችን፣ የሲቪል ተቋማትንና ንብረቶቻቸውን በጥቃት ዒላማው የዕቅድ ዝርዝር ውስጥ አይጨምርም፡፡”
እ.ኤ.አ ከ1991 ጀምሮ የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል የተቆጣጠረው የመለስ (ዜናዊ) አገዛዝ ኦነግን በተለያዩ የሽብር ተግባራት ሲከስ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህም ማለቂያ የሌላቸው የሽብር እንቅስቃሴ ተብዬዎች በእውን የሚታዩ ሳይሆኑ በራሱ በኢሕአዲግ መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ክፍል አማካይነት በቤተ ሙከራ እየተፈበረኩ መንግሥትን በሚቃወሙ ኃይሎች ላይ የሚለጠፉ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ በቅርቡ በዚሁ የወያኔ መንግሥት የደኅንነት ሰዎች የተሠራውንና “ አዲስ አበባን እንደባግዳድ” በሚል ርዕስ ለዕይታ የበቃውን በዶኩመንተሪ ፊልምነት የቀረበ የቤተ ሙከራ ሥሪት ብንመለከት ኦነግን ከሽብር ተግባር ጋር ለማቆራኘት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህ የተ.መ.ድ የሶማሊያና ኢትዮጵያ ተቆጣጣሪ ቡድን ይህን የመንግሥት የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንዳለ ገልብጦ በሪፖርትነት ማቅረቡ ድርጅታችንን ኦነግን በእጅጉ አሳስቦታል፡፡ /ያን ቪዲዮ ለማየት ይህን አድራሻ ይጠቀሙ –http://www.diretube.com/etv-special/addis-like-baghdad-documentary-video_58f9ec467.html/. …
/የድርጅታችንን የኦነግን [የምሥራቅ አፍሪካ] አድራሻ ከፈለጉ ይሄውልዎ፡- P.O.Box 6973 Asmara, Eritrea Tel 2911 110236 Email: abamilki@gemel.com.erhttp://www.oromoliberationfront.org/
ይህ የተ.መ.ድ ተቆጣጣሪ ቡድን (The MGSE group) ድርጅታችንን ከዚህ የሽብር ጥቃት ጋር በዕብለት ከማነካካቱም በተጨማሪ የኤርትራን መንግሥት ከኦነግ ጋር አንዳች ግንኙነት እንዳለው ለማስመሰል ማለትም የኦነግን ዓላማዎች በማስፈጸም ረገድ የኤርትራ መንግሥት እንደሚሠራ ለማሳመን በተሳሳተ ሁኔታ ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ (ለኢትዮጵያው የወያኔ መንግሥት የሚያዳላው) ይህ ቡድን የኤርትራ መንግሥት የኦሮሞን (ሕዝብ) ትግል በበላይነት እንደሚመራ ለማስመሰል ባደረገው ጥረት የተሳሳተ ግንዛቤን ሊፈጥር የሚችል ሪፖርት አሰራጭቷል፡፡ በበኩላችን ይህን ቡድኑ እያወቀም ይሁን ሳያውቅ ያሰራጨውን ስምና ዝናን የሚያጠለሽ ሪፖርት በተመለከተ የኤርትራ መንግሥት በራሱ መንገድ እንደሚሄድበትና ራሱን እንደሚከላከል ሙሉ እምነታችን ነው፡፡ ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት በጉዳያችን ፈጽሞውን ጣልቃ እንደማይገባና የድርጅታችንን ነጻነት እንደሚጠብቅ ለሚመለከተው ወገን ሁሉ ማሳወቅ እንወዳለን፡፡ በሌላም በኩል የኤርትራና የኦሮሞ ሕዝቦች ከመቶ ዓመታት በላይ የዘለቀ ረጂም የጋራ ታሪክና መልካም ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እንሻለን፡፡ የኤርትራ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ አሁን ለሚገኝበት ሁኔታ ያለው ራሮትና ድጋፍም ከዚህ የረጂም ዘመን ትስስር የሚመነጭ ነው፡፡
ክቡር ዋና ጸሐፊ
ደግመን ደጋግመን ለመላው ዓለም እንዳሳወቅነው ኦነግ ማለት የኦሮሞን ሕዝብ ብሔራዊ ትግል በማስተባበር ኦሮሞንና ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ለማውጣት ቆርጦ የተነሣ ሕጋዊ ድርጅት መሆኑን አሁንም በዚህ አጋጣሚ ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ የኦነግ ግብ የኦሮሞ ሕዝብ ማንኛቸውም የዓለም ሀገራትና የተ.መ.ድ ራሱ የሚያምኑበትን መሠረታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲጎናጸፍ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም ኦነግ በአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና ሀገሮች ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር አበክሮ ይጥራል፡፡ …
የተከበሩ ዋና ጸሐፊ፤
olf flagኦሮሞዎች፣ በአፍሪካ ቅርምት ዘመን የአውሮፓ ቅኝ ግዛት የፈጠሯት የቅርብ ጊዜይቱ አፍሪካዊት ቅኝ ገዢ ሀገር አቢሲኒያ ወይም ኢትዮጵያና አውሮፓውያን ራሳቸው በጫኑባቸው አስከፊ ጭቆናና መሪር ቅኝ አገዛዝ ካለፉት አንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት ጀምሮ ስቃይ ላይ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ዛሬ ኦሮሞዎች በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው ሕዝቦች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የኦሮሞዎች ቁጥር 40 ሚሊዮን አካባቢ ይደርሳል፤ ይህ ደግሞ የጠቅላላውን ነዋሪዎች ቁጥር 40 በመቶ ያህል ነው፡፡ የኦሮሞዎች ሀገር – ኦሮሚያ – በተለይ ለኢትዮጵያና በአጠቃላይ ደግሞ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናት፡፡ ኦሮሞዎች ከማንም ሕዝብ በተለዬ ሁኔታ አንድ ዓይነት ባህል፣ አንድ የጋራ ቋንቋ፣ አንድ የጋራ ታሪክ፣ እንዲሁም አንድ ዓይነት የዘር ሐረግና ልዩ የመኖሪያ ግዛት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ኦሮሞዎች ከኢትዮጵያውያንና ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች ጋር ሰፊ የባህልና የኢኮኖሚ ትስስር ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ከኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥታትና ከሌሎች በርካታ የቀንዱ ሀገራት ጋር በድንበር ይገናኛሉ፡፡
የሀበሻ ገዢዎችና የፖለቲካ ምጡቃን(ኤሊቶች) በኦሮሞዎችና በሌሎች ተገዢዎች አጠቃላይ ሕይወት ላይ መድሎን፣ አስገድዶ መግዛትን፣ አፈናና ጭቆናንና ብዝበዛን ጨምሮ ያልጣሉባቸው የክፉ አገዛዝ ቀምበር የለም፡፡ እነዚህ የሀበሻ ቅኝ ገዢዎች የኦሮሞን ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግና ልማድ ወዘተ. ለማጥፋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ በወራሪ የቅኝ ገዢ ኃይል ሥር እንደመገኘታቸው ኦሮሞዎች ሀበሾች በሚቆጣጠሩት የኢትዮጵያ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ እንደሁለተኛ ዜጋ ይቆጠራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምጡቃን ዘረኛ አመለካከትና መናኛ አስተሳሰብ እንዲሁም ሥልጣናቸውን በእጃቸው እንዳለ ለማቆየት ያደረባቸው ጉጉትና ቅዠት ዴሞክራሲንና ልማትን እውን ለማድረግ እንዳይቻል እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዘረኝነትንና መድሎን አስወጋጅ የተ.መ.ድ ኮሚቴ በአንደኛው ሪፖርቱ “ … ከ1995 እስከከ 2005 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከታዩ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች አብዛኞቹ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የተከሰቱ ናቸው፡፡ ከነዚህ ዓመታት ውስጥ ከአንደኛው በስተቀር በሁሉም ዓመቶች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝና ብይን ውጪ ግድያና እሥር ተፈጽሟል፤ በነዚህ ዓመታት ውስጥ በኦሮሞ የተፈጸመውን ያህል ግፍና በደል በሌሎች ክልላዊ መንግሥታት ውስጥ መፈጸሙን የሚያመለክት ዘገባ ወይም ሪፖርት አልቀረበም፡፡ …”ሲል ገልጾኣል፡፡
በተጨማሪም በሰብኣዊ መብቶች መጠበቅ ዙሪያ የሚንቀሳቀስ አንድ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን በዘገባው እንደገለጸው “የርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ተከታታይ የአማራ-ትግሬ ገዢ መደቦች የኦሮሞን ሕዝብ ነጥለው የጥቃት ዒላማ ማድረጋቸውን በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ማቅረብ ይቻላል፡፡” ከዚህና ከሌሎችም ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞን ሕዝብ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ሰበቦች የጥቃት ሰለባ አድርጎ እያሰቃየው እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ … (የአማራውን ማለቅ ለመሸፋፈን ኢሣይያስ በኦነግ በኩል ለወያኔ የሰጠው ፖለቲካዊ ድጋፍና የዕርቅ መጎናበሻ ገጸ በረከት ይሆን?)
የኦሮሞ ሕዝብ የነጻነት ትግል ከቅኝ ገዢው የኢትዮጵያ መንግሥት ነጻ የመውጣት ፍላጎት የወለደው ተፈጥሯዊ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ከውጭ ወራሪ ኃይል ራስን ነጻ የማውጣት ትግልና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ደግሞ የተ.መ.ድን ጨምሮ በሁሉም ሀገራት ዕውቅና የተሰጠው ዓለም አቀፍ መብት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ይህን መብት ለኦሮሞ ሕዝብ ይነፍጋል፡፡ መንግሥት ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት በመፈጸሙም የተባበሩት መንግሥታትን ሕገ ደንብ አንቀጽ አንድ፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ ይጻረራል፡፡ ይህ ሕግ እንዲህ ይላል፡- “ሁሉም ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው፤ ይህን መብታቸውን አለገደብ በመጠቀምም የራሳቸውን የፖለቲካ ሥርዓት በነጻነት የመወሰን፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ዕድገታቸውን በፈለጉት አቅጣጫ የመምራትና የማሳደግ መብት አላቸው፡፡” …
ዳውድ ኢብሣ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግምባር ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር
______________________________________________
እንደተለመደው የራሴን ጥቂት ሃሳቦች በመናጆነት መለጠፌ አልቀረም፡፡ አንጋፋውና የእንጨት ሽበቱ ኦነግ ይህን አስገራሚ ደብዳቤ ከአሥመራ በላከ ሰሞን በአድራሻው ‹አንጀት የሚበላ› አጭር ኢሜይል ብልክም ሣንሱር አድራጊው ሕግሓኤ በቅድሚያ ስለሚያነበው ይመስለኛል መልስ የሰጠኝ አልነበረም፤ ለነገሩ እኔም አልኩ ለማለትና ለኅሊናዊ ውርድ ከራስ እንጂ ዐውቆ የተደበቀ ቢጠሩት እንዳለመስማቱ ከእሥረኛው ኦነግ መልስ መጠበቁ የዋህነት መሆኑን አጥቼው አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉዓላዊነት ከገፈፈ አካል ነጻነትንና ሉዓላዊነትን በምፅዋት መልክ መለመን የለዬለት ጅልነት መሆኑንም ብዙዎች ከበፊቱ ጠንቅቀን እንረዳ ነበር፡፡ በመሠረቱም ነጻነትን ከሚደፈጥጥ ወገን፣ ኢትዮጵያውያንን በኤርትራ ታዳጊ ሕጻናት አእምሮ ውስጥ በማስፈራሪያነት ከሚያሰርጽና በተለይ አማሮችን ለተዋጊዎቹ የዒላማ ተኩስ መለማመጃ ከሚያደርግ፣ የጦር ምርኮኞችን ጨፍጭፍ ራሳቸው በቆፈሩት ጉድጓድ አፈር የሚያለብስ፣ በሕይወት ካሉ ሰዎች የወርቅ ጥርስን በጉጠት እያወለቀ ከሚቀማ … የክፉዎች ክፉ የበላኤሰብ ቡድን ነጻነትን መጠበቅ ከብት ባልዋለበት ኩበት ፍለጋ እንደመሰማራት ነው፤ ይህን በጎ ነገር ከዚህ ዕኩይ ድርጅት መቀላወጥም ‹የጨነቀው ዱቄት ወደ ንፋስ ይጠጋል› እንደሚባለው የተስፋ መቁረጥ ምልክት ነው – ያበጠው ይፈንዳ የሚሰማኝን እውነት እናገራለሁ፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ነጻነት ሐዋርያ ሊሆን የሚችለው? የችግር መፈልፈያ ቋት በየትኛው ሒሣባዊ ቀመር ተገልብጦ ነው የመፍትሔ ምንጭ የሚሆነው?…
አሁን ኦነግ ፈራርሷል ተብሏል፤ ቢዘገይም ከቅሪቶቹ የተወሰኑት እየተጀነኑና በአስደግዳጊ ቅድመ ሁኔታም ታጥረው የኢትዮጵያን አንድነት ለመቀበል እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡ እውነቱን ለመናገር ኦነግ የፈረሰው ዛሬ ወይ ትናንት አልነበረም፡፡ የፈረሰው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቆርጠው ከተነሱ ወገኖች ትዕዛዝ እየተቀበለ በሰው ሣምባ እየተነፈሰ በብዙ የሞኝ ተግባራቱ ምክንያት ቀስ በቀስ ግን በሂደት ከኦሮሞ ሕዝብ ልብ መውጣት ሲጀምር ነው፡፡ ኦነግ ኖረ ከተባለ አንድ ጥጋት ላይ ቁጭ ብሎ ይህን መሰል መግለጫና ደብዳቤ በሚለቀልቅ የወረቀት ላይ ነብር የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ አማካይነት እንጂ በተግባር የኖረበትን ጊዜ ማስታወስ ያቅተኛል፤ እርግጥ ነው ድርጊቱ የተፈጸመው በበላይ ትዕዛዝም ቢሆን በበደኖና በአሰቦት ገዳም በጊነሰ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ሊመዘገብለት የሚገባው ሕጻናትና አእሩግ እንዲሁም መሣሪያ ያልታጠቁ ምሥኪን አማሮችን የመጨፍጨፍ ታላቅ ጀብድ ሠርቷል – በዚያ ድርጊቱ አለቆቹና ያን ግፍ የፈጸሙ የራሱ የኦነግ አባላት ተገቢ ዋጋቸውን ያገኛሉ – ዋናውን ፈላጭ ቆራጭ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ብዙዎቹ ወንጀለኞች ከአሁን በፊት ፍርዳቸውን እንዳገኙ ይገመታል፡፡ ከዚያ በመለስ ግን አንዲት የታወቀች መንደር እንኳን ይዞ ‹እዚህ አለሁ! ማን ነው ወንዱ! አካኪ ዘራፍ› ማለት ያልቻለና ሕይወቱን በስደት ኖሮ በዚያው በስደት ሕይወቱ ያለፈ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አንደኛው ተላላኪ እንጂ እውናዊ የነጻነት ፋኖ አልነበረም – መሪ ተብዬዎቹ የፈረንጅ ፓስቲ ሲገምጡና በዕርዳታና የውጭጭ ገንዘብ በቅንጦት ሲምነሸነሹ ኖረው በመጨረሻው በ’mission accomplished’ ፈረንጃዊ የቃቃ ጨዋታ ኦነግ ከጨዋታ ሜዳ መውጣቱን ለመሸፋፈን ቢሞከርም የኢትዮጵያ ትንሣኤ በሚበሰርበት ቅርብ ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ጠላት የሥራውን እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም፡፡
እናም ኦነግ ለማያውቁት ይታጠን፤ ቋንቋን ማሣመር የኅልውና ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም – ደግሞም ወግ አይቀርምና ‹ሲቪል ዜጎችና ንብረቶቻቸው ከኦነግ የዒላማ ጥቃቶች ውጪ ናቸው› ይባልልኛል፡፡ ለመሆኑ ደካሞችንና መሸሻ መጠለያ የሌላቸውን ዜጎችን ከመግደል ያለፈ የጦር ሜዳ ውሎ አለው እንዴ ኦነግ? የምን ንገሩኝ ባይነት ነው? የሌሎች ሀገሮች ተቃዋሚዎችና አማጺያን በጥቂት ወራትና ዓመታት ውስጥ ግባቸውን ሲመቱና በተናጠል ወይም በሽርክና መንግሥት ሲመሠርቱ ኦነግ በግማሽ ምዕተ ዓመት አንዲትም ወረዳ ሳይቆጣጠር በወሬ ኖሮ በወሬ የተፈታው በአቅም ማነስና በአመራር ጉድለት ሳይሆን በዓላማ ተልካሻነት ነው፡፡ ወንዝ የማያሻግር እንቶ ፈንቶ ዓላማ አንግቦ፣ ያንንም የጥላቻ ዘፈን አይሉት መዝሙር በጠላት አማካይነት እንደቴፕ ሪከርደር ተሞልቶ አሥመራ ላይ ሆኖ እንደጣቃ መቀደድ ድል እንደማያስገኝ እናውቅ ነበር፡፡ ወያኔንና ሻዕቢያን ያመነና ጉም የዘገነ አንድ መሆናቸውንም እናውቅ ነበር፡፡ ሻዕቢያና ወያኔም ባቅማቸው የአፍሪካ ሞሳድና ኬጂቢ ወይም ኤም አይሲክስና ሲአይኤ ሆነው (በሥልት መመሳሰል ማለቴ ነው) ኢትዮጵያን ለመበታተን ይህን ጅላጅል ድርጅት መጠቀማቸውን ልብ ለምንል ወገኖች ለመጥፎ ዓላማም ቢሆን ተግተው ከሠሩ የማይቻል ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ይቻለናል፡፡
ይሁንና እውነት ሁልጊዜም እውነት ስለሆነች በመጨረሻ ማሸነፏ አይቀርምና የኢትዮጵያ ጠላቶች አንድ ባንድ ግን በርግጠኝነት ወደ ከርሠ መቃብራቸው የሚነጉዱበት ዘመን እየመጣ ነው፡፡ ይህን የምንለው ይህኛውን ወይም ያኛውን የተቃዋሚ ቡድን አለኝታ አድርገን ሳይሆን ፈጣሪን ተመክተን ነው፡፡ ከሰው የምንጠብቀው ነገር ብዙም አይደለም፤ ያልታዘዘ ምንም ነገር አያደርግም፡፡ ከታዘዘ ግን ሣምንትም፣ ቀንም፣ ሰዓትም፣ ደቂቃና ሴከንድም የማድረጊያ ጊዜ ናቸው፡፡ የነጻነት ጎሕ ሲቀድ፣ እውነተኛው ሙሤ ሲላክ፣ … ያኔ የቁርጥ ቀን ሲመጣ አጭበርባሪውና ሆድ አምላኪው ሁላ የሚገባበትን ያጣል፡፡ …
በበኩሌ ይታየኛል፤ የሌቦች ዘመን እየተጠቀለለ ነው፡፡ የብርሃን ዘመን እየባተ ነው፡፡ ብዙ እንዳየን ብዙ እናያለን፡፡ እስካሁን ያየነው ሁሉ ባሳለፍነው አጭር ግን አስደንጋጭና አሰቃቂ ጊዜ ውስጥ እናያለን ብለን ካሰብነውና ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ የፈጣሪ ቀን አንዲት ብቻ አይደለችም፤ ቀናት ሁሉ የርሱው ናቸው፡፡ ነገን የማያውቁ ትናንትን የማያስቡና ማስታወስም የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ ናቸው፡፡ ዛሬ አብዛኛው ዜጋ ለሆዱ ተሸንፎ ስለሆዱ አድሮ በሆዱ እያሰበ ቢያድር ቢውልም ፈጣሪ ይህን የእበላ ባይነትና የስግብግብነት ዘመን ሲገፍፈው፣ ኅሊናም ትክክለኛ የዳኝነት ሥፍራውን ሲይዝ የሀገራችን ቅርጽ በቅጽበት ይለወጣል፡፡ ያኔ የጠፋው ሃይማኖት ይመጣል፤ ያኔ የጠፋው መተሳሰባችንና መተዛዘናችን ይመጣል፤ ያኔ ቁሣዊነት ይጫጫና ሰብኣዊነት ይፋፋል፡፡ ያኔ ይሉኝታና ሀፍረት ይወለዳሉ፡፡
በነገራችን ላይ “አንበሣን ፈርቼ ዛፍ ላይ ብወጣ ነብር ጠበቀኝ” እንዲሉ አንዱን ፈርተን ወደ ሌላኛው ልንሸሽ ስንሞክር የኋለኛው ከፊተኛው የባሰ እየሆነብን ስንሰቃይ መቆየታችንን ስናስብ የሀገራችን ነገር የእግር እሳት ይሆንብናል፡፡ እናም እንዳለመታደል ሆኖ ኦነግ ትልቅ ደረጃ መድረስ እየቻለ ባነገበው ውራጅ ዓላማና ግብ እንዲሁም የሰው አሽከር ለመሆን በመቁረጡ ሣቢያ ከስሜትና ከልብ ወጥቶ መሬት ሊቆነጥጥ የሚችል ድል ሊጎናጸፍ አልቻለም፡፡ ይህ ሰባራ ዕድላችን ደግሞ ኦሮሞ ነን ለምንል ወገኖች ትልቅ የልብ ስብራትን ያስከትልብናል – የምትወደውን በማትወድለት ጠባዩ ምክንያት ማጣት ሌላው የእግር እሳት ነው – እየተወደዱ ከመጠላት ይሠውር፡፡ እኔ በኦሮሞነቴ ከማፍርባቸው ነገሮች አንዱ ይህ የኦነግ አይረቤነትና ለአሰለጦች ዓላማ ማስፈጸሚያ የመሆኑ ክፉ ዕጣ ነው፡፡
እኔ ኦሮሞ ነኝ ብያለሁ – እስካሁን ካላልኩም አሁን ነኝ እያልኳችሁ ነው፡፡ ኦሮሞ ለመሆን ደግሞ የማንም ፈቃድና ይሁንታ አያስፈልገኝም – የማንነት ጥያቄ እንደንግድ ሊቼንሳ ግድግዳ ላይ ለጥፈው የተቆጣጣሪ ባለሥልጣንን ተግሣጽና ግልምጫ የሚያስወግዱበት ቁሣዊ ነገር አይደለም፤ ብዙ ምሥጢር አለው፡፡ ኦነግም ሆነ በኦሮሞ ስም የተቋቋሙ ኆልቁ መሣፍርት የሌላቸው ድርጅቶችና ንቅናቄዎች ኦሮሞነትን ለማንም ሊሰጡ ወይ ሊነሱ አይችሉም፤ ከሞከሩ ድፍረትና ብልግናም ነው፡፡ በምርጫቸው ኢትዮጵያዊ መሆንን የወደዱ ነጮች መኖራቸውን ስንረዳ የነኦነግ ኢትዮጵያን የመጥላት አባዜ አልገባችሁ ሊለን ይችላል፡፡ ሌላው ሁሉ ይቅር – ኦሮሞው መንግሥቱ ኃ/ማርያም ምን ይላቸዋል? የኦሮሞው የአጼ ኃይለ ሥላሤ አፅም ምን ይላቸዋል? የሌሎች ኢትዮጵያን አንቀጥቅጠው የገዙ የኦሮሞ ነገሥታት ዐፅሞች ምን ይሏቸዋል? እንደኦሮሞነቴ ቢቻለኝ አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ የሚናገረውን ቋንቋና የሚኖርበትን ባህል ባውቅ መልካምና ተጨማሪ ዕሤት በሆነልኝ፡፡ ያም ቢሆን የግድ ያህል አይደለም፡፡ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች የተነሣ ቋንቋውንና ባህሉን ላላውቅ እችላለሁ፤ ኦሮሞነትን ግን በማንም በጎ ፈቃድ እንደማላገኘው ወይም እንደማላጣው አስረግጬ ልነግራችሁ እችላለሁ – ኦሮሞ ለመሆን ኢትዮጵያዊነቴ ብቻ ይበቃኛል፤ የኔ ደም የኦሮሞን ደም እንደማይመስልና ኦሮሞነቴን ሊያስከለክለኝ የሚችል ብቸኛው መንገድ ናሙና ደሜ ተመርምሮ ‹አንተ አጭበርባሪ! የኦሮሞ ደም የሚባል በደምህ ውስጥ የለም!› የሚል የምሥክር ወረቀት ከታወቀ የዘረመል ጥናት የሕክምና ማዕከል ሲሰጠኝ ብቻ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ኦሮሞ፣ የኢትዮጵያ ትግሬ፣ የኢትዮጵያ አማራ… የሚባለው ምናልባትም ከጭንቀት የሚመነጭ የማደናገሪያም ይሁን የማባበያ ፈሊጥም ትክክል አይደለም፡፡ ራሱን በሺህ ቦታ ይበጣጥሰው ብዬ እንዳልረግመው ከኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ከሃይማኖታዊ ቀኖና አንጻር ይከብደኛልና ‹ኦሮሞነቴን ያልተቀበለች ኢትዮጵያ በሺህ ቦታ ትበጣጠስ› በማለት ይህችን የሚሊዮናትን ሀገር የነገር ማጣፈጫ ለማድረግ የሞከረው ሰውዬም ልብ ሰጥቶት ወደኅሊናው እንዲመለስና በአንድ የጋራ ማንነት ውስጥ አብረን ኢትዮጵያዊነትን እንድንዘምር እጸልያለሁ፡፡
በተረፈ ኦሮሞ ለመሆን ኢትዮጵያዊነት ብቻውን በቂ ብያለሁ – አሁን አልደግመውም፡፡ በመሠረቱ ኦሮሞ መሆን ጮቤ የሚያስረግጥ አይደለም፤ አማራ መሆንም በሀዘን ማቅ እሚያስለብስ ወይም በደስታ ቱልቱላ እሚያስነፋ አይደለም፤ ትግሬ መሆን በከበሮና ክራር ጮቤ እሚያስረግጥ አይደለም፡፡ ምንም መሆን ምንም ማለት አይደለም – ትግሬ ወይም ጉራጌ ሆነህ ለመፈጠር አንተ ወይም አንቺ ምን ቤት ናችሁና? አንዳንዴ እኮ ማፈርም ጥሩ ነው፤ አመኑበትም አላመኑበትም የሃይማኖት መጻሕፍትንም መዳበስ አይከፋም – ሁሉም የአዳምና የሔዋን ዘር አይደለም እንዴ? ታዲያ ቄሱንና ኢማሙን ምን ነካቸው? በጎቻቸው በዘረኝነት ተጠልፈው ከፈጣሪ ትዕዛዝ ሲወጡ እነሱ የት አሉ? ወይንስ ካለበት የተጋባበት እንዲሉ በነሱም ብሶ ተገኘና ተያይዘው ጠፉ? ባልሠራነው ሥራና በማይመለከተን ጉዳይ ዘው ብለን ገብተን ለምንድነው ከሣሽና ፈራጅ ዳኛ መሆን የሚቃጣን? መጀመሪያ እኛነታችን ሰብኣዊነታችን እንጂ የሰው ዘር በሙሉ አንድ መሆኑን መረዳት ተገቢና ከጤናማ ማኅበረሰብም የሚጠበቅ ነው፤ ሰው አበደ ተብሎ ደግሞ ጨርቅ እንደማይጣል ሁሉ የተወሰኑ ሰሜነኛ ወንድምና እህቶቻችን በዘር ልክፍት አበዱ ብለን አብረን ተባብረን ማበድ አይጠበቅብንም፡፡ ማግኘትና ማጣት ባመጡብን ጣጣዎች ተከፋፍለን ሰብኣዊነትን መረጋገጥ አይገባም፡፡ ብዙ ነገሮች የወረት ናቸው፤ ወረት ደግሞ ያልፋልና በማያልፍ የታሪክ መዝገብ ላይ በጉልህ ፊደላት የሚሠፍር የታሪክ ጠባሳ መተው አይኖርብንም፡፡ አንድ ሁላችንም በጥልቀት ልናስብበት ነገር ልናገርና ላብቃ፡፡
እኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ስፈጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 25 ሚሊዮን ገደማ ነበር፡፡ አሁን ያ ቁጥር ተገቢው መንግሥት ስለሌለን ክፉኛ አሻቅቦ ወደ 87 ሚሊዮን አካባቢ ደርሰናል አሉ – ይህን አስደንጋጭ የሕዝብ ቁጥር ስናሰላው የያኔውን ሦስት ነጥብ አምስት ገደማ አጥፏል ማለት ነው ፡፡ ከእኔ ዕድሜ ወደኋላ ጥቂትና ብዙ ዓመታትን ለምሳሌ 50፣ 100፣ 200፣ 500… ሄደን ማየትም እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በነዚያን ዓመታት ስንት ሊሆን እንደሚችልም በምናባችን መቃኘት እንችላለን፡፡ ምናልባት 100 ሚሊዮን፣ 5 ሚሊዮን፣ 2 ሚሊዮን፣ ግማሽ ሚሊዮን… ይህ ሒሳባዊ ፖስቱሌትም እንበለው ቴኦረም እያለ እያለ ወደ ጥቂቶች ቀደምት ዝርያዎቻችን ይወስደናል፡፡ ታዲያን በጣት ከሚቆጠሩ አባት እናቶች ተነስተን 87 ሚሊዮን የገባነው ዘር እየተቋጠርን በመዋለድ ይሆን እንዴ? ብለን ደግሞ እናስበው፡፡ እርግጥ ነው – በአንድ አካባቢ ሰው ሲበዛ በተፈጥሮ ሀብት መሳሳትና ማለቅ እንዲሁም በቦታ ጥበት የተነሣ ወደሌላ አካባቢ ተዛውሮ መሥፈር የነበረና ያለ ነው፡፡ በዚያም የረጂም ዘመን ሂደት ውስጥ የቋንቋና የባህል መለያየት መከሰቱ የማይቀር ነው፡፡ ለዚህም ነው የሰዎች ባህልና ቋንቋ በብዙ መንገድ የሚመሳሰለው፡፡ … እግዚአብሔር አንድ አድርጎ የፈጠረውን ሰው ዘመንና መልክዓ ምድራዊ ልዩነቶች ሊለዩት ደግሞ አይቻላቸውም፡፡ መቅላት መጥቆርም፣ ማጠር መርዘምም… በአንድ ቤተሰብ ሳይቀር የሚታዩ ልዩነቶች በመሆናቸው ያን ያህል ጉባኤ የሚያስቀምጡ የልዩነት መንስኤዎች አይደሉም፡፡
በኔ በዚህች የግማሽ ምዕተ ዓመት በምትሆን ዕድሜየ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ25 ሚሊዮን ወደ 87 ሚሊዮን የደረሰው ኦሮሞ ከኦሮሞ፣ ትግሬ ከትግሬ፣ ኮንሶ ከኮንሶ፣ ከፊቾ ከከፊቾ፣ ጠምባሮ ከጠምባሮ፣ ዳዋሮ ከዳዋሮ፣ ጉራጌ ከጉራጌ ደራሳ ከደራሳ፣ ወላይታ ከወላይታ፣ ሃዲያ ከሃዲያ፣ ከምባታ ከከምባታ፣ አደሬ ከአደሬ፣ ቆቱ ከቆቱ፣ አማራ ከአማራ፣ አገው ከአገው፣ ወይጦ ከወይጦ… እንዲጋባ ሕግና ሥርዓት ተበጅቶ በዚያ ቀጭንና ኢተፈጥሯዊ ሕግ ተጉዘን ሣይሆን ሁሉም እንዳመቸው ካፈቀራትና ካፈቀረችው ጋር እየተጋቡና አንሶላና ጋቢ እየተጋፈፉ ነው – ያኔ እኮ ‹የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ፤ የሐረር ልጅ ነኝ፤ የደሴ ልጅ ነኝ፤ የአዋሣ ልጅ ነኝ፣ የቦንጋ ልጅ ነኝ…› እንጂ ‹የኦሮሞ ልጅ፣ የትግሬ ልጅ፣ የአማራ ልጅ…› የሚባል እንዲህ እንደዛሬው ዐይን ያወጣ የዘረኝነት ልክፍት አልነበረብንም፤ ይህ ዓይነቱ ነገር የመጣብን በተለይ ካለፉት 22 ዓመታት ወዲህ ወያኔ መርዙን ከረጨብን በኋላ ነው፤(አሁንስ ቢሆን እስኪ በየትምህርት ቤቱ ሂዱና እዩ … ተማሪዎች በዘፈቀደ ተበሰጣጥረው እንጂ በይሁንታ በዘር ኩይሣ ነው እንዴ የሚማሩትና በፍቅር ዓለምም የሚመላለሱት?)፡፡ አንዳንድ በስተቀሮችን ወደ ጎን እንተዋቸውና – በአብዛኛው – ጥንት ያኔ ኦሮሞው አማራዋን ያገባል፤ ትግሬው ይፋቴዋን ያገባል፤ አማራዋ ከጀምጀሙ ትወልዳለች፣ ሽናሻይቱ አገውን ታገባለች፤ ቢለኑ ሳሆዋን ያገባል፣ ትግረዋ ትግሬውን ታገባለች፣ ኢሮቡ አፋሯን ያገባል… ምኑ ቅጡ… በዚህ የአሥረሽ ምቺው የፍቅርና የጋብቻ ትስስር ‹ብዝሁ ተባዝሁ ወምሉዕዋ ለምድር› በሚለው ሕገ እግዚአብሔር ተመርተን ኢትዮጵያን ሞላናት – ምን አጠፋንና ነው ታዲያ ወያኔና ኦነግ ከአባታቸው ከሻዕቢያ ጋር በሃሳብ አንድነት ሥሙር ሆነው ሽል ምንጠራ ውስጥ የገቡትና በማን አባት ገደል ገባ ሊያመነቃቅሩን የሚሹት? እኔ አሁን ታዲያ ምንድነኝ ልበል? የትኛው ነው የኔ ‹ጥርት› ያለው ዘር? ‹እኔ የጎንደሬይቱ ልጅ! እኔ የጎጃሜይቱ ልጅ…› የሚለውን መንደርኛ ፈሊጥ ተውት፡፡ ይህ ዓይነቱ ከጠላ ቤት ድንፋታ ሊያልፍ የማይገባውን ተራ ጨዋታና ከዚህ ባስ የሚለውንም ተራ የቀልድ ልውውጥም ከምር አትውሰዱት፡፡ በእናቴ በኩል የምዛመዳቸውን ወንድሞቼንና እህቶቼን አስታውሰህ በቀልድ መልክ ‹ከወሎ ጎረቤት ይሻላል ባዶ ቤት› ብትለኝ እስቅ ይሆናል እንጅ ምንም አልልህም – በዚህ ዓይነቱ ተራ ቧልትም መነካከስ አይገባም፡፡ በአባቴ በኩል የምዛመዳቸውን እህቶቼን አስበህ ‹አንት ግድርድር ጎንደሬ› ብትለኝ ይብስ እየተኮፈስኩ በቀልድ አናድድህ ይሆናል እንጂ በዚህም ምንም አይሰማኝም፡፡ ኧረ ለመሆኑ ወሎስ የማን ሆነና? ስሙ ራሱ የኦሮሞ ስም አይደል እንዴ? ኦሮሞ ያልገባበትና ያልተዋለደው ኢትዮጵያዊ ግዛት ይኖር ይሆን? በኦሮሞነት ብዙም በማይታሙት ኤርትራና ትግራይ እንኳን ዕድሜ ለዚያ የደርግ ዘመን የርስ በርስ ጦርነት ሁላችንም በሁላችንም ውስጥ እንድንቀልጥ ተደርገን የለምን? ከሌላ ጋር የማይዋለድ መንወሳቀስ የማይችል ዛፍና ግንድ ብቻ ነው፡፡ ሰው በተፈጥሮው ተንቀሳቃሽ በመሆኑ ሌላ መሰል ፍጡር እስካገኘ ድረስ ይተኛል፤ ይዋለዳልም፡፡ ስለዚህ የጠራ ዘር ማግነት በነኦነጎችና መሰሎቹ አእምሮ ውስጥ ህልምና ቅዠት ሆኖ የሚቀር እንጂ እውን ሊሆን አይችልም – የነዚህ የበጥባጮቹ የዘር ሐረግ ሲታይ በአብዛኛው የዚህ የመጢቃነት ‹ሰለባ› ናቸው- ለምሳሌ የሕወሓቱን አዲስ ዓለም ባሌማን ብናይ የኦሮሞና የትግሬ መጢቃ ነው – በዚህ ረገድ መረጃው ያላችሁ እባካችሁን የበጥባጮቹን የዘር ሀረግ (pedigree) አሳዩን – እንድንማርበት፡፡ እኔን ታዲያ ማን ነው ከማን ነጻ የሚያወጣኝ? ራስን አለማወቅ ይሏል ይሄኔ ነው፡፡ ኦነግ ራሱን ሳያውቅ በስሜ እየማለና እየተገዘተ ድፍን ግማሽ ምዕተ ዓመት ቀለደብኝ፡፡ እሱ ሩጫውን እንደጨረሰ እኔም አሁን በሃሳብ መዳከሩ ቢበቃኝስ ወገኖቼ፡፡
ማሳሰቢያ፡- እንግሊዝኛ ሁለተኛ ቋንቋየ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡ እናም በትምህርት ብዙም ያልገፋሁና በ‹መሠረተ ትምህርት› ብቻ ተወስኜ የቀረሁ ከመሆኔም በተጨማሪ አማተር ተርጓሚ እንጂ ፕሮፌሽናል አለመሆኔን ተረድታችሁ በሚኖርብኝ የትርጉም ስህተት ከመሣለቅ ይልቅ እናንተው በጎደለ እየሞላችሁ በተጣመመ እያቃናችሁ እውነታውን ብቻ እንድትገነዘቡልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በተጨማሪም ይህን ወረቀት ለማንበብም ሆነ ለማስነበብ የምትጓደዱ ወገኖቼ ኃያሉ አምላክ ጭንቀቴን ያስርፅባችሁና እውነቱን ተረድታችሁ … በቃ እናንተ እውነቱን ከተረዳችሁልኝ ያ ብቻ ለጊዜው በቂየ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment