Monday, 17 June 2013

ከውስጥ በአምባገነን ስርዓት የታፈነችና ከውጭ ዙሪያዋን በጠላት የተከበበች አገር



“ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር፡፡
የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤
ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል፡፡
የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል…” ይላል መጽሓፍ ቅዱስ በኦሪት ዘፍጥረት 2፡10-13፡፡
ግዮን የተባለው አባይ ነው፤ የአባይ ምንጭ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ብዙ ሰዎች የአባይ መነሻ ጣና ሐይቅ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን የአባይ ትክክለኛ መነሻ በምዕራብ ጎጃም ሰከላ ወረዳ ውስጥ የመትገኘው ፈለገ ግዮን ናት፡፡ አባይ ፈልቆ ከምንጭነት ወደ ጎርፍነት በመቀየር ከዚያም ነብስ ዘርቶ ወደ ጅረትነት ከፍ የሚልበትን የተቀነበበ አነስተኛ ጉድጓድ ለአንድ የኃይማኖት አባት ለማሳየት “አባ እይ” ከሚል የሌላ ሰው ንግግር አባይ የሚለውን ስያሜም እንዳገኘ በአፈ ታሪክ በሰፊው ይነገራል፡፡ የአባይን ምንጭ አስሶ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው ጀምስ ብሩስ የተባለ አውሮፓዊ እንደሆነ ይታመናል፡፡
አባይ ዘይት ሆኖ በጣና ላይ ጋልቦበት ኢትዮጵያን ልክ እንደ መቀነት ወገቧን ዞሮ ድንበሯን በመበጠስ ከድቷት ከምድሯ በመውጣት ዜግነቱንም ስሙንም ይቀይራል፡፡ ብሉ ናይል ተብሎ ከቪክቶሪያ ሐይቅ ከሚነሳው ነጭ አባይ ጋር ካርቱም ላይ በመደባለቅ አስር አገራትን አቆራርጦ በርዝመቱ በዓለም አንደኛ በመሆን ሜዲትራኒያን ባህር ይገባል፡፡
ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነውን የውሃ መጠን ከኢትዮጵያ የሚያገኘው ናይል ከሚያልፍባቸው አገሮች ግብፅና ሱዳን ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ ሁለት አገሮች ኢትዮጵያ ወደ እነሱ ምድር የሚፈስ ወንዝ መነሻ ሆና በመፈጠሯ ምክንያት ብቻ በጠላትነት ፈርጀዋት ለረጅም ዘመናት ኖረዋል፡፡ በተለይም ግብፅ ይህችን ስልጣኔን ከዓለም ሁሉ ቀድማ ጀምራ ኃያል የነበረችና ዛሬ ጭራ የሆነች የድሆችና የመከረኞች ምድር ኢትዮጵያ የወደፊት የመኖርና ያለመኖር ህልውናዋ ጠንቅና ስጋቷ ምንጭ እንደሆነች አድርጋ ስትመለከታት አያሌ ዘመናት ነጉደዋል፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያን ያለኃጥያቷ በጠላትነት ዓይን ትከታተላት ብቻ አልነበረም፡፡ ከኢትዮጵያ በምታገኘው ውሃ ከተሞላው ናስር ሐይቋ ወደ ሰማየ ሰማያት በምትለቀው የመሰርይነትና የበቀል ትነት በኢትዮጵያ አድማስ ላይ ያጠላውን ጥቁር ደመና በመበከል በኢትዮጵያ ምድር ላይ አሲድ እያዘነበች ህዝቦቿን ስታነፍራቸው፣ ቡቃያዎቿን አቀጭጫ ስታጠፋቸው፣ ወንዞቿንና ሐይቆቿን ወደ መርዝ ፈሳሽነት ስትቀይራቸው ከተፈጠረች ጀምሮ እስካሁን ድረስ አለች፡፡ አባይን ከነምንጩ በቁጥጥር ስር በማዋል በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛዋ ኃያል አገር ለመሆን ካላት ቅዠት የተነሳ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ወርራለች፡፡ ነገር ግን ክብር ለቀደሙት ጀግኖች አባቶቻችን ይሁንና ህልሟ እንደ ጉም በንኖ ቀርቷል፡፡
አፄ ዮሃንስ ግብፅ የምትፈፅመው ማባሪያ የሌለው ግፍና በደል ሲያንገፈግፋቸው ለእንግሊዝ ንግስት ለንግስት ቪክቶሪያ በፃፉት ምሬትን ያዘለ ደብዳቤ ውስጥ “…በአገሬ ምድር ሰላምን አምጥቼ ከህዝቤ ጋር ወደ ልማት ልዞር ባሰብኩበት ወቅት መሃመድ ባሻ ሳልደርስበት ጠብ እየጫረ አላስቀምጠኝ ብሏል፤ እኔ ጦርነት መግጠም አልፈለግም እባክዎን ንግስት ሆይ ተው ይበሉልኝ…” የሚል ሀሳብ ይገኝበታል፡፡
ከመሃመድ ፓሻ እስከ ከዲቭ ኢስማኤል ፓሻ፣ ከጀማል አብደልናስር እስከ አንዋር ሳዳት፣ ከሙባረክ እስከ አሁኑ ሙርሲ የሚገኙት የግብፅ መሪዎች በጠቅላላ ኢትዮጵያን አንድም ቀን ተኝተውላት አያውቁም፡፡ ጉልበቷን ቄጠማ አድርገው በማሽመድመድ እንዲህ አቅም እንዳጠራት ቀጭጫ እንድትቀር አድርገዋታል፡፡ ከገዛ ምድሯ የሚመነጨውን የአባይ ውሃ “በእፍኝሽ እንኳን ጨልፈሽ ብትጎነጭ እናጠፋሻለን” እያሉ ሲያስፈራሯት ኖረዋል፡፡
ግብፅ ዋነኛዋ የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም እባጭ ህመም ነቀርሳ ናት፡፡ ለዚህ ማስረጃ ወደ ኋላ ተጉዞ ዘመናትን መሻገር አያስፈልግም፤ ወያኔና ሻዕብያ በእሷ የጦር መሳሪያ እየታጠቁ የገዛ አገራቸውን ሲወጉ እንደነበር ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ በዚህ ኢትዮጵያ ከእርስበርስ ጦርነት ተላቅቃ የሰላም አየር እንዳትተነፍስና ፊቷን ወደ ልማት እንዳታዞር በማድረጉ ሴራ ሱዳንም አለችበት፡፡ በደርግ ጊዜ ህወሓት ካርቱም ውስጥ ጽህፈት ቤት ነበረው፡፡ ዋና መግቢያና መውጫ በሩም ሱዳን ነበረች፡፡ ጀብሃን ያደራጀችው ግብፅ ናት፡፡
ግብፅም ሆነች ሱዳን በየጊዜው የኢትዮጵያን ጨቋኝ የአገዛዝ ስርዓት የሚቃወሙትን ቡድኖች የሚያስታጥቁት የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ ለማውጣት አይደለም አገሪቱን በጦርነት ለማዳከምና የኢኮኖሚ አቅም ለማሳጣት እንጂ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከጦርነት ወጥታ እፎይ የምትልበት እድል ካገኘች በማንኛውም ጊዜ አባይን ገድባ ለልማት እንደምታውለው ጠንቅቀው ያውቃሉና፡፡
በእንድ አገር ላይ የተንሰራፋን አፋኝ ስርዓት ለማስወገድ ከሌላ አገር መንግስት እርዳታ መለመን በየትኛውም አለም ካሁን በፊት የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው፤ ለዚያች የአፈና አገዛዝ ለነገሰባት አገር ጠላቶች በመሳሪያነት ማገልገል ግን አገርንና ወገንን መካድ ነው፡፡ ግብፅ ደደቢት በረሃ ክሳድ ግመል ለሸፈተው አስገንጣይ ወንበዴ ህወሓት የደርግን ስርዓት እንዲፋለም ላዩ በማር የተቀባ የሬት ስንቅ ስታቀብለው ኖረች፡፡ ወያኔ ማሩን እየላሰ ኃይልና ሙቀት አግኝቶ ለ17 ዓመታት በመዋጋት አሸንፎ ኢትዮጵያን መልሶ በጠመንጃ አፍኖ ለ22 ዓመታት ለመግዛት በቃ፡፡ ይኸውና አሁን ደደቢት በረሃ ውስጥ እያለ ጀምሮ ይልሰው የነበረው ማሩ አልቆበት ሬቱ ብቻ ቀርቶት እሱን እየላሰ ይጎመዝዘው ይዟል፡፡
ወያኔ የደቂቃ የደስታ እሸትን ከሴት ብልት ማሳ ላይ ለመቅጠፍ ብሎ ከኤች.አይ.ቪ ህመምተኛ ጋር ልቅ የሆነ ግብረ ስጋ በመፈፀም የዓመታት ህይወቱን እንደሚቀጥፍ ስሜቱን ፈፅሞ መግራት የማይቻለው ቅንዝራም ጎረምሳ አይነት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ተግባር ሲፈፅም ነገ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል አያጤንም፡፡ ሳህል በረሃ ውስጥ የመሸገው የሻዕብያ ገንጣይ ወንበዴ ቡድን በአብዮታዊ ህዝባዊ ሰራዊት አከርካሪው ተሰብሮ እስከመጨረሻው ለመክሰም ሲቃረብ በአፉና ባፍንጫው ኦክስጂን ሰጥቶ የመጀመሪያ እርዳታ በማድረግ እስትንፋስ የሆነው ወያኔ ነው፡፡ ከዚያም አውራው መለስ ዜናዊ አገሬን ገንጥሉልኝ ብሎ ለተባበሩት መንግስታት በፃፈው ደብዳቤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተቆርሳ ራሷን የቻለች በሻዕብያ የምትገዛ አገር ሆነች፡፡ በኋላ ሻዕብያ ለራሱ ለወያኔ የቂጥ እከክ ሆነበት፡፡ በእርግጥ ምንጊዜም ቢሆን የችግሩ ገፈት ቀማሽ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ በጦርነቱ በድህነት ቤቱ ያሳደጋቸውን መቶ ሺህ ልጆቹን በከንቱ የገበረው እሱ እንጂ ወያኔ ኢህአዴግ ምንም የጎደለበት ነገር የለም፡፡ በጦርነቱ ጊዜ ሰራዊቱ ኤርትራን እስከ ቀይ ባህር የመቆጣጠር ፍላጎት ነበረው፡፡ በመረብ በኩል ለፍልሚያ የተሰለፈው ሰራዊት ተሰኔ ገብቶ ከአስመራ የሚያገናኘውን አውራ ጎዳና ይዞ በታላቅ ወኔና ጉጉት ወደ ፊት መገሰገስ ሲጀምር ቁምና ቀኝ ኋላ ዙር ተባለ፡፡ በቡሬ ግንባር በኩል የተሰማራው ጦርም አንዲሁ የአሰብን መብራት አሻግሮ እያየ ያለፍላጎቱ ተመለሰ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው እንግዲህ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ በሚቆረቆረውና “ባለራዕይ” በሚባለው መለስ ዜናዊ ብቻ ቀጭን ትዕዛዝ ነው፡፡ ይኸውና ዛሬ ኤርትራ ግብፅ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የምትጠቀምባት ስትራቴጂክ ቦታ እንደሆነች በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ የመለስ ወንድም ኢሳያስ ደግሞ ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ የሚል አይመስልም፡፡ ሻዕብያ አሰብና ምጽዋን ሲይዝ አንድ የኢትዮጵያ ጦር ጄነራል “ከእንግዲህ ወዲህ አገሬ ኢትዮጵያ የሬሳ ሳጥን ሆነች” ብሎ ነበር፡፡ ጀነራሉ ልክ ነበር እናት ኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ ከሬሳ ሳጥን ውስጥ ገብታ የተጋደመች አሳዛኝ አገር ናት፡፡ የሬሳ ሳጥን በርና መስኮት የለውም፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ ወያኔ ነው፡፡
እናም ይሄ ለጠላት አገር በመሳሪያነት የማገልገሉ ጉዳይ መቼ ነው የሚቆመው? የግብፅ መሪዎች እኮ ኢትዮጵያን በማተራመስ የግድቡን ስራ እናስተጓጉለዋለን እያሉ ባደባባይ የሚናገሩት የኢትዮጵያን ጠመንጃ ያነሱ ተቃዋሚ ቡድኖች ላዩ ማር የተቀባ ሬት የመቀበልን የቆየ ባህል ከህወሓት ስለሚያውቁት ነው፡፡ ከንጉሱ ስርዓት ጋር የተኳረፉ መኳንቶችና ግለሰቦች ከጣልያን ጋር አብረው ወገናቸው የሆነውን የኢትዮጵያን አርበኛ አንደወጉት፤ ከደርግ ጋር የተጣሉት ኢህአፓዎችና ሻዕብያዎች ከሶማሊያ ጎን ተሰልፈው የእናታቸውን ልጅ እንደገደሉት፤ ዛሬም ቢሆን የግብፅን ላዩ ማር የተቀባ ሬት ተመፅውተው እየላሱ በመሳሪያነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ከወያኔ ኢህአዴግ ጋር ተኳርፈው ጫካ የገቡ ቡድኖች ሊኖሩ አይችሉም ብሎ ለመደምደም ያዳግታል፡፡
ግብፅ ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን በማለት ጠመንጃ ታጥቀው ጫካ ለገቡ “ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጪዎች” ላዩ ማር የተቀባ ሬት ስንቅ ከማቀበሏ በተጓዳኝ የየብስ የባህርና የአየር ተዋጊ ሠራዊቷን በሚገባ ስትገነባ፣ ጡንቻውን ስታፈረጥም፣ በትጥቅ ስታዘምንና ስታገዝፍ ነው የኖረችው፡፡ የኢትዮጵያ ገዥዎች ግን በተቃራኒው ትራሳቸውን ከፍ አድርገው ተኝተው ነበር፡፡ በተለይ ወያኔ ኢህአዴግ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ስንትና ስንት አንጡራ ሀብት ፈሶበት የተገነባውን የኢትዮጵያ ሠራዊት የደርግ ኢሠፓ በማለት በትኖ የአገሪቱን ወታደራዊ መሰረት በማፈራረስ ያለአለኝታ እርቃኗን አስቀራት፡፡ የአገሪቱን በጠላት ቀለበት ውስጥ የመገኘት ጉዳይ ወደ ጎን በመተው የራሱን ስልጣን ብቻ ለማራዘም ሲል ራሱ ያደራጀውን ሰራዊትም የትግርኛ ቋንቋ የማይናገሩትን በመመንጠር ባብዛኛው የአንድ ብሄር ጦር ብቻ አድርጎታል፡፡
ወያኔ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦ በጠመንጃ የሚገዛበትን ወታደር /አንደ አግአዚ ኮማንዶና ፌደራል ፖሊስ ዓይነት/ በደንብ ሲገነባና በትጥቅ ሲያደራጅ የአገሪቱን የውጭ ጠላቶች ችላ ብሏቸው ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በጠላት የታጠረች አገር መሆኗን ግጥም አድርጎ እያወቀ 22 ዓመታትን በስልጣን ሲያሳልፍ በወታደራዊ ሳይንስ መስኩ አንድ እርምጃ እንኳን አልተራመደም፡፡ አንዴውም የአገሪቱ መከላከያ ተቋም በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ወያኔ ኢህአዴግ የተራቀቀ ወታደራዊ የእድገት ደረጃ እንደደረሰ ሁሉ የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ገና እንጭጭና የግብፅን የመጠቀ የጦር ቴክኖሎጂ የታጠቀ የየብስ፣ የባህርና የአየር ተዋጊ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ መመከት የማይችል ሆኖ እያለ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ማግበስበሻ ፕሮፓጋንዳ በሰፊው እያናፈሰ ይገኛል፡፡ “አባይን ልገድብ ነው” ጩኸት፤ “የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ጣልኩ” ሌላ ጩኸት፤ “ አጨብጫቢዎቹ ሰልፍ ወጥተው በጩኸት ላይ ጩኸት፤ “ቦንድ ግዙ” ተጨማሪ ጩኸት፤ የህዳሴው ግድብ ልደት ክብረ በዓል ጩኸት፤ “አባይን ተፈጥሯዊ የመፍሰሻ አቅጣጫውን አስቀየርነው” ጩኸት… የማያባራ ጩኸት፡፡ በቃ አገሪቱን የጫጫታ ምድር አደረጋት፡፡ ግብፅ እኮ አስዋንና ናስርን ስትገድብ በዝምታ ነው የልቧን የፈፀመችው፡፡ የወያኔ ኢህአዴግን ጫጫታ ምንአመጣው? የሚጮህ ውሻ እኮ አይናከስም፡፡ ደግሞም ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከምቢያው ምንአለ ነው የሚባለው፡፡ ባለፈው ጊዜ የተከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀንም ከባዶ የጉራ ፕሮፓጋንዳ ተለይቶ አይታይም፡፡ ሲሉ ሰምታ ዶሮ ሞተች ከጭስ ገብታ፡፡ ወያኔ ኢህአዴግ እንደለመደው ቆስቁሶ ሊያነደው የፈለገው የጦርት እሳት ያለ ይመስላል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ኢትዮጵያ ከየት ወደየት” በሚል ርዕስ በ1986 ዓ.ም በጻፉት መጽሓፍ ውስጥ “የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው…” የሚል ጠንከር ያለሀሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ እውነትም የጦርነትን ገፈት ያልጨለጡ የኢትዮጵያ ትውልዶች ከቶ ሊገኙ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲህ በምንም መልኩ ከጦርነት እሳት ውስጥ ገብታ መንደድ የለባትም፡፡ የሰላም አንጂ የጦርነት አሸናፊ የለውም፡፡
ዓለም ከአንደኛው እጅግ ዘግናኝ የሆነና ምንም መፍትሄ ያላመጣ የዓለም ጦርነት ምንም ሳትማር ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሰተት ብላ ገባች፡፡ በጀርመኑ የናዚ ሰራዊትና በሶቭዬቱ ቀይ ጦር መካከል በተደረገ ከባድ ፍልሚያ ስታሊን ግራድ ነደደች፤ ለንደንና በርሊን በቦምብ ተቀጠቀጡ፤ ፓሪስ በሞርታር ታረሰች፤ ፒርል ሀርቦር በሚግ ተወገረች፤ ሂሮሽማና እና ናጋሳኪ በ“little boy” እና “fat man” አተሚክ ቦምቦች ተመትተው እንደ ሰም በመቅለጥ ከምድረ ገፅ ጠፉ… በቃ ምድር በጠቅላላ ተናጠች፤ በሰው ልጆች በድን ተሞላች፤ ሚሊዮኖች አለቁ፤ የመጨረሻ ድምር ውጤቱ ግን ዜሮ ነበር፡፡ በዓለም ታሪክ ከጦርነት ያተረፈ ማንም አገርና ህዝብ የለም፡፡ ሰላም ለማምጣት በጎተራ የሞላ ትዕግስት ሰንቆ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ከጦርነት ይልቅ ለኢትዮጵያም ሆነ ለግብፅ ህዝብ የሚበጀው ይህና ይህ ብቻ ስለሆነ፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እኮ ያሁሉ ወጣት ከረገፈ በኋላ መሪዎች በቀጥታ ለሰላም ድርድር ወደ አልጀርስ ነው የሄዱት፡፡ ምናለበት ያ የሰላም ድርድር ከጦርነቱ በፊት በሆነ ኖሮ መቶ ሺህ የድሃ ልጆቸ ባልሞቱ ነበር፡፡
የግብፅ መሪዎች ማንገራገር ዛሬ የተጀመረ አዲስ አይደለም፤ የተለመደና ለሺህዎች ዓመታት የዘለቀ ነው፡፡ ማንገራገርን እንደ “psychological warfare” እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ልክ እንደወትሮው መዘናጋት የለባትም፡፡ ወያኔ ኢህአዴግም ምንም አንኳን ቢረፍድበትም ከእንቅልፉ መንቃት አለበት፡፡
Egypt is a gift of Nile” የሚለውን የሄሮደተስ አባባል “Nile is only a gift of Egypt” በማለት ገልብጠው የተረዱት የሚመስሉት የልበ ደንዳናው ፈርኦን ሽንቶች ከማንገራገር አልፈው እንደለመዱት ከመጡብን ግን ምን እናደርጋለን አንደ ቀደሙት ጀግኖች አባቶቻችን ደማችንን ገብረን የዚህችን ያልታደለች ድሃ ምድር ዳር ድንበር ከማስከበር ውጪ ሌላ ምን አማራጭ አለን፡፡ አንድ የግብፅ ገበሬ ከአረንጓዴ ማሳው መሃል በኩራት ቆሞ “የውሃችንን ምንጭ ለማቆም የሚሞክር ማንም አካል ቢኖር ያለምንም ድርድር በቀጥታ እንፋለመዋለን” በማለት እየተናገረ “Struggle over the Nile” በሚል ርዕስ በተሰራ ዶክሜንታሪ በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ታይቷል፡፡
ምናልባት ኤርትራ የግብፅ ተባባሪ ከሆነች ከሻዕብያ ጋርም በድጋሚ ጦርነት መግጠማችን የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ወያኔ ኢህአዴግ የተገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ አስመራ ድረስ በመግባት ሻዕቢያን እስከመጨረሻው ደምስሶ ድንበራችንን መልሶ ቀይ ባህር በማድረግና ወደባችንን በማስመለስ አገሪቱን ከሬሳ ሳጥን ውስጥ አውጥቶ የተበላሸውን ታሪኩን ያድሳል እንጂ ለሁለተኛ ጊዜ አይሸወድም የሚል የበርካቶች እምነት አለ፡፡
ደግነቱ ዘውዱ

No comments:

Post a Comment