Tuesday, 25 June 2013

ባለ ሀገር እስከምንሆን ትግሉ ይቀጥላል

ሳምንቱ በስራ ውጥረት ሽው ብሎ እንዳለፈ ያወቅሁት እሁድ ማለዳ ከቤተሰቤ ጋር ሳሳልፍ ነው፡፡ ሳምንቱንም ሙሉ ትኩረት ሳልሰጣቸው በምትኩ ሃገራዊ ሃላፊነቴን አቅሜ በፈቀደው መጠን ለመወጣት በርከት ያለውን ጊዜ እንደሰጠሁ የገባኝም እሁድ እለት ነው፡፡
እንደዚህ ‹‹ቢዚ›› ያደረገኝ አንድነት ፓርቲ ሕዝባዊ ንቅናቄውን ይፋ ከማድረጉ በፊት ማለቅ የሚገባቸው በርከት ያሉ ተግባራት ስለነበሩን ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ከትግል አጋሮቼ ጋር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሞት እንዲውጣቸው ስናጣፍጥ ሰነበትን፡፡ ሰንብተንም በእለተ ሐሙስ የሃገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች በተገኙበት ይፋ አደረግን፡፡ ባለ ሃገርነታችንን የነጠቀንን የፀረ-ሽብር ህጉንም ለማሰረዝ በይፋ ‹‹የሚልዮኖች ድምፅ ለነፃነትን›› አበሰርን፡፡ በግልፅም ሚሊዮኖች የሚሳተፉበት ንቅናቄ በግልፅ ተጀመረ፡፡
ይሄ ሁሉ የሚሆነው ለምንድነው? አዎ! ይሄ ሁሉ እየተደረገ ያለው ባለሃገር ለመሆን ነው፤ ከምንደኛነት (ተመፅዋችነት) ለመላቀቅ ነው፣ የሁላችንን ሃገር ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነው፣ አንገታችንን ቀና አድርገን ለመሄድ ነው፣ እውነተኛ ልማት ለማ ምጣት ነው፣ አምባገነንነትን፣ ሙሰኝነትን፣ ጉልበተኝነትን ለመታገል ነው፤ በነፃነት የኖረችውን ሃገር ነፃነት ለማረጋገጥ ነው፣ መንግስትን ላለመፍራት ነው፣ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ እንዲረጋገጥ ነው፤ የእምነት ነፃነት እንዲረጋገጥም ነው፡፡ በአጠቃላይ በሰጪና ነሺ የተዋቀረውን አገዛዝን ለማስተማር ነው፡፡ ይሄ ማለት ባለ ሃገር ለመሆን ነው፡፡
ሃገሩ የኔ ነው፡፡ ሃገሩ የእኛ ነው፡፡ የሁላችን፡፡ ሁላችንም ላባችንን የምናንጠፈጥፍበት፣ አባቶቻችን ደማቸውን ያፈሱበት እኛም ደማችንን ለማፍሰስ የማንሰስትባት ኢትዮጵያ የሁላችን ናት፡፡ የህዝባዊ ንቅናቄው ዓላማም ይሄ ነው፡፡ ብዕር ነጣቂ መንግስት ያላት ሃገር ጉድፏን እንዴት ታያለች? ስለ ኢትዮጵያ ገዥ ሃይል ብእር ነጣቂነት እማኝ ለመጥራት ሩቅ አልሄድም፡፡ ከተወዳጁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋር ሃሳባችንን እንዳንገልፅ ብእር ከተነጠቅነው መካከል ነኝ፡፡ በተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ አዲስ ታይምስና በኋላም ልእልና የጋዜጠኞች ብእር ተነጥቆ በጉልበት እስከሚዘጉ ድረስ በአምደኝነት ፖለቲካዊ ፅሁፎችን ጫጭሬያለሁ፡፡ ከብእር ነጠቃው በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የፃፍኳት ፅሁፍ ይቺ ናት፡፡ የተነጠቀውን ብእር ማስመለስ የምንችለው በትግል ብቻ ነው፣ ባለ ሃገር ስንሆን ብቻ ነው፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስንፈጥር ብቻ ነው፡፡ መፍትሄው ይሄው ነው፡፡ የፖለቲካ ትግል፡፡
ስለዚህ በአንድነት ፓርቲ በኩል ይፋ የተደረገ ሕዝባዊ ንቅናቄ አንድምታው ብዙ ነው፡፡ ባለ-ሀገር ለመሆን ለምንፈልገው ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ነው፡፡ ምንደኛ ላደረጉንና ለማድረግ ለሚፈልጉት ሃይሎች ደግሞ ህመም ነው፡፡ ለህመምተኞች የሚያም ህመም፡፡ ኢትዮጵያን አጥብቀን ለምንወድድ ሁሉ ግን ብስራት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ንቅናቄ ካመማቸው የስርዓቱ ጥገኞች መካከል ሚሚ የተባሉት ግለሰብ አንዷ ናቸው፡፡ ሚሚ ስብሃቱ የተባሉት ሴትዮ የእሁድ ረፋድ ክብ ጠረጴዛ በተባለው ፕሮግራማቸው የፀረ-ሽብር ህጉን ለማሰረዝ የሚደረገውን ህዝባዊ ትግል እንደተለመደው ጥላሸት ለመቀባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ሚሚ የተባሉት ግለሰብ ፕሮግራማቸው ሚዛናዊነት የጎደለውና ዘላፊ መሆኑ በአደባባይ የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎችን ለማደናገር ይችል ይሆናል፡፡ ሚሚና አፈ-ቀላጤዎቻቸው ‹‹ለምን የፀረ-ሽብር ህጉ ይሰረዛል፤ እንዴውም መጠናከር አለበት…›› በማለትና እንደ አለቆቻቸው አንድነትን ባልዋለበት ለማዋል መቁረጣቸው የፀረ-ሽብር ሕጉን እየጠቀሱ አፈናውና ነፃነት ገፈፋው እንዲቀጥል ያላቸውን ጥልቅ ምኞት ሲገልጡ ነበር፡፡ እኛ እያልን ያለነው ሁላችንም በነፃነት እንኑር ነው፡፡ ሁላችንም ባለ ሀገር እንሁን ነው፡፡
የሚሚና ቀላጤዎቿ ስህተት የፀረ-ሽብር ህጉ ከህገ-መንግስቱ ጋር ስንት ጊዜ እንደሚጋጭ አለማወቃቸው ነው፡፡ በአንድ በኩል ህገ-መንግስቱ ተናደ እያሉ ሲናገሩ የነበሩ ህገ-መንግስት የሚጥስ ህግ ምን ይሰራላቸዋል? ይሄ ህግ እየተጠቀሰ አንገታችንን እንድንደፋ የተደረግን ኢትዮጵያውያን ይሄ ህግ እንዲሻር እንታገላለን፡፡ ሁላችንም ባለ ሀገር እስከምንሆንም ትግሉ ይቀጥላል፡፡፡

No comments:

Post a Comment