Saturday, 29 June 2013

የአብዬን ወደ እምዬ

ወያኔና ከወያኔ አፍ የሰሙትን ሁሉ እንደበቀቀን እየደጋገሙ የሚያነበንቡ ሎሌዎች የራሳቸውን መልክ የሚያዩበት መስታወት የተቸገሩ ይመስላል። ወየኔና ሎሌዎቹ እራሳቸውን ማየት ስለተሳናቸው ህዝብም ልክ እንደ እነሱ ኣራሱን የማያይና እነሱንና እኩይ ስራቸዉን የማያዉቅ እየመሰላቸው ሄዷል፡፡ ለዚህም ነዉ በግፈኛ አገዛዛቸው ተንገፍግፎ የሚቃወማቸውን ሁሉ ጥላሸት ለመቀባትና በራሳቸው ስም ለመጥራት ሲንጠራሩ የሚታዩት።
የወያኔ ዘረኞች የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይሎች በሙሉ በፀረ-ኢትዮጵያዊነትና የአገርን ጥቅም ለባዕድ አሳልፎ በመሸጥ ሲከስሱ ስንሰማ አይናቸዉንና ፊታቸዉን ታጥበዉ አይነ ደረቅ ለመመሰል ስንት ኪሎ ጨው እንደፈጀባቸዉ መገመት ያዳግታል።
በአገራችን ታሪክ ውስጥ እንደወያኔ በኢትዮጵያ ህልውናና በወሳኝና ዘላቂ ጥቅሞቿ ላይ የዘመተ ኃይል ኖሮም ተፈጥሮም አያውቅም። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀግኖች አባቶቻችን አጽም ያረፈበትን መሬት በስጦታ ለጎረቤት አገር እናካችሁ ብሎ የሰጠ ማነዉ? ማነው በሽፍትነት ዘመኑ ለተደረገለት ውለታና ተቀናቃኞቹን እንዲጠብቁለት በማሰብ የኢትዮጵያን ድንበር እንደ ዳቦ እየገመሰ ለባዕዳን የሸጠው?
ማነው የገዛ ወገኑን ከአያት ቅድመ አያት አጽመ ርስቱ ላይ እያፈናቀለ አንድ ሲኒ ቡና በማይገዛ ገንዛብ ለምለም መሬታችንን ለባእዳን የሚያቀራምተው? ማነው በህዝብ ስም በልመናና በችሮታ የተገኘን ገንዘብ እየዘረፈ ከአገርና ከህዝብ ደብቆ የባእድ አገር ባንኮችን የሚያደልበው? ኢትዮጵያ በሶማሊያ በተወረረችበት በ1970ዎቹ አመታት የሞቃዲሾን ፓስፖርት ተሸክመው ይንጎማለሉ የነበሩት የዛሬዎቹ የወያኔ አለቆች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ ገና አልረሳዉምኮ!
የዛሬዎቹ የወያኔ መሪዎች ትናንት የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ማየት ከማይፈልጉ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጋር እጅና ጓንት ሆነዉ የኛን የጎሳ ድርጅት እስከረዳችሁ ድረስ ኢትዮጵያን እናደክምላችኋለን የሚሉ ጸረ አገርና ጸረ ህዝቦች ነበሩ።እነዚህ የለየላቸዉ ከሀዲዎች ዛሬ አይናቸዉን በጨው አጥበዉ እራሳቸዉን የኢትዮጵያ ጥቅም አስከባሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነትና ለአገር አንድነት መከበር የሚታገሉትን ዉድ የኢትዮጵያ ልጆች የአገር ጠላት ብሎ ለመጥራት የሚያበቃ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያክል የሞራል ብቃት የላቸውም።
ወያኔዎች ስልጣን በያዙ ማግስት በጻፉትና እነሱን ሲጠቅም በሚጠቅሱት አገርንና ህዝብን ሲጠቅም ግን እየዳጡ በሚያልፉት ህገመንግስት ዉስጥ ደደቢት በረሃ የወሰዳቸዉን ዋነኛ አላማ መገነጣጠልን እንደ አገር ጥቅም በጹሁፍ ካልሰፈረ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ የነበሩበትን ጊዜ እኛ የኢትዮጵያ ነገር የሚቆረቁረን ወገኖች አልረሳነውም። ለመሆኑ ሌሎችን በጸረ-ኢትዮጵያዊነት የሚከሰው ወያኔ እውነት ኢትዮጵያን ከወደደ መገነጣጠልን ለምን ተመኘላት? መገነጣጠልን የመሰለ አደጋ እንደ ብሔራዊ የአገር ጥቅም አይቶ የራሱን ምኞት በህግመንግስት ደረጃ ያጸደቀዉ ወያኔ እንዴት ሆኖ ነው ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር የሚጋደሉና የሚታገሉ ልጆቿን በሀገር ጠላትነት የሚከስሰው? የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ ጋር የሚደረገዉን ትግል ከመብትና ከነጻነት ትግል ባሻገር እንደ አገር አድን ትግል አድርጎ የሚመለከተዉ ይህንኑ ወያኔ በአገራችን ብሄራዊ ጥቅሞች ላይ በተደጋጋሚ ያሳየዉን ጠላትነት በመገንዘብ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ ተቃዋሚ ኃይሎችን በጅምላ የአገር ጠላት ለማስመሰል በሚቆጣጠራቸዉ የመገናኛ አዉታሮችና በታማኝ ሎሌዎቹ በኩል የጀመረዉን የስም ማጥፋት ዘመቻ ከወዲሁ ተረድቶ “የአብዬን ወደ እምዬ” ብሎ ትግሉን ከቀጠለ ዉሎ አድሯል። ወያኔና ለሆዳቸው ያደሩ ሎሌዎች ሁለመናቸውን የወረሰውን የፀረ-ህዝብና ጸረ ኢትዮጵያዊነት እከክ ማንም ላይ ማራገፍ አይችሉም። ድፍን ኢትዮጵያ ማንነታቸውን አሳምሮ ያውቃልና።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment