Wednesday, 13 November 2013

በሳውዲ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ግፍ እንደቀጠለ ነው

ህዳር (ሦስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ካለፉት 5 ቀናት ጀምሮ በሳውዲ አረብያ በተለያዩ የማጎሪያ ጣቢያዎች ታስረው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እንደቀጠለ ሲሆን፣ በዛሬው እለት 2 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ኢትዮጵያውያኑ እንደሚናገሩት ሰዎቹ የተገደሉት ባልና ሚስቶችን ለመለያየት በተደረገ ሙከራ ላይ በተፈጠረ ግርግር ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከሳዑዲው  አቻቸው ልዑል ሳውድ አል ፋይሰል በስልክ መወያየታቸውን የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ገልጸዋል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት  እንደተናገሩት ደግሞ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ከተወያዩ በኋላ በኢትዮጵያውያኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ረገብ ብሏል ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውይይቱን ባደረጉ በሰአታት ውስጥ ሁኔታው ተሻሽሏል የሚል መግለጫ መስጠታቸው ኢትዮጵያውያንንን ያሳዘነ ሆኗል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተመራ ልዑክ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ማምራቱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። የልኡካን ቡድኑ እነማንን እንዳካተተ የተገለጸ ነገር የለም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሀኖም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በደል ሲደርስባቸው፣ ነገሩን እንደቀላል በማየታቸው በማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ትችት እየቀረበባቸው ነው።
መንግስት ችግሩ ረግቧል በማለት መግለጫ ከሰጠ በሁዋላ የነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን በሰጡት አስተያየት ችግሩ አሁንም በአስከፊ ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል። በሪያድ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ  አብዛኛውን ኢትዮጵያውያንን ከከተማ በማውጣት በረሀ ውስጥ አጉረዋቸው እንደሚገኝ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment