Thursday, 21 November 2013

በአስመራ ጀኔራሎች መካከል የስልጣን ሽኩቻ ይጠበቃል (የአሜሪካ መንግስት ለዜጎቹ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል)

 
ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከዕይታ መሰወራቸው አነጋጋሪ ሆኗል
በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም አጋማሽ በኤርትራ ጎዳና መታየታቸው የተነገረላቸው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአደባባይ እና ከኤርትራ ቴሌቪዥን ዕይታ ውጪ መሆናቸው በአስመራ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ የሆነ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
የሰንደቅ ጋዜጣ ዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደገለፁት “ከዚህ በፊት ፕሬዝደንቱ ከሚሰቃዩበት የጉበት በሽታ ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ ሕመም ተዳርገዋል። በአሁን ሰዓት በኳታር ሆስፒታል ሕክምና እየወሰዱ ይገኛሉ” ብለዋል።
በአስመራ ከተማ ውስጥ እየተናፈሰ ያለው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከበሽታቸው አገግመው ሀገር ሊያስተዳድሩ ይችላሉ የሚሉ በአንድ ወገን በሌላ ወገን ያሉት ከዚህ በኋላ ፕሬዝደንቱ ሀገር በሚያስተዳድሩበት ቁመና ውስጥ ሊገኙ አይችሉም የሚሉት ይገኙበታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግስት እ.ኤ.አ. በግንቦት 10 ቀን 2013 ወደ ኤርትራ የሚጓዙ የአሜሪካ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያርጉ የሚያሳስብና ከተቻለ ወደ ኤርትራ ጉዞ እንዳያደርጉ የሚመክር የማሳሰቢያ መልዕክት በዚሁ ሳምንት በድጋሚ ለዜጎቹ አስተላልፏል።
“የኤርትራና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸው ዜጎች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ያስራቸዋል። ስለታሰሩ ዜጎች ከአሜሪካ መንግስት ማብራሪያ ሲጠየቅም ምላሽ አይሰጥም። አስመራ የሚገኘውም የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ መታሰራቸውን ሰምቶ ማብራሪያ ለአስመራ መንግስት ቢያቀርብም ምላሽ አይሠጥም” ሲል መግለጫው ተቃውሞውን አሰምቷል።
በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ የኤርትራ መንግስት በግለሰብ ደረጃ ዜጎቹን አውቶማቲክ መሳሪያ በማስታጠቁ በቀላሉ የአሜሪካ ዜጎች ለአደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ ከሚል ስጋት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ታጣቂዎች በአስመራ ከተማ ሚሊሽያ በሚል ስለሚታወቁ ማንኛውንም ሰው በፈለጉት ቦታና ሰዓት መፈተሽ ይችላሉ። በዚህም የተነሳ በአስመራ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻና የሃይማኖት ቦታዎች ለመጎብኘት የሚመጡ የአሜሪካ ዜጎች በእነዚህ ታጣቂዎች ላይ ሊደርስባቸው ከሚችለው ስጋት ለመዳን ከአሜሪካ መንግስት ዕውቅና ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ መግለጫው አሳስቧል።
በኦክቶበር 3 ቀን 2013 በላምባዱሳ ለተሰውት 350 ኤርትራዊያን ማስታወሻ በተደረገ ስነ-ስርዓት በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ኤርትራዊያን በመንግስታቸው ላይ ባሰሙት ቅሬታ ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱ የሚታወቅ ነው።፡
የኢሳያስ አፈወርቂ ጤና መሻሻል ካላመጣ በአስመራ ወታደራዊ ባለስልጣናት መካከል የስልጣን ሹኩቻ መነሳቱ አይቀርም ሲሉ የዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን ገልፀዋል። አያይዘውም፤ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት እ.ኤ.አ. 2009 የአስመራ መንግስት በሚከተለው የትርምስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መነሻነት በኤርትራ መንግስት ላይ ባስተላለፈው ማዕቀብ የተነሳ እስከ ዛሬ ድረስ የአስመራ መገናኛ ብዙሃን በአሜሪካ መንግስት ላይ ከፍተኛ የስም የማጥፋት ፕሮፖጋንዳ እየፈጸመ መሆኑ ይታወቃል።¾
EthiopianReview.com

No comments:

Post a Comment