Friday, 8 November 2013

የኢትዮጵያዉያን ስቃይና መከራ በሳዉዲ አረቢያ

(በሳዲቅ አህመድ)

የመጣኸዉ ባዶህን ነው! ባዶ ሆነህም ትመለሳለህ!…ኢንተ-ጃኢ-ፋዲ ወተርጃእ-ፋዲ…የሳዉዲዎች አመለካከት!
የፈለጋቹበት ዉሰዱን ግን አትደብድቡን…ይላል ኢትዮጵያዊዉ…ለካስ አትደብድቡን ማለቱ የሚያስደበድብ ነበር…
አይደለም የሰዉ ልጅ እንስሳ እንኳ እንደዚህ አይደረግም። የምታዩአቸዉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሳዉዲ ዜጎች ተይዘዉ ወደ ጀዋዛት (የስደተኛ መምሪያ) ሲወሰዱ ነዉ። እነዚህን ደሃና ከርታታ ኢትዮጵያዉያን በቁጥጥር ስር ያዋለዉ ያገሪቱ ፖሊስ ሳይሆን ያገሪቱ ዜጎች ናቸዉ።”እክስር የዱ!…እጁን ስበረዉ!…” ይላል አንዱ። ከታች ሆኖ የጣር ድምጽን የሚያሰማዉ ኢትዮጵያዊ “ሐላሊ…ሐላሊ… ላቤን ያፈሰስኩበት የልፋቴ ዋጋስ? በማለት ሲጠይቅ ዱላዉ ይጠነክርበታል።
ሰዉ የመሆን ማእረግን የተነፈገዉ ሌላኛዉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ዱላዉን እርግጫዉን እየዋጠ ስቃዩን ለመቀነስ “ኻላስ-አነ-ገልጣን…በቃ! በቃ! እኔ-ነኝ-ጥፋተኛ” ይላል። ከሳዉዲ ዜጎች አንደኛዉ ኢትዮጵያዉያኑ በመያዛቸዉ ባይከፋም ዱላዉን እንዲህ እያለ ይቃወማል “ተራ ኤይብ-መጅሙዓ-ተድርቡነ?… ይህ ነዉር ነዉ በህብረት ትደባደባላችሁ?” ግን ማን ሊሰማዉ። የኢትዮጵያዉያኑን የሰራ-አካል ማሰቃየት ብቻ ሳይሆን የሚያራግፉባቸዉም የቃላት ናዳ ስነልቦናን ይሰብራል።The Misery of Ethiopians in Saudi Arabia
አገር ዉስጥ ካለዉ ስቃይ ለመዳንና የተሻለን ህይወት ለራስም ለቤተስብም ለማምጣት የሚሰደዱት ኢትዮጵያዉን የሚደርስባችዉ መከራና እንግልት ተቆጥሮ አያበቃም። የሳዉዲ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) የሌላቸዉ ወይም ከአሰሪያችዉ ጋር የማይሰሩ (ከፊል) በመጡበት የስራ ዓይነት (ሚህና) የማይሰሩት ከአገር እንዲወጡ ወይም የመኖሪያ ፈቃዳቸዉን እንዲያስተካክሉ የሰጠዉ ግዜ ስላበቃ ሰዎችን በዜግነት በሐማኖት ሳይለዩ ማፈሱን ተያዘዉታል። ባንጻሩ እነዚህ ሰደተኞችን ወደ ሳዉዲ በማስገባት ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙን የሳዉዲ ዜጎች መንግስቱ ወጥ የሆነ እርምጃ ሲወስድባቸዉ አይስተዋልም። ስለዚህ የሳዉዲ ዜጎችም ይሁኑ መንግስቱ ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም።
ሰዎች ወደ ሳዉዲ እንዴት ይገባሉ የሚለዉን ስንቃኝ…
1) በሐሃጅና በኡምራ(ጸሎት)
ሰዎች ከተለያዩ አገራት ጸሎት እናደርጋለን በማለት ወደ ሳዉዲ ከደረሱ በሗላ እዚያዉ ይቀራሉ። እነዚህን ሰዎች ቀጥሮ በማሰራትም ይሁን ከቦታ ቦታ በድብቅ በማመላለስ ህገወጥ ተግባር ላይ የሚሰማሩት የሳዉዲ ዜጎች ናቸዉ። በነዚህ የሳዉዲ ዜጎች ላይ መንግስቱ በቂ የሆነ እርምጃ አይወስድም፤ የርምጃዉ ሰለባ የሚሆኑት ስደተኞቹ ብቻ በመሆናቸዉ መንግስቱ ተጠያቂ ነዉ።
2) የኮንትራት ስራ (ጠለብ)
በኮንትራት የሚመጡት ሰራተኞች ከዘመናዊ ባርነት ባልተናነሰ መልኩ ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል። ረጅም ሰዓታትን መስራት ብቻ  ሳይሆን ከኮንትራቱ ዉል ዉጪ ለዘመድና ለጎረቤት በተጨማሪ እንዲሰሩ የሚገደዱ አሉ። የጠለብ (የኮንትራት) ሰራተኞች ድብደባ፣ግርፋት፣አስገድዶ መድፈር (rape)ወዘተ ይደርስባቸዋል፤ በዚህም ሳቢያ ከአሰሪያቸዉ በመጥፋት በግል ተቀጥረዉ መስራት ይጀምራሉ።የሳዉዲ መንግስት ዜጎቹ የሰራተኛን መብት እንዲያከብሩ በቂ ግንዛቤን ባለመፍጠሩና  ይሕንን መስል ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፍጽሙትን ዜጎች ሕግ ፊት በተገቢዉ መልኩ ባለማቅረቡ ተባባሪ ያስመስለዋልና ተጠያቂ ነዉ።
2) በባህርና ድንበር አቋርጦ መግባት
የሳዉዲ ጎረቤት ከሆነችዉ የመን በኩል ብዙ ስደተኞች ወደ ሳዉዲ ይገባሉ። በተለይም ጀዛን የሚባለዉ የሳውዲ ግዛት ቀድም ሲል የየመን የነበረ ሲሆን ድንበሩን አንድ አይነት ጎሳዎች ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦችም ይጋሩታል፤ በሁለቱም አገራት ያሉ የህግ አስከባሪ አካለት የሚዛመዱበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ። በተቀነባበረ የኮንትሮባንድ ስራ ፖሊሶችና ድንበር ጠባቂ ሐይላት ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በማስገባት ይተባበራሉ። የሳዉዲ መንግስት በድንበሩ ላይ ባሉ የህግ አስከባሪ ሐይላት ላይ በቂ ቁጥጥር ባለማድረጉ ተጠያቂ ነዉ።
ስደተኞች ወደ ሳዉዲ ሲገቡ የአገሪቱን ግዛቶች አቋርጠዉ ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወሩ የኮንትሮባንድን ስራ የሚሰሩት የሳዉዲ ዜጎች ናቸዉ። ለምሳሌ አንድ ስደተኛ ከየመን ድንበር-ጀዛን ወደ ሪያድ ወይም ወደ ጂዳ መግባት ቢፈልግ በጭነት መኪና ከእቃ ጋር ተደብቆ እንዲገባ ይደረጋል፤ካልያም ወንዱ እንደሴት ቀሚስ-ሻሽ-የፊት መሸፈኛ እንዲለብስ ይደረግና የሳዉዲ ዜጎች እንደ ሚስት ወይም ልጆች ጭኖ በኮንትሮባንድ ሰዎችን ከቦታ ቦታ ያመላልሳሉ። በዚህ የኮንትሮባንድ ተግባር ፖሊስ (ሹርጣ) ተባባሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነዉ። ለዚህ ህገ ወጥ ተግባር ከሳዉዲ መንግስት ሌላ ማንም ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።
ወደ ሳዉዲ ለምግባት ኢቃማ (የመኖሪያ ፈቃድ) በዉድ ገዝተዉ የሚገቡ ስደተኞች አንዳንዴ የውሸት አሰሪያቸዉ (ከፊል) ጠፍቶባቸዉ የመኖሪያ ፍቃድ ለማዉጣት የሚቸገሩበት አጋጣሚ አለ። አንዳንዴም የመኖሪያ ፍቃዱን ቢያገኙም ፈቃዳቸዉ ሲቃጠል ለማደስ (ተጅዲድ) አሰሪያቸዉ ጠፍቶ ወይም ፍቃደኛ ሳይሆን ይቀርና ሳይወዱ በግድ ህገወጥ ይሆናሉ። ለዚህ ህገወጥና የተዝረከረከ አሰራር ከሳዉዲ መንግስት ሌላ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል?
በሳዉዲ ከተሞች ዉስጥ በስፋት ያሉት ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮዎች (መክተበል ሙአቂብ) የመኖሪያ ፍቃድን በተመለከተ የተለያዩ የማጭበርበር ስራዎች (ተዝዊር) በመስራት ይታወቃሉ። እነዚህን ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮ ከፍቶ ለመስራት የሳዉዲ ዜጋ መሆኑ ግዴታ ነዉ። በነዚህ ቢሮዎች የዉሸት የመኖሪያ ፍቃድን ከማዘጋጀት ጀምሮ፤ስደተኞች ያለ አሰሪያቸዉ (የዉሸት አሰሪም ቢሆን) ፍቃድ ከአገር ወጥተዉ እንዲመለሱ (ኹርጀል አዉዳ) እስክማድረግ ይሰራል። በነዚህ ቢሮዎች ዉስጥ ሌላዉ ቀርቶ ከስራ ሰዓት ዉጪ ከኢምግሬሽን (ጀዋዛት) በመመላለስ ባዶ ኢቃማ የመኖሪያ ፈቃድ በማምጣት የዉሸት የምኖሪያ ፍቃድ የሚሰጡ የመንግስት ሰራተኞች በርካታ (ነበሩ)ናቸዉ። በዉሸት ከአንድ አሰሪ ወደ ሌላ አሰሪ (ተናዙል-ነቅለል-ከፋላ) በማድረግም የሳዉዲ ህግ አስከባሪ አካላት በመተባበር ህገወጥነትን ያስፋፋሉ። ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ተጠያቂዉ ዛሬ በየመንገዱ እንደ እንስሳ እየታደኑ ኢሰብዓዊ ተግባር የሚፈጽምባቸዉ ስደተኞች ሳይሆኑ የሳዉዲ መንግስት ነዉ። ከሳዉዲ መንግስትም ባሻገር አገሪቷን የተቆጣጠሩት የንጉስ አብድልአዚዝ ቤተሰቦች ያንበሳዉን ደርሻ ይይዛሉ።
በሳዉዲ ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ በትክክለኛዉ መንገድ ሰርትዉ የከበሩ፤ላገር፣ለቤተሰብ፣ለወገን የተረፉ በርካታ ናቸዉ። ባንጻሩም እንደ ወጡ የቀሩ፤ ጤነኛ ሆነዉ ታመዉ የተመለሱም ይኖራሉ። በህገወጥ መንገድ አረቄና አስካሪ መጠጥን በመጥመቅ ብሎም በዝሙት የሚተዳደሩም ይኖራሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ እዚያዉ-ሳዉዲ የተወለዱ ኢትዮጵያዉያን ህጻናት ሲኖሩ በአገሪቱ ደንብ መሰረት ሁለተኛ ደረጃን ከጨረሱ በሗላ የኮሌጅ ትምርት የማግኘት እድላቸዉ የመነመነ ነዉ (አይቻልም ማለት ይቻላል)። አቅም ያለዉ ልጆቹን ወደ አዉሮፓ እና አሜሪካ ለከፍተኛ ትምርት ሲልክ ዉስን አቅም ያለዉ ልጆቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ በተለያዩ ኮሌጆች ያስተምራል። ሁለቱንም ማረግ ያልችለ ልጆቹ ያለትምርት የሚባክኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነዉ።የባህረ ሰላጤዉን ስደት አስመልክቶ ብዙ ግዜ የሚነገረዉ ለአቅመ አዳምና ሔዋን ለደረሱት ኢትዮጵያዉያን ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የወደፊት እጣ ፈንታቸዉን የማያዉቁ ሕጻናት ስለተዘነጉ ለነርሱም ማሰቡ ታላቅ ሰብዓዊ ግዴታ ነዉ።
በዚህ መከራና ስቃያ ዉስጥ ላሉ ኢትዮጵያዉን ለመታደግ ለዜጎቹ የሚቆረቆር ሁነኛ መንግስት ቢያሻም ሪያድ ያለዉ የሳዉዲ ኤምባሲና ጅዳ ያለዉ የቆንስላ ጽ/ቤት በመጣመር ዜጎችን የሚበድሉ ቢሆኑ እንጂ ለዜጎች ደራሽ ሲሆኑ አይታይም። ከተወሳሰበዉ የሳዉዲ ህግ ለመዳንና የመኖሪያ ፍቃድን ለማደስ ለፓስፖርት እድሳት ኤምባሲ የሚሔዱ ኢትዮጵያዉን ከፍላጎታቸዉ ዉጪ ለአባይ ቦንድ ግዙ ተብለዉ እንደሚቸገሩ ቀደም ሲል የተዘገበ እዉነታ ነዉ።ኤምባሲዉ ኢትዮጵያዉያንን በዘር በብሔር እየመተረ በልማት ስም አፍን ብልጓም ሲዘጋ ኢትዮጵያዉያን በየመንገዱ ላይ ከእንስሳ ባነሰ መልኩ እየተደበደቡ እየተገረፉ ክብራቸዉ ተገፎ ወደ ማጎሪያ ቤት (ተርኺል) እየተወረወሩ ነዉ።
ይህ ኢሰብዓዊ ተግባር አለም አቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ ለተለያዩ የስብዓዊ መብት ድርጅቶች ማሳወቁ ተገቢ ሲሆን ጉዳዩ ከፍትኛ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ኢትዮጵያዉያን በያሉበት መንቀሳቀስ አለባቸዉ።የፖለቲካ ድርጅቶችም ኢትዮጵያዉያኑ የሚደርስባቸዉን በደል በማዉገዝ ለጉዳዩ ልዩ አትኩሮትን በመቸር አቅማቸዉ በቻለዉ መጠን ሊንቀሳቀሱ ይገባል። የተለያዩ የሐይማኖትና የሲቪክ ማህበራትም ይሁኑ አክቲቪስቶች በመጣመር የሳዉዲ ኤምባሲዎች በሚገኙበት አገራት ሰላማዊ ሰልፍን ቢያረጉ መግለጫዎችን ቢያወጡ የወገኖቻንን ስቃይና መከራን ማስቆም ባይችሉ እንኳ ሊቀንሱት ይችላሉና-ወገን ለወገን መድረሱ ግድ ይላል።
የመጣኸዉ ባዶህን ነው… ባዶ ሆነህም ትመለሳለህ…(ኢንተ፡ጃኢ፡ፋዲ ወተርጃእ፡ፋዲ) ለሚባሉት ኢትዮጵያዉይን ከኛ  ሌላ ደራሽ የላቸዉምንና እንድረስላቸዉ። ልብ ያለዉ ልብ ይበል!

No comments:

Post a Comment