Wednesday, 13 November 2013

ትግሉ መሯል፤ እኛም ዝግጁዎች ነን

በንቅናቄዓችን ፀሐፊ እና በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አመራር አባላት ላይ የተቃጣው ረዥም ጊዜ የወሰደ የግድያ ሴራ መክሸፉ አስደስቶናል። ይህ ሴራ የወያኔ የስለላና የግድያ ኃላፊዎች በሆኑት ጌታቸው አሰፋ እና ጸጋየ በርሄ የቅርብ ክትትል የተመራ፤ የአሻንጉሊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ እውቅናና ይሁንታ የተሰጠው፤ ወያኔ ከፍ ያለ ተስፋ የጣለበት ሴራ ነበር።
“ወያኔ-ኦ-ሚሊኒየም” የተሰኘው ይህ በወያኔ የመጨረሻ ከፍተኛው አመራር የተመራው ሴራ ስለወያኔ ውስጣዊ አደረጃጀት ጠቃሚ መረጃዎችን ሰጥቶናል። ከዚህም በተጨማሪ የወያኔ ሹማምንት ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ንቀት፤ ከአመት በኋላ ስለሚደረገው ምርጫ ውጤት፤ ለሰላዮቻቸው ስለሚሰጡት ጉርሻ መጠን፤ እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ተስፋ ከጣሉበት ቅጥረኛ ነብሰ ገዳያቸው ጋር ካደረጉት የስልክ ንግግሮች ማድመጥ ይቻላል። ይህ ለበርካታ ጥናቶች በግብዓትነት ሊውል የሚችለውን በድምሩ ከስምንት ሰዓታት በላይ የሚፈጀው የስልክ ንግግር ቅጂ በሕዝባዊ ኃይሉ የመረጃ ክፍል አማካይነት ለሕዝብ በኢንተርኔት በነፃ ተለቋል። በአጋጣሚውም የወያኔ ገበና ተጋልጧል።
በአንፃሩ ደግሞ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የተደራጀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም ምን ያህል ወያኔን እንቅልፍ እንደነሳ ተጨባጭ ማስረጃ ሆኗል። ይህ ለነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ የስነልቦና ብርታት የሚሰጥ ነገር ሆኖ ተገኝቷል።
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የተቃጣበትን ጥቃት ከማክሸፍ በተጨማሪ የወያኔን ገበና ማጋለጥ በመቻሉ የመጀመሪያው ሁነኛ ድል ተቀዳጅቷል።
ግንቦት 7 : የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ወያኔ ኦ ሚሊኒየም” አፕሬሽንን ላከሸፉ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አመራርና አባላት ያለውን አድናቆት ይገልፃል። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊደርሱ የሚችሉ መሆኑን በመገንዘብ የመከላከል ብሎም የማጥቃት ኃይሉን እንዲያጠናክር ይመክራል።
የንቅናቀዓችን እና የሕዝባዊ ኃይሉ አመራርና አባላት ለመስዋዕትነት የተዘጋጁ ናቸው። “ወያኔ ኦ ሚሊኒየም” ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ትግላችን ይገታ ነበር ማለት አይደለም። ትግላችን መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን እናውቃለን። ጓዶች ሲወድቁ ሌሎች ሺዎች አርማቸውን አንስተው ትግሉን ይቀጥላሉ።
ትግሉ የሚጠይቀንን መስዋትነት ከፍለን ወያኔን ከሥልጣን አስወግደን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሆነባት ኢትዮጵያ እንደምትኖረን እርግጠኞች ነኝ።
ትግሉ መሯል፤ እኛም ዝግጁዎች ነን።
ድል ለግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment