Tuesday, 26 November 2013

“አንድ ጊዜ ሆድ ብሶኝ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር” – ከሳዑዲ ተመላሿ ሃያት አህመድ (ቃለምልልስ)

ከዚህ በፊት ባቀረብናቸው ሁለት ዜናዎች ከሳዑዲ አረቢያ ስቃይ ተርፈው ለሃገራቸው መሬት ከበቁት ኢትዮጵያውያን መካከል የሁለቱን ከአዲስ አድማስ ጋዜጠና አበባየሁ ገበየሁ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ማስነበባችን ይታወሳል። አሁንም የምናቀርብላችሁ ሓያት አህመድ የተባለችውን ከሰሞኑ ለሃገሯ ምድር የበቃችውን እህታችንን ቃለምልልስ ይሆናል – እንደወረደ ይኸው፦
ስምሽን ንገሪኝ..?
ሀያት አህመድ
እስቲ አካሄድሽን ንገሪኝ …
ከደሴ ነው በኤጀንሲ የሄድኩት፡፡ የምሰራው በጠለብ/በህጋዊ መንገድ ነበር፡፡ ሰዎቹ ሳይመቹኝ ሲቀሩ..ብዙ ጓደኞቻችን ችግር ሲደርስባቸው ሳይ፣ ስልካችንን ቀምተው ቤተሰቦቻችን በሃሳብ ሲያልቁ፣ እኔም ነገሩ ስላልተመቸኝ ጥዬ ጠፋሁ፡፡ ከዛም በሃጂና ኡምራ የሄድኩ አስመስዬ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡
በጠለብ ስንት ጊዜ ሰራሽ?
ሶስት ወር ነው የሰራሁት፡፡
አሰሪዎችስ ቤት የሚደርስብሽ ችግር ምን ነበር?
በቤት ውስጥ ያሉ ወንዶች ያስቸግሩኝ ነበር፤ አስገድዶ ለመድፈር ይተናነቁኛል፡፡ አሰሪዬ በስራዬ አትደሰትም፣ ያጠብኩትን ነገር እንደገና እጠቢ ትለኛለች፡፡
“የኢትዮጵያ ሰራተኞች ሞያ የላቸውም፣ “ሞዴስ እንኳን በአግባቡ መጠቀም አይችሉም፣ በዚያ ላይ ወንዶቻችንን ያባልጋሉ” የሚል ክስ ከሳኡዲ ሴቶች ይሰማል፡፡ አንቺ ምን ትያለሽ?
በጭራሽ! እኛ ደልቶን ይሄን ልናስብ? አንገታችንን ቀና አድርገን እንኳን ለመሄድ እንቸገራለን እኮ፡፡ እዛ ቦታ ላይ እኛን ብታይ ኢትዮጵያዊነት ያስጠላሻል፡፡ አለባበሳችን ምንድን ነው፣ ሁኔታችንስ፣ ኑሮዋችንስ..እኛ የእነሱን ባል የምናባልግ ምን አምሮብን፣ እንዴት ሆነን ነው? እኛን እኮ ይጠየፉናል፡፡ በምን አንገታችን ቀና ብለን ነው የእነሱን ወንዶች የምናባልገው? እኛ እኮ ለህይወታችን እየሰጋን ነው… እያንዳንዷን ቀን የምናሳልፈው፡፡ በርግጥ የገጠር ልጆችም ይሄዳሉ። እንግዲህ በንፅህና የሚታሙት እነሱ ናቸው፡፡ ግን ስንቱን አእምሮውን አሳጡት…. ወይኔ!!..አሁን ስንመጣ እንኳን ጅዳ ኤርፖርት ውስጥ ሰባት ያበዱ ልጆችን አይቻለሁ፡፡ ‹‹ይዛችኋቸው ሂዱ›› ሲሉን ነበር፤ እንዴት አድርገን እንይዛቸዋለን? ጥለናቸው ነው የመጣን፡፡ አይ ዜጎቻችን! እየቀወሱ፣ እየተደፈሩ፣ እየተደበደቡ፣ እየተጣሉ ነው ሜዳ ላይ ….ተመልካች አጥተው፡፡
ጣትሽ ላይ የጋብቻ ቀለበት አያለሁ … ባለትዳር ነሽ?
ፈትቻለሁ፡፡ የአስር ዓመትና የስምንት ዓመት ልጆች አሉኝ፡፡ እነሱን ላሳድግ ብዬ ነው በሰው አገር የተንገላታሁት፡፡ ገንዘብ እልክ ነበር፡፡ ሆኖም እኔም አልተለወጥኩም፤ ለልጆቼም አልሞላልኝም፡፡ አንድ ጊዜ ሆድ ብሶኝ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር፡፡ ታውቂያለሽ… ልጆቼ በዓይን በዓይኔ መጡብኝና … ከድርጊቴ ታቀብኩ፡፡
አይኔ እንቅልፍ ካጣ ስንት ጊዜው ሆነ መሰለሽ… አይኔ ስር ጥቁር ብሎ የምታይው፣ የበለዘ የሚመስለው እኮ በእንቅልፍ እጦት የተፈጠረብኝ ነው፡፡ ጀርባዬን ያመኛል፡፡ ብዙ ሰዓት የምቆምበት እግሬንም እጅግ ታምሚያለሁ፡፡ አሁን ለትንሽ ጊዜ ማገገም አለብኝ፡፡
ጂዳ ኤርፖርት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚጠባበቁ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ ይባላል…?
በጣም ብዙ እንጂ! ‘ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገር ነቅሎ ነው እንዴ የወጣው ብዬ ተደንቄያለሁ፡፡ በጣም ያዘንኩት ግን ወደዚህ ስመጣ ኤርፖርት ሰባት ያበዱ ልጆች ስመለከት ነው፡፡
እዛ ያለው ኤምባሲያችን እንዴት ወደ አገራቸው አይመልሳቸውም?
‹‹እህ›› ብሎ ችግራቸውን የሚያደምጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ እስቲ አስቢው…ሰባት ሴቶች አብደው አይቻለሁ፤ በአይኔ በብረቱ፡፡ አንዷ ልጅዋ ሞታባት (በረሃብ ነው) የቀወሰችው፡፡ ስድስቱ ደግሞ በስራ ቦታቸው ቀውሰው፣ አሰሪዎቻቸው ናቸው አምጥተው የጣልዋቸው፡፡ የምናየው ነገር ሁሉ ለዓይን ይዘገንናል፡፡
ከዕረፍት በኋላ ምን ልትሰሪ አቀድሽ…?
አሁን ጤንነት አይሰማኝም፤ ካገገምኩ በኋላ እንግዲህ … እንጃ ምን እንደምሰራ፡፡ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ተቀምጬ ነው የመጣሁት፡፡ ከአስርና አስራ አምስት ዓመት በላይ የኖሩትም ‹‹ምንድነው የምንሰራው..›› የሚል ነው ጥያቄያቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ኖረው ቢመጡም ምንም የያዙት ነገር የላቸውም፡፡ በጣም ያሳሰበኝ እሱ ነው፡፡
ከአሁን በኋላ ወደ ሳኡዲ የመመለስ ሃሳብ አለሽ?
አላህ ያውቃል፡፡

No comments:

Post a Comment