Thursday 28 August 2014

በድርጅቶች ውህደትና ቅንጅት አገርን ማዳን!!!

ኢትዮጵያዊያንን በዘር እና በሀይማኖት ለያይቶን እርስ በርስ እያጋጨን በመግዛት ላይ ያለውን ወያኔን ለማሸነፍ እና ከምትኩም ከራሷ ጋር የታረቀች፤ ፍትህ የሰፈነባት፤ እኩልነት የተረጋገጠባት እና በኃያላን አገሮች እርጥባን ሳይሆን በራሷ አቅም የምትተማመን ጠንካራ ሀገር እንድትኖረን የነፃነትና የዲሞክራሲ ኃይሎት መተባበር እንዳለባቸው ሲነገርና ሲወተወት ቆይቷል። ይሁን እንጂ በህወሓት የከፋፍለህ ግዛው ፓሊሲ እና በፓለቲካ ባህላችን ኋላቀርነት ምክንያት እስካሁን የተደረጉ የትብብር ጥረቶች የተፈለገውን ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ቀድሞ የተደረጉት ጥረቶች የተጠበቀውን ውጤት አለማስገኘት ተስፋ ሳያቆርጠን ከእያንዳንዱ ጥረት ልምድ እየወሰደን የኢትዮጵያዊያን አንድነት እስኪረጋገጥ ድረስ አዳዲስ የትብብር ጥረቶችን ማድረግ ያለብን መሆኑ ያምናል። በዚህም መሠረት የትብብር መርህ ነድፎ ትግል ውስጥ ካሉ ሁሉም የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሲነጋገር እና ሲደራደር ቆይቷል። እንደሚታወቀው የንቅናቄዓችን አበይት የትብብር መርሆች ሁለት ናቸው። መርህ አንድ፣ ለውጥ እንዲመጣ የምንታገለው ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ መሆኑ ማመን ነው። መርህ ሁለት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም እርከኖች የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚገባው በሕዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ መሆኑን መቀበል ናቸው።
በምድር ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ኃይሎች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ሁለቱንም መርሆዎች የሚያሟሉ ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ከንቅናቄዓችን የተለየ አቋም የላቸውም። በአለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቶቹ ተቀራርበው እንዲሠሩ በመደረጉ ከአመራር አልፎ አባላት መካከል መልካም ወዳጅነት መመሥረት ተችሏል። የነፃነት ትግላችን የደረሰበት ደረጃ እና የድርጅቶቹም ቅርርብ በመገምገም ሶስቱ ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄና እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ መዋሃዳቸው ትግሉን ያራምዳል ተብሎ ታምኖበታል። በዚህም መሠረት ሶስቱ ድርጅቶች ለመዋሃድ ተስማምተን ስምምነታቸንን ይፋ አድርገናል። ድርጅቶቹን የማዋሃድ ዝርዝር ሥራም ተጀምሯል።
ከስትራቴጄ አንፃር የትብብር ጥረታችን በዚህ አያበቃም። በዓላማ የምንቀራረብ ሆኖ የአደረጃጀት ልዩነት ያለን የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር በጥምረት እየሠራን ድርጅቶቻችን ይበልጥ ለማቀራረብ ጥረት እያደረግን ነው። በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ነው። ንቅናቄዓችን ከትህዴን ጋር ከፍተኛ በሆነ መቀራረብና መተማመን ይሠራል። ይህ መቀራረብና መተማመን ጎልብቶ አንድ የጋራ አመራር የሚፈጥርበት ጊዜ እንዲቀርብ ጥረት እናደርጋለን። ምድር ላይ ከሚገኙ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋርም በመደጋገፍ እንሠራለን። በመጨረሻም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ካሉ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር ለመወያየት ዝግጁዎች መሆናችንን ደግመን እናረጋግጣለን። ልዩነቶቻችን ማጥበብ እንኳን ባንችል የምንተባበርባቸው መንገዶች ይኖራሉ ብለን እናምናለን።
የጦር ኃይሉንና የስለላ መዋቅሩን ዘረኛ በሆነ መንገድ የገባውንና የኢትዮጵያን ሀብት በመዝረፍ የደረጀው ህወሓትን ለማሸነፍ ትብብር ወሳኝ ጉዳይ ነው። ከወያኔ አገዛዝ ውድቀት በኋላ ወደ ተረጋጋ ሰላምና ልማት ፊታችንን የምናዞር መሆናችን ዋስትና የሚሰጠን በአንድ እዝ የሚመራ የአገር አድን ሠራዊት ማደራጀት ስንችል ነው። የአሁኑ ውህደት የዚህ አገር አገር አድን ሠራዊት ጥንስስ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ በኋላ የሚመጣው ምን እንደሆነ ባለማወቅ ሥጋት ውስጥ ሊገባ አይገባም። በዋና ዋና የአገሪቱ የፓለቲካ ድርጅቶች ውህደት እና ቅንጅት የተዋቀረ በአንድ ማዕከላዊ አመራር ሥር የሆነ አገር አድን ሠራዊት በተቻለ ፍጥነት ሊገነባ ይገባል።
ሶስቱ ድርጅቶች ለማድረግ በወሰነው ውህደት የዚህ የአገር አድን ሠራዊት ምሥረታን ጀምረናል። ስለኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ደህንነት ያገባናል የምትሉ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ አገር አድን ሠራዊት ምሥረታ ላይ እንድንነጋገር አበክረን እንጠይቃለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብም የትብብሩ መንፈስ አገርን የማዳን ግብ ያለመ መሆኑን በመገንዘብ ከተባበረው ድርጅት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን። የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዳይ የሚያገባው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲቀላቀለንና እንዲያግዘን ጥሪዓችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

መስዋትነት


መስዋትነት ከኤልሳቤጥ ግርማ (ኖርዌይ)



ዛሬ ወያኔ የሥልጣን ዘመኑ በጨመረ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህ ነፃነትና የዲሞክራሲ መብቱን እያጣ እንዲሁም የሚደርሰበት መከራ እየጨመረ መምጣቱ የማን አለብኝነትና የመኖር ዕድሜውን እያራዘመ እንደሆነ ማሳየቱን ቀጥሎአል።
ይህ ተግባሮት በቅርቡ በአቶ አንድአርጋቸዉ ፅጌ በሃገራችን በኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ጊዜውን እዉቀቱንና ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀና ዝግጅቱንም በዕዉን ያሳየ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍ እንኳን ያልበቃቸዉ ዛሬም ድረስ የስለላቸዉን መረብ እየዘረጉ ከጋሻጃግሬዎቻቸዉ ጋር በማበር ኢትዮጵያውያንን ከየቦታው እያሳደዱ በማሰርና በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ።
እነርሱም አሁንም ቂመኞች ናቸው፤ እነርሱ አሁንም ዘረኞች ናቸው፤ እነርሱ አሁንም የዘር ፖለቲካ እየረጩ ነው፤ እነርሱ አሁንም ለህዝቡ ለፍቅርና ለይቅርታ ምላሻቸዉ ትዕቢትና እቢሪት ጥላቻና እልህ፣ ቂምና ክፋት እየሆነ ነው። ይህም አልበቃ ብሎአቸዉ እንደፈረስ እየጋለቡ በወጣቱ ትውልድ ላይ ዘመቻቸውን እንደቀጠሉ ይገኛሉ።
ታድያ ይህ በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ኢሰባዊነት እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ በመሆኑ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን በተለያየ ቦታና ጊዜ እረፍት እየነሳዉ በቁጭት ላይ ይገኛል። በመሆኑም በሃገራችንና በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል አብቅቶ ያንን የምንናፍቀው ነፃነትና ፍትህ እንድንቀንናጅ ትግላችንን ማጠናከሩ አሁን ላይ አማራጭ የሌለውና እጅ ለእጅ ተያየዘን፣ ተደጋግፈን የአምባገነኑን ወያኔ እድሜ ማሣጠር የምንችልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ሁላችንም የየበኩላችንን አስተዋዕፆ የምናሳይበት ሰዓት አሁን ነው።
አርበኛችንና የቁርጥ ቀን የሆነው ልጃችን አንዳርጋቸው እንዲሁም መሠል ኢትዮጵያዊያንን ወገኖቻችን በጨቋኙ መሪ እጅ ስር መውደቃቸው አንገታችንን የሚያስደፋና ተስፋ የሚያስቆርጠን ሳይሆን እንደውም ከምንግዜውም በላይ የትግላችን ስልት ቀይሮና አጠናክሮት ይገኛል ።
በመሆኑም የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህን በሃገርና በህዝብ እየደረሰ ያለውን በደልና ግፍ ለመታገልና ጨርሶ ከስሩ ለመገርሰስ ለትግሉ የሚጠይቀዉን ሁሉ መስዋትነት እየከፈለ ይገኛል።
በዚህም መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኦገስት 31,2014 ባዘጋጀው ወቅታዊ ስብሰባና የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ በመካፈል ለሀገራችን ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ነፃነት ፍትህ ያስፈልጋታል የምንል ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በተመሳሳይም በኦስሎ በሚዘጋጀው ዝግጅት ላይ ተገኝተን ሃገራዊ ጥሪ አጋርነታችንንና ግዴታችንን መወጣት አለብን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኖራለች!!!

Wednesday 27 August 2014

ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ሐምሌ 2006ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ጉልበት አራዊት የሚተዳደሩበት ሕግ ነው፤ ሕገ አራዊት የሚባለው አራዊት የሚተዳደሩበት ጉልበት ነው፤ በአራዊት ዓለም ማናቸውም ነገር በጉልበት ያልቃል፤ በሰዎችም መሀከል ጉልበት አድራጊ-ፈጣሪ ሆኖ ጎልቶ ሲወጣ የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር ያመለክታል፤ ጉልበት አለን በማለት፣ ወይም ተመችቶናል በማለት፣ ወይም ጠያቂ የለብንም በማለት የማንኛውንም ሰው ሰብአዊ መብቱንና ሰብአዊ ክብሩን መግፈፍ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፤ አንደኛ ጉልበት እንጂ አእምሮና ኅሊና እንደሌለ፣ ሁለተኛ ጉልበት እንጂ ሕግ እንደማይከበር፣ ሦስተኛ በአንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሰዎች ላይ አታድርግ የሚለውን ሕግ መጣስን ያሳያል፤ በመጨረሻም፣ ዘግይቶም ቢሆን በራስ ላይ ቅሌትን መጋበዝን ያስከትላል፤ የሌላውን ሰውነት ስናረክስ ሰውነትን በጠቅላላው ማርከሳችን ነው፤ ሰውነትን በጠቅላላው ስናረክስ ራሳችንን ከነጉልበታችን ማርከሳችን ነው፤ ራሳችንን፣ ሰውነታችንን ካረከስን በኋላ ዋጋ የለንም፤ ለራሳችን ዋጋ ከሌለን ለሌለች ሰዎችም ዋጋ አንሰጥም፤ ያኔ ክፉ በሽታ ይይዘናል፤ እግራችን ስር በወደቀ ሰው ስቃይ የምንደሰትና የምንስቅ፣ የምንፈነድቅ እንሆናለን፤ ያን ጊዜ የለየለት በሽተኛ ሆነናል።ይሄ በሽታ ያቃዣል፤ ከሰው ሁሉ በላይ ያሉ ያስመስላል፤ አግሩ ስር የወደቀው አንድ ሰው የሰው ልጅ በሙሉ ይመስለዋል፤ በሽተኛነቱን ስለማያውቅ በሽታው ከሰው በላይ ያደረገው ይመስለዋል፤ እንዲህ ዓይነቱ በሽተኛ በሕግ አሰከባሪነት ሥራ ውስጥ ሲገባ ሕግ የአንድ ማኅበረሰብ ትምክህትና መከታ በመሆን ፋንታ የበሽተኞች በትር ይሆናል፤ በደርግ ዘመን የአራት ኪሎው ግርማ የሠራውን እናውቃለን፤ ዛሬ ደግሞ ልዩ ግርማዎች አሉ፤ መልካቸውን ከካሜራው ጀርባ ደብቀው በሰው ስቃይና አበሳ በሳቅ እየተንከተከቱ ጀብዱዋቸውን በቴሌቪዥን የሚደረድሩ ጀግኖች መጥተዋል፤ መሣሪያ ይዞ መሣሪያ ባልያዘ ሰው ላይ ጀግና መስሎ ለመታየት የሚሠራው ጨዋታ ራስን ክፉኛ ከማጋለጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።በኢትዮጵያዊ ሰውነት ላይ ማናቸውንም ከሕግና ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ ሙከራ ለማድረግ የውጭ አገር ሰዎች ዕድሉን ይፈልጉት ይሆናል፤ ለነሱ ሰዎች ስላልሆን ሰብአዊነት አይሰማቸውም፤ ከአገራቸው ሕግም ውጭ በመሆናቸው በሕግ አይገዙም፤ ዋናው ውጤት ግን ለኢትዮጵያ ሕግ አስከባሪዎች የሚያስተምሩት ግዴለሽነት ነው፤ መታሰር በብዙ ምክንያቶች ይመጣል፤ ስለዚህ በሠለጠነው ዓለም የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ሁኔታ ይጠበቃሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በቤታቸው ውስጥ እየተጠበቁ ይቆያሉ፤ ኢትዮጵያ በራስዋ ሥልጣኔ በምትተዳደርበት ዘመን መሳፍንትና መኳንንት የሚታሰሩት በወርቅ ወይም በብር ሰንሰለት ነበር፤ ግዞትም፣ የቁም እስርም ነበር፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እስረኞች ሁሉ እኩል ናቸው፤ በቃሊቲ ለየት ያለ አያያዝ የሚታየው ለሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ብቻ ነው።ጉልበትን በጉልበት እቋቋማለሁ የሚል ሰው ሲሸነፍ አያስደንቅም፤ አዲስም አይደለም፤በአለፉት አርባ ዓመታት እየተሸነፉ ከትግሉ ሜዳ ወጥተው በተለያዩ የምዕራባውያን አገሮች የሙጢኝ ብለው የተቀመጡ አሉ፤ በተባበሩት መንግሥታት ደንብ የሙጢኝ ማለት መብት ነው፤ ይህንን መብት መጣስ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ነው፤ በጎንደር የአደባባይ ኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በር መድፈር ነው፤ በአዲስ አበባ የአንዋር መስጊድን በር መድፈር ነው፤ ወደመሬት ስንወርድም የሙጢኝ የተባለው አገርን መንግሥት መድፈር ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ደንብን መጣስ ነው፤ ለነገሩ የመንግሥተ ሰማያትን በር መድፈር ከተቻለ ሌላው ምን ያቅታል!የሙጢኝ ያለን ሰው በአፈና መያዝና ወደአገር ማስገባት አንድ ችግር ነው፤ ይህ የጉልበተኛነት መገለጫው ነው፤ ሁለተኛው ችግር የተያዘው ሰው መብቱና ክብሩ ሳይጓደልበት ማስረጃዎችን ሰብስቦ ለነጻ ፍርድ ቤት አለማቅረቡ ነው፤ በቴሌቪዥን እንደታየው አካላዊ ጉዳት እንደደረሰበት ባይታወቅም፣ ጥልቅ መንፈሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት ይታያል፤ በብዙ አገሮች ሕጎች አንድ ሰው ራሱን እንዲወነጅል አይገደድም፤ ሕጋዊ ምርመራም በቴሌቪዥን በአደባባይ አይካሄድም።ስለዚህም በተጠርጣሪው ላይ የተደረገው ሁሉ ሕጋዊ አይደለም፤ በነጻ ፍርድ ቤት ቢቀርብም በቴሌቪዥን የተናገረው ሁሉ ቢያስታውሰውም በማስረጃነት የሚያገለግል አይመስለኝም፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።ከአፍሪካ አህጉር ወጥቶ የቀይ ባሕርን አቋርጦ አንድ ሰው፣ ገና ወደፊት ክፉ ሊሠራ ይችላል በሚል ሂሳብ በጉልበት አፍኖ ማምጣት የብዙ ነፍሶች ዕዳን ተሸክመው በኢጣልያ ኤምባሲ የሙጢኝ ብለው ተደላድለው የተቀመጡትን የደርግ አባሎች ማስታወስ ግዴታ ይሆናል፤ አድርጋችኋል የተባሉትን ሰዎች የሙጢኝ የማለት መብት አክብሮ አስበሃል የተባለውን ሰው የሙጢኝ የማለት መብት መጣስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።ከፖሊቲካና ከምናምኑ፣ ጉልበተኛነትንም ከማረጋገጡ በላይ ሌላ ትልቅ ነገር አለ፤ አገር የሚባል ነገር አለ፤ ይህ በአንድ ግለሰብ ላይ የተገኘ ጊዜያዊ ድል የአገርን ከብር የሚያጎድፍና የሚያቀል ይሆናል፤ የአንድ አገርን የመንግሥት ሥልጣን የያዘ አካል አንድ ግለሰብን በአደባባይ ከሕግ ውጭ ለማጥቃት ሲሞክር የራሱን ክብር ዝቅ ያደረግበታል፤ ስለዚህም ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል።በእኔ ዕድሜ ሰው በአደባባይ ሲገረፍ አይቻለሁ፤ ሰው ተሰቅሎ አይቻለሁ፤ የዚያን ዘመን የእውቀት ደረጃ የዚያን ዘመን የሰው ልጆች የመንፈስ እድገት ደረጃ ያመለክታል፤ የእውቀትም የመንፈስም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነበረ ማለት ነው፤ ስለዚህም ይህንን ያደረጉትን ዛሬ አንወቅሳቸውም ይሆናል፤ የታሪካችን ጉድፍ መሆኑን ግን ልንፍቀው አንችልም፤ ስለዚህም ሌላ ጉድፍ እየጨመርንበት ታሪካችንን ማቆሸሹ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል።ቅጣት በሕግና በሥርዓት ይደረግ ማለት ያጠፋ ሰው አይቀጣ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ምንም አቅም የሌለውን ሰው ይዞ በአደባባይ ማሰቃየትና ማዋረድ አገርንና ሕዝብን ማዋረድ ነው፤ የሰብአዊነትንም የሕጋዊነትንም ሚዛኖች ይሰባብራል።http://www.zehabesha.com/amharic/archives/33916

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የወያኔን መንግስት በሃይል ለማውረድ የሚንቀሳቀሱ 2 ድርጅቶች ጋር የውህደት ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ፣ ግንቦት7 እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ወደ ውህደት የሚያደርሳቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እንዲሁም የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ በጋራ ባወጡት መግለጫ ”ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ካሉበት አዘቅት በማውጣት ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጋራ ትግልና መስዋዕትነት የግድ የሚለን ደረጃ ላይ ደርሰናል” ብለዋል። ድርጅቶቹ አያይዘውም ”አገራችንና ሕዝባችንን ከአዘቅት ለማውጣት በመጣመር ብቻ ሳይሆን በውህደት አንድ ሆነን አገራችንንና ሕዝባችንን አንድ በማድረጉ ረገድ አስፈላጊው መስዋዕትነት በመክፈል የትግል እድሜ እናሳጥር በሚል ለውህደት የሚያደርሰንን ውይይት ለመጀመር የሚያስችል ሂደቶችን አጠናቀን ወሳኝ ወደሆነው ሂደት ውስጥ መግባታችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ወዳጆች ማብሰር እንፈልጋለን።” ብለዋል።     timthumb
ሶስቱ ድርጅቶች የወያኔን መንግስት በሃይል ለመጣል ከሚንቀሳቀሱት ንቅናቄዎች ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ሰአት ሌሎች ተመሳሳይ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል። በተለይም የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ በወያኔ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ የትግል አቅጣጫው የተቀየረ እና የኢትዮጵያ ህዝብና ለነጻነት እንታገላለን የሚሉ ድርጅቶች ወደ አንድ ጎዳና እየመጡ መሆናቸው በርካታዎችን ያስደሰተ መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰአት ማህበረሰቡ ጠንካራ የሆነ እንቅስቃሳሴ ማየት እንደሚሻ በተደጋጋሚ እየጠየቀ ሲሆን፤ አሁን የጀመረው የስምምነት መስመር ምናልባትም የነጻነት ሃይሎች በከፍተኛ ደረጃ ትግሉን ግብ ለማድረስ የተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው ሲሉ አንዳንድ ከዜናው በሆላ ያነጋገርናቸው ሰዎች ይገልጻሉ።
ከዚህ በሁዋላ በሚኖረው የሽግግር ሂደት ወቅትም በሁሉም የትግል ዘርፍ በጋራ መሥራት መጀመራቸውን ድርጀቶቹ ገልጸዋል። የውህደቱን ስምምነት የሶስቱ ድርጀቶች ተወካዮች፣ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ዜና መሆኑን ተናግረዋል። የውህደት ስምምነቱ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወክል ነው ያሉት የአርበኞች ግንባር የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አርበኛ መንግስቱ ወ/ስላሴ ”ትግላችን መስዋትነትን በሚጠይቅ ትግል ላይ የተመሰረተ መሆኑ ውህደቱን ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል” ብለዋል። ሶስቱም ድርጅቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉን እንዲደግፍ በተለይም የመከላከያ ሰራዊት አባላት አዲሱን ውህድ ሃይል ተቀላቅለው ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለነጻነት የሚደረገውን ትግል እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር  በወያኔ ወታደሮች ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን እየፈጸመ ይገኛል። ይህ የውህደት መስመር ስምምነትም ይህን የተጀመረውን መራራ ትግል ወደ አንድ በማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ስራ ለመስራት የሚያስችል ይሆናል
source – ESAT,  & ABAY MEDIA

የግንቦት 7 ሕዝባዊ ስብሰባዎች በዓለም ሃያ ስድስት ታላላቅ ከተሞች

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በመላው ዓለም ላይ ከሚገኙ አባላት፣ ደጋፊዎቹና በአጠቃላይ ከኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር ዝግጅቱን አጠናቋል።
በዚህም መሠረት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት 26 የዓለም ታላላቅ ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ተጠርቷል።
በላስቤጋስ ዩ ኤስ አሜሪካ ረቡስ ኦገስት 27 ቀን
በሂውስተውን ዩ ኤስ አሜሪካ ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
በአትላንታ ዩ ኤስ አሜሪካ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በዋሺንግተን ዲሲ ዩ ኤስ አሜሪካ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በቦስተን ዩ ኤስ አሜሪካ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በሎስ አንጀለስ ዩ ኤስ አሜሪካ ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
በሳንቲያጎ ዩ ኤስ አሜሪካ እሁድ ሴፕተምበር 7 ቀን
በቶሮንቶ ካናዳ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በካልጋሪ ካናዳ ሴፕቴምበር 1 ቀን
በደርባን ደቡብ አፍሪቃ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪቃ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
ቬሪኒንፍ ደቡብ አፍሪቃ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
ሩስተምበርግ ደቡብ አፍሪቃ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
ፍራክፈርት ጀርመን ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
ሙኒክ ጀርመን እሁድ ኦገስት 31 ቀን
ሄልሲንኪ ፊንላንድ ቅዳሜ ኦገስት 30 ቀን
አምስተርዳም ኒዘርላንድስ ቅዳሜ ሴፕተምበር 13 ቀን
ኦስሎ ኖርዌይ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
ለንደን እንግሊዝ ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
ስቶክሆልም ስዊድን ቅዳሜ ሴፕተምበር 6 ቀን
ፐርዝ አውስትራሊያ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
ሜልቦርን አውስትራሊያ እሁድ ሴፕቴምበር 7 ቀን
ቴላቪቭ እስራኤል ሐሙስ ሴፕቴምበር 11 ቀን
ብራሰልስ ቤልጂየም እሁድ ሴፕቴምበር 14 ቀን
ኦክላን ኒዩ ዚላንድ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
ሲኡል ደቡብ ኮርያ እሁድ ኦገስት 31 ቀን
በእነዚህ ስብሰባዎች ሁሉ የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሥራዎች ይወሳሉ። ወያኔን ማስወገድ በሚቻልበት ስልቶች ላይ ውይይት ይደረጋል። እስከዛሬ ድረስ ንቅናቄዓችንን ለመቀላቀል የተቸገራችሁ ወገኖች ይህንን አጋጣሚ እንድትጠቀሙበት ጥሪ እናደርጋለን። በማናቸውም ምክንያት አባል ሳይሆን ደጋፊ መሆን ለምትፈልጉ ወገኖቻችንን የደጋፊዎች ምዝገባ ሥርዓት አዘጋጅተናል፤ እድሉን ተጠቀሙበት።
ኑ! ኢትዮጵያ አገራችንን፣ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን እና ራሳችን ነፃ ለማውጣት እና በሀገራችን ፍትህ እንዲሰፍን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ይቀላቀሉ። ከዘወትር የህሊና ወቀሳ ይገላገሉ። ለዚህ ትግል ሁሉም የሚያበረክተው ነገር አለ። ስለሆነም በአቅራቢያዎ ወደሚደረገው የግንቦት 7 ስብሰባ ይምጡ፤ ጥያቄዎች ካልዎት ይጠይቁ።
አሁን ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ትግላችን ሶስት የትግል ስልቶችን ያስተባበረ ነው – ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሕዝባዊ አመጽ። ትግላችን በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ነው።
በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከድጋፍ ሰጪነት ወደ ተግባራዊ ተሳትፎ የተሸጋገሩበት ወቅት ነው። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። የወያኔ ድርጅቶችና የወያኔ ሹማምንት በየትኛው አገር ተዝናንተው እንዲኖሩና እንዲነግዱ አንፈቅድላቸውም። በእነዚህ ስብሰባዎች ስለዚህ ጉዳይ ይመከራል።
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ሕይወታቸውን ለመሰዋት ተነስተዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች የአርበኛ ወጣቶቻችንን ጥረት እንዘክራለን። ሺዎች እንዲቀላቀሏቸው ጥሪ እናደርጋለን። በሁሉም ስብሰባዎች በአገር ውስጥም በውጭ አገርም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወጣት ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ ይደረግለታል።
በሁሉም ስብሰባዎች ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥሪ ይደረጋል። የሠራዊቱ መሪዎች የፋሽስት ወያኔ ባለሟሎች ቢሆኑም ሠራዊቱ ግን ከኢትዮጵያ አብራክ የወጣ ኢትዮጵያዊ ነው። ሠራዊቱ የወያኔ መጠቀሚያ ከመሆን የነፃነት ታጋዮችን እንዲቀላቀል፤ ያ ካልተቻለም ለወያኔ ሥልጣን እንዳይሞት፤ ወገኑን እንዳይገል ጥሪ ይደረግለታል።
መጥተው የእነዚህ ታሪካዊ ስብሰባዎች አካል ይሁኑ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
http://freedom4ethiopian.wordpress.com/2014/08/22/as-2