Wednesday 14 January 2015

“ሕዝብን ለማውደም ውጤታማው መንገድ ታሪካቸውን የሚረዱበትን መንገድ ማስካድና ጨርሶውኑ መደምሰስ ነው” ጣይቱ ወደመ ቀጣይ ተረኛ . . .?

“ሕዝብን ለማውደም ውጤታማው መንገድ ሰዎች ታሪካቸውን የሚረዱበትን መንገድ ማስካድና ጨርሶውኑ በመደምሰስ ነው” የሚለው የእንስሶች እርሻ ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ብሒል ሰሞኑን ከፍተኛ መነጋሪያ ሆኗል፡፡ ለዚሁም መነሻው በየተራ እንዲወድሙ ከተደረጉት የሕዝብ የማንነት መገለጫዎች መካከል አንደኛ ቅርስ የሆነው የጣይቱ ሆቴል መውደምን ተከትሎ ነው፡፡
የእንስሶች እርሻ መጽሐፍ ህወሃት በተሰነጠቀበት ወቅት የእነ መለስ መገለጫ ነው ተብሎ በስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲነበብ የነበረ መጽሐፍ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የውኅዳኑ ደጋፊ ሪፖርተርም በየሳምንቱ እየተረጎመ ያቀርበው እንደነበር ጋዜጣው ምስክር ነው፡፡
ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ በጻፈው “አጤ ምኒልክ” መፅሐፍ ገጽ 328-330 የሆቴሉ ታሪክ እንዲህ ይነበባል፡፡
በአዲስ አበባ የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ተሠርታ በምትመረቅበት ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ ያሉ መኳንንት ለምረቃው ተጠርተው ነበር፡፡ ለተጠራው እንግዳ ማሳረፊያ እንጦጦ አይበቃ ስለነበር እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ተራራ ሥር ያለው ሕዝብ ሁሉ ለሚጠራው እንግዳ መጠለያ ቤት እንዲሰጥ ለመኑ፡፡ እንግዳ የሚያሳድር ሁሉ ሽሮ፣ በርበሬና ቅቤ፣ ዱቄትና ሥጋ ከቤተ መንግሥቱ እየወሰደ እንግዶቹን እንዲያስተናግድ አዘዙ፡፡ በዚህ ዓይነት የእንጦጦ ቤተ ክርስቲያን ምረቃ ተፈጸመ፡፡ ከዚህም በኋላ ለሚመጣው እንግዳ ማረፊያና መመገቢያ ችግር እየሆነ መጣ፡፡
ምኒልክ “እህእ” እያሉ ወሬ ያጠያይቁ ጀመር፡፡ “በፈረንጅ አገር ሆቴል የሚባል ቤት ስላለ ማንኛውም እንግዳ ገንዘቡን እየከፈለ ያርፍበታል፤ ምግቡንም ይበላበታል” አሏቸው፡፡ በዚህ መሠረት ሥራው እንዲጀመርአዝዘው ሕንጻው ተሠርቶ ሆቴል ቤቱ በ1898 ዓም በነሐሴ ወር ሥራው ጀመረ፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ስለ ሆቴል ቤቱ ሲያብራሩ “ስሙም ሆቴል ተባለ” ይላሉ፡፡ ኃላፊነቱም፣ ሥራውንም እቴጌ ጣይቱ ተክበው ይመሩና ያስተዳድሩ ጀመር፡፡ በ1900 ዓም ጥቅምት 25 ቀን ምኒልክ በአዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶችንና የውጭ አገር ሰዎችን ጋብዘው ሆቴሉን አስመረቁ፡፡ የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅም ሙሴ ፍሬደሪክ ሐል ነበር:: በኋላ ግን አቶ ዘለቃ አጋርደው ተሾሙ፡፡
እንደ አገር አባባል ጣይቱ እጅ የሚያስቆረጥም ወጥ እያሠሩ ገበያ ቢጠብቁ ጠፋ:: እንኳን ምግብ መብላት ከግሪኮች ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ መጠጣት ነውር ነበረና ጣይቱ ጠዋት የሚያሠሩት ወጥ ለሠራተኞቹ የማታ ራት ይሆን ጀመር፡፡ የሚስታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኩዋንንቶች “ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለችና ኑ እንሂድና ልጋብዛችሁ” ብለው ወሰዱዋቸው፡፡ መኳንንት በላ ጠጣና ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ፡፡
በማግሥቱ እንደተለመደው ገበያ ቢጠበቅ ጠፋ ቀጥሎም ጠፋ፤ ቀጥሎም ጠፋ፡፡ እንደገና ምኒልክ ሆቴል ገብቶ መብላት ነውር ያለ መሆኑን ለመኳንንቱ ገልፀው እንደገና ምሣ ጋበዙ፡፡ በሌላው ቀን አሁንም ገበያ አልተገኘም፡፡ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድርሽ የሚል ሰው ጠፋ፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ አጤ ምኒልክ ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በዙሪያቸው ላሉ መኳንንት “ሰማችሁ ወዳጆቼ” አሉ:: “በፈረንጅ አገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደሆነ ያ የተጋበዘ ሰው በሌላ ቀን ደግሞ ብድሩን ይከፍላል ብድሩን ካልከፈለ ግን እንደ ነውር ይቆጠርበታል፡፡” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መኳንንቱ “እርስዎን ፈርተንና አፍረን ነው እንጂ የሚሆንልን ከሆነ የምኒልክን ብድር ለመመለስ እኔ አለሁ” እያለ ተራ በተራ ከሆቴል ቤት ምኒልክንና ጣይቱን ይጋብዝ ጀመረ፡፡ ገበያ እየደራ ሄደ፡፡ ምሳችንን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ የሚለው ስለበዛም ስሙ እቴጌ ሆቴል ተባለ፡፡
ዛሬ በታላላቅና በሌሎችም ሆቴል ቤቶች ጋሻና ጦር እየተሰቀለ እናያለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አደራረግ የተጀመረው በምኒልክ ነው፡፡
[እምዬ ምኒልክ መጋቢት 3፤ 1900ዓም ለደጃዝማች ሥዩም የላኩት መልዕክት እንዲህ ይነበባል]
ይድረስ ለደጃዝማች ሥዩም፤
“. . . የላክኸው የዝሆን ጥርስ አልጋና ተምቤን የተሠራ ጋሻ ደረሰልኝ፡፡ ጋሻ ግን ለግራኝ ተብሎ ተሠርቶ እንደሆነ ነው እንጂ ሌላ ሰው ይይዘዋል ተብሎ አልተሠራም፡፡ ነገር ግን ለሆቴል ቤት ለላንቲካ እንዲሆን አደረግሁት. . . ”
**********************************
?
አይመስለኝም ነበር እሳት ወኔ ኖሮት
ጣይን የሚገላት
ወልዮልሽ አራዳ … …. ወዮልሽ ሃገሬ
ማን ሊያሞቅሽ ነዉ
አድማስ ተደርምሶ ጣይሽ ጠልቃ ዛሬ?
(Binu Ye Tsehay ፌሰቡክ)

“ሕዝብን ለማውደም ውጤታማው መንገድ ሰዎች ታሪካቸውን የሚረዱበትን መንገድ ማስካድና ጨርሶውኑ በመደምሰስ ነው” ጆርጅ ኦርዌል፡፡

taitu hoteltayitu hotelItegue-Taitu-Hoteltaitu hTaituHotelTaitu-hotelTaitu_hTaytu-Hotel

No comments:

Post a Comment