Saturday 13 August 2016

ትግላችን የመብትና የፍትህ ብቻ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው!(በኤልሳቤጥ ግርማ ከኖርዌይ

በመጀመርያ በሰሞኑ በወያኔ አገዛዝ ውድ ይወታቸውን ላጡ ወገኖቼ የተሰማኝ ሀዘን ከመጠን በላይ መሆኑን ሳልገልጽ አላልፍምከሰማዕታት ወገን ጨምረን ለዘላለም ስናከብራቸው እንደምንኖር ሳስብ ደግሞ ሃዘኔ በመጠኑም ቢሆን ይታደሳል አምላክ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን

ኢትዮጵያ ሃገራችን እንዳለመታደል ሆኖ ህዝቦቿን የሚያስተዳድርላትን፣ዳር ድንበሯን የሚያስከብርላትን መንግስት ወይም ስርዓት በሰላም ቀይራ አታውቅም። ገዢዎች በኃይል ወደ በትረ ስልጣናቸው ይመጣሉ በኃይል ደግሞ ከስልጣናቸው ዳግም ላይመለሱ በህዝብና በአዲስ መጤው ስርዓት ጉልበት የበላይነት ይቀየራሉ። በተለይ የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ስርዓቶች የዚህ ቀጥተኛ ምሳሌዎች ናቸው። የጃንሆይን ንጉሳዊ ስርዓት ደርግ በወታደራዊ አምባ ገነናዊ አገዛዝ ቀየረው። ህዝብ የተሻለ ይመጣል ብሎ ሲጠብቅ ከመቸውም በላይ የከፋ ለህዝብ የማይጠቅም ጨካኝ መሆኑን ሲረዳ ወያኔን ግባ ቤተ መንግሥት ከደርግ ከተሻልክ ብሎ ስልጣኑን አደላድሎ አስረከበው።
ወያኔ ግን እንኳን ከደርግ የተሻለ አስተዳደር ሊያሰፍን ቀርቶ እጅግ የባሰና የሃገርን ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ የከተተ አስተዳድር ሆነ። ከዚህ ክፉ ተግባሩ እንዲመለስ ለ25 ዓመታት እድል ቢሰጥም አገዛዙ ግን አጥብቀህ ግዛን፣ ግድያንና ዘረፋን የዘወትር ተግባሩ አድርጎ ቀጠለ። አሁንም የወያኔ አረመኒያዊ ድርጊት ሲበዛ  ህዝብ ምህረቱንና ትዕግስቱን እያበዛ አገዛዙን ቀይሮ ለህዝብ የቆመ መንግስት እንዲመሰርት መከረ አስመከረ። በየአምስት ዓመቱ በሚያደርገው የይስሙላ ምርጫ ጨው ከሆንክ ጣፍጥ አለባለዚያ ድንጋይ ነህ ተብለህ ወደ ባህር ትወረወራለህ በሚመስል ህዝብ በተለያየ መልኩ ሃሳቡን ገለጸ። ስርዓትህ ሊቀየር ይገባል፣ የአንድ ዘር የበላይነት ይቁም፣ኢትዮጵያ የሁላችንም ናትና ጥቅሟም ጉዳቷም፣ ደስታዋም ሃዘኗም፣ ወንዟም ተራራዋም፣ ህዝቧም ዳር ድንበሯም ይመለከተናል፤ ያገባናል ብሎ በተደጋጋሚ ጠየቀ። 
የህወሓት እኩይ ተግባሩን ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ጎጂ ፈሊጥ የሀገሪቱን አንጡራ ሃብት ሙሉ በሙሉ አሟጦ ለመጠቀም በማንአለብኝነት ማንኛውንም የስልጣን እርከን ተቆጣጠረ፤ ህዝቦቿን ለስደትና ለከፋ ርሃብ ዳረገ። ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ከህዝብ ላይ በአደባባይ ገፈፈ። የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ክብር በዓለም ሁሉ አዋረደ፤ የተናቀች ሀገርና የተናቁ ህዝቦች እንዲሆኑ ህወሓት ሳይሰለች ከበርሃ ጀምሮ ስራውን ሰራ። ብዙዎችን ከቦታቸው አፈናቀለ፤ ሃብት ንብረታቸውን ዘረፈ። ይህን እኩይ ድርጊት በህዝብና  በሀገር ላይ ሲፈጸም ያዩ ህሊናቸው ያላስቻላቸው ንጹሃን ዜጎች ድርጊቱን ሲኮንኑ ህወሓት በእነዚያ ዜጎች ላይ ካለምንም ርህራሄ ሞት፣ እስርና እንግልት በይፋ ፈጸመባቸው፤ እየፈጸመባቸውም ይገኛል።
ዛሬ ላይ ግን ህዝብ ለወያኔ አምባ ገነንና ዘር ገነን አገዛዝ ከ25ዓመት በላይ እድሜ ለመስጠት በፍጹም ፍቃደኛ አይደለም። ትዕግስቱና ኢትዮጵያዊ ጭዋነቱ ተሟጧል። “አጥብቆ ዝምታ ለበግም አልበጀ አስራ ሁለቱን በግ አንድ ነብር ፈጀ” እንደተባለው የህዝብ ዝምታ ለሀገር ጥፋትና ለዜጎች እልቂት ምክንያት ስለሆነ ከእንግዲህ በቃ ብሏል። ህዝብ ከምስራቅ እስከ ደቡብ፣ ከሰሜን እስከ ምዕራብ የወያኔ ስርዓት ከዚህ በኋላ በሃገሪቱ ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይገባም አለ። በተግባርም ወያኔን የማሶገድ ስራ በይፋ ጀምሯል።
በአራቱም አቅጣጫ ጾታ፣ እድሜ፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና የቦታ አቀማመጥ ሳይወስነው ሁሉም ህዝብ በአንድነት በህወሓት አገዛዝ ላይ ተነስቷል። ትዕግስት ፍርሃት አለመሆኑን አሳይቷል። ከዚህ በኋላ  ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ሊመልሰው እንደማይችል በሚገባ ለወያኔ አጻፋዊ መልስ ሰጧል። ለነገሩ ህዝቡ ሞትን፣ እስራትን፣ እንግልትንና ስደትን ለ25ዓመት ተለማምዷል ማንንም አይፈራም ሆ ብሎ ተነስቷል። ዝምታ  ፍርሃት እንዳልሆነ በሚገባው ቋንቋ ማሳየት ጀምሯል። እሾህን በእሾህ እንዲሉ ጦርን በጦር፣ ጥይትን በጥይት መመለስ እንደሚችል ህዝብ በግልጽ አሳይቷል። ሞት ላይቀር ገለን እንሞታለን በማለት ህዝብ ዝምታውን ሰብሮ ሁሉም በያዘው ዱላም ሆነ ድንጋይ፣ ጦርም ሆነ ጠብ መንጃ ወያኔንና ተላላኪውን መበቀል ጀምሯል።
ህወሓት መረዳት ያቃተው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ሊቀይር አለመቻሉን ነው። ኢትዮጵያዊ እኮ ለአፍሪካ  የነጻነት ተምሳሌት የነበረ ህዝብ ነው፤ ነጮችን በጎራዴና በጦር አንበርክኮ የመለሰ ጀግና ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ እኮ ጣሊያንን ከእነ ሙሉ ትጥቁ ድባቅ መቶ ሰንደቅ ዓላማውን በዓለም ህዝብ ፊት የአውለበለበ ታላቅና ኩሩ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ በማንነቱ የማይደራደር፣ ለሃገር ዳር ድንበር ህይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ቆራጥ ህዝብ  ነው። ኢትዮፕጵያዊ እኮ ተሸናፊነትን መቀበል የማይችል፣ ጠላቱን ጊዜ ጥብቆ የሚያጠቃ ጥበበኛና አስተዋይ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ ታጋሽና ጨዋ ህዝብ እንጂ ፈሪና ውርደትን መቀበል የሚችል ህሊና ቢስ አይደለም። ታሪኩን፣ ባህሉን እና ሃይማኖቱን የማያስነካ የተከበረ  ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ እኮ  በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ለሚመጣበት ማንኛውም ነገር አጻፋዊ ግብረ መልስ ከመስጠት ወደ ኋላ የማይል ታሪካዊ ህዝብ ነው።
ወያኔ/ህወሓት የኢትዮጵያን ህዝብ ማንነቱንና ምንነቱን ዘንግቶት አገዛዙን አጠናክሮ በህዝቡ ላይ መከራና  ስቃይን ቢያበዛም፣ ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ከጫካ ጀምሮ ቢሰራም፣ ህብረተሰቡን ለዳቦ እንጂ ለመብትና ለፍትህ እንዳያስብ በኑሮ ዝቅተኛ ለማድረግ ቢጥርም፣ የተማሩና ለሃገር ይጠቅማሉ የሚባሉ ዜጎችን ለእስርና  ለስደት ቢዳርግም፣ ትውልድ ገዳይ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ ትውልዱን እውቀት አልባ ለማድረግ ቢሞክርም፣ በዘር ፣በሀይማኖት፣ በጎሳና በቋንቋ ከፋፍሎ ለመግዛት ቢጥርም፣ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ዲሞ ክራሲ፣ ፀረ-ሰላም እያለ ንጹሃን ዜጎችን በይስሙላ የሽብርተኛ ህግ ወንጅሎ እውነተኛ ትግልን ለማኮላሸት ቢጥርም፣ ነጻ  ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ወያኔያዊ ተቋም ቢያደርጋቸውም ህዝብ ግን ከዚህ በኋላ በምንም መልኩ የወያኔ ስርዓት ለተጨማሪ ጥፋትና እልቂት በስልጣን ላይ መቆየት እንደሌለበት በሰላማዊ መንገድ ደጋግሞ ጠይቋል፤ ዛሬም አጥፊዎችና አምባ ገነኖች ቦታ እንደሌላቸው አስረግጦ እየተናገረ ነው።
ህዝብ ለ25 ዓመታት የህወሓት አገዛዝን በሰላማዊ መንገድ የጠየቃቸው ጥያቄዎችን ለአብነት ያክል ብናነሳ፡
  • ·             በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደራዊ ስርዓት ይዘርጋ
  • ·             ስልጣን የህዝብ እንጂ የእናንተ አይደለምና ከማንአለብኝነት ተቆጠቡ
  • ·         አድሎ፣ ሙስናና ዘረፋ በግልፅ ይቁም
  • ·         በብሄር ስም ሆን ብላችሁ ጥላቻን አትፍጠሩ
  • ·         ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ መንግስት በህጋዊና ፍትሃዊ ምርጫ ይረጋገጥ
  • ·         ስልጣን በህዝብ በጎ ፈቃድ እንጂ በሃይልና በጉልበት ለማራዘም አትሞክሩ
  • ·         ህዝብን ከትውልድ ቦታ በግፍ ማፈናቀል ይቁም
  • ·          የሃገርን ዳር ድንበር እንደ መንግስት አስከብሩ
  • ·         በየትም ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ጥብቅናና አለኝታ ሁኑ
  • ·         ፖሊሲው ይፈተሽ፣ ህገ መንግስት በህዝብ ጸድቆ ተግባር ላይ እንዲውል ይደረግ
  • ·         በነጻ ተቋማትበፍትህ፣ በፖሊስ፣ በሃይማኖትና ማህበራት ውስጥ ጣልቃ አትግቡ
  • ·         አገዛዙን ለማራዘም ማንኛውንም ኃይል ከመጠቀም ተቆጠቡ እና ወዘተ በማለት ህዝብ ሳይሰለች ደጋግሞ መፍትሄ የሚሻቸውን ጉዳዮች ምንም እንኳ ወያኔ ጆሮ ባይሰጥም በሰላማዊ መንገድ ለሩብ ክፍለ ዘመን ጠይቋል።

ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ጥያቄ ህወሃት መፍትሄ ይሰጣል ብሎ  ህዝብ የሚጠይቀው ጉዳይ የለም፣ አይኖርምም። ምክንያቱም መፍትሄ ከህወሃት አይጠበቅም። አሁን ጥያቂያችንና ትግላችን የስርዓት ለውጥ ብቻ ነው። ህዝብ በአንድነት ወጥቶ ኢትዮጵያን ሊመራና ሊያስተዳር የሚችል፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚሰማው፣ ህዝቦቿንና የሃገርን ሉዓላዊነት ሊያስከብር የሚችል፣ የቀደመ ታሪኳን፣ ሰንደቅ ዓላማዋን፣ ባህሏንና የህዝቦችን ማንነት ሊያከብር ሊያስከብር የሚችል ዲሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት ይገባል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሀገር እንደ ሃገር ፣ ህዝብ እንደ ህዝብ በነጻነትና በእኩልነት መኖር የሚችለው። 
ለዚህ ዲሞክራሲያዊ መንግስት የመመስረት ታላቅ ተግባር ላይ ደግሞ ጥቃቅንና አነስተኛ ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን አድርገን ህዝብ በህብረት በመጀመርያ ወያኔ የሚባል ሰው በላ አገዛዝን ማሶገድና ለጥያቄዎቻችንና ለችግሮቻችን መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል አካል መመስረት ለነግ የማይባል ታላቅ ተግባር መሆኑን ተገንዝበን ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ ከቻልን ብቻ ነው ኢትዮጵያ እንደ  ኢትዮጵያ  ልትቀጥል የምትችል።
በኢትዮጵያ ደግሞ  የማንደራደር ህዝቦች መሆናችን አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ክቡር ህይወታቸውን ሰውተው ለኛ አስረክበውናልና ወያኔ የሚባል ባንዳ ከፋፍሎ ለመግዛት የሚያደርገውን ከንቱ ጥረት በማኮላሸት በአማራና በኦሮሚያ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመጽ ወያኔን እንዲያቃጥለው ሁላችንም ቤንዚን የማርከፍከፉን ስራ መስራት አለብን፤ ትግላችን የስርዓት ለውጥ፤ ጥያቂያችን የአገዛዝ ለውጥ ነውና ወያኔ ከዚህ በኋላ  የሚያመጣውን ማንኛውንም የአማልዱኝ ጥያቄ እንደማንቀበል የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ የሃይማኖት አባቶች የተባበሩትም ሆኑ የአውሮፓ ህብረት፣ የመብት ተሟጋቾችም ሆኑ ማህበራት ሊገነዙቡ ይገባቸዋል እኛ ኢትዮጵያውያን በቃን የስርዓት ለውጥ እንፈልጋለን የወረቀትና የይስሙላ ሳይሆን ፍጹም ዲሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል
ስለዚህም ይህን የተቀጣተለውን ህዝባዊ  አመጽ በአንድነት ሊያስተባብርና ሊመራ  የሚችል አካል መሰየም፣ ህዝባዊ አመጹን ሊያስተጓጉል የሚችል ማንኛውንም ነገር በአስቸኳይ ማውገዝ፣ የመከፋፈልና የኢ-ኢትዮጵያዊነት ስሜትን ማስወገድ፣ ሊያታግሉ የሚችሉ ስልቶችን መንደፍ፣ ለትግሉ የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ ማድረግና ከስርዓት ለውጥ በኋላ ለሚመሰረተው ዲሞክራሲያዊ መንግስትና ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ ከወዲሁ መዘጋጀት የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮችን በተግባር ላይ አውለን የተጀመረውን ወያኔን ለማሶገድ የሚደረገውን ትግል አጠናክረን ከቀጠልን ድሉ ቅርብና የህዝብ እንደሚሆን ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም 

ትግላችን የስርዓት ለውጥ ነውና የወያኔ አምባ ዘር ገነን ስልጣኑ እስኪያከትም ድረስ በጽኑ እንታገላለን!!!

ግድያና አፈና ከትግላችን ወደኋላ አንድ እርምጃ አይመልሰንም!!!

No comments:

Post a Comment