Sunday 17 March 2013


አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ በአስገድዶ መድፈር ሙከራ አቤቱታ እንደቀረበበት ተዘገበ። ሠራዊት በበኩሉ <<ወሬው በሬ ወለደ >>ነው ይላል።

መጋቢት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በገዥው ፓርቲ ቀንደኛ ደጋፊነቱ የሚታወቀው አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ  በ አስገድዶ መድፈር ሙከራ ወንጀል ክስ እንደቀረበበት አዲስ አድማስ ዘገበ።
ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው የሠራዊት መልቲ ሚዲያ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆነው ሠራዊት ፍቅሬ  ላይ የአስገድዶ መድፈር ሙከራ ክስ ለፖሊስ  ያቀረበችው አንዲት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነች።
ሠራዊት ፍቅሬ ግን፤ በመድፈር ሙከራ አቤቱታ እንደቀረበበት መወራቱን በተመለከተ ተጠይቆ፤ “በሬ ወለደ ወሬ ነው፤ምንም የማውቀው የለም” ሲል አስተባብሏል፡፡
አክሎም፦<<ካሁን በፊት ከወገቤ በላይ ብዙ ተብያለሁ፤ አሁን ደግሞ ከወገቤ በታች መጡ>>ማለቱን ጋዜጣው አስነብቧል።
የጋዜጣው ምንጮች እንደሚሉት ግን ሠራዊት  ባለፈው ቅዳሜ አንዲትን የዩኒቨርቲቲ ተማሪ፦ “ለማስታወቂያ ስራ እፈልግሻለሁ” ብሎ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ለመሳምና ለማሻሸት ሲሞክር አምልጣዋለች።
እርሷም የሆነውን ነገር በማስመልከት ለፖሊስ አቤቱታ ማቅረቧ ተገልጿል።
ይሁንና  የአቤቱታው ሂደት ተቋርጦ፣ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ መደረጉን አድማስ ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል፡፡
ጋዜጣው ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱንም አመልክቷል።
<<ሠራዊት የገዥው ፓርቲ አቀንቃኝ ከመሆኑ አኳያ ይህን ድርጊት ባይፈጽም ኖሮ ፖሊስ ስለ ንጽህናው ይመሰክርለት ነበር>> ያሉት የዜናው አንባቢዎች፤ <<ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ  ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ላለመስጠት የፈለገው የሆነ ነገር ቢኖር ነው>> ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም፦<< እንዲሁም  ነገር ባይኖር የህዳሴውን ግድብ ጅማሬ አስመልክቶ  ከረዥም ጊዜ የሙያ ጓደኛው ከአርቲስት ሙሉ ዓለም ታደሰ ጋር በመሆን፦<ድህነት ታሪክ ሆኖ ቀረ>> እያለ በሚቀሰቅሰው በአርቲስት ሠራዊት ላይ ከመሬት ተነስቶ ዜና ባልተሠራ ነበር>> ብለዋል።
ከዓመታት በፊት በራቁት ዳንስ ቤቶች በተደረገ የሌሊት አሰሳ ከተያዙት ሰዎች መካከል፤ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች እንደሚገኙበት መዘገቡ ይታወሳል።
ኢህአዴግ ያን መረጃ ተገን በማድረግ በወቅቱ በአንዳቸውም ላይ  ክስ ባይመሰርትም፤ ከመካከላቸው አንደኛቸው ለማፈንገጥ ከሞከሩ ግን  ሊመዘዝባቸው የሚችል ፋይል አድርጎ እንዳስቀመጠው መዘገቡ ይታወቃል።
ከዚህ አንጻር ከታዋቂ ሰዎችም ሆነ ከ አርቲስቶች ከ ኢህአዴግ በላይ ኢህአዴግ ሆነው በ የ አደባባዩ የሚታዩ ሰዎች  በ አንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር ንክኪ እንዳላቸው በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።

No comments:

Post a Comment