Thursday, 14 March 2013

ታሪካዊው ኢትዮጵያ ሆቴል ሊፈርስ ነው


ታሪካዊው ኢትዮጵያ ሆቴል ሊፈርስ ነው

መጋቢት ፫ (ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ ሆቴልን የገዙት ባለሀብት  ሆቴሉን ሙሉ በሙሉ አፍርሰው ሌላ ሆቴል ሊገነቡ እንደሆነ ተዘገበ።
-ኢትዮጵያ ሆቴልና አዳማ ራስ ሆቴል ለባለሀብቱ የተሸጡት፤ በ134 ሚሊዮን ብር ነው
በመሀል አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንግዶችን እንዲያስተናግድ 50 ዓመታት በፊት የተገነባው የኢትዮጵያ ሆቴል ፈርሶ፣በምትኩ 60 ፎቅ ያለው ሆቴል እንዲገነባ የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ መወሰኑን ምንጮቹን በመጥቀስ የዘገበው ሪፖርተር ነው።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤ የአስተዳደሩ ካቢኔ ለሆቴል ፕሮጀክቱ 1,700 ካሬ ሜትር ተጨማሪ መሬት የፈቀደ ሲሆን፤ይህ  መሬት – ኢትዮጵያ ሆቴል ካለበት ጀርባ ያሉ የንግድና መኖርያ ቤቶች ያረፉበት ቦታ ነው፡፡
እነዚህ ቤቶች ፈርሰው ለፕሮጀክቱ እንዲውሉ ካቢኔው ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሆቴልን ከፕራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በ94 ሚሊዮን ብር በመግዛት የራሱ ያደረገው ቀደም ሲል አዳማ ራስን የገዛው በላይነህ ክንዴ ኢምፖርት ኤክስፖርት ኩባንያ ነው፡፡
ምንጮች እንደሚሉት በላይነህ ክንዴ ኢትዮጵያ ሆቴልን እንደ አዲስ ለመገንባት ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን የሚያመለክት ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ለከተማው አስተዳደር አቅርበዋል።
በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው የከተማው ካቢኔም  ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ስብሰባ በመቀመጥ  ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ይሁንታውን  ሰጥቷል፡፡
በመሀል አዲስ አበባ ከመከላከያ ሚኒስቴር አጠገብ የሚገኘው ኢትዮጵያ ሆቴል የአፍሪካ አንድነት እንግዶችን እንዲያስተናግድ በአፄ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ የተገነባ መሆኑ ይታወቃል።
የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ፤ታላላቆቹን ኢትዮጵያ ሆቴልንና የአዳማ ራስ ሆልን ለበላይነህ ክንዴ  የሸጠው በ134 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
የኩባንያው ባለቤት በሁለቱም ሆቴሎች አዲስ የማስፋፊያ ዕቅዶችን በመንደፍ ለሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች አቅርበው ማስወሰናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ባለአምስት ፎቅ ከፍታ ያለው ኢትዮጵያ ሆቴል በዕድሜ ብዛትና በማኔጅመንት ችግር አገልግሎት አሰጣጡ እየተዳከመ መምጣቱ  የማይካድ ቢሆንም፤  ሆቴሉ ታሪካዊነቱንና ቅርስነቱን ሳይለቅ ሊታደስ፣ ሊያድግና ሊስፋፋ ሲገባው  ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስና በሌላ እንዲተካ መደረጉ ፤  የሠሩትን እያፈረሱ አዲስ ከመጀመር አዙሪት ልንወጣ አለመቻላችንን የሚያሳይ እንደሆነ ዘናውን ካነበቡት መካከል ብዙዎቹ በሰጡት አስተያት ገልጸዋል።
ፕራይቪታይዜሽን ኤጄንሲ ከ ዓመታት በፊት ታሪካዊውን ጣይቱ ሆቴልን በወደቀ ዋጋ ለህወሀት ሹማምንት ዘመዶች መሸጡ አይዘነጋም።
በመሀል ከተማ የሚገኝ በመሆኑና የአዲስ አበባ አስተዳደር ሥራና ኮንስትራክሽን ልማት ቢሮ ባወጣው ደረጃ ያረፈበት ቦታ ለረጃጅም ሕንፃዎች ብቻ የሚፈቀድ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ከዚህ ሆቴል አጠገብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቱ ረዥሙ የሚባለው ሕንፃ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ነው፡

No comments:

Post a Comment