በአፋር ህጻነት በርሀብ እየረገፉ ነው
መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በክልሉ ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ የተከሰተው ከፍተኛ ረሀብና የውሀ እጥረት የበርካታ ህጻናትን ህይወት መቅጠፉን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ምንም እንኳ 60 በመቶ በሚሆነው የአፋር አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የምግብና የውሀ እጥረት ቢከሰተም ፣ ችግሩ ከሁሉም ወረዳዎች አስከፊ ሆኖ በቀጠለበት የእዳ ወረዳ 6 ህጻናት በአንድ ወር ውስጥ ሞተዋል። ይህ አሀዝ በአንድ ሰፈር ብቻ የተጠናከረ እንጅ በአጠቃላይ በወረዳው በተከሰተው ረሀብና የውሀ እጥረት የሟቾች ቁጥር በብዙ መቶዎች ሊደርስ እንደሚችል የአካባቢው ተወላጆች ገልጸዋል።
አንድ ጀሪካን ውሀ በ60 ብር ለመግዛት መገደዳቸውን የገለጹት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የእዳ ወረዳ ነዋሪ፣ የአካባቢው ነዋሪ ፍየሎቹና ግመሎቹ አልቀውበት ወደ አሳይታ ስደት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ አሳይታ በሰላም የደረሱት በህይወት ሲትረፉ ሌሎች ደግሞ በመንገድ ላይ አልቀዋል ።
የመንግስት እርዳታ እንዳልመጣላቸው የተነጋሩት ነዋሪዎቹ ፣ አስቸኳይ እርዳታ ካልደረሰ አስከፊ እልቂት ይፈጠራል ብለዋል።
በአካባቢው የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘው የአፋር ጋድሌ ሊ/መንበር ኮሎኔል ሙሀመድ አህመድ ለኢሳት እንደገለጡት ከፍተኛ ረሀብ በአካባቢው መግባቱን ድርጅታቸው እንደሚያውቅ ገልጸዋል።
በዚህ አመት ከአፋር ሌላ በሶማሊና በተለያዩ የአማራ፣ የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ድርቅ መግባቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአዲስ አበባ ህጻናት በምግብ እጦት ትምህርታቸውን መከታተል እንዳልቻሉ ሸገር ኤፍ ኤምን በመጥቀስ ኢሳት ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።
በግብርናው መስክ ከፍተኛ እመርታ እንዳገኘ ከመናገር ተቆጠቦ የማያውቀው የኢህአዴግ አገዛዝ ፣ ላለፉት 21 አመታት ኢትዮጵያን በምግብ ራሱዋን እንደሚያስችል ቢናገርም እስካሁን ድረስ የታየ ለውጥ የለም። በቅርቡ ይፋ ሆነ አንድ ጥናት እንዳለመከተው ከ7 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በምግብ ለስራ ታቅፈው ከአለም ባንክና ከአውሮፓ ህብረት በሚለገስ ስንዴ እየተደጎሙ ነው። በዚህ አመት የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በመላው አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውሀ እና የምግብ እጥረት ቢከሰተም ገዢው ሀይል በቅርቡ 200 ሚሊዮን ብር በማውጣት የብሄር ብሄረሰቦችን በአል አክብሮአል። ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ደግሞ የመከላከያ ቀንን አክብሮአል።
No comments:
Post a Comment