ሳዑዲና ዓባይ ምን አገናኛቸው?
Source:- Fitih le Ethiopia
በዘሪሁን አበበ ይግዛው
በዘሪሁን አበበ ይግዛው
ሳዑዲ ዓረቢያንና አፍሪካን (ዓባይን) የከፈለውን ቀይ ባህርን ስናስብ እንዴት ሳዑዲ ዓረቢያ ከዓባይ ጋር ልትያያዝ የምትችለው ብለን ላናስብ እንችላለን፡፡ ምንም ዓይነት መቀራረብም ሆነ ጉርብትና የላቸውም፡፡ የሰውየውን መልዕክት አዘል ንግግር ስናስብ ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ ለግብፅና ለሱዳን ጠበቃ ለመቆም የተናገረችው ሊመስለን ይችላል፡፡ ይህንንም ከተለያዩ መላምቶችና ምክንያቶች ብለን ከምናስባቸው ጉዳዮች እየተነሳን ልናትት እንችላለን፡፡ሆኖም ግን የዓባይ ውኃ ፖለቲካን ጠለቅ ብለን ስንመረምር የምናገኘው እውነት ሳዑዲ ዓረቢያ በአንድም በሌላም መልኩ በዓባይ ውኃ ፖለቲካ ውስጥ እጇን ለማስገባት መፈለጓን እንረዳለን፡፡ ይህንም ከኢትዮጵያው ባሮ (ጋምቤላ) በተከዜ አትባራ (ፖርት ሱዳን) እስከ ቶሽካ ፕሮጀክቶች እንደሚከተለው እንቃኛለን፡፡
ሳዑዲ ስታር የማንና ለማን ነው?
ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጥግ ብቻውን አገር ሆኖ የሚታየው ትልቁ የሚሊኒየም አዳራሽ በአንድ ወቅት በውጭ በኩል ባለው ግድግዳው እጅግ ትልቅ የሆነ ማስታወቂያ ሰቅሎ ነበር፡፡ ስለ “ሳዑዲ ስታር አግሪካልቸራል ዴቭሎፕመንት” ኩባንያ የሚለፍፈው ያ ማስታወቂያ እጅግ አረንጓዴ የሆነ የሩዝ ማሳ ያሳያል፡፡ ባለቤቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሳዑዲው ዜጋ ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ናቸው፡፡ በምዕራብ ጋምቤላ ወደ 10,000 ሔክታር መሬት እጅግ ርካሽ በሆነ የሊዝ ኪራይ (158 ብር በዓመት ለአንድ ሔክታር) የተረከበው ይህ ድርጅት እስከ 2020 ድረስ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ያፈስበታል የተባለው ይህ ፕሮጀክት ዋና ምርቱ ሩዝ ሲሆን፣ በዋናነትም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በምግብ ራሷን ያልቻለችው ኢትዮጵያ ለም መሬቶችን ለግዙፍ ኩባንያዎች እየሰጠች ሲሆን፣ በዋናነትም የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር እሳቤው ባይከፋም ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ግን ሳንገልጽ አናልፍም፡፡
እንግዲህ ሳዑዲ ስታር የተባለው የሼክ አል አሙዲ ድርጅትም ምርቱን በዋናነት ለሳዑዲ ዓረቢያ ሊያቀርብ የታሰበ እንደሆነ የታመነና የተነገረ ነገር ነው፡፡ ባለሀብቱም ከሳዑዲ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ጋር ባላቸው መቀራረብ ጋር ተነጋግረው የተጀመረ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲናገሩ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ ይህ የሚያሳየን ሳዑዲ ዓረቢያ በአንድም በሌላም መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የራሷ የሆነ የጥቅም ፍላጎት አላት ማለት ነው፡፡ ጋምቤላ ውስጥ ያሉ ወንዞች የዓባይ ገባር መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ዋናው ጥያቄ የሚሆነው ይህ ጥቅም እያለ እንዴት የሳዑዲው ምክትል መከላከያ ሚኒስትር በእንደዚያ ዓይነት አካሄድ “ኢትዮጵያ የዓረቡን ዓላም ከመጉዳት ቦዝና አታውቅም” ሊሉ ቻሉ? እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ አገሮች የተሻለ ነው የሚሉትን ጥቅማቸውን እንደሚያሳድዱ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡ ይህ ጥቅማቸውም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በመነሳት ሚዛን ወደሚደፋው ጥቅማቸው ያጋድላሉ ማለት ነው፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያም ያን እንዳደረገች የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፡፡ ይህንም ለመረዳት በሳዑዲ ዓረቢያና በታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) መካከል ያለውን ከዓባይ ውኃ ጋር የተያያዘ ግንኙነት ማጤን ይገባል፡፡
የግብፁ ቶሽካ ፕሮጀክትና ሳዑዲ ዓረቢያ
አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የግብፅ መሪ ሆስኒ ሙባረክ እ.ኤ.አ በ1997 “New Nile Valley Project” “የአዲሱ የናይል ሸለቆ ፕሮጀክት” በሚል ግዙፍ የሆነውን የሰሐራ በረሃን የማልማት ዕቅድ ነድፈው ያም ዕቅድ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡ በተያዘለት ዕቅድ ከተከናወነ ይህ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2017 ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል የማጠናቀቂያ ጊዜው እስከ 2020 ድረስ መሆኑን በቅርብ ጊዜ ከወደ ግብፅ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ፕሮጀክት በዋናነት ሁለት ምዕራፎች ሲኖሩት አንደኛው በሰሜን ምሥራቅ ግብፅ የሚገኘው የአል-ሰላም ቦይ (canal) ፕሮጀክት ነው፡፡ እሱም ውኃ ከዓባይ ግርጌ በመጥለፍ ወደ ሲና በረሃ ማሻገር ነው፡፡
ይህን በማድረግ ብዙ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት በማልማት 750 ሺሕ ግብፃውያንን ለማስፈር ያለመ ነው፡፡ ዋናውና ትልቁ ፕሮጀክት ግን የቶሽካ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህም የደቡብ ምዕራብ ግብፅ በረሃን ለማልማት ያቀደ ፕሮጀከት ነው፡፡ በግብፃውያኑ ዘንድ ይህ ፕሮጀክት አሁን ባለው ሁኔታ እ.ኤ.አ 2020 ያልቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት አዲስ ግብፅን በበረሃው ለመፍጠር ያቀደ ሲሆን፣ የተለያዩ በርካታ የውኃ ቦዮችንና የውኃ መምጠጫ ፓምፖዎችን በመገንባት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህን በማደረግ በረሃውን በማልማት ወደ ሦስት ሚሊዮን ግብፃውያንን የማስፈር ዕቅድ አላቸው፡፡ እንደ ግብፃውያኑ ከሆነ ይህ ፕሮጀክት ውኃውን የሚያገኘው በናይል ላይ ከተሠራው የአስዋን ግድብ ጀርባ ከሚገኘው የናስር ሐይቅ ነው፡፡ ግብፃውያኑ ይህን ሥራ የትኞቹንም የላይኛውን የተፋሰስ አገሮች ሳያናግሩ ሲሠሩት ውኃውን ከየት እንደሚያመጡት ያሰቡ አልመሰሉም፡፡ እነሱ እ.ኤ.አ በ1959 ከሱዳን ጋር የተፈራረሙት በሌሎቹ አገሮች ውድቅ የተደረገው “ስምምነት” ለራሳቸው በሰጡትና በመደቡት 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ራሽን/ኮታ መሠረት “ያላቸውን” ውኃ ለመጠቀም በማሰብ ነው፡፡
ሆኖም ግን ይህ ኮታ በሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ዘንድ ተቀባይነት ስለሌለው ግብፃውያኑ ውኃውን ከየት እንደሚያመጡት አሁንም ግልጽ አይደለም፡፡
እንግዲህ የሳዑዲ ዓረቢያ ሚና በዚህ ፕሮጀክት ላይ ምንድን ነው? ስንል ታላቅ ኢንቨስትመንትን እናገኛለን፡፡ የሳዑዲው ልዑል አል ዋሊድ ቢን ጣላል ቢን አብዱላዚዝ አልሳዑድ “ዘ ኪንግደም አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት” የተሰኘ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ፣ ግብፅ ውስጥ በጥቅሉ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያንቀሳቅሳሉ፡፡ በቶሽካ ፕሮጀክት ደግሞ ከ10 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ተረክበው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለማምረት ከግብፅ የውኃና የመስኖ ልማት ሚኒስቴር ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በየዓመቱም በሚሊዮኖች ለዚሁ የቶሽካ ፕሮጀክት አካል ለሆነው መሬት እንደሚያፈሱ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ግብፅ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ያሉት የሳዑዲ ቤተሰብ የሆኑት የንጉሡ ዘመድና ልዑሉ እንጂ ከኢትዮጵያዊ እናት የተገኙት ሼክ አል አሙዲ አይደሉም፡፡ ይህም ማለት ለሳዑዲ ዓረቢያ ቤተ መንግሥትም ሆነ ለምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ የሚቀርቡት ሼክ አል አሙዲ ሳይሆኑ ልዑል አል ዋሊድ ቢን ጣላል ናቸው፡፡ ስለዚህ የምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ንግግር ከዚህ አንፃርም ሊታይ ይችላል፡፡
ዓባይ ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ከሚለው ፅሁፍ የተወሰደ
በዘሪሁን አበበ ይግዛው
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው zerihun.yigzaw@graduateinstitute.ch ማግኘት ይቻላል፡
በዘሪሁን አበበ ይግዛው
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው zerihun.yigzaw@graduateinstitute.ch ማግኘት ይቻላል፡
No comments:
Post a Comment