Thursday, 21 March 2013

በአባይ ግድብ ከሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛው ተጠቃሚ የወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተሰብ ድርጅት ነው ተባለ


በአባይ ግድብ ከሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛው ተጠቃሚ የወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተሰብ ድርጅት ነው ተባለ

መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከሁለት ዓመት በፊት ኢሳት በወ/ሮ አዜብ መስፍን የእህት ልጅ በወ/ሮ አቲኮ ስዩም አምባየ የተመሰረተው ኦርቺድ ቢዝነስ ግሩፕ በጣሊያኑ  ሳሊኒ ኮንስትራክሽን አማካኝነት በሚገነቡት ግልገል ጊቤ አንድ እና ግልገል ጊቢ ሁለት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ስሚንቶ እና የግንባታ እቃዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ማሺነሪዎችን በማቅረብ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ ማጋበሱን ዘግቦ ነበር።
በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራውን የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ለኢሳት እንደተናገሩት ይህ ኩባንያ ከሳሊኒ ጋር ግልጽነት የጎደለው የቢዝነስ ስምምነት በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ስሚንቶ እንዲሁም ከባድ ማሺኖችን በማቅርብ ላይ ይገኛል።
የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት ግድቡን ከሚገነባው ሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛ የሆነ ትርፍ የሚያገኘው ኦርቺድ ፣ ከየትኛውም ድርጅት ጋር ሳይወዳደር በእነ ወ/ሮ አዜብ መስፍን አማካኝነት የስሜንቶና ማሸንሪዎች አቅራቢ ሆኖ ቀርቧል።
ከድርጅቱ ድረገጽ ላይ ለመረዳት እንደተቻለው ድርጅቱ በግልገል ጊቤ የሀይል ማመንጫ የመንገድ ስራ፣ በአዲስ አበባ ጅማ የመንገድ ጥገና፣ በግልገል ጊቤ ሶስት ኤር ስትሪፕ ግንባታ፣ በኮሌ ሃላላ የመንገድ ጥገና፣ በአዲስ አበባ አዳማ የመንገድ ፕሮጀክት፣ በአርባ ምንጭ አየር ማረፊያ የመንግድ ጥገና እና በሌሎችም የመንገድና የህንጻ ስራዎች ላይ ተሳትፎአል።
ኩባንያው ቦዲ ዋይዝ ጂም፣ ካፌ ፓኒኒ፣ ኦርቺድ ጄኔራል ኮንትራክተር፣ ኦርቺድ ትራንስፖርት፣ ኦርጂድ ትራንዚት፣ ኦርቺድ ማሽነሪ ሬንታል፣ ኤስ ኤንድ ኤስ እርሻ፣ ሂላላ ቱር ኤን ትራቭል፣ ሜትሮሉክስ ፍላወር፣ ናይል ስፕሪንግ ውሀ፣ ሬንቦው ጊፍት ሾፕ፣ ሪል ሳሎን፣ ወንደር ዊል ቢዝነስና ሌሎችም በአዲስ አበባና በመላው አገሪቱ ታዋቂ የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን በስሩ አቅፎ የያዘ ነው።
ወ/ሮ አቲኮ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ይህ ነዉ የሚባል ኃብት እንዳልነበራቸው ታሪካቸውን ያጠኑ የኢሳት ዘጋቢዎች ያረጋገጡ ሲሆን ባለፉት 20 አመታት ግን በልዩ ትዕዛዝ “ኦርቺድ” ቢዝነስ ግሩፕ የሚባል ድርጅት ተከፍቶላቸው ሆን ተብሎ አያሌ የግንባታ ጨረታዎችን እንዲያሸንፉና በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቱጃሮች ተርታ ለመመደብ እንደቻሉ መግለጻችን ይታወሳል።
የሀወሀት ኢህአዴግ ባለስልጣናት በዘመዶቻቸው ስም የሚገነቡዋቸው የቢዝነስ ተቋማት እየተበራከቱ መምጣቱን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል። የባለስልጣናትን የሀብት ምዝገባ ጨርሶ በአጭር ጊዜ ይፋ አድረጋለሁ በማለት ሲፎክር የነበረው ጸረ ሙስና ኮሚሽንም  ቃሉን ለመጠበቅ እንደተሳነው መዘገባችን ይታወሳል። ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱ በዘመዶቻቸው ስም ዬያዙትን ሀብትና ንብረት ለመመዝገብ ስልጣን እንዳልተሰጠው መግለጹ ይታወሳል።
የህዳሴውን ግድብ ለመጨረሽ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ይታወቃል። በቀን እስከ 30 ሰራተኞች በክፍያ ምክንያት ስራቸውን እየለቀቁ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment