Wednesday, 13 March 2013

መነገር ያለበት ቁጥር አምስት “መሪዎቻንን የት አሉ?”


ልጅግ ዓሊ
እኔ ምን አገባኝ የምትለው ሐረግ፣
እሱ ነው ሃገሬን ያረዳት እንደበግ፣
የሚል ግጥም ልጽፍ፣
ስሜት አንዘርዝሮኝ ብድግ አልኩኝና፣
ምን አገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና ።
ኑረዲን ዒሣ
ጀርመን ፍራንክፈርት በታማኝ በየነ ስብሰባ ታምሳ ከረመች። ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደገና ብዙ የፍራንክፈርት አካባቢ ነዋሪዎች ተገናኘን። አልፎም ተርፎም ችግራችንን ተወያየን። በዚሁ አጋጣሚ ይህንን ዝግጅት ላዘጋጁት ለወ/ሮ አሳየሽኝና ለአቶ ጥላሁን ምስጋናየን በግሌ አቀርባለሁ።
ብዙ ተናጋሪዎች ፣ ብዙ ምርጥ ዝግጅቶች ስለነበሩ በደስታ ስንከታተል ቆየን። በመጨረሻም ታማኝ ንግግሩን ጀመረ። እኔ ማነኝ? በሚል ነበር የጀመረው። ራሱን ዝቅ አድርጎ ሃገራችን የመሪ እጦትን እንደደረሰባት አስረዳን። እሱ ስለመሪ እጦት ሲያስረዳን እኔ በሃሳብ ፍራንክፈረት ያስተናገደቻቸውን <<መሪዎቻችን>> አስባቸው ነበር። የመጀመሪው ስብሰባ የኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ነበር። ከዛ በኋላ ብዙ ስብሰባዎች አድርገናል። ከብዙ አድካሚ ጉዞ በኋላ ነው ዛሬ በታናሽ ወንድም ታማኝ ስብሰባ ላይ የተገኘነው።
ዛሬ እነዛ ፍራንክፈርት ያስተናገደቻቸው <<መሪዎቻችን>> ሁሉ የት አሉ ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ልብ ድካም የሌለበት ሰው መሆን ያስፈልጋል። <<የፍራንክፈርት የስብሰባ ታሪክ ከኃይሉ ሻውል እስከ ታማኝ ድረስ>> ብዙ ነው። ወያኔን ለመዋጋት ሠራዊት አስልፈናል ብለው የፎቶግራፍ መረጃ ይዘው ከመጡት ጀምሮ እስከ ወያኔን በቅርብ እንጥለዋለን የሚል መፈክር ያነገቡ ብዙ <<መሪዎችን>> አይተናል። ይመሩናል፣ ለድልም ያበቁናል ብለን አጨብጭበን፣ የቻልነውን አድርገን የሸኘናቸው፣ እንኳን ሁላችንን አንድ አድርገው ሊመሩን የራሳቸውን ድርጅት ሲበትኑና ሲከፋፍሉ ያየናቸው ብዙ ናቸው። ከዚህን አልፈው ወያኔን የተቀላቀሉ ትንሽ አይደሉም። ፍራንክፈርት ብዙ አይታለች። ብዙም ታዝባለች።
ከኤርትራውያን ጋር ጥርስ የተናከስንበት፣ ሁላችንም ዘብ የቆምንበት የጎሹ ወልዴ ስብሰባ ትዝ ይለኛል። ፍራንክፈርት ውስጥ መድህን ጠንካራ ከሚባሉት ድርጅቶች አንዱ ነበር። የፍራንክፈርትን የጸረ ወያኔ ትግል የመድህን መፈረካከስና ብሎም መፍረስ አዳከምው ብል ስህተት ላይ አልወድቅም። በታማኝ ስብሰባ ላይ ላገኘኋቸው የመድህን አባሎች ፊት ለፊት ስለሞገትኳቸውም አሁን ሃሜት አይሆንብኝም። አዎ ዛሬ ያ ድርጅት የለም። ቢኖርም እንዳለ አይቆጠርም። ግን አባሎቹ አሁንም ለኢትዮጵያዊነት እንደቆሙ አሉ።
ሌላው ድርጅት የቀድሞው መላው ዐማራ(መዐአድ) የአሁን መኢአድ ነበር። በአባላትም በጥንካሬም ሰፋ ያለ ነበር። ይህ ድርጅት በጸረ ወያኔ ትግል በጀርመን ውስጥ የማይካድ አስተዋጽኦ አድርጎ አልፎል። ከዚህ ድርጅት ብዙ አመራሮች ተጋብዘው ተጠርትን ነበር። ዛሬ የዚህ ድርጅት መሪዎች ማለት የመኢአድ መሪዎች ከአባላቶቻቸው ጋር እንደማይገናኙ የታወቀ ነው። ፍራንክፈርት የሚገኙ የዚህ ድርጅት አባላት አሁንም ኢትዮጵያዊነትን እንዳነገቡ ነው።
ሌላው ድርጅት ደግሞ ኢሕአፓ ነበር። ፍራንክፈርት የተለያዩ ኢሕአፓ አመራሮችን ጋብዛ አስተናግዳለች። ኢሕአፓ በጀርመን በዛ ያለም አባሎች የነበሩት ድርጅት ነበር ። በዘመኑ ፖለቲካ በሁለት ተከፍሎ አብዛኛው አባላት ድርጅቱን ጥለው ከመሄዳቸው በፊት ጠንካራ ነበር ማለት ይቻላል። ሁለቱም ድርጅቶች በጣት የሚቆጠር አባላት ይዘው አንዱ ሌላውን ለመጣል ፍልሚያ ከገጠሙ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ፍራንክፈረት የድርጅት መሪዎችንም ብቻ ሳይሆን የሕብረት መሪዎችንም አስተናግዳለች። ከኢደኃቅ እስከ ሕብረትና ቅንጅት ድረስ የተደረገው ጉዞ መራራ ነበር። ለተፈጠሩት ሕብረቶች በሙሉ ድጋፋችንን ሰጥተናል። ሲፈርሱም አዝነናል። ከበየነ ጴጥሮስ እስከ ብርሃኑ ነጋ፣ ከመርሻ ዮሴፍ እስከ ኃይሉ ሻውል መሪ ፍለጋ ባዝነናል። እንደ ሕዝብ ምሩን ብለናል። ግን መሪ አላገኘንም። የሚከፈፋፍል፣ የሚበታትን መሪ እንጂ የሚያስተባብር መሪ አላየንም።
ዛሬ ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ለምን መሪ አጣን ? ብለን ብንጠይቅ ስህተት አይሆንም።<<መሪዎቻችንም>> <<እኛ እያለን!>> ብለው እንደማይፎክሩ ተስፋ አለኝ። የታናሽ ወንድም ታማኝ ጥያቄም ዲፕሎማሲያዊ ሆኖ እኔ ማነኝ? የሚለው ይሁን እንጂ ጥያቄው መሪዎቻችን የታሉ? ነው።
መሪዎችንን ሊመሩን እንዳልቻሉ ግልጽ ነው። ከመከፋፈል ፖለቲካ አልፈው ወደ አንድነት መምጣት አልቻሉም። ራዕይ የላቸውም። ሊያስተባብሩን አልቻሉም። እንኳን ሁላችንን፣ እንመራዋለን የሚሉትንም ድርጅት አንድ አድርገው ለመቀጠል አዳግቷቸዋል።
ሕዝብ ከመሪዎቹ የሚጠብቀውን ባለማግኘቱ ለመሪዎች የሚገባውን ክብር ነፍጓቸዋል ብንል ስህተት አይሆንም። ለመሆኑ የማንኛው የፖለቲካ መሪ ነው ዛሬ ሕዝባዊ ስብሰባ ቢጠራ የታማኝን ያህል ሕዝብ የሚሰበሰብለት? አንወሻሽ ማንም የለም። ግን ምክንያት አለው።
ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንደጻፍኩት ስለ ድርጅቶች ወይም ሕብረቶች መከፋፈል ግልጽ የሚታይ እውነት አለ። ይህ እውነት ግን <<መሪዎቻንን>> አያሳስባቸውም። ድርጅት ወይም ሕብረት ሲከፋፈል አባላት አብረው ይከፈሉ። ጥያቄው ግን ስንት ያህሉ አባላት ናቸው በተከፋፈሉት ድርጅት ውስጥ የሚቀሩት? የሚለው ነው።
በልምድ እንዳየነው ብዙኃኑ ድርጅት ሲከፋፈል ከማንኛውም ወገን ላለመወገን ከትግሉ ይወጣል ወይም ራሱን ያስወግዳል። ዛሬ የግንቦት 7 ሆነ የመኢአድ፣ የመድረክም ሆነ የአንድነት አባላት ቢሰበሰቡ ቁጥራቸው የቅንጅትን ደጋፊ ያህል ሊሆን አይችልም። ዛሬ ኢሕአፓም ሆነ ኢሕአፓ ዴ ከከፍፍሉ በፊት የነበራቸውን ደጋፊ ያህል የላቸውም። ዛሬ መድህን በስም እንጂ በተግባር የለም። ወዘተ. . .
ምን አገባን ብለን ካልተውነው በስተቀር እውነቱን ከተናገርን 70 በመቶ የሚሆነው በእንቶ ፈንቶው ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባት ከትግሉ ራሱን ያገላል። እዚህ ላይ ነው << መሪዎቻችን >> 70 በመቶውን ጥለው ለሁለት የተከፈለውን 30 በመቶ ከሆነው ውስጥ ብዙሃኑ ከእኛ ጋር ነው ብለው ሲሟገቱ የምናያቸው። እዚህ ላይ ነው << መሪዎቻችን >> ለብዙኃኑ ግድ የሌላቸው። እዚህ ላይ ነው << መሪዎቻችን>> የሚሠሩትን አይውቁም እንዴ? ብለን ለመጠየቅ የምንገደደው። << መሪዎቻችን>> ሲከፋፈሉ 70 በመቶ ለሚሆኑት አባላት ደንታ የላቸውም። ትኩረታቸው 15 በመቶው አባል ላይ ነው ። ለዚህም ነው << መሪዎቻችን >> ራዕይ የላቸውም ብንል ስህተት ላይ የማንወድቀው። ብዙኃኑ አንድነታቸው እየፈለገ እነሱ ግን አናሳም ቢሆኑ ታማኝ አገልጋያቸውን ይዘው፣ ድርጅት ነን ብለው ሲኮፈሱ የምናያቸው።
ድርጅት ሲከፋፈል ካለን ልምድ ስንመለከተው የብዙኃኑ ከትግሉ መሸሽ ብቻ ሳይሆን ብዙ አብረው የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። ቅንጅት ለማፍረስ በትደረገው ትግል ኪስና ኪል የሚባሉ ተቋቁመው ነበር። በእነዚህ በሁለቱ ድርጅቶች ማህል ስንት መናቆር ተደርጓል። ስንት ስም ማጥፋት ፣ ስንት ቅስም ሰባሪ ንግግር ተደርጓል። ይህን የርስ በእርስ ትግል ደግሞ ወያኔን እያጠናከረው ተቃዋሚውን ክፍል በሰፊው አዳከመው። ብዙሃኑ ለፖለቲካ መሪዎች ያለውን ክብር አሳጣው። ያ ሁሉ የቅንጅት አባል ሜዳ ላይ ተደፋ ። በተለይ በአውሮፓ ስንት ተአምር የሚሰሩ ዜጎቻችን ተበተኑ። ታማኞኝ ተፈጡ። የማይታመኑት ከድርጅት እንዲወገዱ ተደረገ። ይህ ራዕይ ካላቸው መሪዎች የማይጠበቅ ነበር። ግን ተደረገ።
በኢሕኢአፓና በኢሕፓ ዴ መካካል ያለው እንዲሁ ነው። ብዙኃኑ አባል ትግሉን ትቶ የኢሕፓን አንድነት መጠየቅ ከጀመረ ሰንብቷል። ግን <<መሪዎቻችንን>> ለዛ ብቁ አይደሉም። ከተነከሩበት የክፍፍል አባዜ ወጥተው ወደ አንደነት ከመምጣትና ለሃገር ጠቃሚ ነገርን ከመሥራት፣ በጥቂት ደጋፊዎቻቸው እየተጨበጨበላቸው አንቱ መባልን ከመረጡ ሰንበትበት ብለዋል።
ዛሬ ጠንካራው መኢአድ በተደጋጋሚ በተደረገው መከፋፈል ተዳክሞ ይገኛል። ዛሬ የግንቦት 7 ምሥጢር የወያኔን ድረ ገጾች ሞልተውታል። ዛሬ የኢሕአፓ አመራሮች የብዙኃኑን ድምጽ መስማት ተስኗቸው የ40 ዓመት ፓርቲያቸውን ወደ ከርሰ መቃብር ለመክተት የቁም ተዝካር አውጥተው አዝጋሚውን ጉዞ ጀምረውታል።
ድርጅት ሲከፋፈል ደግሞ በድርጅት ውስጥ ያለ ዴሞክራሲ እየሞተ ይመጣል። <<መሪዎቻችንን>> የተቃወማቸውን በሙሉ የሌላው ቡድን አባል አድርገው ይፈርጃሉ። በዚህም ምክንያት ካለተቃዋሚ የፈለጉትን እያደረጉ ስለሚቀጥሉ ተመልሰው ወደ አንድነት ለመምጣት ፍርሃት ያድርባቸዋል። የክፍፍሉ ዋና ምስጢሩ እዚህ ላይ ያለ ይመስለኛል።
መሪዎቻችን የታሉ? ለሚለው የታማኝ ጥያቄ መልሱ አንድ ነው። << መሪዎቻችንን >> በሠሩት ደሳሳ የድርጅት ጎጆ ውስጥ ተቀምጠው ድርጅታቸው አቃጥለው እየሞቁ ናቸው ብለን ብንመልስ ስህተት አይሆንም። ለዚህ ነው ሕዝብ ራዕይ ለሌላቸው መሪዎች ከመሰብስብ ይልቅ በጽናት የሃገራቸንን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ለ20 ለታገለው ለታማኝ ክብሩን የሠጠው።
<< መሪዎቻንን >> ከታማኝ አንድ ነገር መማር ይችላሉ። ለአንድነት ለሕብረት መቆም እንደሚያስከብር ሊማሩ ይገባል። አለበለዛ ግን <<ጨው ለራስህ ስትል ጠፍጥ ካለዚያ ድንጋይ መሆንህ ነውና>> የሚለውን ማስታወስ ይገባል።
ዛሬ ሕዝብ የሚጠብቀው መሪ ከክፍፍል አባዜ ወጥቶ የሠራነው ስህተት ነውና ድርጅታችንን አንድ እናድርግ ብሎ በቆራጥነት የሚነሣ መሪ ነው። ቅንጅትን ማፍረሳችን ስህተት ነበር ብሎ አምኖ ለዳግማዊ ቅንጅት የሚነሳን መሪ ነው። ኢሕአፓን መከፋፈላችን ትክክል አይደለምና ኢሕአፓን አንድ እናድርግ ብሎ የሚነሳ መሪ ነው። መኢአድን አንድ አድርጎ ቀደም የነበረበት ደረጃ ፣ ብሎም ከዛ የተሻለ የሚደርስ መሪ ነው። እሱ ለሚደግፋቸው የፖለቲካ እስረኞች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ድርጅቶች የፖለቲካ እስረኞች የሚቆም መሪ ነው። ሕዝብ የሚፈልገው መሪ መስዋዕትነትን ለመክፈል የተዘጋጀን መሪ ነው። ሕዝብ የሚፈልገው በውጭ ሆኖ የሚታገልን መሪ ሳይሆን ከሕዝብ ውስጥ ሆኖ የሚሞትለትን ነው።
ጥያቄው የጨውና የድንጋዩ ጉዳይ ነው። ጨው መሆን ለፈለገ መንገዱ ቀላል ነው።
ስለ አንድነት የሚቆሙ በሰላም ይክረሙ !
ፍራንክፈርት / ማርች 2013
Beljig.ali@gmail.com

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/6491

No comments:

Post a Comment